Skip to main content
x
ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረሱና የሚቃረኑ አዋጆችን የማሻሻል ጅማሮ
የሕግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በአጥኚ ቡድኑ የቀረቡትን ግኝቶች ሲከታተሉ

ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረሱና የሚቃረኑ አዋጆችን የማሻሻል ጅማሮ

ከአሥራ ሰባት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ1983 ዓ.ም. ደርግን በማሸነፍ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ጀምሯል፡፡ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ አገሪቱ የምትመራበትን ሕገ መንግሥትም በ1987 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ካፀደቀ በኋላ ሕዝቡ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እምብዛም ግንዛቤ ባይኖረውም በ1987 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ ተደርጎ፣ ኢሕአዴግ አብላጫ የፓርላማ መቀመጫ በማግኘት አሸናፊ በመሆን አገር ማስተዳደሩን ቀጠለ፡፡ ከ1987 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት ዓመታት በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙኃን በመፈጠራቸው የአገሪቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ንቃተ ህሊናቸው እንዲጎለብት የቻሉትን ያህል አስተዋጽኦ በማድረጋቸው፣ ሕዝቡ በመረጠው መሪ መመራት እንዳለበት ከፍተኛ ግንዛቤ አግኝቶ ነበር፡፡ በመሆኑም በ1997 ዓ.ም. በተደረገ አገራዊ ምርጫ፣ አገሪቱን ለ14 ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረውን የኢሕአዴግ መንግሥት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች የበርካታ ፓርቲዎች ስብስብ የነበረውን ‹‹ቅንጅት››ን መምረጡ ይታወሳል፡፡ በተፎካካሪው ቅንጅት በከፍተኛ ድምፅ የተሸነፈው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ በከተሞች በተደረገ ምርጫ 85 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ አርሶ አደር የመረጠው እኔን በመሆኑ አገር የማስተዳደር ሥልጣን የእኔ ነው በማለቱ በአገሪቱ ደም ያፋሰሰ ሁከት ሊፈጠር ችሏል፡፡ ቅንጅትም የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ባሸነፈባቸው አካባቢዎች ያገኛቸውን የፓርላማ መቀመጫ ‹‹አልረከብም›› በማለቱና የሕዝቡ ተቃውሞ በመቀጠሉ፣ ኢሕአዴግ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የቅንጅት ተመራጮች መብት በፓርላማ በማንሳት እንዲታሰሩ በማድረግ አገር መምራት ቀጥሏል፡፡

ኢሕአዴግ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በምርጫው የበላይነት የተወሰደበትን ምክንያት በማጥናት፣ የተለያዩ ለውጦች አደረገ፡፡ በመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም. ‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓት ጉዳዮች ግንባታ በኢትዮጵያ›› የሚል ስትራቴጂ በመቅረፅ፣ ይመራበት የነበረውን ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› በድጋሚ ትርጉም በመስጠት ‹‹ልማታዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› በማለት ኅብረተሰቡን የልማታዊ ኃይሎችና የፀረ ልማትና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች በማለት በሁለት እንዲከፈል አደረገ፡፡ በወቅቱ ያለው ብቸኛ ልማታዊ ኃይል ኢሕአዴግና አጋሮቹ ብቻ መሆናቸውን፣ በወቅቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሙሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችና የውጭ ኃይሎች ጥገኛና ዓላማ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ሊባሉ እንደማይችሉ በቀረፀው ስትራቴጂ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ኢሕአዴግ ሲቪል ማኅበረሰብ የሚላቸው በሕዝብ ወጪ የሚንቀሳቀሱ፣ የወጣቶችና የሴቶች ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች ብቻ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡

