Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የእስር ቤት ኃላፊ ጋ ደወሉ

ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የእስር ቤት ኃላፊ ጋ ደወሉ

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም እፈልግዎታለሁ፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • ቁጭ ብለን ማውራት አለብን፡፡
 • በምን ጉዳይ?
 • የሚገርም ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • የአንተ ሐሳብ መቼ መቆሚያ አለው?
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼኛው የሚገርም የቢዝነስ ሐሳብ ነው፡፡
 • ሰውዬ ጊዜውን ረሳኸው እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከለውጡ ጋር የሚሄድ የቢዝነስ ሐሳብ ነው፡፡
 • እየቀለድክ መሆን አለበት?
 • የምን ቀልድ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ ካሁን አሁን እስር ቤት ገባን እያልን በምንጨነቅበት ወቅት ሌላ የሌብነት ሐሳብ አምጥተህ ጉድ ልታደርገኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በቢዝነሱም ቢሆን እኮ መደመር ያስፈልጋል፡፡
 • እኔ ይኼ መደመርና መቀነስ የሚሉት ነገር አይገባኝም፡፡
 • ማለቴ ተደምሬያለሁ ምናምን ካሉ እኮ ችግር የለውም፡፡
 • ነገርኩህ እኮ ተደመርኩ ስትል ቀንሰውህ ቁጭ ልትል ትችላለህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የሚገርም የቢዝነስ ሐሳብ እኮ ነው ያለኝ፡፡
 • ለመሆኑ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መግለጫ ሰምተኸዋል?
 • ምን አሉ?
 • ማንም ወንጀለኛ ለዘለዓለም ተደብቆ አይቀርም ብለዋል፡፡
 • እሱ ለሚዲያ ፍጆታ ነው የተናገሩት፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ያው ባለፈው ጊዜ ዶላር ምናምን የደበቁት ላይ ዕርምጃ እንወስዳለን ብለው በተግባር ግን ተቸግረዋል፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • አሁን እንደዚያ ይበሉ እንጂ እርስዎ ተነኩ ማለት ከሚያጋልጡዋቸው ሰዎች ብዛት አንፃር ያሉት እስር ቤቶች ሊበቁን አይችሉም፡፡
 • ለመሆኑ ምን ዓይነት የቢዝነስ ሐሳብ መጥቶልህ ነው?
 • ሰሞኑን ሚዲያ ከተከታተሉ ሐሳቡ በጣም ይገባዎታል፡፡
 • እኮ ምንድነው?
 • የቴሌ ቢዝነስ ውስጥ እንድንገባ ነው፡፡
 • ሰውዬ አሁን እንደለየልህ ነው የገባኝ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ኩንታል ሲም ካርድ ተይዟል ሲሉ አልሰማህም?
 • ምን ችግር አለው ታዲያ አንዳንዱ ሰው ጤፍ ይበላል፣ ለአንዳንዱ ደግሞ ሲም ካርድ ነው እንጀራው፡፡
 • እኔን እዚህ ውስጥ እንዳታስገባኝ፡፡
 • ለነገሩ ቢዝነሱ ከቴሌ ጋር የተገናኘ እንጂ የሲም ካርድ አይደለም፡፡
 • ስማ ትንሽ ያካበትነው ሀብት በአንዴ ድምጥማጡ እንዲጠፋ ነው?
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ቴሌ በከፍተኛ መጠን ታሪፉን ቀንሶ እኛም እንድንከስር ነው የቴሌ ቢዝነስ ውስጥ እንግባ የምትለኝ?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ ምን ነካህ ልበል እንጂ?
 • ቴሌ ታሪፉ በመቀነሱ እኮ በርካታ ሰው የቴሌ ደንበኛ መሆኑ አይቀርም፡፡
 • ያ ታዲያ ለእኛ ምን ይፈይዳል?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህ ወቅት የስልክ ገበያ ይደራል፡፡
 • እኛ እኮ ከስልክ ቢዝነስ የወጣነው ቴሌ አንድ ሰው ከውጭ ሲመጣ ከአንድ ስልክ በላይ ይዞ መግባት አይችልም ስላለ ነው፡፡
 • እሱም መመርያ ተነሳ እኮ፡፡
 • ቢነሳስ ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር እንዴት መወዳደር እንችላለን?
 • ገበያውን ሰብረን የምንገባበትን መንገድማ መቼም አይጠፋዎትም?
 • ሒሳብ ቀንሰን እናምጣ እያልከኝ ነው?
 • እንደዚያ አልወጣኝም፡፡
 • ታዲያ ፎርጂድ ስልክ እንድናመጣ አስበህ ነው?
 • የለም የለም፡፡
 • እንዴት ነው ታዲያ ገበያውን ሰብረን የምንገባው?
