Skip to main content
x
‹‹ኢትዮጵያ በየትም ሥፍራ በነፃነት ተንቀሳቅሰን የምንሠራባት የጋራ ቤታችን መሆኗን መቀበል አለብን››

‹‹ኢትዮጵያ በየትም ሥፍራ በነፃነት ተንቀሳቅሰን የምንሠራባት የጋራ ቤታችን መሆኗን መቀበል አለብን››

አቶ ብዙአየሁ ታደለ፣ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ መሥራችና ሊቀመንበር

           በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከተሰማሩ ውጤታማ ከሚባሉ ባለሀብቶች መካከል፣ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያ መሥራችና ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ብዙአየሁ በኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሥር የሚተዳደሩና በተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ከ25 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ኩባንያዎችን በሊቀመንበርነት ይመራሉ፡፡  ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀው የቢዝነስ ልምዳቸው፣ ከቤተሰብ የተወረሰና እሳቸው ማስቀጠል የቻሉት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች በውጭም በአገርም ሠርተዋል፡፡ ገና በ18 ዓመታቸው ራሳቸውን ችለው መሥራት መጀመራቸው፣ በተለይ የአባታቸው ጥንካሬና ከእሳቸው የወረሱት ምግባር አሁን ላሉበት ደረጃ መድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው ይላሉ፡፡ ኩባንያዎቻቸው በእርሻ፣ በተለይ በሻይ ልማት፣ በግል ንፅንና መጠበቂያ፣ በምግብ ዘይት፣ በምግብና አልሚ ምግቦች፣ በሲሚንቶና በድንጋይ ከሰል ምርቶች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ በሪል ስቴትና በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ውስጥም እየሠሩ ሲሆን፣ የፓኬጂንግ ማምረቻ ይጠቀማሉ፡፡ አቶ ብዙአየሁ ከ40 ዓመታት በላይ በቢዝነስ ሥራዎች ከስድስት ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን ይዘዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ፎርብስ የተሰኘው መጽሔት ‹ቢሊየነር ኢትዮጵያውያን› ብሎ ከጠቀሳቸው አምስት ባለሀብቶች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ፣ ሊንከን ዩኒቨርስቲ በተሰማሩበት መስክ ላስመዘገቡት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት አበርቶላቸዋል፡፡ ረዥም በሚባለውና ውጤታማ እንደሆነ በሚታመንበት የሥራ ክንውናቸው፣ እንዲሁም የአገር ኢንቨስትመንትን ከማሳደግ አኳያ ምን መደረግ እንደሚኖርበትና በሌሎች ወቅታዊ አገራዊና ቢዝነስ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ ብዙአየሁ ታደለን አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከ40 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ ወደ ቢዝነስ እንዴት ገቡ? ከየት ተነስቼ የት ደርሻለሁ ይላሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- እኔ የመጣሁበት ቤተሰብ ሦስተኛ ትውልድ ነኝ፡፡ መጀመርያ ቢዝነሱን የጀመሩት አያቴ ናቸው፡፡ አያቴ የመጡት ከዲማ ጊዮርጊስ ነው፡፡ በአነስተኛ ቢዝነስ ዕጣን፣ አቡጄዲና የመሳሰሉትን በመነገድ ነው፡፡ አያቴ የሚሠሩትን ሥራ አባቴ ተረከቡ፡፡ ከዚያ እኔም የአባቴን ፈለግ ተከተልኩ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አባቴም ቤተሰቦቼም በጣም ውጤታማ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባና በደቡብ ክልል እንደ ዲላ ባሉ ከተሞች ሠርተዋል፡፡ በሪል ስቴት ውስጥም ነበሩ፡፡ በዲላ ከተማ በ1941 ዓ.ም. አካባቢ መብራት የለም ነበር፡፡ የመጀመርያውን የታጠበ ቡና መፈልፈያ ሥራ እኛ ነን የጀመርነው፡፡ የቡና እርሻዎች ነበሩን፡፡ አባቴ ጠንካራ ሠራተኛ ነበሩ፡፡ እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ከአባቴ ጋር እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የቤተሰብ ቢዝነስ በደርግ ጊዜ ተወረሰ፡፡ በዚህ በምክንያት እህቶቼና ወንድሞቼ ወደ አሜሪካ ሄደው ነበር፡፡ እኔ ቤተሰቤን መጠበቅ ስለነበረብኝ አባቴን ጥዬ አልሄድም ብዬ ቀረሁ፡፡ ለቤተሰብ ስል ትንሽ የተረፈችውን ከአባቴ ጋር መሥራት ቀጠልኩ፡፡ በጥቅሉ ረዥሙ ጉዞ የሚጀምረው ወታደራዊ ደርግ ሥልጣን ሲቆናጠጥ በተከተለው ፖሊሲ አቅጣጫ ምክንያት፣ ቀደምት ቤተሰቦቼ በብዙ ጥረትና ውጣ ውረድ ያፈሩትን አብዛኛውን ሀብትና ንብረት በወረሳቸው ወቅት ነው፡፡ የቤተሰቦቼን መልካም ስምና ሥራ ማስቀጠል አለብኝ በሚል ቁጭትና እልህ በመግባት፣ በውስጤ ይመላለስ የነበረውን የቢዝነስ ሕይወት በማውጣት ከአባቴ በተሰጠኝ መነሻ ካፒታል በአፍላ የወጣትነት ዕድሜዬ በፅናት የተሳካ ሥራ ለማከናወን ወደ ንግድ ዓለም ተሰማራሁ፡፡ ከዚያም የፋይናንስ አቅሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ ቢሄድም በደርግ ዘመን የነረው ነባራዊ ሁኔታ ብዙም አመቺ ስላልነበር፣ ከጓደኞቼ ጋር በጋራ በመሆን ወደ ጎረቤት አገሮች ማለትም ኬንያና ጂቡቲ አልፎም እስከ ዱባይና ሲንጋፖር መንቀሳቀስ ችዬ ነበር፡፡ ሆኖም ቀደም ሲል የነበረውና ህልሜ በአገሬ በማምረቻና በኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት ነበር፡፡ በውጭና በአገር ውስጥ በንግድ ያፈራሁትን ጥሪት በመያዝ የረዥም ጊዜ ህልሜና ውጥኔ ወደነበረው የማምረቻ ኢንዱስትሪ መስክ ተሰማራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ራስዎን ችለው ሲወጡ የመጀመርያ ሥራዎ ምን ነበር?

አቶ ብዙአየሁ፡- እንግዲህ በአብዛኛው የአባቴ ቢዝነስ ቡና ነበር፡፡ ከአባቴ ጋር የታጠበ ቡና እሠራ ነበር፡፡ በቤተሰባችን ውስጥ ገና ሰባትና ስምንት ዓመት አካባቢ እንደሆነን፣ ከአባቴና ከቤተሰባችን ጋር የመሥራት ልምድ ነበረን፡፡ ባህሉ እሱ ነው፡፡ በአዕምሮአችን አሠራር ሰው ቋንቋ እንኳን የሚማረው በሰባት በስምንት ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ እኔም ራሴን ችዬ ሥራ ስጀምር የታጠበ ቡና በመሥራት ነው፡፡ በአጠቃላይ በቤተሰባችን ውስጥ ከቢዝነስ ሥራ ውጪ የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡ ልጅ ሆኜ ለታጠበ ቡና  ሁለት ሦስት ሰው ይዘን እንሠራ ነበር፡፡ ቢዝነስ ደማችን ውስጥ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሥራ ከጀመርኩ በኋላ አገር ውስጥ የነበረው ፖለቲካ ችግር ነበረው፡፡ መዋቅሩ አያሠራም፡፡ ስለዚህ የተንቀሳቀስኩት ወደ ጎረቤት አገር ነው፡፡ ወደ ጂቡቲና ኡጋንዳ ሄድኩ፡፡ እዚያ አጋጣሚውን የማግኘት ዕድል ገጠመኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኬንያና ጂቡቲ ከሄዱ በኋላ ምንድን ነበር የሚሠሩት?