በመሆኑም ከ15 በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጭ አገሮች የሚያገኙ ድርጅቶች፣ በማንኛውም ሁኔታ በዴሞክራሲ ግንባታ እንቅስቃሴ ውስጥ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ በቀረፀው ስትራቴጂ ውስጥ አስፍሯል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኪራይ ሰብሳቢ መሆናቸውን፣ በወቅቱ የነበሩ የግል መገናኛ ብዙኃንና አብዛኛዎቹ የግል ዘርፉ አባላት ኪራይ ሰብሳቢ መሆናቸውን በስትራቴጂው ውስጥ ካሰፈረ በኋላ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚቃረኑና የሚጥሱ በርካታ አዋጆች እንዲወጡ ማድረጉ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በዋናነት ከሚጠቀሱት አዋጆች ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አዋጆቹ አፋኝና የዜጎችን መብቶች የሚጥሱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ ሕገ መንግሥቱንና የአገሪቱን መደበኛ የወንጀል ሕግና የሥነ ሥርዓት ሕጎች የሚቃረኑና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መሆናቸውም ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ የሕዝብ ተቃውሞዎች ምክንያት፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በ2010 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ አመራሩን ለመቀየር ተገዷል፡፡ በመሆኑም አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ኃላፊነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ በመልቀቃቸው፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተክተዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተሰየሙ በቀናት ውስጥ ትኩረት ካገኙና የሪፎርም ሥራ ከተሠራባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል አንዱ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዲስ ዋና ዓቃቤ ሕግ በተሾመለት በቀናት ውስጥ፣ በመላ አገሪቱ በተለይ ከፖለቲካ ጋር በተገናኝ ለእስር የተዳረጉ በርካታ ዜጎች ክሳቸውን በማቋረጥና ይቅርታ በማድረግ ከእስር እንዲፈቱ አድርጓል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የታሰሩት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ድንጋጌዎች ተላልፈዋል በሚል መሆኑንም ዋና ዓቃቤ ሕጉ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ችግር አለባቸው የሚባሉ አዋጆችን ብቃት ባላቸው ምሁራንና ባለሙያዎች ማስፈተሽና ማሻሻል በማስፈለጉ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሆነ ‹‹የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ›› ተመሠረተ፡፡ ጉባዔው 13 አባላትን ያካተተ ሲሆን፣ በሕግ ጉዳዮች ላይ መንግሥትን የማከር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ጉባዔው ከተቋቋመ ሁለት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ችግር አለባቸው የተባሉ አዋጆችን አጥንቶና መርምሮ የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ቡድን በማሰባሰብ ሥራ ጀምሯል፡፡ ጉባዔው ካደራጃቸው ቡድኖች መካከል ብዙ እሮሮና ውዝግብ እንዳለባቸው የሚታወቁትን የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅን ያጠናው ሁለት ቡድን ማሻሻያ ሐሳቦችንና ረቂቆችን ለመጀመርያ ውይይትና ግብዓት ለመሰብሰብ፣ ቅዳሜ ነሐሴ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል የአንድ ቀን ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001ን ታደሰ ካሳ (ዶ/ር)፣ አቶ ቁምላቸው ዳኜና አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤልን ጨምሮ አሥር አባላት ያሉት ቡድን ገምግሞ፣ ግኝቱንና በቀጣይ አዋጁ እንዴት ተሻሽሎ መውጣት እንዳለበት ረቂቅ አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል፡፡፡ በአቶ ደበበ አማካይነት የቀረበው የቡድኑ ጥናት ግኝት፣ አዋጁ ሕገ መንግሥቱንና ኢትዮጵያ ተቀብላ የፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የጣሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዋናነት አዋጁ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀደን የዜጎች የመደራጀት መሠረታዊ መብት የሚጥስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ዜጎች በማንኛውም መንገድ የመደራጀት መብት በሕገ መንግሥት ተፈቅዶላቸው በአዋጅ ሊከለከሉ እንደማይገባም በመነሻ ጥናታቸው አካተዋል፡፡ ዜጎች ማኅበራትን የማደራጀት መብት ተሰጥቷቸው ገደብ ሊደረግባቸው ቢገባ እንኳን፣ በመርህ ደረጃ በግልጽ በሕጉ መቀመጥ ሲገባው አስፈጻሚው ‹‹ኤጀንሲ›› እንደፈለገ የሚያደርግበት ሕግ መውጣቱ ተገቢ አለመሆኑንም የጥናት ቡድኑ አመልክቷል፡፡

