ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው
[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ሰውዬ ለመሆኑ ጤነኛ ነህ?
- ክቡር ሚኒስትር ያጋጠመኝን እኮ ስላላወቁ ነው፡፡
- ሁለት ቀን ሙሉ ስልክህን አጥፍተህ?
- በእነዚህ ሁለት ቀናት የደረሰብኝን መከራ ስለማያውቁ እኮ ነው?
- የላኩህ ቦታ ብጥብጥ አለ እንዴ?
- ብጥብጥ እንኳን አልነበረም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን ሆነህ ነው ልትገኝ ያልቻልከው?
- የላኩኝን መልዕክት ለማድረስ ስንት መስዋዕት ስከፍል ነበር፡፡
- የምን መስዋዕትነት ነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር የሰጡኝ ሥራ ከፍተኛ መስዋዕት የሚያስከፍል ነበር፡፡
- እህቴ የምትበላው ስለተቸገረች ለእሷ ጤፍ አድርስ አይደል እንዴ የተባልከው?
- እሱማ ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ይኼን መሥራት ካልቻልክ ምኑን ሾፌር ሆንክ?
- ክቡር ሚኒስትር ሥራው እንዲህ ቀላል አይደለም እኮ?
- ምን ታካብዳለህ ሴትዮዋ በረሃብ ትሙት?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ማንም ኢትዮጵያዊ በረሃብ መሞት የለበትም፡፡
- ስማ ይቺ ሴትዮ ብትሞት ግን አንተ እንደገደልካት ማወቅ አለብህ፡፡
- የተባለውን አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተባለ?
- መግደል መሸነፍ ነው ተብሏል፣ ስለዚህ እኔ መሸነፍ አልፈልግም፡፡
- የፖለቲካ ዲስኩርህን እዚያው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔማ የሰጡኝ ሥራ በቴክኖሎጂ ሳይቀር ታግዤ ለመሥራት አስቤያለሁ፡፡
- ምንድነው የምታወራው?
- ይኸው እህሉን እንዴት ለእህትዎ በድሮን ማድረስ እችላለሁ ብዬ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡
- የምትበላው የላት የምትከናነበው አማራት አሉ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለሥራችን እኮ ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን፡፡
- ሰውዬ ለመሆኑ ስለድሮን ታውቃለህ?
- እንዴ ይኸው በአገራችን ድሮን በመጠቀም የተለያዩ ነገሮች ለሰዎች እየተላኩ እኮ ነው፡፡
- እና አንተም በድሮን 100 ኪሎ ጤፍ ልታደርስ አስበህ ነው?
- ምን ችግር አለበት ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ አንተ ስለቴክኖሎጂ ታውቃለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ቀኑን ሙሉ ፌስቡክ ላይ ተቀምጬ አይደል እንዴ የምውለው?
- ስለዚህ ቴክኖሎጂ በሚገባ ታውቃለህ ማለት ነው?
- ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር ይኼንን የድሮን ቴክኖሎጂ ራሱ እሱ ላይ አይደል እንዴ ያየሁት?
- እንደ አንተ ዓይነቱ እኮ ነው ሁሉን አውቃለህ እያለ አገር የሚያጠፋው፡፡
- ቴክኖሎጂ ብዙ አይመችዎትም መሰለኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ ለማንኛውም እስካሁን እህሉን ባለማድረስህ ቅጣት ይጠብቅሃል፡፡
- የምን ቅጣት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የደመወዝ ቅጣት፡፡
- ምን አጥፍቼ ክቡር ሚኒስትር?
- ይኸው ለእህቴ አድርስ የተባልከውን እህል ሳታደርስ ሁለት ቀን የት ቆይተህ እንደመጣህ አይታወቅም፡፡
- ምክንያቴን ቢያውቁት እኮ እንደዚህ አይሉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ምክንያትህ?
- የእህትዎት ቤት ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡
- አካባቢውን አውቀኸዋል አይደል እንዴ?
- አካባቢውን ባውቀውም ቤታቸው ለመግባት ዘዴ ስዘይድ ነበር፡፡
- ቤቷ ለመግባት ለምን አልቻልክም?
- ቤታቸው ለመግባት የሠፈሩ አቀማመጥ አይመችም፡፡
- ምን ሆነብህ?
- አባጣ ጎርባጣ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ምነው ተከፍተሃል?
