Skip to main content
x
የዳያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያግዝና በአገር ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚያስተባብር ኤጀንሲ እንዲቋቋም ተወሰነ፡፡

ሐሙስ ጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የኤጀንሲውን መቋቋም አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም፣ ‹‹በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለማስተባበርና መብታቸው እንዲከበር ለማድረግ፣ እንዲሁም በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ለማቋቋም በሒደት ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሚቋቋመው ኤጀንሲው ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚሆንና ይህንን ተግባር እስካሁን ሲያስተባብር የቆየው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ያለው የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ የኤጀንሲውን መመሥረት ተከትሎ እንደሚከስም ታውቋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ የሚቋቋመው ኤጀንሲ የማቋቋሚያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ፣ ኤጀንሲው እንዲቋቋም በምክር ቤቱ ውሳኔ እንደተሰጠም ተነግሯል፡፡

የዳያስፖራ ኤጀንሲ ለማቋቋም የሚዘጋጀው ደንብ ማብራሪያ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ኤጀንሲው የዳያስፖራ ጉዳዮችን መከታተልና በሥልጣኑ ሥር የሚወድቁ ጉዳዮች ላይ ማስተባበር፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የምዝገባና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘርጋት፣ በውጭ አገሮች የተቋቋሙና አዲስ ለሚቋቋሙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ መገናኛ ብዙኃን ድጋፍ ማድረግ፣ ከዳያስፖራው የሚገኙ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት፣ የዳያስፖራ የገንዘብና የሕዝብ አስተዋጽኦ አሰባሰብ ሥርዓት መዘርጋትና ማስተባበር፣ በአገር ውስጥና በውጭ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለሚዘጋጁ መድረኮችና ዝግጅቶች ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ሥልጣኖችና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡፡

ኤጀንሲው አማካሪ ምክር ቤት የሚኖረው ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተሮችን ጨምሮ አስፈላጊ ሠራተኞች እንደሚኖሩትም ሰነዱ ያስረዳል፡፡

ይሁንና ይህ የዳያስፖራ ኤጀንሲ እንዲቋቋም በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሁን ያለን ሐሳብ መስከረም ላይ አብዛኛውን ሚኒስቴር ማጠፍ ነው፡፡ ምክንያቱም በጣም ባለሥልጣን በዛ፣ ባለሥልጣን ሲበዛ ውጤታማነት ስላልተለመደ አንዴ ከተሾምክ መውረድ ከባድ ስለሆነ ዕዳው እንዳይበዛ፣ ቢያንስ የዳያስፖራን ጉዳይ ቀስ ብለን እንጀምረዋለን፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ የዳያስፖራ ኤጀንሲ እየተቋቋመ መሆኑን በመግለጽ ዋና መሥሪያ ቤቱን አዲስ አበባ በማድረግ፣ እንዳስፈላጊነቱ በክልሎች መሥሪያ ቤቶች ሊኖሩት እንደሚችል አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ባለው የዳያስፖራ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የሚሰጠው አገልግሎት፣ ምንም አንኳን የራሱ ባለሙያ በኤምባሲና በቆንስላዎች  ተመድቦ ቢሠራም፣ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ  እያደገ የመጣውን የዳያስፖራ ተሳትፎ ይበልጥ ያቀላጥፋል የተባለለት ይህ ኤጀንሲ ቻይና፣ ህንድ፣ ናይጄሪያ፣ ኮሪያና የመሳሰሉት አገሮች የሚሠሩባቸው ልምዶች ተቀምረው እንደሚቋቋም ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት በዳያስፖራው እንደተደረገ፣ በብዛት መደበኛ ባልሆነ መንገድ እየመጣ አሁን በዓመት አምስት ቢሊዮን ዶላር የደረሰውን ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ በመደበኛው መንገድ እንዲገባ ለማድረግ ኤጀንሲው ያግዛል ተብሏል፡፡