ማኅበራት በግልጽና በነፃነት ያለ ምንም ተፅዕኖ ከፈለጉ ተመዝግበው ወይም ሳይመዘገቡ ተደራጅተው መንቀሳቀስ ሲገባቸው፣ በአዋጅ አስገዳጅ የምዝገባና ዕውቅና የማግኘት ገደብ ሊጣልባቸው እንደማይገባም የጥናት ቡድኑ ገልጿል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ነገር ግን በሕዝብ፣ በልማትና በዴሞክራሲ ላይ በመሥራታቸው አሳሪ ሕግ ሊወጣባቸው ስለማይገባ አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሻሻል እንዳለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ቡድኑ ገልጿል፡፡ አዋጁ ድርጅቶቹ ሲደራጁ የፋይናንስ ምንጫቸው በሁለት ዓይነት እንዲሆን ያስቀመጠ ሲሆን፣ የገቢ ምንጩ 90 በመቶ ከውጭ ከሆነ መሰማራት የሚችለው በልማታዊ ሥራ ላይ ብቻ እንጂ፣ በዴሞክራሲ ግንባታና በሰብዓዊ መብቶች ላይ መሥራት መከልከሉ ዜጎችን መበደል መሆኑንም ቡድኑ አብራርቷል፡፡

አሥር በመቶ ከውጭ ገቢ የሚያገኙ ድርጅቶች 90 በመቶ ከአገር ውስጥ እንዲያሰባስቡ መደረጉ፣ ዜጎች ካላቸው ግንዛቤ አንፃር ዕርዳታ ለማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ድርጅቶቹ እየተዘጉ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡ የሕጉ ዋና ትኩረት ከገንዘብ ጋር የተገናኘ በመሆ ዓለም አቀፍ ትችትም እንደደረሰበት ጠቁሟል፡፡ በቅርብ የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ኡጋንዳንና ናይጄሪያን በምሳሌነት መጥቀስ ቢያስፈልግ፣ የሲቪክ ማኅበራትና ድርጅቶች ከ13 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ በደረሱበት በአሁኑ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ 3,000 ብቻ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ መሥራት የሚችሉ አንድ ሺሕ እንደማይሞሉ አስረድቷል፡፡ ሕጉ ከመደራጀት፣ ከምዝገባ፣ የባንክ ሒሳብ ከመክፈት፣ ሪፖርት ከማቅረብ፣ ከደንብ፣ ከመመርያና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለበት ቡድኑ በጥናቱ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡

ማኅበራቱንና ድርጅቶችን እንዲቆጣጠር የተቋቋመው ኤጀንሲ ጭምር ችግር እንዳለበት፣ በአጠቃላይ ሕጉ የወጣው የልማት አጋርነትን ለማረጋገጥ ሳይሆን፣ ከምርጫ 97 ጋር በተገናኘ አንዳንድ ድርጅቶች በምርጫው ውስጥ ያደጉትን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለመቅጣት መሆኑን ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ ዓላማውም ቁጥጥር ማድረግ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ሕጉ ዜጎች ለፈለጉት ዓላማ መደራጀት ይችላሉ የሚለውን ዓላማ የሚቃረን መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎች፣ ድርጅቶቹና ማኅበራቱ በሰብዓዊ መብት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ በአዋጅ ቢከለከሉ ተጎጂው ዜጎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሴቶች፣ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች መብት ላይ መሥራት ጉዳቱ ምንድነው?›› በማለት የሚጠይቁት ተሳታፊዎች፣ ከውጭ ገንዘብ እንዳያገኙ በሕግ መከልከል ጉዳቱ ለዜጎች እንጂ ለድርጅቶቹ አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡ ለምሳሌ ለ20 ሺሕ ሴቶችና ሕፃናት ይሠራ የነበረው የሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ሥራ ሲያቆም፣ የድርጅቶቹ መሪዎች ሌላ ቦታ ተቀጥረዋል፡፡ ተጎጂ የሆኑት ግን ተረጂዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ዜጎች መብቶቻቸውንና ግዴታዎቻቸው እንዲያውቁ፣ በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ውይይትና የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር ማድረግን በሕግ መከልከል ‹‹ምቀኝነት ነው›› ብለዋል፡፡ የሕዝብ ድምፅ ሲታፈን መጨረሻው አመፅ መሆኑን፣ ይኼም በአገሪቱ ውስጥ በተግባር መታየቱን ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖ፣ የብሔርና የፍትሕ ሥርዓት ላይ መሥራት ጥቅሙ ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥት መሆኑንም አክለዋል፡፡ ድርጅቶችና ማኅበራት የውጭ ኃይሎች ዓላማ አስፈጻሚና የሌሎች አገሮች ርዕዮተ ዓለም አራማጆች እንደሆኑ አድርጎ መፈረጅ ተገቢ እንዳልነበረም አክለዋል፡፡ አሁን በተጀመረው የነፃነትና የመደመር መንፈስ ዜጎች የመደራጀት መብታቸው መረጋገጥ እንዳለበት፣ ድርጅቶችን የማቋቋም ነፃነት እንዲኖርና መንግሥትም መርዳት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ በክልሎች ጭምር ያለምንም ገደብ እንዲሠሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ ስያሜው ጭምር ተቀይሮ ሕጉ መሻሻል እንዳለበት ሰፋ ያለ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 621/2001 ውስጥ ያሉ በርካታ አንቀጾች ተሻሽለው፣ በረቂቅ ሕጉ የቀረቡ አንቀጾች ላይ በቀጣዩ በሚደረጉ ውይይቶች በሚገኙ ግብዓቶች ዳብረው ለሕግ አውጪው አካል እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል፡፡

