Skip to main content
x
‹‹እኛ ቢሮ ኩላሊት መሸጥ እንፈልጋለን የሚሉ በርካታ ወጣቶች ይመጣሉ››

‹‹እኛ ቢሮ ኩላሊት መሸጥ እንፈልጋለን የሚሉ በርካታ ወጣቶች ይመጣሉ››

የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ሰለሞን አሰፋ

የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሠረተ ሰባት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱን የመሠረቱት 43 ታማሚዎች አንድ ላይ በመሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ መሥራቾች ሞተው በሕይወት የቀሩት አንዱ ብቻ ናቸው፡፡ መቀመጫውን በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ያደረገውን ይኼንን ማኅበር የሚመሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሰለሞን አሰፋ ናቸው፡፡ ድርጅቱ በሆስፒታሉ ቅጥር የሚገኝን አንድ አሮጌ ሕንፃ ተቀብሎ ለዲያሊስስ በሚመች መልኩ አስተካክሎ ለሆስፒታሉ አስረክቧል፡፡  በአሁኑ ወቅት ያሉት የድርጅቱ አባላት 614 ዲያሊስስ የሚደረግላቸው ሕመምተኞች ናቸው፡፡ በቀን ከ30 እስከ 40 ሰዎች ኩላሊታቸው የሚታጠብ ሲሆን፣ ኩላሊታቸው ሥራ በማቆሙ የሚሰቃዩ ወገኖችንና የሕክምናውን ተደራሽነት በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዋና ሥራ አስኪያጁን አቶ ሰሎሞን አሰፋን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ አባላቱን የሚረዳው በምን መንገድ ነው?

አቶ ሰሎሞን፡- 614 የሚሆኑ ዲያሊስስ የሚያደርጉ አባላት አሉ፡፡ ለእነዚህ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የምናደርገው ድጋፍ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ታካሚዎች ነው፡፡ እስካሁን ባለን አቅም 413 ሰዎችን ረድተናል፡፡ በመንግሥት ተቋማት የሚታከሙ 500 ብር ከፍለው ለመድኃኒት ደግሞ ተጨማሪ 100 ብር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለአንድ ዲያሊስስ 600 ብር ያወጣሉ፡፡ 980 ብር ከፍለው በግል ቦታዎች የሚታከሙን ደግሞ 200 ብር ከድርጅቱ ብንረዳቸው ከኪሳቸው የሚከፍሉት ወደ 700 ብር ይወርዳል፡፡ ስለዚህ በሳምንት እስከ ሦስት ጊዜ ዲያሊስስ ሲያደርጉ በየሳምንቱ የእኛ ድርጅት ለእያንዳንዳቸው 600 ብር ይሰጣል፡፡ ለ413 ሰዎች በየሳምንቱ 600 ብር ስንሰጥ በወር የሚመጣው በርካታ ነው፡፡ እኛ የምንሰጣቸውን ይኼንን ገንዘብ የምንሰበስበው ከሕዝብ ነው፡፡ እኛ አገር ባለሀብት እንጂ በርካታ ባለፀጋ የለም፡፡ ባለፀጋ ካለው ላይ ቀንሶ ይሰጣል፡፡ ሕክምናውን ለማዳረስ ካላቸው የሚያካፍሉ ባለፀጎች ቢኖሩን ቀላል ነበር፡፡ በሽታው ቤታቸው እስኪገባ ድረስ ጉዳዬ የማይሉ በርካታ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በዘውዲቱ ሆስፒታል የዲያሊስስ አገልግሎት እንዲጀመር ሕንፃ ከማዘጋጀት ሥራ ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን ማድረጋችሁ ይነገራል፡፡ በኩላሊት በሽታ የሚሰቃዩ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍ ሕክምናው ተደራሽ እንዲሆን ግፊት የምታደርጉት እንዴት ነው?

