Skip to main content
x
የዓመቱ ዓበይት የፋይናንስ ክንውኖች

የዓመቱ ዓበይት የፋይናንስ ክንውኖች

በአገሪቱ ታሪክ ልዩ የፖለቲካ ክስተት ያስተናገደው ተሰናባቹ የ2010 ዓ.ም. ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ክንዋኔዎች ባሻገር፣ በአገሪቱ እንግዳ ኢኮኖሚያዊ ክስተቶችንም ሲያስተናገድ ከርሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ከኢሕአዴግ ነባር አሠራሮች ወጣ ባለ መንገድ መተግበር የጀመሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች እየታዩ ነው፡፡

ግዙፎቹን የመንግሥት ተቋማት በሙሉና በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ውሳኔ ዓበይት ከሚባሉት አንዱ ነው፡፡ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ለማሻሻል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በውጥን ከነበሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአንዳንዶቹን ትግበራ በመግታት፣ በተመረጡት ላይ ብቻ እንዲተኮር መንግሥት እንደወሰነ ማስታወቃቸውም አንኳር ከሚባሉ ክንውኖች ውስጥ ይመደባል፡፡ የወጪና ገቢ ንግዱም የኤርትራ ወደቦችን መጠቀም መጀመሩ ዓይነተኛ ለውጥ ነው፡፡ ዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎች የታዩበት ሆኖ መጠናቀቁና  በ2011 ዓ.ም. ወደ ተግባር ይለወጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ትልልቅ ውሳኔዎች የተላለፉበት ሆኖ ተገባዷል፡፡ በርካታ ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮች በተሸኘው ዓመት ቢስተናገዱም በዚህ ዘገባ የፋይናንስ ተቋማት የነበራቸው አፈጻጸምና በዘርፉ የተስተዋሉ ለውጦች ተቃኝተዋል፡፡    

የምንዛሪ ለውጥ

በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ከተስተናገዱ ዓበይት ክንውኖች ውስጥ በቀዳማዊነት የሚጠቀሰው፣ ከአሥር ዓመታት ቆይታ በኋላ የብር መግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲዳከም መደረጉ ነው፡፡ የምንዛሪ ለውጡ ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነና የዋጋ ግሽበት እንደማያስከትል በመስከረም መገባደጃ ላይ መግለጫ የሰጡት በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ የነበሩት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ነበሩ፡፡ የዋጋ ግሽበት ሊኖር እንደማይችል፣ ከተከሰተም የምንዛሪ ለውጡን ያህል ብቻ እንደሚሆን ገልጸው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ሳይውል ሳያድር ከውጭ የሚገባውም በአገር ውስጥ የተመረተውም ሸቀጥ ዋጋ አሻቅቦ ችግር አስከተለ፡፡ እንደ ብረታ ብረት ያሉ ምርቶች ዋጋቸው አልቀመስ በማለቱ፣ የተጋነነ የዋጋ ግሽበት አይከሰትም የሚል ሙግት ያቀርቡ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ፣ ማስጠንቀቂያ ለብረት አስመጪዎችና ነጋዴዎች በመስጠት፣ ያላግባብ ዋጋ ጨመሩ በተባሉት ላይ ዕርምጃ ስለመወሰዱም ጭምር አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ግን ብዙም አላስኬደም፡፡ እንደውም የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የምንዛሪ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ በአማካይ ከ51 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማሳየታቸው ብዙ ሲያነጋገር ሰነበተ፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦችም የምንዛሪ ለውጡን አስታከው ተደጋጋሚ የዋጋ ጭማሪ በማሳየት ዓመቱ ከፍተኛ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ የተስናገደበት አድርገውታል፡፡ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት እስከ 17 በመቶ ያሻቀበበት ዓመት ነበር፡፡

አዲሱ አመራርና የፋይናንስ ተቋማት

የአገሪቱን ማዕከላዊ ባንክን ጨምሮ በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊዎች በአዳዲሶች እንዲተኩ መደረጉ የዓመቱ ዓበይት ክስተት ነበር፡፡

በአመራር ለውጡ ሳቢያም የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉና ምክትላቸው ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በአዲስ ተሿሚ ተተክተዋል፡፡ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ይናገር ዶሴ (ዶ/ር) የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሲደረጉ፣ በዮሐንስ (ዶ/ር) ቦታ ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ከብዙ ማንገራገር በኋላ ምክትል ገዥ ሆነው ለመሥራት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ የብሔራዊ ባንክን ለረዥም ዓመታት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተክለ ወልድ ከገዥነታቸው ቢነሱም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪና የብሔራዊ ባንክ የቦርድ አባል ሆነው መሰየማቸው፣ የፋይናንስ ዘርፉ የዓመቱ ሹም ሽር ነበር፡፡ የምክትል ገዥነቱን ቦታ የለቀቁት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በመሆን ተመድበዋል፡፡