ሌላው ‹‹ይሻሻል? ወይስ ይሻር?›› ተብሎ ለውይይት የቀረበው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ነው፡፡ አጥኚ ቡድኑ ሕጉ ከመውጣቱ በፊት የነበሩ የሕግና የውይይት ሐሳቦች፣ ከወጣ በኋላ ደግሞ የነበሩ ክርክሮችን፣ በሰዎች ሰብዓዊ መብት ላይ የነበረውን ሚና፣ ያደረሰውን ጉዳት፣ እንዲሁም ተከትለው የተነሱ ጥያቄዎችን መዳሰሱን ለውይይት የቀረበውን ጥናት ያቀረቡት ወ/ሪት ብሌን ሳህሉ ተናግረዋል፡፡ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተያየቶችን፣ የምሁራን መጣጥፎችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዕይታዎችን፣ የሕግ አስፈጻሚ ተቋማት ሪፖርትን፣ ፖሊስን፣ ዓቃቤ ሕግን፣ ሌሎችንና ቀደም ብሎ የተደረጉ ሁለት የምክክር መድረኮች ሐሳብ ያካተተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሪት ብሌን እንዳብራሩት፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ሲወጣ መደበኛው የወንጀል ሕግ ከሚያስቀምጣቸው ከለላዎችና የሰብዓዊ መብት ለመገደብ ከሚያነሳቸው ሐሳቦች በተለየ ሁኔታ መሆን ነበረበት፡፡

 ሌሎች የወንል ሕጎችን ከሚመልሱት የተለየ ምላሽ ያስፈልጋል ተብሎ በማሰብ የሚወጣ ነው፡፡ ይኼ ሲባል ግን በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚያሳድረው ጫና አለ፡፡ ይኼ የሚያሳየው ለሰብዓዊ መብት ድጋፍ ይሰጣሉ፣ ይጠቅማሉ የተባሉትን መለያዎች በሙሉ ፈቀቅ እያደረገ በር እንከፍታለን ማለት ነው፡፡ ግን ምን ዓይነት ጫና ያሳድራል የሚለውንም ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አሁው ባለን የወንጀልና ፍትሕ ሥርዓት ሊመለስ ያልቻለ ጥያቄ ኖሮ ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ካልተቻለስ? ምን ያህል ነው ክፍተት ሊሰጠው የሚገባው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን አጥኚ ቡድኑ አሳስቧል፡፡

