Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከውጭ ከመጡ ፖለቲከኞች አንዱን አግኝተው እያወሩት ነው

ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከውጭ ከመጡ ፖለቲከኞች አንዱን አግኝተው እያወሩት ነው

[ለክቡር ሚኒስትሩ የእህታቸው ልጅ ስልክ ይደውልላቸዋል]

 • እንኳን አደረሰህ ጋሼ፡፡
 • ጎረምሳው ሳልደውልልህ ቀደምከኝ፡፡
 • እኔማ ጤንነትህን በዚያው ላረጋግጥ ብዬ ነው፡፡
 • ኧረ እሱስ ደህና ነኝ፡፡
 • ታዲያ ምነው ረሳኸን?
 • ኧረ ረስቻችሁስ አይደለም፣ ልደውል እያሰብኩኝ ነበር፡፡
 • ምነው ታዲያ ድምፅህ ጠፋ?
 • ድምፅህ ጠፋ ስትለኝ?
 • ያው በፊት በዓል ከመድረሱ ከሳምንት በፊት ቀጠሮ ታስይዘኝ ነበር፡፡
 • የምን ቀጠሮ ነው?
 • ጋሼ በበዓል ያስለመድከን ነገር አለ እኮ?
 • ምንድነው ያስመለድኳችሁ?
 • በእውነት ጋሼ ሁሉም ነገር ጠፍቶብሃል ልበል?
 • ለምን ግልጽ አድርገህ አትነግረኝም?
 • ለበዓል ያስለመድከንን ረሳኸው እንዴ?
 • በዓል ደረሰ እንዴ?
 • እትዬ እኮ ምነው ዝም አለን ደውልለት ብላኝ ነው፡፡
 • እኔማ በዓል መድረሱን ራሱ ረስቸዋለሁ፡፡
 • ለነገሩ ሥራ እንደሚበዛብህ አውቃለሁ፡፡
 • ታዲያ ምን እንዳደርግላችሁ ነው የምንትፈልጉት?
 • የተለመደውን የበግና የዶሮ መግዣ ነዋ፡፡
 • እ. . .
 • እንዴ ጋሼ ሌላ ጊዜማ ለአዲሱ ዓመት እኮ ተጨማሪ ስጦታዎችን ትሰጠናለህ፡፡
 • ለእሱ ነው አሁን የደወልከው?
 • አዎን ጋሼ፡፡
 • እሱን የማደርግላችሁ የነበረው እኮ ያኔ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 11 በመቶ እያደገ በነበረበት ወቅት ነው፡፡
 • አሁንስ ቢሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ነው እያላችሁ አይደል እንዴ?
 • ስማ ያኔ አገሪቱ ስታድግ በቀጥታ እኛ ነበርን የምናድገው፡፡
 • አሁንስ ጋሼ?
 • አሁንማ ኢኮኖሚው በቀጥታ ከእኛ ጋር እንደማይገናኝ ታውቃለህ፡፡
 • የእነዚያ የስኳር ፋብሪካዎች ፕሮጀክት መጓተታቸው በእርግጥ ጎድቶሃል ማለት ነው?
 • ምን እሱ ብቻ አሁንማ የግድቡም ተጨምሮበት ይኸው ባዶ ቀርቻለሁ፡፡
 • ስለዚህ ሁሉ ነገር የውሸት ነው ማለት ነው?
 • ምኑ ነው የውሸት?
 • አገሪቱ 11 በመቶ አድጋለች ምናምን የምትሉት?
 • ማደግ አድጋለች ግን አገር የሚለው ፍቺ ላይ ነው የማንስማማው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ድሮ አገር የምንለው ራሳችንን ብቻ ነው፡፡
 • እነማን?
 • ባለሥልጣናቱን፡፡
 • ለማንኛውም ጋሼ አሁን እኛ በዓል የምናሳልፍበት ምንም የለንም፡፡
 • ስማ እኔ ራሱ በዓል የማሳልፍበት የለኝም፡፡
 • እንዴ ጋሼ ምን እያልክ ነው?
 • አሁን ከለውጡ ጋር አንድ ላይ መራመድ አለባችሁ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • መንግሥት ራሱ ለበዓል የሚወጣው ወጪ ይቀነስ የሚል መመርያ እንዳወጣ ታውቃለህ አይደል?
 • እንዲያውም መመርያው ከወጣ በኋላ እኮ ነው በመንግሥት በኩል ድግስ የበዛው፡፡
 • ቢሆንም እንዲህ ዓይነት በዓሎችን እኔ በየዓመቱ መደጎም አልችልም፡፡
 • ታዲያ በየስንት ጊዜው ነው የምትደጉመን?
 • በየሁለት ዓመቱ፡፡
 • እንደ አፍሪካ ዋንጫ?