ይህ ሹም ሽር ብዙ ያነጋገረ ነበር፡፡ በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተደረገው ለውጥ በዚህ አልተገደበም፡፡ ንግድ ባንክ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ባከበረ ማግሥት አዲስ ፕሬዚዳንት እንዲሰየምለት መደረጉም በፋይናንስ ዘርፉ ተጠቃሽ ክስተት ነው፡፡ አዲሱ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት አቶ ባጫ ጊና ናቸው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት ሹመት በመንግሥታዊ ተቋማት በተለይም በፋይናንስ ተቋማት ረገድ ይታይ ከነበረው ልምድ ወጣ ያለ የአሿሿም ለውጥ የተደረገበት ነበር፡፡ አዲሱ የንግድ ባንክ ተሿሚ ከግል ባንክ ተመርጠው መምጣታቸው ሒደቱን የተለየ አድርጎታል፡፡ አቶ ባጫ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ከዚያ ቀደሞም በአዋሽ ባንክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡

እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ለውጦችን አስተናግዷል፡፡ እርግጥ የአመራር ለውጡ በመንግሥት በኩል ከመደረጉ ቀደም ብሎ ባንኩን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩትና ኃላፊነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ በለቀቁት አቶ ጌታሁን ናና ምትክ ምክትላቸው አቶ ኃይለየሱስ በቀለ የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ አቶ ኃይለየሱስ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ባንኩ በንግድ ባንክ ሲጠቀለል በምክትል ፕሬዚዳንትነት ተቀላቅለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተደረገው የኃላፊዎች ሹምሽር የቦርድ አባላትም የሚመለከት ነበር፡፡ ለብሔራዊ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበርነት አቶ ግርማ ብሩ ሲሰየሙ፣ ቦርዱን በአባልነት የሚመሩ አዳዲስ አባላትም ተሾመዋል፡፡ የንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩትና ሰሞኑን አነጋጋሪ ሆነው የሰነበቱት አቶ በረከት ስምዖንም የፋይናንስ ተቋማት የለውጥና እንቅስቃሴ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ራሳቸውን ከኃላፊነት ስለማግለላቸው ዜናው የተሰማበት ዓመት ነበር፡፡  

እንጥልጥሉ የፋይናንስ ሪፎርም

የብሔራዊ ባንክን አሠራሮችን ለማሻሻልና ለውጦቹም ወደ ተግባር እንዲሻገሩ ለማድረግ አዳዲሶቹ ሹማምንት ከፋይናንሱም፣ ከንግዱ ማኅበረሰብም ጋር ተወያይተው ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር (ዶ/ር)፣ በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳ ዘንድ የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎችና የሪፎርም ሥራዎች እንደሚወሰዱ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር በተናጠል በመወያየትም ለሪፎርም ሥራው ያግዛሉ የተባሉ ሐሳቦችን እንደተቀበሉም ገልጸው ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክን የአመራርና የፋይናንስ ነክ አሠራሮችን የመለወጡ ሥራ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ በማቋቋም እንደተጀመረ ታውቋል፡፡ ኮሚቴው በሚፈልገው ደረጃ ለውጥ ያስገኛሉ የተባሉ የመፍትሔ ሐሳቦችን ስለማቅረቡ እስካሁን ባይታወቅም፣ ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ፣ በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ የተጠበቁትን ያህል ውሳኔው እንዳላስደሰታቸው የባንክ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ከኮሚቴው ውሳኔዎች ውስጥ ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ ባንኮች የሚያስቀምጡት የገንዘብ መጠን ላይ ተጥሎ የቆየው የ50 ሺሕ ዶላር ገደብ መነሳቱ ትልቅ ዕርምጃ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

ፕራይቬታይዜሽን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳለፈው ያልተጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል እንዲዛወሩ ማለቱ ነው፡፡ ውሳኔው በዓመቱ ከተስተናገዱ አስገራሚ ክስተቶች ውስጥ አሁንም ድረስ በአነጋጋሪነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል የማዛወሩ ሥራ የሚደገፍ ስለመሆኑ በርካታዎች ቢስማሙም፣ አንዳንዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ  መካተት አልነበረበትም የሚል አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑትን ጉምቱ ባለሙያ ዓለማየሁ ገዳና ሌሎችም የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች አየር መንገዱ መሸጥ የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) መንግሥት እነዚህን ብርቅዬ ተቋማት ወደ ግል ለማዛወር የተገደደው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው በፈጠረው ችግር የተነሳ እንደሆነ የተከራከሩበት ዓመት ነበር፡፡ ወደ ግል በማዛወሩ ሒደት ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል በማለት ምሁራኑ ማሳሰቢያቸውን ያስተላለፉትም፣ አገሪቱ ለሽያጭ ያቀረበቻቸው ተቋማት የሚያወጡት ዋጋ በማንና እንዴት እንደሚሰላ፣ የመንግሥት የድርድር አቅምና ሌሎችም በርካታ ታሳቢዎችን በመጠቆም ነበር፡፡