ነገሩ ነጥሮ የሚወጣው የደኅንነት ተቋማትና ፖሊስ ምን ዓይነት ምርመራዎች (ሐሳብ ማቅረብ) ሊፈቅዱላቸው እንደሚገባ፣ የሥነ ሥርዓት ሕጎቻችን ዋና ዓላማቸው ሊሆን የሚገባው፣ የተከሳሾችን መብት ሳይነካ የፍትሕ ሥርዓቱ ለአገሪቱ ሕዝብ አደጋ የሆኑ ነገሮችን ወይም ሰዎችን አደብ የሚያስይዙበት መንገድ ማቅረብ መሆኑንም ቡድኑ በጥናቱ ጠቁሟል፡፡ ይኼ ሲደረግ ግን የሰዎችን ነፃነት እንዴት መጠበቅ እንደሚገባ ማወቅ እንደሚገባም አክሏል፡፡ ይኼ የሚጠቅመው ደግሞ ሕጉ ሲወጣ እንዴት እንዲህ ሆኖ ሊወጣ እንደቻለ፣ ‹‹ለዚህ ተቋም ይኼ ነገር እንዴት ሊፈቀድለት ቻለ?›› የሚለውን መልስ ሊሰጥ ስለሚል መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ‹‹መሻር? ወይስ ማሻሻል? ለሚለው ጥያቄ ወይም ምርጫ፣ ይሻሻል ከተባለስ ‹‹እንዴት ይሻሻል?›› ወይም ይሻር ከተባለስ ‹‹ለምን?›› የሚሉ ምላሾች አስፈላጊ መሆናቸውን አጥኝ ቡድኑ ተመልክቷል፡፡ መሻሻል ካለበት ‹‹የትኞቹ አንቀጾች ወይም የትኞቹ መሠረታዊ የፍሬ ነገር ሕጎች?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕጎችን ማየት ተገቢ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

አዋጁ ሲገመገም በየትኛው ዓለም አቀፍ ሕግ ደረጃና አገራዊ ሕጎች የሚለውን መለየትም አስፈላጊ መሆኑን፣ ሕጉ ‹‹ይሻር? ወይም ይሻሻል? ለማለት መጀመርያ መታየት ያለበት፣ ‹‹ሽብር ኢትዮጵያ ውስጥ አለ? ወይስ የለም?›› የሚለውን  ተቀዳሚ ነገር ማወቅ ተገቢ መሆኑንና የሽብር ጥቃት ካለስ በሕግ መከላከል ይቻላል? የሚለውን ማወቅ ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሕጉ በወጣበት ወቅት ኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሥጋት ነበረባት የሚለው ሲታይ፣ በወቅቱ ክርክር ያደርጉ የነበሩ የመንግሥት አካላት፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት እንደነበረባት የሚያሳይ መሆኑን ከሰነዶች ማረጋገጥ እንደቻለ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሌላው ክርክር በሥራ ያለው የወንጀል ሕጉ ላለው ሥጋት ምላሽ አይሰጥም የሚል ምክንያት ማንሳታቸውንም አክሏል፡፡ ሌላው በተባበሩት ድርጅት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 13/73 መሠረት፣ ኢትዮጵያ ሽብርን የመዋጋት ግዴታ ስላለባት ነው የሚል ክርክርም አንስተው እንደነበር ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ እንደ ቡድኑ ጥናት ግን የተጠቀሱት ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ለፀረ ሽብርተኝነት ኮሚቴ ሪፖርት ስታደርግ፣ በተደጋጋሚ እንደ አገር ይጠቀስ የነበረው (ሕጉ ከመውጣቱ በፊት) ‹‹በቂ ሕግ አን፡፡ የሽብር ጥቃት ሥጋት የለብንም፤›› የሚል ነበር፡፡ ሪፖርቶቹ በዚህ መልክ ይወጡበት በነበረበትና ሕጉ በወጣበት ዓመት ምን እንደተከሰተና ምን እንደተቀየረ የሚያስረዳ ነገር አልተገኘም፡፡ ነገር ግን ለሕጉ መውጣት እንደ ምሳሌ ሆነው የቀረቡት ሥጋቶች ሕጉ ከመውጣቱ በፊት የነበሩ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ይኼ ለፀጥታው ምክር ቤት ሲላክ ከነበረው ሪፖረት ጋር የሚጋጭ ሆኖ ማግኘቱን አጥኚ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ያለምንም ማብራሪያ የአቋም ለውጥ መደረጉንም አክሏል፡፡