 • በኮንትሮባንድ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስልክ ከውጭ ተደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር?
 • ማን ልበል?
 • ረስተውኝ ሊሆን ይችላል ድሮ እንተዋወቅ ነበር፡፡
 • ይቅርታ አላወቅኩህም?
 • ሃይ ስኩል አንድ ላይ ተምረን ነበር፡፡
 • ያው ጊዜው ረዥም በመሆኑና በወቅቱም በርካታ ተማሪዎች በመኖራቸው አላስታወስኩህም፡፡
 • ለማንኛውም እኔም በትግል ውስጥ ነበርኩ፡፡
 • ከእኛ ጋር ጫካ ገብተህ ነበር?
 • አይ ከእናንተ በተቃራኒው ጎራ ሆኜ ስታገል ነበርኩ፡፡
 • አሁን የት ነው ያለኸው?
 • እኔ ከአገር ከወጣሁ ወደ 30 ዓመት እየተጠጋኝ ነው፡፡
 • ውጭ አገር ነው ይኼን ያህል ዓመት የታገልከው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋባዥነት ወደ አገር ቤት ልመለስ ነው፡፡
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያውቁሃል እንዴ?
 • ማለቴ ዳያስፖራዎች ወደ አገራችሁ ግቡ ባሉት መሠረት ወደ አገር ቤት ለመመለስ አስቤ ነው፡፡
 • ስለዚህ እዚህ መጥተህ ሥራ ልትጀምር አስበሃል?
 • ሥራውንማ እናንተ ናችሁ የምትሰጡን፣ ከእኔ የሚጠበቀው ወደ አገር ቤት መመለስ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ውጭ አገር ምንድን ነበር የምትሠራው?
 • እኔ ሥራ ወዳድ ስለሆንኩ ምንም ሥራ አልመርጥም፡፡
 • በጣም ደስ ይላል፡፡
 • አሁን አገሪቱ ውስጥ እየተደረገ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ነው የምመጣው፡፡
 • እኛም ሁሌም አገራችንን የሚደግፍልን ዜጋ እንፈልጋለን፡፡
 • እኔ ወደ አገር ቤት ከመምጣቴ በፊት ግን ማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡
 • ምንድነው ማወቅ የምትፈልገው?
 • ማለቴ አገር ቤት ከመጣሁ ወደ 30 ዓመታት ሊሆነኝ ስለሆነ፣ ስለአጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
 • መቼም በሚዲያ እንደምትሰማው አገሪቱ በከፍተኛ ዕድገት ላይ ናት፡፡
 • እንግዲህ የእኔም አመጣጥ እዚህ ዕድገት ላይ ተጨማሪ ዕድገት ለማምጣት ነው፡፡
 • ይቅርታ እዚያ ምንድን ነበር የምሠራው ያልከኝ?
 • አብዛኛውን ጊዜዬን በዌልፌር ነበር ያሳለፍኩት፡፡
 • እ. . .
 • አጋሚውን ባገኘሁባቸው ጊዜያት ደግሞ ከሳህን አጠባ እስከ ታክሲ ሾፌርነት ሠርቻለሁ፡፡
 • በእውነት ሥራ አክባሪ ሰው ነህ፡፡
 • ለማንኛውም አሁን የደወልኩልዎት አንድ ነገር ሰምቼ ነው፡፡
 • ምን ሰምተህ?
 • ከውጭ ለሚመጡ ዳያስፖራዎች አቀባበል የሚያደርጉት እርስዎ ነዎት ሲባል ሰምቼ ነው፡፡
 • አልገባኝም ምን እያልክ ነው?
 • ማለቴ ለእኔም አቀባበል እንዲደረግልኝ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት አቀባበል?
 • ያው በምመጣበት ቀን ኤርፖርት የመንግሥት ልዑክ እንዲጠብቀኝ ነው፡፡
 • እሺ?
 • በዚያ ላይ እዚያው ኤርፖርት የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተጋብዘው መግለጫ እንድሰጥ ነው፡፡
 • ኪኪኪ. . .
 • ምን ያስቅዎታል?
 • ለመሆኑ ምን ስለሆንክ ነው አቀባበል የሚደረግልህ?
 • ሌሎቹ ምን ስለሆኑ ነው አቀባበል የተደረገላቸው?
 • እ. . .
 • ለማንኛውም ስለኔ አቀባበል ምላሽዎን እፈልጋለሁ፡፡
 • አትቀልድ እንጂ ሰውዬ?
 • ለነገሩ እኔም አሁን ነው የገባኝ፡፡
 • ምኑ ነው የገባህ?
 • መንግሥት አቀባበል እንዲያደርግልኝ መጀመርያ መግባት አለብኝ፡፡
 • የት ነው የምትገባው?
 • ጫካ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • አንተ ምንድነው የሰማሁት?