አቶ ሰሎሞን፡- ሕክምናው በእኛ አገር አልተጀመረም ነበር፡፡ የእኛ ድርጅት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ በመነጋገር እኛ አገር ዲያሊስስ እንዲጀመር መንገድ እንዲከፈት አድርጓል፡፡ በመጀመርያ የግል የጤና ተቋማት የዲያሊስስ አገልግሎት እንዲጀምሩ ተደረገ፡፡ ቶም የሚባለው የዲያሊስስ ማዕከል ነበር ቀድሞ ሥራ የጀመረው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በመንግሥት የጤና ተቋማት ሕክምናው መሰጠት አለበት ብለን ግፊት ማድረግ ጀመርን፡፡ ይኼንንም ተከትሎ የመጀመርያው የመንግሥት ዲያሊስስ አገልግሎት በጳውሎስ ሆስፒታል ተጀመረ፡፡ በዚህ የጀመረው የዲያሊስስ አገልግሎት በእኛ አገር በአሁኑ ወቅት እስከ ንቅለ ተከላ ሕክምና ደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕክምናው በኢትዮጵያ መሰጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ ታማሚዎች የት እየሄዱ ይታከሙ ነበር?

አቶ ሰሎሞን፡- ውጭ አገር እየሄዱ ነበር የሚታከሙት፡፡ አብዛኞቹ ህንድ ይሄዱ ነበር፡፡ የሚሄዱት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ የንቅለ ተከላ ሕክምና እስኪደረግላቸው ድረስ የኩላሊት እጥበት እየተደረገላቸው ይቆያሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው መካከል ተመርጦ ከአንዱ ተወስዶ ይተከልላቸዋል፡፡ አቅሙ የሌላቸው ግን እዚሁ ይሞታሉ፡፡ ከ43ቱ መሥራች አባላት መካከል አንድ ብቻ የቀሩት እኮ ለዚህ ነው፡፡ ዲያሊስስ ካላደረጉ ይታፈኑና ይሞታሉ፡፡ አገልግሎቱ እዚህ ሲጀመር በመጠኑም ቢሆን እፎይታን ፈጠረ፡፡ ነገር ግን ዋጋው በጣም ውድ ስለነበር አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉት አቅሙ ያላቸው ብቻ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ለአንድ ዲያሊስስ ይከፈል የነበረው ወደ 4,500 ብር አካባቢ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው ዲያሊስስ ሳያገኝ እስከ ስንት ቀናት ሊቆይ ይችላል?

አቶ ሰሎሞን፡- ዲያሊስሱን ማግኘት ካልቻሉ ዕድሜያቸው በቀናት ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈውን ፈቃዱ ተክለማርያምን ብንመለከት መግለጫውን ሲሰጥ ደህና ነበር፡፡ ብዙ ውኃ፣ ምግብ የምትወስጂ ከሆነ የሚወጣ ነገር ስለማይኖር የመታፈን ዕድልሽ በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ ለዚህም ታማሚዎች አመጋገባቸው ላይ ከባድ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ መብላት እየፈለጉ ካለባቸው ችግር አኳያ ትንሽ ለመብላት ይገደዳሉ፡፡ የኩላሊት ሥራ ማቆም ሰገራ እንዳይወጣ አይከለክላቸውም፡፡ ነገር ግን የምንመገበው ምግብ ከፍተኛ የውኃ ይዘት አለው፡፡ ይኼንን ፈሳሽ የሚያጣራው ኩላሊት ሥራውን ሲያቆም ፈሳሹ ወደ ሳምባና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ፊታቸውና መላ ሰውነታቸው ያብጣል፡፡ በዚህ የመተንፈስ ችግር ያጋጥማቸዋል፣ ልባቸውም ይታፈናል፣ ይሞታሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኩላሊት እጥበት ሕክምና በኢትዮጵያ የተጀመረው መቼ ነበር? ያኔ የነበረው የሕክምና ዋጋና አሁን ያለውንስ እንዴት ያነፃፅሩታል?