አቶ ብዙአየሁ፡- ንግድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ እናመጣለን ከዚያ እንልካለን፡፡ ከምፅዋ ጨው እንጭናለን፡፡ በጊዜው የነበረው አብዛኛው ሥራ እሱ ነው፡፡ አባቴም ቢሆኑ ንግዱን አይወዱትም ነበር፡፡ ወፍጮና የመሳሰሉትን ይሠሩ ነበር፡፡  ከጀርመኖችና ከግሪኮች ጋር በጋራ የሚሠሯቸው ሥራዎች ነበሩ፡፡ እርሻ ላይ ሰፊ ሥራ ነበረን፡፡ ቡና ማጠቢያ ላይ ነው የምንሠራው፡፡ የቤተሰቡ ባህል ወዲያው ገንዘብ የሚገኝበት ሥራ ላይ አልነበረም፣ እንደ እርሻና የመሳሰሉት ላይ ነው የሚሠራው፡፡  ሁሉም ሰው ንግድ ላይ በሚሠራበት ጊዜ እሳቸው ከዚህ የተለየ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር፡፡ አባቴ ሁሌ የሚገፉኝ እንዲህ ያለውን ሥራ እንድሠራ ነው፡፡ የበለጠ ደግሞ ታክስ እንድከፍል፣ አገሬን እንዳገለግል ነበር፡፡ ይህ ተፅዕኖ ኢዱንስትሪን እንድመለከት አድርጎኛል፡፡ በ18 ዓመቴ እንደ ትልቅ ኢንዱስትሪ የሚታየውን የታጠበ ቡና እሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያውን የግል ኢንደስትሪ ዞን በመገንባት ስምዎ ይጠቀሳል፡፡ በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ ኢንቨስትመንቶችና ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞችም አሉዎት፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት ብዙ የሠሩ ቢሆንም፣ ድምፃቸው የማይሰማ ኢንቨስተር ናቸው ይባላል፡፡ ለምን?

አቶ ብዙአየሁ፡- የአስተዳደግ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ዋነኛው ምክንያት ግን ድርጅታችን ውስጥ እንደ ባህል አድርገን የምንከተለው ድርጅቶቻችንንና ምርቶቻችንን በማስተዋወቅ፣ በመጀመርያ ሥራን በማስቀደምና በጋራ በመጣር መታወቅ ያለብን በኩባንያችን ስኬት ነው የሚል መርህ መያዛችን ነው፡፡ ድርጅታችን ተልዕኮውን ግልጽ በሆነ አሠራርና ሥነ ምግባር በመከተል ለአካባቢውና ለማኅበረሰብ በኃላፊነትና በተቆርቋሪነት በመሥራት፣ የራሱ የሆኑ የተለያዩ ምርቶችን በጥራት በማቅረብና ከግል ዝናና ስም ይልቅ የኩባንያውን ዓላማ በማለማመድ መታወቅ የሚል ዓላማ በመያዝ ነው፡፡ ብዙም ወጣ ብዬ ልታይ የምል አይደለሁም፡፡ ሌላው ገና ምን ተሠራና ነው? በሌሎች አገሮች ከሚገኙ ኢንቨስተሮች አኳያ ስንነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል ሀብት አላፈራንም፡፡ እንዲሁ  አገራችን ደሃ በመሆኗ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኢኮኖሚ አቅም ስለፈጠርን ብቻ ብዙ ልታይ ልታይ ማለት ጠቃሚ ካለመሆኑም በላይ፣ የአገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞች አገራቸውን በጣም ዝቅተኛ በሚባል ክፍያ በሚያገለግሉበት አገር ውስጥ እንደ ባለሀብት ራስን በዲስፕሊን መግዛት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የተሰማሩባቸውን የኢንቨስትመንት መስኮች እንዴት መረጡዋቸው? ስለሚያንቀሳቅሱዋቸው ኩባንያዎች ይዘትና የተሰማሩባቸውን ዘርፎች ይጥቀሱልኝ? እንዴትስ ነው 20 እና 30 ኩባንያዎች የሚመሩት?

አቶ ብዙአየሁ፡- የተሰማራንባቸውን የኢንዱስትሪ መስኮች ስመርጥ አገራችን በኢንዱስትሪ ዘርፍ የምትጫወተውን ሚና ለማሳደግ ያለኝ ምኞት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አዲስ የሚከፈቱ ፋብሪካዎች አዋጭነትና ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ተደራሽ መሆናቸው፣ በአገር ደረጃ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸው፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ወይም ወጪውን በማስቀረት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ፣ ለመንግሥት የታክስ ገቢ በማሳደግ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጥቅሞችን በማስገኘት ረገድ የሚኖራቸውን ፋይዳ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ በሚደረስበት ውጤት በመመርኮዝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የተሰማሩባቸው የቢዝነስ ዘርፎች በርካታ ናቸው፡፡ በየትኞቹ ዘርፎች ላይ እየሠሩ ነው?

አቶ ብዙአየሁ፡- የተሰማራሁባቸው የኢንዱስትሪና የልማት ዘርፎች በጥቅል በክላስተር ሲታዩ የሻይና ቡና ልማት አንዱ ነው፡፡ የእርሻ ልማቱንና ተጨማሪ እሴት በማከል ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ማቅረብን ይጨምራል፡፡ ሌላው የግል ንፅህና መጠበቂያና የሰውነት ማስዋቢያ ምርቶች ማለትም የልብስና የገላ ደረቅና ፈሳሽ ሳሙናዎችን፣ የሰውነትና የፀጉር ቅባቶችንና ሽቶ የመሳሰሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ናቸው፡፡ የምግብ ዘይት ማምረትና ማከፋፈል፣ የምግብ ውጤቶችንና አልሚ ምግቦችን እናመርታለን፡፡ የሲሚንቶና የድንጋይ ከሰል ማምረት፣ የሪል ስቴት ግንባታ ማካሄድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ የፓኬጂንግ ምርቶችን ማምረት፣ የማከፋፈልና የንግድ ሥራዎች ያካትታል፡፡ ፋብሪካዎቹ በቁጥር ብዙ እንደ መሆናቸው መጠን እነዚህ ተቋማት የሚያስተዳድሩትን ገንዘብ ጨምሮ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ሀብት መጠን በቢሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ለስኬታችን ወሳኝ የሆነው የሰው ኃይል ቁጥርም ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን ጨምሮ ስድስት ሺሕ ያህል ይደርሳል፡፡  ይህን ሁሉ ሀብት ለማስተዳደር፣ በገበያው ውስጥ ብዙ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቆየትና በኅብረተሰቡ ዘንድ የፋብሪካዎቻችንን መልካም ስምና ዝና በዘላቂነት ይዞ ለመቆየት ለስኬት ቁልፍ የሆነው ዘመናዊ የማኔጅመንት ሥርዓት መዘርጋትና ሥራ ላይ ማዋል ግድ ይላል፡፡ በዚህ ረገድ ባደጉ አገሮች እንደሚደረገው በእኛም የኢንቨስትመንት ተቋማት የኮርፖሬት ገቨርናንስ መርህ በመከተል አያሌ ሥራዎችን አከናውነናል፡፡ ለአብነት ያህል ለእያንዳንዱ ፋብሪካ የራሱ ድርጅታዊ መዋቅር፣ ፖሊሲዎችና መመርያዎች ተዘርግተው ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረገ በመሆኑ፣ ፋብሪካዎቻችንን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር አስችሎናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእያንዳንዱን ፋብሪካና የኢንቨስትመንት መስክ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ፣ ዓመታዊ በጀት፣ እንዲሁም የሥራ አፈጻጸም በየጊዜው የሚገመግምና ተገቢውን ድጋፍ የሚሰጥ በኮርፖሬት ደረጃ የተቋቋመ ማዕከል አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች አለመረጋጋቶች ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ብዙ ኢንቨስተሮች ችግሩ ውስጥ ነበሩ፡፡ የእርስዎስ ኩባንያዎች ይህ ችግር አልገጠማቸውም?  እንዴት አሳለፉት? ተፅዕኖውስ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ብዙአየሁ፡- የነበረው ችግር እንደ ድርጅት ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም የተፈተንበት ነው፡፡ እንደ ግለሰብም የመኖር ያለመኖራችን ጉዳይ በጣም አሳሳቢ የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ከእኛ አንፃር ብዙ ተፅዕኖዎችን አሳልፈናል፡፡ ከስድስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ይዘን የምንሠራ ከመሆናችን አንፃር፣ እንዲሁም ከሲሚንቶ ፋብሪካው ሌላ  ሌሎች አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎቻችን የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ በመሆናቸው የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላችን ከአቅማቸው በታች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለእነዚህ ስድስት ሺሕ ሠራተኞች ደመወዝ እየከፈልን ለመዝለቅ ስናደርገው የነበረው ጥረት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የፀጥታ ችግሩም ለሥራችን እንቅፋት ነበር፡፡ እንዲህ ባለው በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ እንደ ድርጅት መቆየታችን ራሱ ይገርመኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት ማለፍ ቻላችሁ?

