Skip to main content
x
አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው!

አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው!

አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱ ሲገባ መንፈስን ማነቃቃትና መልካም ነገሮችን መመኘት የተለመደ ነው፡፡ ሁሌም በአዲስ ዓመት መቀበያ ላይ መልካም ምኞቶችን መለዋወጥ፣ ሥጦታ መሰጣጠት፣ መደጋገፍና ብሩህ ተስፋ መሰነቅ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያዊነትን በማድመቅ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሕዝባችን ሽር ጉድ ላይ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በርካታ ጉዳዮች አሉብን፡፡ በአሮጌው ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁትን በከፍተኛ ሞራል ተነሳስቶ ለማሳካት፣ አዳዲስ ዕቅዶችን ውጤታማ ሆኖ ለማከናወን፣ በብሔራዊ ጉዳዮች የሚያጋጥሙ ውጣ ውረዶችና መሰናክሎችን በብልኃት ተሻግሮ ካሰቡበት ለመድረስ ንቁ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ አዲሱን ዓመት በተስፋ መቀበል የሚቻለው እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ የሚያበረክተው ምን እንደሆነ በቅጡ ሲያስብ፣ አገርን የሚያስቸግሩ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማስቆም ሲችል፣ ካለፉት ስህተቶች በሚገባ በመማር አብሮ የመብላትን ብቻ ሳይሆን አብሮ የመሥራት ባህልን ማጠናከር ሲቻል ነው፡፡ አዲስ ዓመት ደግሞ አዲስ አስተሳሰብ ይፈልጋል፡፡

ዘወትር እንደምንለው ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ የታላቅ ሕዝብም አገር ናት፡፡ ፍቅር፣ ይቅር ባይነት፣ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ አገርን በጋራ መጠበቅና ማሳደግ፣ ከልዩነቶች ይልቅ ለጋራ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት፣ ታማኝነት፣ አርቆ አስተዋይነትና ጨዋነት የታደለ ኩሩ ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህች ታላቅ አገር በተለያዩ ጊዜያት በገጠሟት ፈተናዎች ምክንያት ደግሞ የኋላ ቀርነት፣ የረሃብ፣ የግጭትና የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆና ዘመናትን ማሳለፏ ሳይበቃ የአምባገነን አገዛዞች ሰለባ መሆኗ የታሪክ ጠባሳዎቿ ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ የድህነት አረንቋ ውስጥ የዘፈቃትን መርገምት ተረት ማድረግ የሚቻለው የጥንታውያኑን ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የአገር ፍቅር ወኔ ወደ ዴሞክራሲ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ልማትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማዞር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት መንፈስ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ ከጎራና ከቡድን ጠባብ አስተሳሰብ በመውጣት፣ ከጽንፈኝነት በመላቀቅ፣ ጥላቻና ቂም በቀልን በማስወገድና እርስ በርስ በመከባበር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታው ጫፍ ማድረስ ይገባል፡፡ በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ በአንድነት ለመቆም መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር የምትችለው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጣቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ሲሰርፅ ነው፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ስብስብ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ሥርዓት አስይዞ ለዴሞክራሲያዊ ሕግጋት መገዛት ይኖርበታል፡፡ ሥልጣን የሚገኘው በጉልበት ወይም በአፈሙዝ ሳይሆን፣ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት በሆነው የሕዝብ ድምፅ መሆኑን የእያንዳንዱ ፓርቲ መሪ፣ አባልና ደጋፊ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የራስን ዓላማና ፍላጎት ሌሎች ላይ ለመጫን መሞከር አደጋ እንዳለው ግንዛቤ ሊያዝ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ጥርጊያውን ለማመቻቸት ሁሉም ወገን የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመርያ ለግጭት የሚዳርጉ ማናቸውንም አማራጮች በመተው ለሰላም መስፈን መሥራት ይገባል፡፡ ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ለማድረግ መዘጋጀት እንጂ፣ በግብዝነት ተነሳስቶ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ መግባት ቀውስ ያስከትላል፡፡ በአዲሱ ዓመት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አጀንዳዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ለሕዝብ እንደሚያቀርቡ ስለሚጠበቅ፣ ከዚህ በፊት ይታወቁ የነበሩ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መግታት ተገቢ ነው፡፡ ሕዝባችን ከምንም በላይ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንደሆነ በብርቱ መታሰብ አለበት፡፡ አዲሱ ዓመት ብቃትና ተፈላጊነትን በአሳማኝ መንገድ ማሳያ እንዲሆን፣ የሚመለከታቸው ሁሉ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ የግድ ይላቸዋል፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር አለባቸው፡፡