አቶ ሰሎሞን፡- የእኛ ድርጅት ከተቋቋመ ከሦስት ዓመታት በኋላ ይመስለኛል በአገሪቱ የዲያሊስስ ሕክምና መሰጠት የተጀመረው፡፡ በወቅቱ ለአንድ ዲያሊስስ የሚከፈለው 4,500 ብር አካባቢ ነበር፡፡ አገልግሎቱ በሌሎች የግል የጤና ተቋማትና የመንግሥት ተቋማት መሰጠት እንዲጀምር የመወትወት ሥራ መሥራት ጀመርን፡፡ ተሳክቶልንም ጥቂት የማይባሉ ድርጅቶች አገልግሎቱን መስጠት ጀመሩ፡፡ ለአንድ ዲያሊስስ የሚከፈለው ዋጋ እንዲቀንስም መንግሥት የዲያሊስስ ማዕከል መክፈት ነበረበት፡፡ እንዳሰብነውም የመንግሥት ተቋማት አገልግሎቱን መስጠት ሲጀምሩ ዋጋው እየተረጋጋ መጣ፡፡ በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ሆስፒታሎች ለአንድ ዲያለስስ 500 ብር ነው የሚያስከፍሉት፡፡ 500 ብር የሆነው የተለያዩ ነገሮች የመብራት፣ የውኃ፣ የሠራተኛን ወጪ ሳይጨምር ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ ምንም የሚያገኘው ትርፍ የለውም፡፡ ይኼንንም ተከትሎ የግል ተቋማትም ዋጋቸውን እየቀነሱ መጡ፡፡ በአንድ ወቅት ዋጋው ከ4,500 ብር ተነስቶ እስከ 2,500 ብር ደርሶ ነበር፡፡ ቀጥሎ 2,000 ብር ገባ፡፡ ከዚያ አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት ባለሀብቶችን ሰብስበን ቀንሱላቸው ብለን አነጋገርናቸው፡፡ ዲያሊስስ የሚጠቀሙት ቤት ንብረታቸውን አሟጠው ሸጠው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሕክምናውን መቀጠል ስለማይችሉ ይሞታሉ፡፡ ከእነዚህ ጥቅም ማግኘት ቢቀርባችሁ ምነው አልናቸው፡፡ በዚህም ክፍያው እስከ 1,000 ብር ሊወርድ ችሏል፡፡ ቶም የሚባለው ክሊኒክ ብዙዎቹን ታካሚዎች የያዘ ነበር፡፡ ዋጋው ከተስተካከለ በኋላ የሚያስከፍለው 980 ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህም አነስተኛ የሚባል ዋጋ ነው፡፡ የሌሎቹ ግን 1,300 ብር አካባቢ ነበር፡፡ ስለዚህ የተወሰኑ ሆስፒታሎችን ሰብስበን እንደ ቶም ለምን ዋጋችሁን 980 ብር አካባቢ አታደርጉም ብለን ተደራደርንና ዋጋቸውን ወደ 980 ብር ዝቅ አደረጉት፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የኩላሊት እጥበት አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት ሆስፒታሎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ሰሎሞን፡- በአዲስ አበባ ዘውዲቱ፣ ምንሊክ፣ ጳውሎስ ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ይቀላቀላል፡፡ በሌሎች ከተሞች ላይ በተለይ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባለባቸው 12 ሆስፒታሎች አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግን ጀምሮ የማቆም ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማቱ በቀን እስከ ስንት ሰዎችን ያስተናግዳሉ?

አቶ ሰሎሞን፡- ለምሳሌ ቶም የዲያሊስስ ማዕከል በቀን እስከ 70 ሰዎችን ዲያሊስስ ያደርጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ግን በቀን የሚሠሩት ትንሽ ነው፡፡ ዘውዲቱን ብንመለከት በቀን እስከ አሥር አካባቢ ነው የሚሠራው፡፡ በዘውዲቱ ስድስት የዲያሊስስ ማሽኞች አሉ፡፡ አንዱን ለአኪውት አስቀምጠው አምስቱን ነው ለክሮኒክ የሚጠቀሙት፡፡ የሚሠሩትም በቀን ሁለት ጊዜ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ተጨማሪ ማሽኖች እንደሚገቡና የሚያስተናግዷቸው ሕመምተኞች ቁጥርም እንደሚጨምር ሰምተናል፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጥበት ሕንፃም የማስፋፊያ ግንባታ ተደርጎበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ገንዘብ የምታሰባስቡት ምን ዓይነት መንገዶችን ተጠቅማችሁ ነው?