አቶ ብዙአየሁ፡- ከአንዱ ድርጅት ወደ ሌላው ድጎማ በማድረግ ነው፡፡ አንደኛውን ድርጅት ወደ ሌላው እያመጣን የነፍስ አድን ሥራ ሠርተናል፡፡ ሠራተኛው እንዳይበተን ብዙ ጥረት አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ፍትሐዊ የሆነ የውድድር ሜዳ አለ ብለው ያምናሉ? አመቺ አሠራር አለ?

አቶ ብዙአየሁ፡- የለም፡፡ እውነት ለመናገር በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ መሰል አገሮች ብትሄድ፣ የባንክ ብድር ማግኘት ከፈለግክ በአንድ ሳምንት ሊያልቅልህ ይችላል፡፡ እዚያ ብድር ለመስጠት ኢንተርፕሪነርሽፕ (ሥራ ፈጠራ) ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ እዚህ ያሉት ባንኮች ስለኮራቶራል (መያዣ) ነው የሚያወሩት፡፡ እንዳይጠየቁ ስለሚፈሩ አስቀድመው ኮላተራል ነው የሚጠይቁህ፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን ለመከላከል ነው የሚሠሩት፡፡ ለምሳሌ እኔ ደቡብ አፍሪካ ብሄድ እንዴት አድርገን ቢሊየነር እናድርግህ? እንዴት ስኬታማ እናድርግህ? ብለው ነው የሚሠሩት፡፡ አሁን እዚህ ለውጭ ኩባንያዎች በሩ ቢከፈት የሚያስፈራን፣ እኛን እስከ እራት አይጠብቁንም ቁርስ ነው የሚያደርጉን፡፡ የሥራ ግንኙነታቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡ እነሱ ስለአዳዲስ ግኝቶች ነው እንጂ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይገጥመኝ ይሆን? ብድር እንዴት አገኛለሁ? ብለው አይጨነቁም፡፡ ሊጨነቁ የሚችሉት እንዴት አድርገን እንሥራ ነው፡፡ እዚህ እኛ የምናስበው እንዴት ብናደርግ ነው ብድር የምናገኘው? በሚል መጨነቅ ነው፡፡ ሥራችን ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አንድ ኢንቨስተር የአገሪቱን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል? በነፃነት የመሥራት ዕድል አግኝቼ የምፈልገውን ሠርቻለሁ ወይም እየሠራሁ ነው ብለው ያምናሉ? በሁለቱም መንግሥታት ኢንቨስትመንቶችዎን ሲያከናውኑ ቆይተዋልና የሁለቱ ሥርዓቶች ጉዞዎ እንዴት ነበር?

አቶ ብዙአየሁ፡- በአገራችን የሚታየው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ለማንኛውም ባለሀብት ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ለፖሊሲው የሚመጥን መልካም አስተዳደርና በተረጋጋ አዕምሮ ሊያሠራ የሚችል ሰላም መኖሩን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚታየው ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም፣ ወደፊት በሕዝቡ ውስጥ መሠራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ በየክልሉ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ከተቻለ ቀሪዎቹ ሥራዎች በሒደት እየተሟሉ ይሄዳሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለመሥራት ያሰብኩትን ሁሉ በነፃነት የመሥራት ዕድል ነበረኝ ብዬ አላምንም፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት ባሳለፍኩባቸው 40 ዓመታት ውስጥ በሁለት መንግሥታት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተከፈተው ዕድል፣ ቀደም ሲል ከገለጽኩት መልካም አስተዳደርና ፖሊሲ አንፃር ሲታይ አመቺ አልነበሩም ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ይህም በወቅቱ ከነበሩት የአገዛዝ ሥርዓቶች ባህሪ የሚመነጩ ነበሩ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዘመን በትምህርት ላይ ስለነበርኩ ብዙ መናገር አልችልም፡፡ በደርግ ዘመን ሥርዓቱ የሶሻሊዝምን መንገድ እከተላለሁ በሚል ወታደራዊ አገዛዝ የሰፈነበት ስለነበር፣ ውስን በሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከነበረኝ ተሳትፎ የዘለለ ሥራ የመሥራት ዕድል አልነበረኝም፡፡ ሰፊ ወደ ሆነ ኢንቨስትመንት መግባት የቻልኩት ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ነው፡፡ ሆኖም ሥራዎቼን ሁሉ በተሟላ ነፃነትና ሰላም ስመራ ቆይቻለሁ ማለት አልደፍርም፡፡ ሆኖም የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና የፀጥታ ችግሮች በየጊዜው የተስተዋሉ ቢሆንም እነዚህን ተግዳሮቶች በፅናት እንደ አመጣጣቸው በመቋቋም፣ በእነዚህ ውስጥ የተገኙ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ዛሬ የምንገኝበት ዕድገት ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድና በኢንቨስትመንት ላይ ያለዎት ፍልስፍና ምንድነው? ውጤታማ አድርጎኛል ብለው የሚገልጹት ነገር ምንድነው? ነጋዴ ነዎትና ኪሳራ ገጥሞዎት ያውቃል?