መንግሥት ወደ ግል የሚያዛውራቸውን ድርጅቶችን በተመለከተ ሥራውን የሚከታተል ተቋም አቋቁሟል፡፡ በዚህ ሒደት ንግድ ምክር ቤቶችና የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ባለመካተታቸው ቅሬታቸውን ማስደመጣቸው አይዘነጋም፡፡ የመንግሥት ኩባንያዎች ወደ ግል የማዛወሩን ውሳኔ ተከትሎ ትኩረት የሳበው የፋይናንስ ጉዳይ የካፒታል ገበያ የማቋቋም ውትወታ ነበር፡፡ በዓመቱ የመጨረሻዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ወደ ግል የሚዛወሩትን ኩባንያዎች የአክሲዮን ሽያጭ ለማስፈጸምም ሆነ ለወደፊቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያግዝ የካፒታል ገበያ ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ስለመሆኑ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ግፊት ሲደረግበት የሰነበተ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከወራት በፊት ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክሌ፣ የአክሲዮን ዝውውሩን በተገቢው መንገድ ለማስፈጽም የካፒታል ገበያ ማቋቋም የግድ እንደሚል ገልጸው ነበር፡፡ በካፒታል ገበያ ምሥረታ ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን ከሚገልጹና ግንባር ቀደም አንቀንቃኝ ከሆኑ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ጉምቱዎች መካከል አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አይዘነጉም፡፡ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች በዚህ ሐሳብ ላይ የጋራ አቋም አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርም በቅርቡ ለብሔራዊ ባንክ ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ የካፒታል ገበያ አስፈላጊነትን የሚመለከት እንደሆነ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ይገልጸዋል፡፡  

ይሁንና አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኃላፊነታቸውን በተረከቡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የካፒታል ገበያን ለማቋቋም የሚያስችሉ የጥናት ሰነዶች ቀርበውላቸው እንደተመለከቱ ገልጸው ነበር፡፡ የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ስለመሆኑ ከመግለጻቸው በቀር ተጨባጭ ነጥቦችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ውግዙ የ27 በመቶ ቦንድ

የግል ባንኮች ለሰባት ዓመታት ያለማቋረጥ እንዲታዩላቸው ሲወተውቱ ከቆዩባቸው ጥያቄዎች ውስጥ በብድር ከሚሰጡት ገንዘብ ላይ 27 በመቶ ቀንሰው ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድደው መመርያ ዋናው ነው፡፡ መመርያው በብዙ ሲተችና ሲብጠለጠል ቢቆይም፣ ከሰሞኑ በተደረገው ለውጥ ለቦንድ ገዥው ይታሰብ የነበረው የተቀማጭ ወለድ ምጣኔ ከሦስት በመቶ ወደ አምስት በመቶ ተሻሽሏል፡፡ ዕርምጃውን ባንኮች ቢደግፉትም በቂ እንዳልሆነ ግን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ ባንኮች የሰባት በመቶ ወለድ እየከፈሉ ለሚሰበሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ፣ ብሔራዊ ባንክ ሦስት በመቶ ብቻ ሲከፍል መቆየቱ ሲያስተቸው ቆይቷል፡፡ ሆኖም የ27 በመቶው የቦንድ ግዥ አስፈላጊነት ላይ በርካቶች አይስማሙም፡፡ ዓላማው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚውል ፋይናንስ ማመቻቸት ሲሆን፣ በቦንድ ግዥ የሚሰበሰበው ገንዘብ ወደ ልማት ባንክ ገቢ ተደርጎ፣ ለአምራቾች የሚውል ብድር እንዲፈጠር ለማድረግ ነው፡፡ ይሁንና ልማት ባንክ የብድር አሰጣጥ ሥርዓቱ ክፍተት ያለበት በመሆኑና የ27 በመቶው ቦንድ ለተፈለገው ዓላማ አልዋለም የሚለው ስሞታ እየጎላ በመምጣቱ፣ የመመርያው አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንደሚገልጹት፣ የግል ባንኮች ከእያንዳንዱ ብድራቸው ላይ ለቦንድ ግዥ የሚያውሉት የ27 በመቶ ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባ ያምናሉ፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ እስካሁን ከ72 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ምን ያህሉ ሥራ ላይ ዋለ ሲባል ግን አሻሚ ምላሽ ስለሚሰጥ፣ የቦንድ ግዥ መመርያው ሙሉ ለሙሉ ባይሻር እንኳ የግል ባንኮች ተቀናሹን በራሳቸው ማንሳት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡ ባንኮቹ ቦንድ የሚገዙበትን ገንዘብ መንግሥት ለሚያስፈልገው የኢንቨስትመንት ዘርፍ በራሳቸው እንዲያበድሩ ማድረግ እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡ መመርያው ግን በበርካታ መድረኮች ሲያከራክር ሰንብቷል፡፡   