አቶ ሰሎሞን፡- እኛ በኤስኤምኤስ እናሰባስባለን፡፡ በባንክም ገንዘብ እናሰባስባለን፡፡ በባንክ አካውንታችን ውስጥ ሰዎች እስከ አሥር ብር ድረስ ሲያስገቡ እናያለን፡፡

ሪፖርተር፡- በተሠሩ ሥራዎች የአገልግሎት ዋጋ ከነበረበት 4,500 ብር  ወደ 500 ብር ማውረድ ተችሏል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ለዓመታት የሚደረግን ሕክምና ለዚያውም በየሳምንቱ እስከ 2,500 ብር ድረስ የሚጠይቅ አሁንም ድረስ እጅግ ውድ የሚባል ነው፡፡ አባላቶቻችሁ ሕክምናውን ለማግኘት የሚያዩት ፈተና ምን ይመስላል? ምን ምን ነገሮች ያጋጥማቸዋል?

አቶ ሰሎሞን፡- በመንግሥት ሠራተኛ አቅም የማይታሰብ ነው፡፡ መጀመርያም ከራሱ ተርፎ የሚያስቀምጠው ነገር የለውም፡፡ የሚያስቀምጡ ቢኖሩም ለዲያሊስስ ብቻ በወር 12 ሺሕ ብር ያስፈልጋችኋል ሲባል ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ያለውን ንብረት ሸጦ፣ ከዘመድ አዝማድ ገንዘብ ሰብስቦ የቻለውን ያህል የሚታገልም አለ፡፡ የሚበዳደር፣ የሚለምንም አለ፡፡ ይኼ ሰውዬ ሲሞት አናየውም ብለው ያላቸውን የሚሸጡ ዘመድ አዝማዶች አሉ፡፡ በዚህ መልኩ እስከ አሥር ዓመት ድረስ እየታጠቡ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ተሟሙተው ነው ሕይወታቸውን የሚያቆዩት፡፡ ትንንሽ ልጆች፣ ተማሪዎችም ያጋጥማሉ፡፡ በሳምንት ሦስት ጊዜ ማድረግ ሲገባቸው ገንዘብ ስለማያገኙ አንድ ጊዜ ብቻ ያደርጉና ታፍነው ይሰነብታሉ፡፡ ዲያሊሲሱን በሁለት ሳምንት አንዴ ብቻ ለማድረግ ከራሳቸው ትግል የሚገጥሙ አሉ፡፡ ታፍነው ሲጨንቃቸው አንድ ጊዜ ብቻ ላድረግ ብለው ለመታጠብ ይሄዳሉ፡፡ ሕመምተኞቹም እዛው እርስ በርስ ይረዳዳሉ፡፡ አንዳንዱ ሦስት ጊዜ መታጠብ ያለበት ዛሬ ይቅርብኝ ይሄ ልጅ ታፍኗል እሱ ይታከምበት የሚሉ አሉ፡፡ ይኼንን ዕድል ለመጠቀም ሆስፒታል ቁጭ ብለው የሚውሉ አሉ፡፡ ዛሬ ባይሳካለት ነገ ይሳካል በሚል የሚመላለሱም ይኖራል፡፡ ሕመሙን ስለሚያውቁትና እርስ በርስ አይጨካከኑም፡፡ እነዚህ ሰዎች የንቅለ ተከላ ሕክምና አግኝተው ገንዘብ ቢያፈሩ ሌሎቹን ለመርዳት ወደ ኋላ አይሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ዋጋው አሁንም ድረስ ውድ የሆነበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ሰሎሞን፡- አምስት መቶ ብር የሚያስከፍሉት የመንግሥት ሆስፒታሎች ናቸው፡፡ በግል የሚሰጠው አገልግሎትም በአማካይ 1,000 ብር አካባቢ ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ ዶላር ጨመረ ተብሎ በአንዴ ከ300 ብር አስከ 500 ብር ድረስ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡ ዋጋቸውን ወደ 980 ብር ዝቅ አድርገው የነበሩ በትንሹ ወደ 1,300 ብር አሳድገውታል፡፡ በዶላር ምክንያት የተፈጠረውን ጭማሪ በሳምንት ከ900 እስከ 1,500 