አቶ ብዙአየሁ፡- የአንድ ባለሀብት የኢንቨስትመንት ፍልስፍና እያንዳንዱ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊደርስ ከሚያስበው ዘላቂ የሕይወት ግብና በሒደት ከሚገጥሙት ነባራዊ ሁኔታዎች ተነጥሎ ሊታይ አይችልም፡፡ በመሆኑም የእኔ የኢንቨስትመንት ፍልስፍና ዘላቂ በሆነና ለአገር ዕድገት በሚጠቅም የሥራ መስክ ኢንቨስት በማድረግ፣ ለወሰድኩት ከፍተኛ ሪስክ (የአደጋ ተጋላጭነት) በዘላቂነት ተመጣጣኝ የሆነ ጥቅም ማግኘት ነው፡፡ ይህም ማለት ከአየር በአየር ንግድ ወይም በተለያዩ የንግድ መስኮች በመሳተፍ ከሚገኝ ዳጎስ ያለ ጥቅም ይልቅ በሚጨበጥ፣ በሚዳሰስና በሚታይ የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ለራስም ሆነ ለአገር ዘላቂ ጥቅም ማስገኘት የኢንቨስትመንት ፍልስፍናዬ ነው፡፡ ለዚህም ፍልስፍናዬ መነሻ የሆነኝና ትልቁ ሀብት ከቤተሰቦቼ በተለይም ከአባቴ የወረስኩት ጥበብ፣ ጠንካራ የሥራ ባህልና ሀቀኝነት ነበር፡፡ ልጅ ሳለሁ ገና አባቴ የንግድ ሥራ እንዴት መከናወን እንዳለበት ሲያወሩ ከሰማሁት ይጀምራል፡፡ ወደ ቢዝነስ ዓለም ስገባ የሰማሁትን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ የአባቴ ዋነኛ ምክር የነበረው ‹‹ንፁህ ያልሆነ ገንዘብ ይዘህ ወደ ቤት አትምጣ፣ የማታ ማታ ያጠፋሃል፤›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር እስከ ዛሬ አብሮኝ ይኖራል፡፡ ይህንን ምክርና ማስጠንቀቂያ እንደ መርህ መከተሌ ለስኬት በአያሌው ረድቶኛል፡፡ በቀጣይም በልምድና በተግባር ሥራዎቼ ተሞክሮ እንደ አንድ ፖሊሲ በመውሰድ፣ በግልጽነት አሠራር ላይ ምንም ዓይነት ድርድር ባለማድረግ ድርጅቱን የምመራው ያለምንም የክርስትና አባት ነው፡፡ ዋጋ ቢያስከፍለኝም ይህ እምነት ፍርኃትን ከማስወገዱም በላይ ለአሁኑም ሆነ ለቀጣይ ጉዞዬ ትልቅ አቅም ፈጥሮልኛል፡፡ በእርግጥ ይህ ፍልስፍና የንግድ ሥራና የኢንቨስትመንት መስኮችን የረዥም ጊዜ ግብ ቀርፆ፣ ሥራን በዕቅድ መምራትና በድፍረት መራመድን ይጠይቃል፡፡ ማንኛውም ሥራ ከጅምሩ ከፍፃሜ ሊደርስ የማይችል መስሎ ከታየና ውድቀት ያስከትል ይሆናል ተብሎ በሥጋት ከታጀበ ወደፊት መራመድ አይችልም፡፡ ስኬት የሚገኘው ውድቀትን ማስቀረት ይቻላል ከሚል የድፍረት ውሳኔ ጫፍ ላይ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ረገድ ሳልፈራና ሳላመነታ ያሰብኩትን ለመፈጸም ወደ ሥራ ደፍሬ ስለምገባ ውጤት አግኝቼበታለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለስኬቴ ትልቁ የረዳኝ ተቋማዊ አቅም መገንባቴ ነው፡፡ ሌላው ትልቁ የእኔ ሚስጥር የአገርና የውጭ ባለሙያዎቼን መጠቀሜ ነው፡፡ ሦስተኛ ግልጽ መሆኔ ነው፡፡ ግልጽነት ፈጠራን ያሳድጋል፡፡ ፍርኃት ግን ይገድላል፡፡ ስለዚህ ሳልፈራ ስለምሠራ፣ ስለማልሰርቅና የፈለግኩትን ባለሙያ አመጣለሁ፣ እመልሳለሁ፡፡ በራስ መተማመን ስላለኝ መዝለቅ የቻልኩ ይመስለኛል፡፡ በሥራ ዘመኔ ኪሳራ ደርሶብኝ እንደሆን ላቀረብከው ጥያቄ እኔ በአንድ ውስን በሆነ የንግድ ወይም የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማራሁ ባለመሆኔ፣ ኪሳራ ደርሶብኝ ነበር ብዬ መናገር አልችልም፡፡ በአንድ የሥራ መስክ ባይሳካልኝ ወይም ችግር ቢገጥመኝ በሌላው አሸፍነዋለሁ፣ ወይም አካክሰዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመሥገን እስካሁን በጥቅሉ አልከሰርኩም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ኢኪኖሚዋ እያደገ ነው ቢባልም፣ አሁንም ብዙ ተግዳሮቶች ያሉባት አገር ነች፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ብዙ ዕድል እያላት በሚፈለገው ደረጃ አለማደጓ ከምን የተነሳ ይመስልዎታል? መፍትሔውስ? የግሉ ዘርፍ ሚናስ እንዴት መቃኘት አለበት ብለው ያምናሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- የኢኮኖሚ ጠበብቶች ፖለቲካና ኢኮኖሚ የተሳሰሩ በመሆናቸው፣ ያለፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ የለም ይላሉ፡፡ ያለኢኮኖሚ የፖለቲካ መፍትሔ የለም ይላሉ፡፡ ስለዚህ ላነሳኸው ጥያቄ መፍትሔው ለእነዚህ ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ጠበብቶች በዚህ ላይ የመፍትሔ ሐሳብ ማፍለቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ ልምድ ያላቸውን የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን ጥናት በማሠራት ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ በመንግሥት በኩልም ለሕዝቡ የፖሊሲ አማራጮችን በማቅረብ ዘላቂ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ለአገራችን ዕድገት ቁልፉ ያለው በሚመራንና በሚያስተዳድረን መንግሥት እጅ ነው፡፡ ለዕድገትና ለብልፅግናችን መሠረቱ አገራችን ያላትን ዕምቅ ሀብት ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅና በዚያ ላይ ተመሥርቶ የልማት ምርጫዎቻችንን መወሰን ነው፡፡ ላለማደጋችን ሚስጥር ከተጠናወተን ድህነት የሚያላቅቀንን የዕድገት ቁልፍ ፈትሸን አለማግኘታችንና በዚህ አቅጣጫ መሥራት በነበረብን በጊዜ አለመሥራታችን ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ የኅብረተሰባችን አካል እንደ መሆኑ የሚጠበቅበትን የዜግነት ኃላፊነት የሚወጣው በዚሁ የልማት ዕቅድና ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡  በተለይ የግሉ ዘርፍ በታክስ፣ በኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ዙሪያ እንደ ግዴታ በመውሰድ አገራችንን ካለባት ችግር ማዳን ይጠበቅበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንደ ትልቅ ተግዳሮት ከሚታዩት ውስጥ አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የተሰማሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አለባቸው፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ምን ያህል ይፈትናሉ? የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መንስዔው ምንድነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- ለማንኛውም ዓይነት ኢንዱስትሪያዊ ልማት የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ አቅርቦት መኖር ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን በተፈለገው ጊዜና በበቂ ማግኘት ባለመቻላችን ሥራችንንና ግባችንን በእጅጉ ሲፈታተን የኖረ ችግር ነው፡፡ ለምርት ግብዓቶች በውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት ድርጅቶቻችን ካላቸው አቅም እጅግ በጣም ያነሰና ከ15 እስከ 20 በመቶ ያህል ብቻ ቢሆንም፣ በድርጅቶቻችን በየወሩ ከጥቅማ ጥቅምና ተያያዥነት ካላቸው አስተዳደራዊ ወጪዎች ውጪ ለደመወዝ ብቻ በየዓመቱ ብር ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንፈጽማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንደገለጹልኝ የእርስዎ ኩባንያዎች ብዙዎቹ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን የሚጠቀሙ በመሆናቸው፣ የአገር ችግር ሆኖ የዘለቀውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ምን ቢደረግ ይበጃል ይላሉ? እርስዎ በሌሎች አገሮች  በተመሳሳይ ቢዝነሶች ሠርተዋልና የኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ችግር ከሌሎች አገሮች አንፃር እንዴት ያዩታል? በጥቅሉ በውጭ ምንዛሪ ችግር ላይ እንደ መፍትሔ የሚያቀርቡት ሐሳብ አለ?