የፋይናንስ ተቋማት ክራሞት

 የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት አትራፊነታቸውን ላይ ተፅዕኖ የሚያመጡ ሕጎችና አሠራሮችን ሲቃወሙ ቢከርሙም፣ ከወትሮው ትርፋማነታቸው ሳይቀንሱ ዘልቀዋል፡፡ የኢኮኖሚው እንቅሰቃሴ በተዳከመባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት እንኳ  ሁሉም ባንኮች የተሻለ ውጤት አስመዝግበው የትርፍ መጠናቸውን ያለማቋረጥ ስለማሳደጋቸው የተቋማቱ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርቶች አመላክተዋል፡፡ የዘንድሮው ዓመት የማበደር አቅማቸውና አጠቃላይ ክንዋኔያቸው ከ2009 ዓ.ም. ብልጫ ያለው ውጤት እንደተመዘገበበት ታይቷል፡፡

አሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች በ2010 ዓ.ም. ያስመዘገቡት ትርፍ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከ120 ሚሊዮን ብር ጀምሮ እስከ 2.9 ቢሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡ አዋሽ ባንክ 2.9 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ቀዳሚነቱ የተገለጸው በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ነው፡፡ ከግል ባንኮች ከፍተኛው ትርፍ ነው፡፡ የባንኮቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ720 ቢሊዮን ብር በላይ ሲያስመዘግብ፣ አጠቃላይ ሀብታቸውም ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ የተገለጸው በተሸኘው ዓመት ነው፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያተረፉበት ዓመት ሲሆን፣ ከ16ቱ የግል የመድን ኩባንያዎች መካከል ኒያላ ኢንሹራንስ ከፍተኛውን የትርፍ መጠን በማስመዝገብ ቀዳሚው ለመሆን እንደቻለ የኢንዱስትሪው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም ከ940 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳተረፈ በበጀት አስታውቋል፡፡ በጠቅላላው የኢንሹራነስ ኩባንያዎች ከ8.6 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ የሰበሰቡበት ዓመት ነበር፡፡

ግዙፍ ሽያጮች

በ2010 ዓ.ም. ከታዩ የቢዝነስ ክንውኖች መካከል ሁለት የቢራ ፋብሪካዎች በከፍተኛ ዋጋ አክሲዮኖቻቸውን መሸጣቸው ነው፡፡ ቢጂአይ ኢትዮጵያና እህት ኩባንያው ካስትል ግሩፕ ራያ ቢራንና ዘቢዳር ቢራን ለመግዛት ባደረጉት ድርድር መሠረት፣ የራያ ቢራ አክሲዮኖችን በ2.5 ቢሊዮን ብር ገዝተዋል፡፡ የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ 60 በመቶ አክሲዮኖችን እስካሁን ይፋ ባልተደረገ ዋጋ ካስትል ቢራ ግዥውን ፈጽሟል፡፡ ቀሪዎቹን የ40 በመቶ የዘቢዳር ቢራ አክሲዮኖችን በ1.3 ቢሊዮን ብር ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ፣ ባለድርሻዎቹ አነስተኛ ነው በማለታቸው፣ ካስትል ግሩፕ ሊጠቀልለው ያሰበበት ግዥ ሳይካሄድና የአክሲዮን ዝውውሩም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካን የ40 በመቶ ድርሻን ባቀረበው ዋጋ መሠረት እንኳ ቢሸጥ፣ ካስቴልና ቢጂአይ ለራያና ለዘቢዳር ፋብሪካዎች ግዥ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ እንዳወጡ ይታመናል፡፡ እንዲህ ያለው ግብይት በ2010 ዓ.ም. በከፍተኛ ወጪ ግዥና ሽያጭ የተፈጸመበት ብቻ ሳይሆን፣ ባለአክሲዮኖችም ከፍተኛ ትርፍ ያገኙበት ግዙፍ የአክሲዮን ዝውውር፣ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተያያዘ ግብይት መፍጠሩም ታይቷል፡፡ ለአክሲዮኖቹ ግዥ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከሁለት የግል ባንኮች 1.35 ቢሊዮን ብር እንዲበደር አስገድዶታል፡፡ ከአዋሽና ከዳሸን ባንኮች የተገኘው ብድር ለአክሲዮን ግዥ የሚውል ነው፡፡ በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ በአንድ ጊዜ፣ ለአንድ ፕሮጀክት የተፈቀደ ትልቅ የብድር መጠን ሆኖ የተመዘገበበት ዓመት ነበር፡፡  

ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የፋይናንስ ተቋማት

በ2010 ዓ.ም. ከግል ባንኮች በተያያዘ አነጋጋሪነቱ ወደፊትም እንደሚቀጥል የሚጠበቀው ክስተት፣ የአክሲዮን ድርሻ የነበራቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮኖቻቸው በሐራጅ ተሸጠው ከፋይናንስ ተቋማቱ ባለድርሻነት በግድ እንዲወጡ መደረጉ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ አክሲዮኖቻቸው ተሸጠው የአክሲዮን ድርሻቸውና አክሲዮናቸው እስኪሸጥ ድረስም የትርፍ ድርሻቸውን ተቀብለው እንዲወጡ የሚያስገድደው መመርያ በሁሉም የግል ባንኮችና ኢንሹራንሶች ተፈጻሚ ተደርጓል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ መሠረት ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባወጡት ጨረታ አክሲዮኖቹ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ታክሎባቸው ተሸጠዋል፡፡ ይህ የጨረታ ሒደት ግን በዓመቱ መጀመርያ ላይ እንደነበረው ባይሆንም፣ የተንጠባጠቡ የውጭ ባለአክሲዮኖች ድርሻቸውን ለሽያጭ እያቀረቡ ነው፡፡ በአንዳንድ ባንኮች አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን እስከ 14 ሺሕ ብር ሲሸጥ የታየበት አጋጣሚም ታይቷል፡፡ ከአክሲዮኖቹ የዋጋ ልዩነት የተገኘው ገንዘብ በሙሉ ለመንግሥት ገቢ የተደረገ ሲሆን፣ መመርያው ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች በጠቅላላው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች እንደመለሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

መመርያውን ለማስቆም በተናጠልም በጋራም የተሞከሩ እንቅስቃሴዎች ብዙም ለውጥ አላመጡም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መመርያው እንዳይተገበር የሚያሳስቡ ጠንካራ ትችቶች ሲሰነዘሩ እየታየ ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያኑ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ የሚወተውቱ ግፊቶች እያየሉ መጥተዋል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለድርሻ እንዳሆኑ የሚከለክለውን መመርያ እንዲያስተካክል የሚጠይቁ አካላት፣ የተጀመረው ሪፎርም ውስጥ የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳግም እዲካተቱ ይደረግ እየተባለ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር በወቅቱ አነጋግሯቸው የነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሞሼ ሰሙ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ይፈቀድ የሚለው ጥያቄ ተገቢነቱ እንዴት እንደሚታይ አስረድተው ነበር፡፡ ወደ ግል ይዛወራሉ የተባሉት የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ አክሲዮን እንዲገዙ እየተጠየቁ፣ በሌላ ጎን የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ድርሻ እንዳይኖራቸው መከልከል ተገቢ አይደለም ብለው ነበር፡፡

አዝጋሚው የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ

በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማትን የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል አንዱ የፋይናንስ ተቋማትን የሚመሩ ፕሬዚዳንቶችንና የቦርድ አባላትን ሹመት ማፅደቅ ነው፡፡ የምርጫ ጊዜያቸው ደርሶ በአዲስ የሚተኩ የቦርድ አባላቱን ሹመት፣ እንዲሁም የየክልሉ ዳይሬክተሮች ቦርድ ለባንኮቻቸው የሚመድቧቸው ፕሬዚዳንቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎችን ካጩ በኋላ ሥራ ለመጀመር የግድ የብሔራዊ ባንክን ይሁንታ ማግኘት አለባቸው፡፡