አዲሱ ዓመት የአዲስ ምዕራፍ መንደርደሪያ መሆን የሚችለው ከሸፍጥ፣ ለአሻጥር፣ ከሴራ፣ ከቂም በቀል፣ ከክፋት፣ ከሌብነት፣ ከዘረኝነትና ከመሳሰሉ አውዳሚ ተግባራት መታቀብ ሲቻል ነው፡፡ ለብጥብጥ፣ ለግጭትና ለሰላም መደፍረስ ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶች የሚጎዱት ሕዝብንና አገርን ነው፡፡ በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ የሚያስፈልገው፣ ሕዝብንና አገርን የሚጎዱ ድርጊቶች በምንም ዓይነት እንዳይከሰቱ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ የተለያዩ ሐሳቦች እንዲፋጩና የተሻለው ነጥሮ እንዲወጣ፣ ፖለቲካው በትርፍ ጊዜ ሥራነት ሳይሆን በልሂቃኑ የሙሉ ጊዜ ሥራ መመራት አለበት፡፡ ስሜታዊነት በምክንያታዊነት የሚገራው ፖለቲካው በገባቸው ልሂቃን ሲመራ ብቻ ነው፡፡ ፖለቲካው የጡረተኞች፣ የሥራ ፈላጊዎች ወይም የአኩራፊዎች መሰባሰቢያ ሲሆን፣ ከምክንያት ይልቅ ስሜታዊነት ይበዛል፡፡ በስሜት የሚነዱ ደግሞ መርህ ስለሌላቸው ለጥፋት ይነጉዳሉ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአባላትና ለደጋፊዎች ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቃተ ህሊና ማጎልበቻ ሥራዎች ላይ ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የሲቪክ ማኅበረሰቡ አብበው እንዲያግዟቸው ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ በአዲሱ ዓመት በስሜት የሚነዳ ሳይሆን፣ በምክንያት የሚንቀሳቀስ ትውልድ ፖለቲካውን በስፋት እንዲቀላቀል ማድረግ ይገባል፡፡ በሰንደቅ ዓላማና ከውጭ በሚገቡ ፖለቲከኞች አቀባበል ላይ የሚታየው ፉክክር፣ በአዲሱ ዓመትም የሚቀጥል ከሆነ ችግር ነውና ከወዲሁ ቢታሰብበት ይበጃል፡፡ አዲስ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ በቀድሞው ዓይነት የስህተት መንገድ ላይ መመላለስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘውን ነፃነት መጠበቅ የሚቻለው ማስተዋል ሲኖር ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፈልላቸው መብቶች በቀላሉ እንዳልተገኙ እየታወቀ፣ ከአገር ህልውና በታች ለሆኑ ጉዳዮች የሚደረገው ፉክክር ያሳዝናል፡፡ አገርን የምታህል ግዙፍ የጋራ ቤትን ከቡድን ፍላጎት በላይ ለማስበለጥ መሯሯጥ ፋይዳ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከአስፈሪ ቀውስ ውስጥ ወጥታ የተሻለ ዓውድ ውስጥ ባለችበት በዚህ ጊዜ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት በመትጋት መጪውን ጊዜ ማሳመር ሲገባ፣ ያልተገቡ ድርጊቶችን ለመፈጸም እንቅልፍ ማጣት ተገቢ አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአዲሱ ዓመት ትልቅ ዋጋ የተከፈለባቸውን መብቶችና ነፃቶች ማልከስከስ አይገባም፡፡ ከዚህ ይልቅ በብሔራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በመሰባሰብ ልዩነትን አስጠብቆ፣ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት መነሳት ይሻላል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ማንፀባረቅ የምትችለው ልጅቿ በነፃነት ሲኖሩ፣ በፈለጉት ሥፍራ ሲሠሩና ሀብት ሲያፈሩ፣ ፍትሕ ሲያገኙና ብሔራዊ ግዴታቸውን መወጣት ሲችሉ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በዚህ መንፈስ መነሳት ይገባል፡፡

በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያችን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት መናኸሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የፍትሕና የርትዕ አገር መሆን አለባት፡፡ በተዛነፉ የታሪክ ማስታወሻዎች ላይ ብቻ ተንጠላጥሎ ቀውስ ለመፍጠር ከመሽቀዳደም ይልቅ፣ በቅን ልቦና መነጋገርና ለአዲስ ጅማሮ መነሳት ይጠቅማል፡፡ አዲሱን ዓመት በፍቅር፣ በይቅር መባባልና በአንድነት መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ከራሷ አልፋ ለምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ በተለይ የግጭትና የውድመት ሰፊ ታሪክ ያለው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም አግኝቶ በትብብር መሥራት ሲቻል ብልፅግና ይመጣል፡፡ መሰንበቻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቀጣናውን ከጦርነትና እርስ በርስ ከመጠፋፋት ለማላቀቅ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጂቡቲንም በመጨመር የቀጣናውን ትልቅ አቅም በመጠቀም የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የሌሎችን እጅ ባለማየት ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡ በዚህ ሰፋ ያለ ዕቅድ በአግባቡ መሥራት ከተቻለ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ትሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ከቡድናዊና ከግላዊ ፍላጎቶችና ጥቅሞች በላይ መሆኗን በቅጡ መገንዘብ ከተቻለ ደግሞ መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፡፡ ስለሆነም አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ እንቀበለው!