አቶ ብዙአየሁ፡- እውነት ለመናገር እኔ ኢኮኖሚስት አይደለሁም፡፡ ይህንን በአኃዛዊ መረጃ ላቀርብልህ አልችልም፡፡ ግን በበቂ ሁኔታ እረዳለሁኝ፡፡ በተለይ የውጭ ሸሪኮች አሉኝና በዚህ ጉዳይ እንወያያለን፡፡ ከዚህ አንፃር ለችግሩ ዋና ምንጭ ፖሊሲው መሆኑን ነው የምናስበው፡፡ ለምሳሌ በጣም ደካማ የምንላት ሶማሌላንድ ስለውጭ ምንዛሪ ችግር አይወራም፡፡ በኬንያንና በጂቡቲ ችግሩ የለም፡፡ ለምንድነው ሌላው አገር የሌለ ችግር እዚህ የሚከሰተው? የሚለውን ጥያቄ ለኢኮኖሚስቶቻችን አቀርባለሁ፡፡ ለምሳሌ በጂቡቲ ሰባት ስምንት የሚሆኑ ባንኮች አሉ፡፡ ለምንድነው እነዚያ ባንኮች እዚያ የመጡት? ምን ሊሠሩ መጡ? ለምንድነው እነዚህ ባንኮች እዚህ የማይመጡት? ለምንድነው ጥሬ ዕቃዎች በኮንትሮባንድ ወደ ጂቡቲ የሚሄዱት? ለምንድነው የቀንድ ከብቶቻችን በኮንትሮባንድ በሶማሌ በኩል የሚወጡት? ለምን በእኛ በኩል በሕጋዊ መንገድ አልወጡም? ሶማሌላድ የቀንድ ከብቶች አሏት፡፡ ግን እነዚህ የቀንድ ከብቶች ወደ እኛ ገብተው በእኛ በኩል አልመጡም? የእኛ ሲስተም ጥሩ ቢሆን እኮ የሶማሌ የቀንድ ከብቶች በእኛ በኩል ወጥተው ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይቻል ነበር፡፡ ሰው የውጭ ምንዛሪ ለምንድነው የሚያሸሸው? ሌባ ስለሆነ ነው? አይደለም፡፡ ስለዚህ እንዲህ የሚሆንበት ምክንያት ታይቶ ፖሊሲዎች መሻሻል አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር ሰፊ ነው፡፡ ይህንን ድንበር በፖሊስና በወታደር ጠብቀህ አትችልም፡፡ ስለዚህ ደግሜ ደጋግሜ የምገልጸው ፖሊሲው መፈተሽ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ፖሊሲው ይፈተሽ ሲሉ ምን ዓይነት ቅርፅ ይያዝ? እንዴት ዓይነት ቅኝት ይኑረው ብለው ይመኛሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- መጀመርያ ኢኮኖሚው ሊብራላይዝ መደረግ አለበት ነው የምልህ፡፡ የውጭ ባንኮች መግባት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ኢንቨስተሮች ስለውጭ ምንዛሪ ምንም አያስቡም፡፡ ስለፈጠራ ነው የሚያስቡት፡፡ በሰፕላይ ክሬዲት ያመጣሉ፡፡ በጋራንቲ ያመጣሉ፡፡ ስለዚህ ችግር የለባቸውም፡፡ አሁን እዚህ ለውጭ ባንኮች በሩ ቢከፈት ብዙ ሊጠቅሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ባለንበት አቅም የሚያሰፈራን ነገር ስላልተዘጋጀን ጠራርገው ያጠፉናል ይባላል፡፡ በዕውቀትም በሀብትም ይበልጡናል፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ባንኮች ይግቡ ቢባል አሁን እርስዎ የጠቀሱልኝ ሥጋት ካለ፣ ሥጋቱ ሳይከሰት አገር በሚጠቅም መንገድ ገብተው እንዲሠሩ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ብዙአየሁ፡- መንግሥት እንደ አንድ ትልቅ ስትራቴጂ ጉዳዩን ይዞት የንግዱን ኅብረተሰብን ወይም ባለሀብቶችን ማዳመጥ፣ በተለይ ከውጭ ይመጣሉ የሚባሉትን እንደ ሞዴል ወስደው በመሠልጠን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ኮሪያ ያሉ አገሮች ይህንን ነው ያደረጉት፡፡ በሩን ከመክፈት በፊት ንቁ ሆኖ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች እገዛ በማድረግ አቅማቸውን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ ውድድር ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ እኔ እንደማስበውና እንደምናገረው በሩ ለውጭ ኩባንያዎች ተከፈተም አልተከፈተ፣ የእኔ ጥያቄ እዚህ ያሉት አንድ ሺሕ ሁለት ሺሕ ነጋዴዎችን ከማዳን ጉዳይ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ትልቁ ችግር አገሪቱ ውስጥ ያለው የሥራ አጦችን ቁጥር በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ መፍታት አለመቻሉ ነው፡፡ የሥራ አጥነቱን ችግር የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሊፈቱት አልቻሉም፡፡ አቅሙም ጉልበቱም የለም፡፡  እየተበራከተ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የግድ የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ በሩ ይከፈት የምለው ለእኔ  ሳይሆን፣ ለቄሮና ለፋኖ ነው መከፈት ያለበት፡፡ አገሪቱ በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ ትፈልጋለች፡፡ ብር ብቻ ሳይሆን ሐሳብ ትፈልጋለች፡፡ አቅምና ጥናትም ይፈለጋል፡፡ እንዲህ ያለው የመፈለግ አቅም ደግሞ በአገር ውስጥ ባለሀብት እጅ የለም፡፡ ለምሳሌ እኔን እንደ ምሳሌ ብትወስድ መሥራት ከምፈልገው ወይም ከተመኘሁት የሠራሁት አሥር በመቶ እንኳን አይሞላም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ብዙአየሁ፡- የፖሊሲው ጉዳይ ነዋ፡፡ የ17 ዓመቱን የሶሻሊዝም ጊዜ በለው፣ አሁንም ያለው የልማታዊ መንግሥት በለው የማያሠሩ ነገሮች አሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዴት ያለው ፖሊሲ ይስተካከል? መንግሥት መሥራት ያለበት ምንድነው?   

አቶ ብዙአየሁ፡- መንግሥት መሥራት ያለበት ጥቂት ነገሮችን ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ያሉትን?

አቶ ብዙአየሁ፡- መሠረተ ልማቶችን ብቻ ነው መሥራት ያለበት፡፡ እንደ መንገድ ካሉ መሠረተ ልማቶች ውጪ ከሌሎች ተግባራት መውጣት አለበት፡፡ ገበያው ለውጭ ኩባንያዎች ቢከፈትና የውድድር ሜዳው ምቹ ከሆነ እኛ የሚጠበቅብን በጥረት መሥራት ብቻ ይሆናል፡፡ እርግጥ ትንሽ ልንንገታገት እንችላለን፡፡ የሚያስከፍለን ነገር ይኖረናል፡፡ ለዘለቄታው ግን መቀጠል ይኖራል፡፡ አገሪቱ ታድጋለች፡፡ የእኔ እምነት ይህ ነው፡፡ ሌላው አገር እንዲህ የለም፡፡ እዚህ እንደሚታየው የበዛ ስብሰባና ግምገማ አይኖርም ነበር፡፡ የሚያሠራ ጥሩ ፖሊሲ ታወጣለህ፣ ጥሩ ሕግ ታወጣለህ፣ ሰው ሕጉን ያስፈጽማል፡፡ እንዲያውም ስለኛ ሲናገሩ ምን ይላሉ መሰለህ? የእኛን ሲስተም ያደንቁታል፡፡ ባህላችንን ያደንቁታል፡፡

ሪፖርተር፡- የትኛውን ሲስተምና ባህል ነው የሚያደንቁልን?

