Skip to main content
x

በመቶ ቢሊዮን ዶላር ስለሚገመተው ኢኮኖሚ ከሚታሰበውና ከሚነገረው

ባለፈው ሳምንት ከተከናወኑ ኩነቶች ውስጥ መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ማስታወቁ ነው፡፡ ማሻሻያው በጥቅሉ ከፋይናንስ ዘርፉ፣ ከወጪ ንግዱ፣ ከዓመታዊው የኢኮኖሚ ዕድገት እስከ ውጭ ብድር፣ ዕዳና መሰል ጉዳዮች የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምሁራንና የመንግሥት ሹማምንት ተወያይተዋል፡፡ ስሞታና ቅሬታም ተደምጧል፡፡

መንግሥት አሻሽለዋለሁ ለሚለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መነሻ ይሆናሉ ያላቸውን ሐሳቦች ያስደመጠበት መድረክ፣ በርካታ ሙግት አዘል ሐሳቦችን አስተናግዶ ነበር፡፡ መንግሥት አሁን ባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢቀጥል ወይም ማሻሻያዎችን በማድረግ ማለትም የግሉና የመንግሥት አጋርነትን በማክሮ ኢኮኖሚው ሥርዓት ውስጥ እንዲታቀፍ በማድረግ የሚመጡ ለውጦች ምን እንደሚመስሉ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የኢኮኖሚ ባለሙያው ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ‹‹የኢትዮጵያ የልማት ግቦችና የመዋቀራዊ ሽግግር ፍላጎቶች የአጭርና የረዥም ጊዜ ተግዳሮቶችና ዕድሎች›› በሚል ርዕስ ባካሄደው የመጀመርያው የከፍተኛ ኃላፊዎች የኢኮኖሚ ፎረም ላይ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ያመላከተው የዋና ዳይሬክተሩ ጽሑፍ፣ የአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2025 ባለው ጊዜ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን አቋም የሚተነብይና፣ ለኢኮኖሚው መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን መላ ምቶችን ያካተተ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ምዕራፎች ውስጥ ለውጥ እያስመዘገበ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል እየሰፋ የመጣ ልዩነት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፎች ያስመዘገበው ተወዳዳሪነት ችግር ዕድገቱን እየጎተተው መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በማሳያነትም የቻይና፣ የማሌዥያ፣ የታይላንድ፣ የደቡብ ኮሪያና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ አንስተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነቱ እየነቀሰ ሲመጣ የቻይና፣ የማሌዥያና የደቡብ ኮሪያ ግን እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተወዳዳሪነት አቅም ለመገንባት በመጪዎቹ ስምንት ዓመታት ውስጥ ማስተካከያ ይደረግባቸዋል ከተባሉት ውስጥ የግብርናው፣ የኢንዱስትሪውና የአገልግሎት ዘርፎች ብሎም በፊስካልና በገንዘብ ፖሊሲዎች ላይ ለውጦች የሚደረጉበትን መንገድ የሚያመላክት የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴል አቅርበዋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ሞዴሉ ድርቅን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችና ወሳኝ ችግሮች እንደማይከሰቱ ታሳቢ በማድረግ ባስመጣቸው ሁለት የትንበያ መነሻዎች መሠረት፣ አሁን የሚታዩበትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታል ተብሏል፡፡

ይሁንና በመድረኩ ስለማክሮ ኢኮኖሚው የሚወራው በማይክሮ ደረጃ እንደሆነ በመግለጽ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቢበዛ ከአምስት በመቶ በላይ ዕድገት ላያስመዘግብ እንደሚችል ትንበያ ማስቀመጣቸውን የገለጹት፣ ዕውቁና አነጋጋሪው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚጽፏቸው ኢኮኖሚ ነክ ጽሑፎች ውስጥ ደጋግመው የሚጠቅሱት፣ በስብሰባውም የተናገሩት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ‹‹ኮማ›› ውስጥ ስለመግባቱ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ወደ ሞት እያዘገመ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ንዝረት የሚያስፈልገው የልብ ምቱ እንዳይቆም የሚያግዝ ሞገድ የሚያሻው ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ በዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) የቀረበውን መነሻ አጣጥለውታል፡፡

የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ባቀረቡት የኢኮኖሚ ሞዴል መሠረት፣ መሠረታዊ የተፈጥሮ አደጋዎችና ግጭቶች እስካልተፈጠሩ ድረስ አገሪቱ ኢኮኖሚ አሁን እየተወሰዱ በሚታዩ ዕርምጃዎችና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሳቢያ ዕድገቱ ይቀጥላል፡፡ እንደውም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ በ80 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ በሁለት ዓመታት ውስጥም ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ትንበያቸውን ያስቀመጡት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የወጪ ንግድ ችግሮችና የውጭ ምንዛሪ ድርቀቱ እንደተፈቱ ታሳቢ ተደርጎ የሚቀርቡ ትንተናዎች ትክክል አይደሉም ከሚሉት ወገን አቶ ኤርሚያስ ዋነኛው ሆነው አጣጥለውታል፡፡

‹‹[የኢኮኖሚው] በሽታ ሳይፈታ ለበሽታው ትኩሳት የሚሰጡ መፍትሔዎች ላይ ነው የምናወራው፤›› ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረበት የአምስት ቢሊዮን ዶላር አቅም ተነስቶ አሁን ላይ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመድረሱ መንግሥት ያደረጋቸው የመሠረተ ልማትና መሰል ኢንቨስትመንቶች (አቶ ኤርሚያስ ‹‹ቢግ ቡሽ›› ይሉታል) በመግለጽ ትክክለኛው የኢኮኖሚ በሽታ መድኃኒት አለማግኘቱን ይናገራሉ፡፡ ከነዚህ በሽታዎች መካከልም የፋይናንስ ዘርፉ የሚገኝበት ደረጃና የሚጎድለው የመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ ችግር ነው፡፡

ከዚህ ሐሳብ በተጨማሪ ስለአገሪቱ ኢኮኖሚ መነጋገሪያ ከነበሩት ውስጥ የካፒታል ገበያ ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ መንግሥት የካፒታል ገበያን የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ማድረጉን እንዲተው የሚጠይቁ ድምጾች ተሰምተዋል፡፡ የካፒታል ገበያው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት በሕዝቡ ዘንድ ለማሠራጨት፣ የሀብት ክፍፍሉ እንዲስፋፋ ይረዳልና መንግሥት እንደ መፍትሔ ይመልከተው የሚሉ ሐሳቦች ተደምጠዋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ስለሚያገኙት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ስለሚሰጣቸው ልዩ ድጋፍና መሰል ጉዳዮች በአንፃሩ የኢትዮጵያን ሀብት በማሸሽ (ካፒታል ፍላይት አንዱ ነው)  በመሳሰሉት ድርጊቶች ኢኮኖሚውን ዋጋ እያስከፈሉት ነውና ይህም ይፈተሽ የሚሉም ነበሩ፡፡

መድረኩ የመጀመርያው ነው ቢባልም፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ከተነሱት ሐሳቦችና ከተሳተፉት ምሁራን እንዲሁም ነጋዴዎች ውስጥ የግብርና ባለሙያዎችና የዘርፉ ተሳታፊዎች አለመካተታቸውን የሚገልጹ ቅሬታዎች እየተነሱ እንደሚገኙም ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ እንዲህ ያሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን የተመለከቱ ቅሬታዎች የተነሱበት የማክሮ ኢኮኖሚው ፎረም በሁለተኛው መድረኩ በምን መልኩ እንደሚያስተናግዳቸው በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ነው፡፡