ብር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ደማቸው ሙሉ በሙሉ ማሽን ውስጥ ገብቶ ነው የሚወጣው፡፡ በዚህ ጊዜ የኤሌክትሮ ላይት ሚዛኑ ሊበዛ ይችላል፡፡ ይኼንን ሚዛናዊነት ማስጠበቅ የሚችል መድኃኒት ይታዘዝላቸዋል፡፡ ሁሌም ባይሆን አንድ ሰው ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የኤሌክትሮላይት መዛባት ስለሚገጥመው መድኃኒት ያስፈልጋዋል፡፡ መድኃኒቱም ዋጋው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ ከዲያሊስስ ሲወጡ በጣም ይደክማቸዋል፡፡ ትራንስፖርት አለ፡፡ ብዙዎቹ እኮ ስለሚፈሩ ምግብ አይመገቡም፡፡ እየፈለጉና እያማራቸው አይበሉም፡፡ የሚወዱትን ነገር ጠግበው የሚበሉት ዲያሊስስ ለማድረግ በሚሄዱበት ቀን ነው፡፡ በሽታው ከወጪው በላይ ብዙ አሰቃቂ ነገሮች አሉት፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሕክምናው ዋጋ የማይቀመስ ዓይነት ነው፡፡ የሕክምናው ዋጋ ውድ የሆነበት ምስጢር ለማጠብ እንደ ግብዓት የምትውለው ኬሚካል ውድ መሆኑ ነው፡፡ ኬሚካሉን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣዊ ወጪም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ኬሚካሉን በብዛት ለማጓጓዝ አይመችም፡፡ ስለዚህም ምልልሱ ይበዛ ነበር፡፡ አሁን ግን ዋናው ኬሚካል በፓውደር መልክ እንዲገባና እዚሁ የሚቀጥንበትን ሁኔታ ተመቻችቶ በጣም በቅናሽ ዋጋ ለሁሉም እንዲከፋፈል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ወር ድረስ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አቅርቦቱ ከእዚሁ አገር ማድረግ ከተቻለ የዲያሊስስ አገልግሎት ከሚሰጡ የግል ተቋማት ጋር በቅናሽ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደራደራለን፡፡ ይኼ እስከ ጥቅምት ድረስ ካለቀ የኬሚካሉ አቅርቦት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ማግኘት ከተቻለ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከሚታሰበው በላይ ዋጋው እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼንን ሁሉ ውጣ ውረድ ማስቀረት የሚችለው የኩላሊት ንቅለ ተከላ እስካሁን ለምን ያህል ሰዎች ተካሂዷል?

አቶ ሰሎሞን፡- ንቅለ ተከላው ከተጀመረ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 84 ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደርጎላቸዋል፡፡ 83 ሙሉ ለሙሉ የተሳካ ሲሆን፣ አንደኛው ብቻ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተጀመረ ሁለት ዓመት አካባቢ ይሆነዋል ግን እስካሁን 84 ሰዎችን ብቻ ነው ማገልገል የቻለው፡፡ ይህ ለምን ሆነ?