አቶ ብዙአየሁ፡- ለምሳሌ የኢትዮጵያን የአስተዳደር ሲስተም ያደንቁታል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው በድህነት ነው የሚሠራው፡፡ በቂ ደመወዝ አይከፈለውም፡፡ ብሔራዊ ስሜቱ በጣም ይገርማቸዋል፡፡ እነሱ ይህ ችግር አለባቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ከእኛ የሚሻሉት ነፃ የሆነ አስተሳሰብ፣ የሚያሠራና የወዳጅነት ቢዝነስ ከባቢ አላቸው፡፡ እኛ ጥሩ አስተዳደር አለን፡፡ በተነፃፃሪ የእኛ አመራሮች ጥሩዎች ናቸው፡፡ በጣም ያደንቋቸዋል፡፡ የእኛ መሪዎች በሩን ብንከፍት እንደ ኬንያ እንሆናለን ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ኬንያ አንሆንም የሚል አስተሳሰብ አለን፡፡ ስለዚህ ያለንን አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅመን የሚያሠራ ፖሊሲ መተግበር ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የንግዱ ኅብረተሰብ እንደ ችግር የሚያነሳቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በእርስዎ ዕይታ የንግዱ ኅብረተሰብ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ? የግሉ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ምትክ የለውም የሚባለውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ምን ቢመቻችለት ይገባል ይላሉ? እንደ አንድ ትልቅ ኢንቨስተር አገርን ለማሳደግ የበኩሌን ተወጥቻለሁ ይላሉ? ለምሳሌ ጥሩ ግብር ከፋይ ነዎት? ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር ምን ያህል ተራምጃለሁ ይላሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- የንግዱ ማኅበረሰብ የሚያነሳቸውን ችግሮች በመገምገም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት፣ ይህን ለማስፈጸም የተቋቋሙ ባለድርሻ አካላት ከአድልኦና ተዛማጅ ከሆኑ አሠራሮች በመፅዳት ቀልጣፋ መዋቅር ማደራጀትና መምራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ገቢ የሚሻሻልባቸውን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ማሻሻል ማድረጉ ትልቁ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የታክስ ሕጎችን፡፡ ሕጉን እንዲያስፈጽሙና እንዲያስተዳድሩ የተቋቋሙ አገልግሎት ሰጪ አካላትና የመሳሰሉትን ብቃት ባለው የሰው ኃይልና የማበረታቻ ክፍያዎች ማየት ይጠቅማል፡፡ ኔና የሥራ ባልደረቦቼ በምንመራቸው የንግድ ድርጅቶች ወቅቱን ጠብቀን ለመንግሥት መክፈል የሚገባንን ግብር ገቢ ለማድረግ የሚቻለንን ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡ ሠርተን ለማትረፍ በምንተጋው መጠን የግብር ግዴታችንን ለመወጣት እንጨነቃለን፡፡ በዚህ ረገድ በየዓመቱ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚደርስ በተለያዩ የታክስ ርዕሶች ለመንግሥት ገቢ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃርስ?

አቶ ብዙአየሁ፡- ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚለው እጅግ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠበቅብንን ሁሉ ሠርተናል ብዬ ለመናገር አልደፍርም፡፡ ሆኖም በግል ጥረት ብዙ የደከምንባቸውን አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አቋቁመን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠራችን፣ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በመወጣት ረገድ ሊጠቀስ የሚችል ክንውን ነው፡፡ በቀጣይ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን በተቀናጀና በላቀ ሁኔታ ለመወጣት እንዲያስችለን በድርጅቶቻችን የማይቋረጥ የገንዘብ ድጋፍ የሚተዳደር ራሱን የቻለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም ጥናቱን ጨርሰን፣ ሕጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በጎ አድራጎት ድርጅቱ ምን ዓይነት ሥራ ያከናውናል?

አቶ ብዙአየሁ፡- ሥራችንን በምናካሂድባቸው አካባቢዎች ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና ብክነትን ለመከላከል የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለአካባቢ ማኅበረሰቦች ድጋፍ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚያካትት ነው፡፡ እንደ ትምህርት ቤት፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የሕክምና አገልግሎት፣ ለተፈናቃይ ወገኖች መጠሊያዎችን የመገንባት ድጋፍና የብክለት ማስወገጃና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ለመስጠት ታስቦ የተቀረፀ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉትን ሥራዎችን ለማከናወንና በመቆጣጠር ረገድ የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ በዚህ ዘርፍ ወደፊት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ስለምንገነዘብ፣ እስካሁን ያደረግነው በቂ ነው ብለን ለመናገር አንደፍርም፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቂት ወራት ወዲህ ከተፈጠረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ አዳዲስ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ቴሌና አየር መንገድ በከፊል ወደ ግል እንዲዛወሩ ተወስኗል፡፡ እንዲህ ያለውን አካሄድ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ብዙአየሁ፡- በመንግሥት ውሳኔ የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማዛወር የተደረሰበት ውሳኔ የሚደገፍ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከገጠማት ችግር አንፃር፣ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮች ድርጅቶችን በመግዛት ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ በተለይ አሁን አገሪቱ የሚታይባትን የአቅም ውስንነትን ለመቅረፍና የተሻለ የሥራ ባህል ተሞክሮ ይዘው ስለሚመጡ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ ባለፉት ዓመታት ወደ ግል የዞሩ ድርጅቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ የቢራ ፋብሪካዎች ከየት ተነስተው የት እንደደረሱ ይታወቃል፡፡ በራሴ ድርጅትም በመንግሥት ድርጅት ሥር የነበረው ናሽናል ሲሚንቶ በ80 ዓመታት ከነበረበት በቀን 70 ቶን የማምረት አቅም ወደ አራት ሺሕ ቶን ማሳደግ ችለናል፡፡ ይህ ለውጥ የፕራይቬታይዜንን መልካም ዕድል ሊያሳይ ይችላል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ ንድፈ ሐሳባዊ ክርክሮች ቢኖሩም፣ እኔ መንግሥት አመቺ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም አመቺ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲዎችን በማጥናት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር መሥራት ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ የእርስዎ ኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫ ምን ሊሆን ይችላል? በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ኩባንያዎች ዘመን ተሻጋሪ አይደሉም ይባላል፡፡ ዕድሜ ጠገብ ኩባንያዎች ስለሌሉ፣ የእርስዎ ኩባንያዎች ነገም እንዲቀጥሉ በሚያስችል አደረጃጀት ላይ የተዋቀሩ ናቸው ብለው ያምናሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- እኔ እስካሁን የሠራሁት በቂ ነውና መቆም አለብኝ ብዬ አላምንም፡፡ አቅሜ እስከፈቀደ ወደፊትም በሚኖሩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፍላጎቱ አለኝ፡፡ በተቻለኝ መጠን ተተኪዎቼን ለማፍራትና ለዘመናት የደከምንባቸው ሥራዎች ለቀጣይ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ ማብቃት የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ኩባንያዎች የትውልድ ቅብብሎሽ የታየባቸውና የቀደምት ወላጆቼ አሻራ ያረፈባቸው ቅርሶቻችን ናቸው፡፡ ይህ ታሪክ እኔም በማልኖርበት ጊዜ እንዲቀጥልና ኩባንያዎቻችን የዜጎች መተዳደሪያ ሆነው እንዲዘልቁ የፀና አቋም አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ መደረግ ያለበት ዝግጅትና መሠራት ያለበት ሁሉ ተጠናቋል ማለት አይቻልም፡፡ መሠረቱን ጥለናል፡፡ ምሰሶውን ማጥበቅና ግንባታውን ማሳመር ቀጣይ የቤት ሥራችን ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች አገር ልምዶች በመውሰድና ጥናት በማድረግ ድርጅቶቹ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ምን ማድረግ እንደሚገባ በማጥናት ላይ እንገኛለን፡፡ ከአሁን በኋላ የበለጠ መሥራት የምፈልገው በአማካሪ ቦርድ ነው፡፡ እኔ የበለጠ ትኩረት ማድረግ የምፈልገው ወደ ፋውንዴሽኑ ነው፡፡ የተረጋጋ ሁኔታ ከመጣ አብዛኛውን ጊዜዬን ፋውንዴሽኑ ላይ ይሆናል የሚለው በዚህ አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ብዙ ካፒታሊስቶችንና ሚሊየነሮችን ብፈጥር ደስ ይለኛል፡፡ ብዙ ባለሀብቶችን ፓርላማ ውስጥ ባይ ደስ ይለኛል፡፡ የእኛን መብት፣ የእኛን ስሜት ማንፀባረቅ የሚችሉ እንደራሴዎች ቢኖሩ ምኞቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የበለጠ አቅም ኖሯቸው እንዲሠሩ እንዴት ቢደገፉ ይገባል ይላሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- ደምረህ ቀንሰህ ስታየው የፖሊሲ ጉዳይ ነው ቀድመህ የምታነሳው፡፡ ይህ ይታወቃል፡፡ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ እኔ የምፈልገው የተመቻቸ ሜዳ ነው፡፡ አስጠንተህም ልትመጣ ትችላለህ፡፡ የተጠና ጉዳይ ይታወቃል፡፡ ይህ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት ሲባል፣ እኔ የማምነው ሊብራል በሚባለው ነው፡፡ እኔ የምለው በሩ ቢከፈትና ብንሠራ አገሩ ያድጋል፡፡ ከሌሎች አገር የተሻለ መንግሥት ስላለን የተሻለ ነገር ይመጣል፡፡ ለምሳሌ ኬንያውያን እኛ ወደ እናንተ ብንመጣ አንሰርቅም ይላሉ፡፡ በአንድ ወቅት የኬንያ የቢዝነስ ሰዎችን አግኝቼ ሲስተማችሁ ‹ኮራፕትድ› ነው አልኳቸው፡፡ እነሱ ሲመልሱልኝ፣ ‹እኛ ኮራፕሽን ደማችን ውስጥ ስላለ አይደለም፡፡ ኬንያ ቢሮ አለን፡፡ ለንደንና ካናዳ ቢሮ አለን፡፡ ለንደንና ካናዳ ያለው ቢሮአችን ሲስተሙ ግልጽና ጥሩ ስለሆነ አንሰርቅም፡፡ የምንሰርቀው ኬንያ ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የኬንያ ሲስተም ኮራፕትድ ስለሆነ ነው› የሚለው ምላሻቸው ትዝ ይለኛል፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ የውጭ ኩባንያዎች ወደዚህ ሲመጡ አስፈጻሚ አካላት ማጠናከር ነው፡፡ ጠንካራ መንግሥት አለን፡፡ ይህንን ዕድል ቀደም ብለው ቢከፍቱት ኖሮ የት በደረስን ነበር፡፡ አሁን የእኔ ሥጋት እየሆነ ያለው ነገር ሥራ አጥነት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ልንኖር አንችልም፡፡ አሁን ባለሀብቱ በእያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ላይ መሥራት አለበት፡፡ ይህንን ለውጥ መደገፍና ይህ ነፃነት እንዳያመልጥህ ከፈለግክ ይህንን ነው መሥራት ያለብህ፣ ታክስ በመክፈል ነው መባል አለበት፡፡ እያንዳንዱ ባለሀብት 50ም ሆነ 100 መቅጠር የሚያስችል ሥራ ላይ መሰማራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ዕድል አለ፡፡ ለምሳሌ ሲንጋፖሮች ለቻይና እየሠሩ ነው፡፡ ዱባዮች ያንን ሞዴል ወስደው ለዓረብ አገሮች ይሠራሉ፡፡ እኛ ደግሞ ለአፍሪካ መሥራት እንችላለን፡፡ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርበት ትልቅ ገበያ ፊት ለፊታችን አለ፡፡ ሰው አሜሪካ ይሰደዳል፡፡ እዚሁ ቀጣናችን ውስጥ ብሠራ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ አገሬ ይዤ ልመጣ እችል ነበር፡፡ የመንግሥት ዕገዛ ኖሮ ኡጋንዳ ሄደህ ስትሠራ የኡጋንዳ መንግሥት ይቀበልሃል፡፡ ውጭ ያለውና ይሠራል የሚባለው ወጣ ባለ መንገድ ነው፡፡ ታግሎ ነው የሚነሳው፡፡ ይኼ ውጭ ያለ ሰው ቢረዳኝ የተለየ ደረጃ ይደረሳል፡፡ እዚህ አስረን የያዝነው ትልቅ አቅም ነው፡፡ በጣም ዲሲፕሊን ያለው ኃይል አለ አገር ውስጥ፡፡ ይኼ ቢከፈትና ሶማሊያ ብንሄድ ሱዳን ብንሄድ ብዙ እንሠራለን፡፡ ኮርፖሬት ቢሮአችንን አዲስ አበባ አድርገን ብንሠራ ብዙ ይሠራ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ እንዲህ ያለውንና ለአገር ጠቃሚ ነው ብላችሁ የምታምኑትበትን ሐሳብ አሁን ላለው የመንግሥት አካል የማቅረብና የመደመጥ ዕድል አለ ብላችሁ ታስባላችሁ? የሞከራችሁትስ ነገር አለ?

