Skip to main content
x
ሜቴክ የሠራተኞች ቅነሳ ሊያደርግ ነው

ሜቴክ የሠራተኞች ቅነሳ ሊያደርግ ነው

ሃያ ሺሕ ያህል ቋሚና የፕሮጀክት ሠራተኞች ያሉት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጀመረው ለውጥ ምክንያት ሠራተኞችን እንደሚቀንስ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም መሠረት 4,382 ሠራተኞች እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ ዕረፍት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በተለይ ሜቴክ ከዚህ በፊት ይገነባቸው በነበሩ የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች እንደሚቀነሱ ታውቋል፡፡

ሜቴክ በቅርቡ በሥሩ የነበሩ የስኳር ፕሮጀክቶችን ለኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እንዲያስረክብ በመንግሥት መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ዕረፍት እንዲወጡ የተደረጉ ሠራተኞች ቁጥር ሰሞኑን እንደሚጨምር ታውቋል፡፡  በዋናነት በመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የኢንዱስትሪ አደረጃጀትና አሠራር ላይ የነበሩ ችግሮች፣ በሰው ኃይልና በአጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ መዋቅር ላይ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ፣ የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በሚደረገው ለውጥ መሠረት በሥሩ 14 ንዑስ የኢንዱስትሪ ክፍሎችና 93 ፋብሪካዎች ያሉት ሜቴክ ለሁለት እንደሚከፈል አክለዋል፡፡ ‹‹ሥራውን እስከ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ አቅደን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ሲከፈል ግማሹ በመከላከያ ሚኒስቴር ሥር ሲደረግ፣ የንግድና የሲቪል ነክ ምርቶችን የሚያመርቱት ደግሞ በኮርፖሬሽኑ ሥር እንደሚቆዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወታደራዊ፣ የንግድና የሲቪል ምርቶችን የሚያመርተው የቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭ ዕጣ ፈንታ ገና እንዳልተወሰነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከሜቴክ የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን እያየው ነው ሲሉ አቶ አብዱላዚዝ አስረድተዋል፡፡ በሚደረሰው ውሳኔ መሠረት ቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭ ለሁለት እንዲከፈል ይደረጋል፣ ወይም ደግሞ አንድ ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል ተብሏል፡፡

ሜቴክ ውስጥ በሥራ ላይ ከሚገኙ ሠራተኞች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲሆኑ፣ በመከላከያ ሠራዊት ወይም ደግሞ በሜቴክ ሥር እንዲታቀፉ ምርጫ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም የሜቴክ ሠራተኞች ደመወዛቸው የተሻለና እንደ መንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረ መሆኑን፣ አሁን በሚደረገው ለውጥ ግን በደመወዝ ስኬል ላይ ማስተካከያ እንደሚኖር በመገመት ቅሬታ መፈጠሩን ሪፖርተር ያናገራቸው የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሥራው ሲያልቅ እንደሚወሰን አቶ አብዱላዚዝ አስታውቀዋል፡፡