አቶ ሰሎሞን፡- ኩላሊት ማግኘት በጣም ችግር ስለሆነ ነው እንጂ ወረፋ በዝቶ አይደለም፡፡ ኩላሊት የሚወሰደው ከቤተሰብ ነው፡፡ አንዳንድ ቤተሰብ መስጠት አይፈልግም፡፡ አንዳንድ ታካሚ ደግሞ ከቤተሰብ ከምወስድ ብሞት ይሻለኛል ይላል፡፡ የአንዳንዱ ደግሞ ቤተሰብ ሆነውም የአንዱ ከአንዱ የማይስማማ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እስካሁን 84 ሰዎች ብቻ ሊሠራላቸው የቻለው፡፡ እኛ ይኼንን ተመልክተን ከቤተሰብ ብቻ የሚለው ቀርቶ ከቅርብ ጓደኛ ጭምር መውሰድ እንዲቻል ግፊት እያደረግን ነው፡፡ ምክንያቱም ከቤተሰብ ብቻ የሚለው ነገር የሕመምተኞችን የመዳን ዕድል ያጠበዋል፡፡ ለምሳሌ አባትና እናት ብቻ ቢኖርሽ ያንቺ የመዳን ተስፋ በሁለቱ ላይ ብቻ ይወሰናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ደም ግፊትና ስኳር በሽታ ካለባቸው ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ አንድ ኩላሊት ልትሰጥሽ ፈቃደኛ የሆነች ያንቺ ጓደኛሽ ኩላሊቷ ካንቺ ጋር ተስማሚ ቢሆንም ሕጉ በዚህ በኩል ስለማይፈቅድ አትሰጥሽም፡፡ ሰው ሲወለድ ጀምሮ በአንድ ኩላሊት ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ኩላሊት ብቻ እንደሆኑ በሆነ አጋጣሚ እስኪያውቁ ድረስ ምንም የተለየ ነገር ሳይኖር ጤናማ ሆነው ይኖራሉ፡፡ አብዛኞቹ የሚያውቁት ካደጉ  በኋላ ለሆነ ምርመራ አልያም አንዱን ኩላሊታቸውን ሊሰጡ ሲሉ ነው፡፡ አንድ ኩላሊት ብቻ እንዳላቸው ሲያውቁ እስካሁን ስለኖሩ ምንም አይመስላቸውም፡፡ በአንድ ኩላሊት መኖር እንደሚቻል ያውቃሉ፡፡ በአደጋ ምክንያት አንድ ኩላሊታቸው ወጥቶ በአንድ ብቻ የሚኖሩም አሉ፡፡ ሰጥተው በአንድ ኩላሊታቸው የሚኖሩም በርካቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ለሌሎች በአንድ ኩላሊት መኖር ይቻላል ብሎ አሳምኖ ለታማሚ እንዲሰጡ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ሰውም በቂ ግንዛቤ የለውም፡፡ ከቤተሰብ ውጪ የማይሰጥበት ምክንያት ሰው የአካል ክፍሉን እያወጣ እንዳይሸጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወሳኙ ምርመራ የሚደረገው ጀርመን አገር ተልኮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶበት ነው፡፡ ይኼንን ገንዘብ የሚከፍለው መንግሥት ነው፡፡ ይኼንን ያህል ወጪ ወጥቶበት ለምርመራ ሲላክ ከቤተሰብ መሀል ሲሆን፣ የመሳካት ዕድሉ ሰፊ ይሆናል ስለዚህ ቅድሚያ ለቤተሰብ ይሰጣል፡፡ ከቤተሰብ ውጪ ሲሆን ግን የማይሳካበት ዕድል ሰፊ ስለሆነ ደግሞ ደጋሞ ውጭ እየላኩ ማስመርመር ግድ ይላል፡፡ ይህም የመንግሥት ወጪ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ሰዎች ለዚህ የሚወጣውን ገንዘብ አያውቁትም፡፡ ሁሉም ነገር የሚደረገው በነፃ ነው፡፡ ንቅለ ተከላውም ያለምንም ክፍያ በነፃ ነው የሚካሄደው፡፡ ዋናው ምክንያት ግን በሰው ልጆች አካል መነገድ ለመከላከል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቤተሰብ ውጪ ኩላሊት መውሰድ ይፈቀድ ስትሉ በሰው ልጆች ሰውነት መነገድ ቢኖርም ይኑር ከሚል እሳቤ ተነስታችሁ ነው?