ከመስከረም 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉ ሦስት ተከታታይ ወራት ወደ አሥር የሚደርሱ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አዲስ የቦርድ አባላትን የመረጡ ሲሆን፣ የምርጫው ውጤት እንደፀደቀላቸው ለብሔራዊ ባንክ አመልክተዋል፡፡ ይሁንና የሁሉም በሚባል ደረጃ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን የምርጫ ውጤት ለማፅደቅና አንዳንድ ባንኮች የሾሟቸውን ፕሬዚዳንቶች ሹመት ለማፅደቅ የወሰደው ጊዜ አነጋጋሪ የሆነበት ዓመት ነበር፡፡ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ የበርካታ የፋይናንስ ተቋማት በፍጥነት ምላሽ ሳይወጣበት ረዥም ጊዜ የወሰደው ዘንድሮ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ15 ቀናት ውስጥ ውሳኔውን ማሳወቅ ሲገባው አብዛኛዎቹ ከሁለት ወራት በላይ ጊዜ መውሰዳቸው በተቋሞቹ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የአንዳንድ የፋይናንስ ተቋማት ዓመታዊ የትርፍ ክፍፍል በጊዜው እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ከስድስት ወራት በላይ የወሰደበት አንድ ባንክም በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ መዘግየት ችግር ውስጥ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጉዳያቸው በእንጥልጥል ላይ ያሉ አሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያሉ የሹመትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ውጤቶችን በቶሎ አፅድቆ ወይም ለማፅደቅ እንደማይችል አሳውቆ ምላሽ አለመስጠቱም ተቋማቱ የቀድሞ አመራሮች በሕገ ደንቦቻቸው ከተቀመጠላቸው ጊዜ በላይ በሥራ ላይ እየቆዩና አዲሶቹ ሥራ እንዳይጀምሩ እንቅፋት ሆኗል፡፡

እንዲህ ባለው የዘገየ ውሳኔም ቢሆን በ2010 ዓ.ም. ዳሸን፣ እናት፣ ብርሃንና ዘመን የመሳሰሉት ባንኮች አዲስ የቦርድ ሊቀመናብርቶችን የሰየሙ ሲሆን፣ ዘመን ባንክና ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ኩባንያዎቻችሁን በፕሬዚዳንትነትና በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩ ኃላፊዎችን የሰየሙበት ዓመት ሆኗል፡፡ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የባንኩ ፕሬዚዳንት ለማድረግ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበውን የሹመት ይፅደቅልኝ ጥያቄ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ የቀድሞዎቹን የቦርድ አባላት ድጋሚ መርጠው ሁሉም ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክም የቦርድ አባላቱ ምርጫ ውጤት የፀደቀለት ከስድስት ወራት በኋላ እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

የውጭ ምንዛሪ እጥረት

አገሪቷ ውጭ ምንዛሪ እጥረት ክፉኛ የተመታችበት ጊዜያት ውስጥ አንዱ ይህ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ነው፡፡ ለኢንሹራንስ መግዣ መጥፋቱ በይፋ የተገለጸበት፣ አገሪቱን የመድኃኒት ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ከማምረት አቅማቸው በ20 በመቶው ብቻ ለመሥራት የተገደዱ ስለመሆኑ ያሳወቀበት ነው፡፡ እንደ ቴሌ ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ገንዘብ እያላቸው በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ዕዳቸውን ለመክፈል ያልቻሉበት ዓመት ነበር፡፡ ችግሩ ብዙ ማምረቻዎችን ከአቅማቸው በታች እንዲሠሩ ያስገደደ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ዕደላና አስተዳደርን የተመለከቱ የተለያዩ መሥሪያዎችና አመራሮችን እንዲተገብር ያስገደደበት ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አንዳንድ ትልልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የተፈቀደላቸው ባንኮች ብሔራዊ ባንክ የፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሪ እንዲሸጡ መገደዳቸው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥን ጉራይማሌና አነጋጋሪ ያደረገው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ችግር ውስጥ ነን ያሉበት ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሮች በተለያዩ መንገዶች የተገለጸ ሲሆን፣ ብዙዎች ከፖሊሲ ችግር ጋር ያያይዙታል፡፡

የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሊቀመንበር አቶ ብዙዓየሁ ታደለን የመሳሰሉ ባለሀብቶች ደግሞ የችግሩ ምንጭ በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዘለቄታውም መሻሻል ያለባቸው ፖሊሲዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ አገሪቱ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት መሆን ቢችል ችግሩን ለማቃለል ያግዛል የሚል እምነት አላቸው፡፡

የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በመንግሥት ከተወሰዱ ዕርምጃዎች አንዱ የብር የመግዛት አቅምን በ15 በመቶ መዳከም በዋናነት የሚጠቀስ ቢሆንም፣ ይህ ድንጋጌ ላኪዎች ምርቶቹን ለመላክ ይበረታታሉ በሚል ሲሆን፣ የታየው ግን ይህ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሌላው ዕርምጃ ደግሞ እያንዳንዱ ባንክ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ በመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችለኝን ሥራ እሠራለሁም እስከማለት የደረሰው ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ያለውም ቢሆን በአግባቡ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡

እጥረቱ ይዞ የመጣው ሌላው ጉዳይ ደግሞ አገሪቱ የግል ባንኮች ከሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 30 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪን በገዙበት ዋጋ አስገቡ መባላቸው ነው፡፡ ባንኮች ማስታወቂያዎችንና የተለያዩ ሽልማቶችን በመስጠት ያሰባሰቡትን የውጭ ምንዛሪ፣ የውጭ ምንዛሪውን በገዙበት ዋጋ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረባቸው ኪሳራ ውስጥ እየከተታቸው ነው፡፡ የባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ እንደሚገልጹትም ሲሠራበት የቆየው አሠራር ባንኮችን ኪሳራ ውስጥ መክተቱን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባንኮችን ከአንድ ሳምንት በፊት የተወሰነው ውሳኔም ከኪሳራ እንደሚያድናቸው የገለጹበት ዓመት ሆኗል፡፡    

ሐራጅ

የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ስለመሆኑ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ከዓመት ዓመት በአትራፊነት የዘለቀ ነው፡፡ ከሚቀርበው የብድር ጥያቄ አንፃር የተሰጠው የብድር መጠንም ቢሆን ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ ነው፡፡ የአገሪቱ ባንኮች ይህንን ብድር የሚሰጡት የተለያዩ ንብረቶችን በመያዝ ነው፡፡

በመሆኑም ለብድሩ ተመጣጣኝ የሆነ ንብረት በመያዝ የሚለቀቅ ብድር ወቅቱን ጠብቆ ካልተመለሰ ለባንኮች በተሰጠ ሥልጣን መሠረት ንብረቱን ሸጦ ብድሩን የማስመለስ አሠራር ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ ነገር ግን እስከዛሬ ከነበረው ሒደት በበጀት ዓመቱ ከሌሎች ዓመታት በርከት ያሉ ተበዳሪዎች በወቅቱ ብድራቸውን ባለመክፈላቸው ለብድር ማስያዣነት የተመዘገቡ ንብረቶች በሐራጅ እንዲሸጡ የሕዝብ ማስታወቂያ ወጥቶባቸዋል፡፡ ከተለያዩ ባንኮች የተገኘው መረጃም ቢሆን ይህንኑ ያሳያል፡፡ ይህ ክስተት በመንግሥትም በግል ባንኮችም የተስተዋለ ነው፡፡

የ2010 ዓ.ም. ለምን የተለየ ሆነ ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ ምላሾች የሚሰጡበት ሲሆን፣ ካነጋገርናቸው የተለያዩ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች መገንዘብ የሚቻለው የሐራጅ ማስታወቂያዎች መብት ነው፡፡ አንዳንዶች በየዓመቱ የሚሰጠው ብድር በፈጣን እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ላይመለሱ የሚችሉ ብድሮች በዚያው መጠን ሊያድጉ ስለሚችሉ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ ይህ የሚጠበቅ ነው ይላሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ከተፈጠረው አገራዊ ቀውስ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ተበዳሪዎች ያለባቸውን ብድር በወቅቱ ለመክፈል ካለመቻላቸው ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡

አንዳንድ ተሳታፊዎች ደግሞ ተገቢው ጥንቃቄ ካለመደረጉ ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር መሆኑን ነው፡፡ በተለይ ዘንድሮ ብድር ለማስመለስ ከተደረጉ ንብረቶች ጋር እስከ ዛሬ ገጥሞን የማያውቅ ትግል አሳልፈናል ያሉ የአንድ የግል ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ብድር በመክፈል የታወቁ የነበሩ ተበዳሪዎች ሳይቀሩ በወቅቱ ብድራቸውን ለመክፈል የተቸገሩበት ነበር ይላሉ፡፡ ስለዚህ ብድሩን ማስታመም የማይችል ከሆነ የግድ ወደ ሐራጅ ጨረታ ይገባል ይላሉ፡፡

ወደ ሐራጅ የሚገባው ግን በርካታ ሒደቶችን አልፎ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኮች ወደዚህ የሚገቡት የተበላሸ ብድር መጠናቸውን ላለመጨመር ጭምርም ነው፡፡

ምርት ገበያና ባንኮች

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ለማስፋፋት ባንኮች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በጥምረት የሚሠሩበት አሠራር ተዘርግቶ እየተሠራበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሥራ ሲጀመር ተግባራዊ ካደረጋቸው አሠራሮች መካከል አንዱ በምርት ገበያው የሚካሄዱ ግብይቶች በሙሉ ክፍያዎች በባንኮች በኩል መካሄዱ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት አሁን በሥራ ላይ ካሉ ባንኮች እስካሁን 15 ባንኮች ከምርት ገበያው ጋር በመዋዋል የግብይት ፈጻሚዎች ክፍያዎች በእነዚህ ባንኮች በኩል እንዲካሄድ እያደረገ ነው፡፡ በ2010 በጀት ዓመትም የምርት ገበያውን ክፍያዎች ለማስፈጸም ሦስት ባንኮች ብርሃን፣ ዓባይና ደቡብ ግሎባል ባንክ ውል ፈጽመዋል፡፡ ቀሪዎቹ ባንኮችም ይህንን ስምምነት ለመፈጸም እየተሠራባቸው ነው ተብሏል፡፡