[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • በጣም ስፈልግዎት ነው ያገኘሁዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ደግሞ ምን ተገኘ?
 • ስልክዎን ብለው ብሠራው እኮ በጣም አስቸገረኝ፡፡
 • ምን ፈልገህ ነው?
 • ለነገሩ ዘንድሮ ከእርስዎ ሊያቆራርጠኝ የተነሳው ይኼ ቴሌ የሚሉት ድርጅት ነው፡፡
 • ምን አድርጎ?
 • ሳይሉት ዋጋውን ቀንሶ በቃ ሁሉም ደዋይ ሆነና እርስዎን በየትኛው ኔትወርክ ላግኝዎት?
 • አሁን ለምንድነው የፈለግከኝ?
 • በመጀመርያ እንኳን አደረሰዎት፡፡
 • ምን ያደርሰኛል፣ ደረሰብኝ እንጂ?
 • ክቡር ሚኒስትር በሆነው ባልሆነው አይማረሩ፡፡
 • እንደዚህ አዲስ ዓመት የቀፈፈኝ የለም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ ሁሉ ነገር ተቆላልፎ በጣም ያስጠላል፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር አሁን አንድ አሪፍ ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • የምን ሐሳብ ነው?
 • ባለፈው ያስታውሳሉ የማይሆን የቢዝነስ ሐሳብ ነው ያሉኝ?
 • የትኛው?
 • ያ የቲሸርትና የባነር ማተሚያ ሥራ ነዋ፡፡
 • እሱን አታስታውሰኝ ምን ያህል እንዳከሰርከኝ ታውቃለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ያን መመርያ ማን ይወጣል ብሎ አስቦ ያውቃል?
 • ትንሽ እንኳን ሳልሠራ ነው እኮ መንግሥት ቲሸርትና ኮፍያ መታተም ይቅር ያለው፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ፣ ግን የእርስዎም ጥፋት ነበረበት፡፡
 • ምን አጠፋሁ?
 • ማሽኑን መጋዘን ውስጥ ከሚቆልፉበት እኔ ብሠራበት ጥሩ ነው፡፡
 • አሁንማ ገዥ ፈልግልኝና ሸጬ ልገላገለው፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆንክ?
 • አሁንማ አሪፍ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል፡፡
 • የምን አጋጣሚ?
 • ሕዝቡን አይመለከቱትም እንዴ በየሳምንቱ እኮ ነው ሠልፍ እየወጣ ያለው፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ ግን አመለጠን እኮ?
 • ክቡር ሚኒስትር ገና ከዚህ በኋላ በጣም በርካታ የሕዝብ ሠልፎች ይኖራሉ፡፡
 • ታዲያ ሌሎቹ ቢዝነሱን ተቆጣጥረውት እንዴት እኛ እንሠራዋለን?
 • መጀመርያ ታዲያ ማሽኑን ለምን አስመጡት?
 • እኔማ ያለ ውድድር የመንግሥትን ሥራ አገኛለሁ ብዬ ነው፡፡
 • ለማንኛውም እኔ ተወዳዳሪ የምንሆንበትን ሐሳብ ይዤ ነው የመጣሁት፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • አዩ ሕዝቡ አሁን አንዴ ለመንግሥት ይወጣል፣ በሚቀጥለው ደግሞ ለተቃዋሚ ይወጣል፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ምን እሱ ብቻ ክቡር ሚኒስትር ለተቃዋሚዎች አክቲቪስቶች የወጣው ሕዝብ፣ በሚቀጥለው ለመንግሥት አክቲቪስቶች ይወጣል፡፡
 • ስለዚህ ቢዝነሱ አዋጭ ነው እያልከኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ በቲሸርት ወጪ ተማሯል፡፡
 • ሕዝቡ ወዶ መስሎኝ ሠልፍ የሚወጣው?
 • ሕዝቡ ሠልፍ የሚወጣው ወዶ ሳይሆን ፈርቶ ነው፡፡
 • ለመሆኑ ተወዳዳሪ የምንሆንበት ሐሳብህ ምንድነው?
 • ቲሸርቱን በላይ በኩል መንግሥትን የሚያወድስ፣ በውስጥ በኩል ደግሞ ተቃዋሚን የሚያወድስ አድርጎ ማተም ነዋ፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይመታል ማለት ነው?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ቲሸርቱን ምን የሚል ስም እናውጣለት?
 • ተለዋዋጭ ቲሸርት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • መቼም ቴሌቪዥን ላይ የማየው ነገር ያስገርመኛል፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስገርምሽ?
 • ሰው ወረተኛ ብቻ አይገልጸውም፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ ሥራ ምናምን ካሉ በኋላ በቃ ግማሹ ቤት ይገዛል፣ ግማሹ ቤት አፍርሶ ይሠራል፡፡
 • ይኼ አሁን የምታይው ሆይ ሆይታ የሚቀጥል እንዳይመስልሽ፡፡
 • እኔ እሱ አስገርሞኝ አይደል እንዴ የምነግርህ?
 • ስሚ ሕዝቡ አንዴ መንግሥትን፣ ሌላ ጊዜ ተቃዋሚን ይደግፋል እኮ?
 • ለነገሩ አንተ ሁሌም ቢሆን የሕዝቡ አካሄድ አይጥምህም፡፡
 • ስሚ እኛ አሁን ከመንግሥት የተቀበልነውን ሐሳብ መተግበር አለብን፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • የመደመር ሐሳብ ነዋ፡፡
 • እኔም ተደምሬያለሁ ልትለኝ ባልሆነ?
 • መደመርን በሌላ ሐሳብ ነው የተረዳሁት፡፡
 • አንተ እንዴት ነው የተረዳኸው?
 • መደመር ማለት መጨመር ማለት አይደል?
 • አዎ ልክ ነው፡፡
 • ስለዚህ እነዚያ አምስት ቪላዎች ላይ የቤት ኪራይ መጨመር አለብን፡፡
 • ምን?
 • እሱ ብቻ ሳይሆን ሕንፃችን ውስጥ ያሉ ሱቆች ላይ ሒሳብ ይደመራል፡፡
 • በቅርቡ ነበር እኮ ኪራይ የጨመርንባቸው?
 • በቃ ከመንግሥት የተቀበልነው ሐሳብ እንደሆነ ንገሪያቸው፡፡
 • ስለዚህ የሠራተኞች ደመወዝም ሊጨመር ነው ማለት ነው?
 • በነገራችን ላይ መደመር ውስጥ እኮ መቀነስም አለ ተብሏል፡፡
 • ስለዚህ ምን እያልክ ነው?
 • በመጀመርያ የሠራተኞቻችንን ጥቅማ ጥቅሞች እንቀንሳለን፡፡
 • አባ መላ እኮ ነህ፡፡
 • ከተቻለ ደግሞ ሠራተኞቻችን ላይ ጫና መጨመር ነው፡፡
 • ሰውዬ ሕዝቡ ግን እንዳይጠምድህ?
 • ነገርኩሽ እኮ እኔ ከመንግሥት በተቀበልኩት አቅጣጫ ነው የምሠራው፡፡
 • እንደዚህ ካደረክ ግን በቅርቡ ስም ይወጣልሃል፡፡
 • ምን የሚል?
 • ሆዳም!