አቶ ሰሎሞን፡- እኛ እንዲፈቀድ አንልም፡፡ እኛ ቢሮ ኩላሊት መሸጥ እንፈልጋለን የሚሉ በርካታ ወጣቶች ይመጣሉ፡፡ ኩላሊት መሸጥ በሕግ የተፈቀደ ቢሆን ምን ዓይነት ችግር ሊከሰት እንደሚችል ያሳስበኛል፡፡ ያላቸው ከመግዛት፣ የሌላቸው ኩላሊት ከመሸጥ ወደ ኋላ አይሉም ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ እኛ ከሞቱ ሰዎች ላይ ይወሰድ የሚል ሐሳብ ነው ያለን፡፡ ሰው ዓይኑን ሲሞት ለዓይን ባንክ ገቢ ይደረግ ብሎ እንደሚፈርመው ሲሞትም ኩላሊቱ በኩላሊት በሽታ ለሚጠቁ ይሁን ብሎ ይፈርማል፡፡ 106 ሰዎች ሞተው ለ106 ሰዎች ብርሃን መስጠት ችለዋል፡፡ እኛ እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ነው መፍጠር የምንፈልገው፡፡ ከዚህ በፊት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በጉዳዩ ተነጋግረን ተቀባይነት አግኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የሕግ ማዕቀፍ ሊወጣለት ስለሚገባ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበን ማዕቀፉ ወጥቶለት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡ ይኼንን ለምን አናጠናክረውም በሚል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አሚን  አማን (ዶ/ር) ጋር ተነጋግረን ዶክመንት ይዛችሁ ኑ ተባልን፡፡ ከጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመሆን ያዘጋጀነውም ዶክመንት በጤና ጥበቃ በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ደርሷል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የአካል ክፍል የመለገሥ ባህሉ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዓመታት ሲሠራበት በቆየው በዓይን ባንክ እንኳ እስካሁን የ106 ሰዎችን ብርሃን ብቻ ነው መመለስ የተቻለው፡፡ በዚህ ረገድ እናንተ ምን ያህል ውጤታማ ልትሆኑ ትችላላችሁ?

አቶ ሰሎሞን፡-  እኛ ቢፈቀድልን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንሠራለን፡፡ በእኛ ድርጅት የሞቱትን ጨምሮ 1,200 አካባቢ የተመዘገቡ ሰዎች አሉ፡፡ ደውለን ስንጠይቅ በአንዴ 700 ይደርሳሉ የተወሰኑት ሞተው እንደገና ደግሞ ሌሎች ታማሚዎች ይከሰቱና እንደገና ቁጥሩ ከነበረበት ሊጨምር ይችላል፡፡ ዛሬ ስድስት መቶ ናቸው ብዬሽ ነገ ብንቆጥር 500 ሆነው ይጠብቁናል፡፡ ምንም ይሁን ምን 2,000 ሰዎች ነበሩ ብለን ብናስብና አሁን የቀሩት 600 ብቻ ናቸው ብንል፣ እስካሁን 1,400 ሰዎች ሞተዋል ማለት ነው፡፡ ስለ ኩላሊት ከፍተኛ ግንዛቤ ያላቸው የ2,000 ታካሚዎች ቤተሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ቤተሰቦች በኩላሊት በሽታ የሚገጥመውን ስቃይ ስለተመለከቱ ስሞት ኩላሊቴን ለግሻለሁ ብለው ይፈርማሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስትራቴጂዎች ከተጠቀምን ቀላል ነው፡፡ የግንዛቤ እጥረት ጉዳይ ሆኖ እንጂ ማኅበረሰቡ አይለግስም ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በሕገወጥ መንገድ ኩላሊት ለመግዛት ተዋውለው ኩላሊታቸው የሚሸጡ ችግርተኞች፣ የሚገዙ ሕመምተኞች ስለመኖራቸው ጭምጭምታ ሰምተናል፡፡ እንዲህ ባለ ድርጊት የሚሳተፉ ሕመምተኞ የንቅለ ተከላ ሕክምና የሚያገኙት በምን ዓይነት መንገድ ነው?