አቶ ብዙአየሁ፡- ይሄ እኮ የፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ክፍል ደግሞ የራሱ አመለካከት አለው፡፡ እኛ የምንለውም ነገር አለ፡፡ አሁን ለመጪው ጊዜ ግን ዕድል አለን፡፡ መድረክ እናገኛለን፡፡ በግለሰብ ሳይሆን በፓርቲ ወይም በተሻለ አደረጃጀት የምትሠራው ነው፡፡ አሁን የተሻለ ዕድል መጥቷል፡፡ የመደመጥ ጊዜ መጥቷል፡፡ ድሮ የሚያዳምጥህ የለም፡፡ የተዘጋ ነው፡፡ ድሮ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እየተደረገ ባለው ለውጥ መንግሥት ማድረግ አለበት ብለው የሚያስቡት ምንድነው? ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የንግዱ ኅብረተሰብ ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ፣ ከሁሉም ወገን ሊጠበቅ የሚገባው ተግባር ምንድነው? እንደ ትልቅ ኢንቨስተር ምን ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ ሊደረግ ይገባል ይላሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- አሁን በአገራችን በሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴ በኢንቨስትመንት ዘርፍ አጥጋቢ ውጤት ለማስመዝገብ በሚከተሉት መስኮች መሠረታዊ ለውጥ መደረግ ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሥራ ላይ ያሉት ሕጎች እየተፈተሹ ኢንቨስትመንትንና ኢንዱስትሪን ይበልጥ ለመደገፍና ለመጋበዝ መሻሻል አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ በጎ ጅምር ያለ መሆኑን እየሰማንና እያየን ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠልና በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ያለበት ሥራ ነው፡፡ ባለሀብቶች ያለምንም ሥጋትና ጥርጣሬ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበት ነፃነትና ሰላም መኖሩ መረጋገጥ አለበት፡፡  ለኢንቨስትመንት የፋይናንስ አቅርቦት በበቂ መጠን መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት አማራጭ ፋይናንስ ምንጭ ማግኘት እንዲቻል ካፒታል ማርኬት ሊቋቋም ይገባል፡፡ አቅሙ ያላቸው የአገሪቱ ባለሀብቶች በሕጋዊ መንገድ ከአገር ውጭ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ የኢኮኖሚ ትስስር ካላቸው ጎረቤት አገሮች እንደ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ሶማሊያ በመሳሰሉት አገሮች በመሥራት ስኬታማ የሚሆኑበትንና ሀብት ማመንጨት የሚችሉበትን መንገድ ማገዝና ፖሊሲውን ማሻሻል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ሐሳብ አመንጪዎች በተለይ ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፈጣን ዕድገትና ለውጥ በማምጣት አሁን የጀመሩትን ተስፋ ሰጪ ጉዞ በአፋጣኝ ስኬታማ ለማድረግ ልምድ ካላቸው እንደ ዱባይ፣ አቡዳቢና ሲንጋፖር መሪዎች ጋር የግል ጓደኛ በመሆን ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን ቢወስዱ፣ የአገራችንን ሥራ አስፈጻሚዎቻችንንም ወደ እነዚህ አገሮች በመላክ የልምድ ልውውጥ እንዲቀስሙ በማድረግ በተለይ በአገልግሎት ኢንዱስትሪው ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የማደግ ዕድል አላት ቢባል ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ ብዙአየሁ፡- መቶ በመቶ ዕድል አለን፡፡ ኢትዮጵያውያንን በተፈጥሯችን ጥሩዎች ነን፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲስተም ውስጥ ውጤታማ ነን፡፡ በቢዝነሱ ረገድ ግን ይህ ዕድል አልገጠመንም፡፡ ለምሳሌ አሜሪካኖች እንደ ኢራቅ ያሉ አገሮች ሄደው ይዋጋሉ፡፡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እነዚያ አገሮች ውስጥ የሚገቡት የአሜሪካ ቢዝነሶች ናቸው፡፡ እኛ ሶማሊያ እንዋጋለን፡፡ ደቡብ ሱዳንን ነፃ አውጥተናል፡፡ ሩዋንዳ ሄደናል፡፡ ነገር ግን ፖሊሲያችን ወደ እነዚህ አገሮች ሄደን እንድንሠራ እንኳን አይፈቅድም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ብዙአየሁ፡- የውጭ ምንዛሪ ገደብ አለ፡፡ ሕጉ አይፈቅድም፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሄደህ ካልሠራህ እንደ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ መሥራት አትችልም፡፡ ግን ሁሌ ስኬታማ የምትሆነው ፓስፖርትህን ይዘህ ስትሄድ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተጠይቋል፣ አልተመለሰም፡፡ አሁን ደቡብ ሱዳን በሕጋዊ መንገድ መሄድ አትችልም፡፡ ኬንያ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ሀብት ይዘህ መምጣት ትችላለህ፡፡ ልምድ ታመጣለህ፡፡ እኔ ለምሳሌ ሲንጋፖር፣ ዱባይ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ ቢሮ ነበረኝ፡፡ የትሬዲንግ ሥራዎች አከናውን ነበር፡፡ ዱባይ ላይ ማምረቻ ነበረኝ፡፡ የሠራሁት የመሥራት ዕድል ስለነበረ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጉ ወጥቶም እንዲሠራ ማድረግ አለበት፡፡ ስንሠራም የመንግሥት ድጋፍ ከተደረገ ብዙ ነገር ይዘን እንመጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሁኑ የመንግሥት ለውጥ ምን ይጠብቃሉ? ሪፎርም ይደረግባቸው የተባሉ ጉዳዮች አሉ ሪፎርሙ ማካተት ያለበት ምንድነው?