አገሮች የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ እንዲያወጡ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 13/73 ግዴታ መጣሉ ሲታይ፣ ‹‹አገሮች ድንበር ዘለል ሽብርተኝነትን እንዲቆጣጠሩ ይፈለጋል፡፡ የአገር ውስጥ ጥቃት ለመቆጣጠር ግን የሚጥለው ግዴታም የለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምክንያቶች አሳማኝ ካልሆኑና ሕጉ ወጣ የተባለበት ምክንያት የማያሳምን ከሆነ፣ ‹‹ለምንድነው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾን፣ ጋዜጠኞችን፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት የሚመቸውን ሕግ ማቆየት ለምን አስፈለገ?›› የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ግድ እንደሚል አጥኚ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡

ሕጉ የተተገበረበት ሁኔታ ሲታይ ማቆየቱ ፋይዳ እንደሌለውም አክሏል፡፡ ከፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ በላይ ቅጣትን ማሳለፍ የሚያስችል መደበኛ የወንጀል ሕግ እያለ፣ ‹‹ሕጉን ማውጣት ለምን አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ሕጉ በወጣበት ወቅት ብቻውን እንዳልወጣ የጠቆመው ቡድኑ፣ አረው ተያያዥ ሆነው የወጡ ሌሎች ሕጎችም መውጣታቸውን ገልጿል፡፡ እነሱም የሚዲያና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕግን በመጥቀስ ገልጿል፡፡ ይኼ መሠረታዊ የሆነ የመንግሥትን አቋም ለውጥ የሚያመላክት እንደነበርም አስታውቋል፡፡ ይኼ ደግሞ በ1997 ዓ.ም. የተደረገውን አወዛጋቢ አገራዊ ምርጫ ተከትሎ መሆኑን እንደሚያሳይም ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ ሕጉ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነባቸውን አካላት መመልከት ቢቻል፣ በአብዛኛው በአርበኞች ግንቦት ሰባትና በኦነግ አባላት ላይ ተፈጻሚ ሆኖ ይገኛል፡፡ እስሮች የሚካሄዱባቸው ወቅቶችም አሉ፡፡ ከተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ፖለቲካዊ ክስተቶች ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመጀመርያው የዓረብ አገሮች ተቃውሞ የድምፃችን ይሰማ ተቃውሞ፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንና ሌሎችንም መጥቀስ እንደሚቻል አጥኚ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ ይኼ የሚያሳየው የብዙኃኑ የፖለቲካ ተሳትፎን ወደ ኋላ ለመጎተት ሕጉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን እንደሆነም ጠቋሚ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሕጉ በአጠቃላይ የሚያሳየው የፖለቲካ ማጥቂያ መሣሪያ እንደሆነ፣ ‹‹ሕጉ ይሻር›› የሚሉ ተከራካሪዎች እንዳሉ ቡድኑ በጥናቱ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ሕጉ ካደጉ አገሮች ቃል በቃል የተወሰደ መሆኑን፣ በተለይ የመንግሥት አካላት ሲከራከሩ ይሰማል፡፡ ነገር ግን የተወሰደባቸው አገሮች ሕጉን እንዴትና በማን ላይ እንደሚወስዱ የተደረገ ጥናት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ በማንኛውም መንገድ ከላይ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ስለማያሳይ፣ ሕጉ መሻር እንዳለበት የሚናገሩ ብዙ ተከራካሪ ወገኖች እንዳም አጥኚ ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ ምክንያቱም ይሻሻል ቢባል አብዛኛው አንቀጽ ስለሚሻሻል፣ የሕጉን ዓላማ የሚደግፍ አንቀጽ እንደማይኖርም አክሏል፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦግራፊ አቀማመጥ ሕጉ ሊኖራት የግድ ይላል የሚሉ ተከራካሪ ወገኖችም መኖራቸውን ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሽብር ሊወገዝና አቋም ሊያዝበት የሚችል ወንጀል በመሆኑ፣ እንደ ሌላው ወንጀል መመልከት ተገቢ እንዳልሆነም የሚከራከሩ አሉ፡፡ ጥቃቱ ባይኖር እንኳን እስከሚከሰት መጠበቅ ስለማያስፈልግ ሕግ ያስፈልጋል በማለትም ያክላሉ፡፡ መንግሥት ሕጉን ለመጥፎ ዓላማና በመጥፎ ሁኔታ ስለተጠቀመበትም አያስፈልግም ማለት እንደማይቻልም ይናገራሉ፡፡ ትግበራውን ሳይሆን የሕጉን አስፈላጊነት ማወቅ ተገቢ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሌላው ሕጉ በሰፊው ተለጥጦ ስለተተረጎመ፣ ጠቦ ሊተረጎም እንደሚገባም አንቀጾችን በመጥቀስ የተከራከሩ እንዳሉ አጥኝ ቡድኑ ገልጿል፡፡ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ባላጠበበ መንገድ መተርጎም እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