 • ምን ሰማሽ ደግሞ?
 • ሚዲያ ላይ የሚወራው ሁሉ አሥጊ ነገር ነው፡፡
 • ምን ተወራ?
 • በርካታ የንግድ ቤቶች እየታሸጉ ነው እኮ፡፡
 • ምን ሆነው?
 • ጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ ንግድ ቤቶች እየታሸጉ ነው፡፡
 • ምን ትቀልጃለሽ?
 • ለነገሩ እኔ በትውውቅ ስለምሠራ ችግር የለውም፡፡
 • ቢሆንም መጠንቀቅ አለብሽ፡፡
 • አሁን ያሳሰበኝ ሌላ ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • አዲሱ ከንቲባ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ምንም አልተመቸኝም፡፡
 • አንቺ ደግሞ አሁን እሳቸው ደሃዎችን ረዱ እንጂ ምን አደረጉ?
 • ስለእሱ እኔ ምን አገባኝ?
 • ታዲያ ምንድነው የምትይው?
 • ከተማ ውስጥ በርካታ ሕንፃዎች አሉ እየተባለ ነው፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፣ ሕንፃዎቹ እኮ የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ናቸው፡፡
 • አንተ ምንም አልገባህም፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • በሕንፃዎች ላይ አሰሳ እየተደረገ ነው፡፡
 • እኛ ታዲያ ምን አገባን?
 • ከተማው ውስጥ ከአንድ አይሉ ሦስት ሕንፃዎች እንዳሉን ረሳኸው እንዴ?
 • ቢኖሩን ምን ችግር አለው?
 • ከየት አምጥተው ሠሩት ተብለን መዋረዳችን አይቀርም፡፡
 • ስለእሱ አታስቢ?
 • ለምን አላስብም?
 • ሕንፃዎቹን እኮ ያለባለቤት ነው የሠራናቸው፡፡
 • እሱ አይደል እንዴ እኔን ያሳሰበኝ፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰበሽ?
 • ከተማዋ ውስጥ ባለቤት የሌላቸው ሕንፃዎች መኖራቸው ተረጋግጧል እያሉ ናቸው፡፡
 • እ. . .
 • ስማ ያ ሁሉ ሀብት ከንቱ ሊቀር ነው፡፡
 • ይኼማ አይሆንም፡፡
 • ምናለ ገንዘቡን በዶላር ቀይረን በያዝነው ኖሮ?
 • ሴትዮ ልታሳብጂኝ ነው እንዴ?
 • እሱማ የተሻለ ነበር፡፡
 • እና ተደርሶብናል ነው የምትይው?
 • እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም፣ ሕንፃዎቹ ግን ተደርሶባቸዋል፡፡
 • ሕንፃዎቹ ምን ሊደረጉ ነው ታዲያ?
 • እኔማ መንግሥት እንትን እንዳይለን ነው የፈራሁት፡፡
 • ምን እንዳይለን?
 • እሟ ቀሊጦ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የእስር ቤት ኃላፊ ጋ ደወሉ]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ዛሬ ከየት ተገኙ ክቡር ሚኒስትር?
 • በእውነት በጣም አዝኜ ነው የደወልኩልህ፡፡
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እስር ቤታችሁ ውስጥ ይኼን ያህል የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም አላውቅም ነበር፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው በየሚዲያው ታሳሪዎች የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው ሲናገሩ ሰምቼ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ታዲያ ይኼ ምን አዲስ ነገር ነው? እርስዎ በሚገባ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡
 • ለመሆኑ ታሳሪዎቹ ኢቲቪ ብቻ ነው የሚያዩት?
 • ከኢቲቪ ውጪ ሌሎቹን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ያያሉ፡፡
 • ስማ ፕሪሚየር ሊግ አያዩም ማለት ነው?
 • እ. . .
 • ናሽናል ጆግራፊክና ሌሎች ፊልሞችንም አይመለከቱም እያልከኝ ነው?
 • ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር?
 • ቆይ ቆይ ሌላው ቢቀር እስር ቤቱ የተሟላ ፈርኒቸር አለው?
 • ምንም አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለቴ ታሳሪዎቹ ሶፋ ምናምን አላቸው?
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የእውነቴን ነው እንጂ፡፡
 • እኔ እኮ የእስር ቤት ኃላፊ እንጂ የሆቴል ኃላፊ አይደለሁም፡፡
 • ስማ አሁን ከለውጡ ጋር መራመድ አለብህ፡፡
 • አልገባኝም?
 • ምናለበት እስር ቤቱን ሆቴል ብታስመስለው?
 • አሁን ነው የገባኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የገባህ?
 • በቅርቡ ሊመጡ ነው ማለት ነው፡፡
 • የት?
 • እኛው ጋ!