አቶ ብዙአየሁ፡- የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚበረታቱበት አሠራር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ ትልቁ ነገር ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የባለሙያ ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ሀብት ካለህ ትሠራለህ፡፡ ሀብት ካገኘህ፣ ሐሳብ ካለህ አገሪቱ ትልቅ ናት፣ 100 ሚሊዮን ሕዝበ አላት፣ በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ይጨምራል፡፡ ይህ እንቅልፍ የሚሰጥህ ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ሲስተሙ ለቀቅ ቢደረግ እኔ አሥር በመቶ ብቻ እየሠራሁ ከሆነ ይህንን አሳድጋለሁ፡፡ አሁን ያሉኝን ስድስት ሺሕ ሠራተኞች 60 እና 70 ሺሕ ላደርስ እችላለሁ፡፡ አሁን ግን ሲስተሙ የለም፡፡ ብድር ለማግኘት ሁለት ሦስት ዓመት እኮ ይፈጃል፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች የረዥም ጊዜ ልምድዎ ተስፋ አስቆራጭ ነገር አላጋጠመዎትም? ከነበረስ እንዴትስ አስተናገዱት?

አቶ ብዙአየሁ፡- ተስፋ ብቆርጥ ኖሮ አያሌ ውጣ ውረዶችን አልፌ ለራሴም ሆነ ለአገር የሚጠቅሙ ታላላቅ ሥራዎችን አከናውኜ  ዛሬ የደረስኩበት ደረጃ መድረስ አይቻለኝም ነበር፡፡ ለዚህም ፅናቱን የቸረኝን ፈጣሪን አመሠግናለሁ፡፡ ሆኖም ተስፋ ወደ መቁረጥ አዝማሚያ የተገፋሁበት አጋጣሚ አልነበረም ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእነዚህ የሥራ ዓመታት ውስጥ እዚህ ለመድረስ ያሳለፍኩት ጊዜ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ አሁንም ገና ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ ሌሎች አገሮች በኢንቨስትመንት መስክ ምን አድርገው ውጤታማ እንደሆኑ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ምን ማድረግ አቅቷት ወደ ኋላ እንደቀረች ያምናሉ?

አቶ ብዙአየሁ፡- አገራችን ኢንቨስትመንትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ዕምቅ ሀብት በበቂ እንዳላት ይታወቃል፡፡ ትልቁ ችግር በየጊዜው ከሚከሰተው የሰላምና የፀጥታ አሳሳቢነት ባሻገር ዕምቅ ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችለን ጠንካራ ሥርዓት አለመዘርጋታችንና ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች አለመጠቀማችን ነው፡፡ የዚህ ዋነኛ መገለጫው ተስማሚ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለመኖርና የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች አደረጃጀትና አሠራር ግልጽነት የጎደለውና ቀልጣፋ አለመሆን ነው፡፡ እንደ ምሳሌ እነ ሲንጋፖርና ዱባይ ያደጉት ከአገራችን የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ኖሯቸው ሳይሆን፣ ክፍተታቸውንና ችግራቸውን በማወቅ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ሥራ ላይ በማዋላቸው ነው፡፡ ለአፈጻጸሙም ከፍተኛ ብቃትና ዕውቀት ያላቸውን ሥራ አስፋጻሚዎች በከፍተኛ ክፍያ ወደ አገራቸው በማምጣት ማሠራታቸው ጭምር ነው፡፡  ለምሳሌ የዱባይን ዲዩቲ ፍሪ ብንወስደው የአይሪሽ ዜግነት ያለውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በከፍተኛ ክፍያ በማምጣት፣ በአሁኑ ጊዜ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭና ስድስት ሺሕ የሰው ኃይል ያለው ተቋም ለመፍጠር ችለዋል፡፡ እንግሊዝን የሚያህል አገር ስንት ባለሙያ ካለባት አገር የካናዳ ዜጋ በማምጣት በባንክ ኦፍ ኢንግላንድ የባንኩ ገዥ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ አገራችን ላጋጠማት ብቃት ያላቸው ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች እጥረት መፍትሔ ለማስገኘት በአማካሪዎች ደረጃ የሚያስፈልገው ባለሙያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተጨማሪም የተለያዩ ቁልፍና ወሳኝ ተቋሟትን የሚመሩ የሥራ አስፈጻሚዎችን ከውጭ አገር ማምጣትና ብሎም ልምድና ዕውቀታቸውን እንዲያስተላልፉ በማድረግ በሒደት በዜጎች መተካት ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅድሚያ አገርና ሕዝብ በዴሞክራሲ፣ በፍቅርና በአንድነት መንፈስ የሚመራበትና የሚተዳደርበትን  አስተዳደር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ  በየትም ሥፍራ በነፃነት ተንቀሳቅሰን የምንሠራባት የጋራ ቤታችን መሆኗን መቀበል አለብን፡፡ በእርግጥ ይህ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ግን አቅጣጫውን የሚያመላክት የአመራርና የአስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት መተማመን ላይ መድረስ ይኖርብናል፡፡ ለኢንቨስትመንት ዋስትናው ከምቹ  ፖሊሲ ባሻገር በነፃነት መንቀሳቀስ፣ ሰላምና ፀጥታ በሰፈነበት አካባቢ ተረጋግቶ መሥራት መቻል ነው፡፡ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የውጭ አገር መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን እንቀበላችኋለን ብሎ መጋበዝ፣ ማግባባትም ሆነ ማሳመን አይቻልም፡፡ ዋጋ የሚያስከፍል ተግዳሮትን ከጋባዥ መንግሥታት ጋር አብረው መጋፈጥና መጋለጥ የሚደፍሩ ኢንቨስተሮችን ማግኘት ከባድ ስለሚሆን፣ ይህ ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በሩ መከፈት አለበት፡፡