አቶ ሰሎሞን፡- ይኼ ዝም ብሎ ወሬ ነው፡፡ የትም ቦታ ሄደው ማሠራት አይችሉም፡፡ ለምሳሌ ህንድ ቢሄዱ ያለ ጤና ጥበቃ ዕውቅና ሕክምናውን መስጠት አይችሉም፡፡ ከኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ይቀየርላቸው የሚል ድጋፍ መሰጠት አለበት፡፡ ይኼንን ደግሞ ጤና ጥበቃ ዝም ብሎ አይጽፍም፡፡ ክትትል የሚያደርግበት ሆስፒታል ለጤና ጥበቃ የሁለቱ ኩላሊት ተስማሚ መሆኑን፣ ለጋሹም ቤተሰብ መሆኑን ጭምር የሚያሳይ የድጋፍ ጽሑፍ መሰጠት አለበት፡፡ ያለውን ሥርዓት ሳትከተይ ገንዘብ ስላለሽ ብቻ አሜሪካ ሄደሽ አትታከሚም፡፡ አንዳንዶች ይኼንን ሳያውቁ ተያይዘው ህንድ ይሄዳሉ፡፡ በህንድ ሁሉን ምርመራ ጨርሰው ልክ ንቅለ ተከላውን ሊያደርጉ ሲሉ የጤና ጥበቃ ድጋፍ የታለ ይባላሉ፡፡ በሠለጠኑ አገሮች የኩላሊት ንቅለ ተከላ በአንድ ሰዓት ከ30 ደቂቃ የሚያልቅ ነገር ነው፡፡ ከባዱ ነገር ኩላሊት ማግኘቱና ንቅለ ተከላውን ለማካሄድ መታለፍ ያለባቸው ሥርዓቶች ማለፍ ናቸው፡፡ ለጋሹ ራሱ ይጠጣል፣ ያጨሳል፣ ሌሎች ሱሶች አሉበት የሚለው በሙሉ ከታየ በኋላ ነው መለገስ የሚችለው፡፡ ከዘመዶቹም ቢሆን በፈቃደኝነት ሊሰጥ ነው የመጣው አይደለም የሚለው በሚገባ ይፈተሻል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በነፃ ስለተሰጣችሁ ቦታ እስኪ ይንገሩን? በቦታው ምን ለመሥራትስ አስባችኋል?

አቶ ሰሎሞን፡- እኛ የሰው ፊት ማየት ሰልችቶናል፡፡ የምናደርገውም ዕርዳታ በቋሚነት ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ባለፈው የኬኬ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ አምስት ሚሊዮን ብር ሰጡን አሁን ያ ብር አልቋል፡፡ ለአምስት ወር ብቻ ነው ያገለገለው፡፡ እስካሁን ወደ 11 ሚሊዮን ብር ጨርሰናል፡፡ ቀሪውን ስድስት ሚሊዮን ብር በኤስኤምኤስና በተለያዩ መንገዶች ያሰባሰብነው ነው፡፡ 11 ሚሊዮን ብር በትንሽ ጊዜ ውስጥ ነው ያለቀው፡፡ ስለዚህ ሕንፃ አስገንብተን አከራይተን በምናገኘው ገቢ ለምን ራሳችንን አንችልም አልን፡፡ እነዚህ ሰዎች እፎይ ማለት አለባቸው፤ ሕመማቸው ይበቃቸዋል፡፡ ስለዚህም ሁለገብ ሕንፃ ለማሠራት ነው ያሰብነው፡፡ ሕንፃው ዲያሊስስ ማዕከልም ይኖረዋል፡፡ ለገቢ ማመንጫነት የሚሆን ግንባር ቦታ ባምቢስ አካባቢ 1,410 ካሬ የሰጡን ሲሆን፣ ባለ አራት ፎቅ ነው ለመሥራት ያሰብነው፡፡ ከ52 እስከ 55 ሚሊዮን ብር ወጪም ይጠይቃል፡፡