[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከውጭ ከመጡ ፖለቲከኞች አንዱን አግኝተው እያወሩት ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
 • እንኳን ለአገርህ በሰላም አበቃህ፡፡
 • እናንተም እንኳን በደህና ጠበቃችሁን፡፡
 • ከዚህ በኋላ እኛም ውጭ ስንወጣ ከስድብ ተገላገልን፡፡
 • የሚያሰድባችሁ እኮ ሥራችሁ ነው፡፡
 • ይኸው እናንተ እዚህ ስትመጡ ደማቅ አቀባበል አይደል እንዴ የተደረገላችሁ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ ለሕዝቡ ስንታገል ነው የቆየነው፡፡
 • እኛስ ለማን ነበር የታገልነው?
 • እናንተማ የራሳችሁን ሆድ ለመሙላት ነው የታገላችሁት፡፡
 • እዚህም ገብተህ ስድብ አላቆምክም ማለት ነው?
 • ለነገሩ አሁን ወደ አገር ቤት የገባሁት ለመሳደብ ሳይሆን ሕዝቡን ለማረጋጋት ነው፡፡
 • እናንተ ደግሞ ከስድብ ውጪ ለሕዝቡ መቼ ፕሮግራማችሁን አስታውቃችሁ ታውቃላችሁ?
 • እሱን እንግዲህ በምርጫው ሜዳ ላይ ይለያል፡፡
 • ሕዝቡማ ሁሌም ከእኛ ጎን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር 97 ምርጫ ላይ እንዴት እንደተጫወትንባችሁ መቼም ያስታውሳሉ?
 • ሥራ እንጂ መኮፈስ አያዋጣም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኛ ብቸኛ ፀሎታችን ቀጣዩ ምርጫ ነፃ እንዲሆን ነው፡፡
 • ከምን?
 • ከኮሮጆ ሌባ!