መሠረታዊ የሕግ ጉዳዮችን (Substantive Law) በሚመለከት ክርክሮች መነሳታቸውን ቡድኑ ገልጿል፡፡ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (3) የተሰጠው ትርጉም ሰፊና አሻሚ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ወንጀል በተቻለው መጠን ግልጽና ውስን መሆን እንዳለበት፣ ምክንያቱም በማጠጋጋት ወንጀሎችን መፍጠር ስለማይቻል ነው፡፡ ያሰበው፣ ያደረገውና ውጤቱ ወንጀል ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ሕጉ ግን ሰፊና አሻሚ በመሆኑ ለአስፈጻሚው ሚገባው በላይ ሥልጣን እንደሚሰጠው አጥኚ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ሕግ አውጪው፣ የሕግ አስፈጻሚውን ሥልጣን የሚገድበው ሕጎችን ግልጽ አድርጎ በማውጣት መሆኑንም አክሏል፡፡ ንብረትን በሚመለከትና ሌሎችም አንቀጾች በሰፊው በመተርጎማቸው አስቸጋሪ መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡ ፍፃሜ ያላገኙ ወንጀሎች ማቀድ፣ ማሴር፣ መዘጋጀት፣ ማነሳሳትና የሽብር ተግባርን መሞከር የሚለው ሰፊና ብዙ ወንጀሎችን በአንድ ላይ አጭቆ የያዘ መሆኑን ቡድኑ ጠቁሟል፡፡ ለእያንዳንዱ ለብቻው ትርጉም መሰጠት ሲገባው፣ በአንድ አንቀጽ ማካተት ተገቢ አለመሆኑንም አሳይቷል፡፡ በወንጀል ሕግ መቅጣት የሚቻለው ወንጀልን የፈጸመን እንጂ፣ ያሰበን መቅጣት ስለማይቻል ትክክል አይደለም፣ ሌላው ማወቅ ሲገባው ዝም በማለት የሽብር ድርጊትን መደገፍ የሚል አንቀጽ ተካቷል፣ ‹‹ማወቅ ሲገባው ማለት ምን ማለት ነው? መሳተፍ ምንድነው?›› የሚለው በዝርዝር መቀመጥ እንደነበረበት ቡድኑ ገልጿል በአጠቃላይ የጥናት ቡድኑ እያንዳንዳቸውን የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን አንቀጾች በማንሳት ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡  

አንድን ሰው ከጠረጠረው ያለ ፍርድ ቤት መያዝ እንዲችል ለፖሊስ ሥልጣን መስጠት ተገቢ አለመሆኑን፣ በምርመራ ወቅት ዝቅተኛ 28 ቀናት፣ ከፍተኛ አራት ወራት መደረጉ በፍርድ ቤት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርና ፍርድ ቤቱ በአዋጁ ከተቀመጠው ቀናት በታች ገልጾ ትዕዛዝ እንዳይሰጥ እንደሚያደርገው ቡድኑ ተመልክቷል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋምን ተሳታፊ ማድረጉም፣ ያለ ገደብ በመሆኑ ተገቢ አለመሆኑንም አክሏል፡፡ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን የሕጉን አንቀጽ በመጥቀስ ቡድኑ ሕጉን ገምግሞታል፡፡ በተጠርጣሪ ላይ የሚሰበሰቡ ማስረጃዎች የሕግ መርህን የተከተለና ሕጋዊ መሆን ሲገባቸው፣ እየተደረጉ አለመሆናቸው በጥናቱ ተዳስሷል፡፡ ሕጉ ከሳሽና ተከሳሽን እኩል ማገልገል ሲገባው፣ ለዓቃቤ ሕግ እንደሚያዳላም አክሏል፡፡ በመሆኑም ሕጉ መሻሻል እንዳለበት አጥኝ ቡድኑ ያቀረበው የውይይት ሐሳብ ያሳያል፡፡