አዲስ የሚመሠረቱ ባንክና ኢንሹራንስ

የፋይናንስ ዘርፉ ውስጥና አዲስ ክዋኔ የታየው ደግሞ ከዓመታት በኋላ አንድ ባንክና አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እንቅስቃሴ የጀመሩበት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ባንክ ለማቋቋም የጠየቀውን የተከፈለ ካፒታል ከ100 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከፍ ሲያደርግ፣ 100 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አሰባስበው ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመሩ ወደ አራት ባንኮች እንቅስቃሴያቸው እስከማቋረጥ ደርሰው ነበር፡፡ ከስምንት ዓመት በኋላ ግን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ለማሰባሰብ እንደሚቻል አስታውቆ ዳሎል የተባለ ባንክ አደራጅቶ ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገባበት መሆኑ ዓመቱን የተለየ ያደርገዋል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን ኢንሹራንስ የአክሲዮን ሽያጭ የጀመረው ዘመናዊ መሆን 18ኛ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመሆን የሚያስችለውን የአክሲዮን ሽያጭ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻው ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነው፡፡

በበጀቱ ዓመቱ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በተያያዘ የዜና ሽፋን ከተሰጣቸው አንዳንድ አነጋጋሪ ጉዳዮች መካከል የፋይናንስ ተቋማት ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጋገን ባንክ አዲሱን ሕንፃ መከራየቱ አንዱ ነው፡፡ በአሠራር ላይ ችግር ሊያመጣ አይችልም ወይ የሚለውን ጥያቄ እስከማስነሳት የደረሰ ነበር፡፡ የአቢሲኒያ ባንክ የመድኃኔዓለም ቅርንጫፍ የዘረፋ ሙከራ ከዓመቱ ፋይናንስ ነክ ክስተቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቆጣጣሪነት መላቀቅ አለባቸው የሚለው ሐሳብም በባለሙያዎች ተደጋግሞ የተነሳበት ነው፡፡

ከ160 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን የያዙት ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመረጡዋቸው ቦርድ አባላት ድምፃቸው ሊደመጥ ይገባል በሚል ፋይናንስ ተቋማት አባላትን የሚወክለው ማኅበር የተቋቋመውም በዚህ ዓመት ነው፡፡ ይህ ማኅበር ግን ፈቃድ ለማግኘት እየተፈተነ ነው፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ከበታች ስትራቴጂም ተቀርፆ ይፋ የሆነው በዚህ ዓመት ነው፡፡  

ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች

በአዲስ አበባ ከዚህ በኋላ ጎልተው የሚታዩ ሕንፃዎች ቢኖሩ የፋይናንስ ተቋማት የሚገነቡዋቸው ሕንፃዎች ናቸው፡፡ በተለይ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መንደር በሚባለው ሰንጋ ተራ የፋይናንስ ተቋማት የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ እያስገነቡ ሲሆን፣ ሁሉም የመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደማጠናቀቂያ ሥራቸው እየተሸጋገሩ ነው፡፡ ከ30 ግለሰቦች በላይ ያሉዋቸው ሕንፃዎች ከአንዱ በስተቀር ሁሉም በቻይና ኮንትራክተሮች እየተገነባ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ሕንፃ እንደሚሆን የሚጠበቀውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ እየተፋጠነ ነው፡፡

ዳሸንና ወጋገን ባንኮችም 2010 ዓ.ም. የዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ ግንባታ አጠናቅቀው በማስመረቅ ሥራ ያስጀመሩበት ዓመት ነው፡፡

የ2010 ዓ.ም. የነሐሴ ወር የመጨረሻው ቀን የተሰማው ዜና ደግሞ የዓመቱ ዓበይት ክንውን የተፈጸመበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ መርከቦቿን ወደ ኤርትራ ልካ ከምፅዋ ወደብ ዕቃ መጫንዋና የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ወደ ሥራ መግባታቸው የተገለጹበት ሲሆን፣ ሌላው ተያያዥ ክዋኔ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ብቻ ይሠሩበት የነበረው የዕቃ ማመላለሻ ሥራ ዘርፍ ለሁሉም ክፍት መሆኑ ነው፡፡