ወ/ሪት ብሌን የጥናት ቡድኑ ሕጉን በሚመለከት ያዘጋጀውን ዝርዝር ጥናት ለተሳታፊው በግልጽ ካቀረቡ በኋላ፣ ተሳታፊዎች ሐሳባቸውን እንዲሰጥ መድረኩን ክፍት አድርገዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሰለባ የሆኑ ጦማሪያንና ሌሎች ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡ ጦማሪ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁና ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔ ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ እነሱ ምንም ሳያደርጉ ሐሳባቸውን ብቻ በመግለጻቸው ለእስር ማዳረጋቸውን ቁመው፣ ሕጉ ‹‹አስፈላጊ አይደለም፡፡ የዜጎችን መብት የሚያፍን፣ በተለይ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ባለመሆኑ ለውይይትም መቅረብ የለበትም፤›› በማለት ይሻር የሚሉትን ተከራካሪዎች ደግፈዋል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ ሕጉ ሕገ መንግሥቱን የሚጥስና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚጥስ በመሆኑ፣ ሊሻሻልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሕግ ሆኖ ሊፀድቅ ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አጥኚ ቡድኑ ለውይይት ያቀረበው ሐሳብ ገና ጅምር መሆኑን ጠቁሞ፣ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ሊዳብር የሚገባው መሆኑን በመጠቆም፣ ተከታታይ ውይይቶችን በማዘጋጀት ግብዓት እንደሚሰበስብም አስታውቋል፡፡ ጥላሁን ተሾመ የሕግና ፍትሕ ጉዮች አማካሪ ጉባዔ ሰብሳቢ (ፕሮፌሰር) እንደተናገሩት፣ ሕጎች ጊዜያዊ ችግሮችን የሚቀርፉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ዘለቄታዊ፣ ምክንያታዊ፣ ፍትሐዊና ዘመን ተጋሪ እንዲሆኑ ማድረግ የጉባዔው ዓላማ ነው፡፡ ሕጎች ፊት ዓይተው የማያዳሉ፣ ከወገንኛነት የፀዱና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የሚካሄዱ አስተማማኝ የፍትሕና የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲኖሩ ለማድረግ እሳቸውም ሆኑ ጓደኞቻቸው በአንድነት ቆመው ለመተግበር እየሠሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሠራራችን አንዱን አጥፊ ሌላውን አቃፊ፣ ሕግ ለፍትሕ ግዴለሽ ሆኖ፣ ተቋሞቻችን ለዜጎች ነፃነትና ለሀቅ ጀርባቸውን ሰጥተው፣ ባለሙያዎች አንድም አግላይ በሆነ የአስተዳደር መዘውር የሩቅ ታዛቢ ሆነው፣ በፍርኃትና በምንቸገረኝነት አስተሳሰብ ታጥረን፣ ከዚያም አልፎ በአድርባይነትና ወገናዊነት ተሸብበን መቆየታችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤›› ብለዋል፡፡ ከጥፋት አፋፍ ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር፣ ዘላቂ ዕድገትና ልማት ለማምጣት፣ የበለፀገችና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረቱ ፍሕት መሆኑንም አክለዋል፡፡ የሕግ የበላይነትንና የዜጎችን መብቶች የሚጠብቁ ለፍትሕና ለነፃነት ዘብ የሚቆሙ ጠንካራና ነፃ ተቋማትን መገንባት ካልተቻለ፣ አገሪቱን ከቀውስ ማውጣት እንደማይቻል አስምረውበታል፡፡