- እንዴት አልከፋ ክቡር ሚኒስትር?
- እኮ ምን ሆንክ?
- ክቡር ሚኒስትር ብዙ የቢዝነስ አጋጣሚዎች እኮ እያለፉን ነው፡፡
- አገሪቱ እንደዚህ እየታመሰች እንዴት ቢዝነስ መሥራት ይቻላል?
- አዩ ክቡር ሚኒስትር ሁለታችንም አርጅተናል ማለት ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በፊት እኮ በብጥብጥ ውስጥ ሳይቀር ቢዝነስ እንሠራ ነበር፡፡
- ያኔማ የእኛ ሰዎች ሁሉም ቦታ ተቀምጠው ስለነበር ነው፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር በዚህ ከቀጠለ ዋጋ የለንም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- እንደዚህ ማሰብ ካቃተን የያዝናቸውን ቢዝነሶች ራሱ እንዳናጣቸው እሠጋለሁ፡፡
- ምን ሆነህ ነው ይኼን ያህል?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ምን የመሳሰሉ ዕድሎች እኮ እያለፉን ነው፡፡
- ከቲሸርትና ከባነሩ ቢዝነስ ሌላ ምን አመለጠን?
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚህ የተደበርኩት እኮ ሌላ ቢዝነስ ስላመለጠን ነው፡፡
- እኮ የምን ቢዝነስ ነው?
- የቀለም ቢዝነስ ነዋ፡፡
- ሰውዬ እኔ መቼም ቢሆን የቀለም ፖለቲካን ስታገል እንደኖርኩ ታውቃለህ፡፡
- እኔም እሱን ብዬ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ መቼም ቢሆን የቀለም ፖለቲካን አልደግፍም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ዝም ብለው ከበሩ እኮ?
- እነማን ናቸው የከበሩት?
- ምነው ያን ዝም ብሎ የተቆለፈ መጋዘን የቀለም ፋብሪካ አድርገነው ቢሆን ኖሮ?
- ምንድነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር ከአዲስ አበባ ወጣ ሲሉ እኮ ሁሉ ነገር ቀይና አረንጓዴ ነው የተቀባው፡፡
- በነገራችን ላይ በእሱ ነገር በጣም ነው የተቃጠልኩት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ብቻ ምን አለፋዎት በቀላሉ የምንከብርበት አጋጣሚ ነው ያለፈን፡፡
- ይኸው አሁን መንግሥት ማንም እንዳይቀባ ከልክሏል አይደል እንዴ?
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር፣ ስልክ እንጨቱ አይሉ አጥሩ ምን አለፋዎት ሰው ራሱ ረዘም ላለ ሰዓት ቆመው ካገኙ ይቀቡ ነበር አሉ፡፡
- ነገርኩህ እኮ ከዚህ በኋላ ቢዝነሱ ያከትምለታል፡፡
- እኔስ ያናደደኝ ምንም ሳንሠራ ቢዝነሱ በመሞቱ አይደል እንዴ?
- አሁን ስናወራ ግን አንድ ሐሳብ መጣልኝ፡፡
- የምን ሐሳብ ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን መንግሥት የፅዳቱን ፕሮጀክት እንዲሰጠኝ አላደርግም?
- የምን የፅዳት ፕሮጀክት?
- በቃ የተቀባውን ቀለም ለማጥፋት እኛ ሥራውን እንውሰደዋ፡፡
- አባ መላ እኮ ነዎት፡፡
- ስለዚህ እንዲያውም በአፋጣኝ ማምጣት ነው፡፡
- ምንድነው የምናመጣው?
- ኬሚካሉን ነዋ፡፡
- የምን ኬሚካል?
- የቀለም ማስለቀቂያ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን ቢሯቸው አስጠሩት]
- ሪፖርቱን ተመለከቱት ክቡር ሚኒስትር?
- እስኪ ቁጭ በል፡፡
- ችግር አለ እንዴ?
- ሥርዓት አልበኝነት እኮ እዚህ እኛ ቢሮ እንደገባ አላወቅኩም ነበር?
- የምን ሥርዓት አልበኝነት?
- ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ሥርዓት አልበኝነት እንዲመጣ ነው የምንጠብቀው?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ያዘዝኩት ነገር ካልተከበረ ከዚህ በላይ ሥርዓት አልበኝነት የት አለ?
- ኧረ ይረጋጉ ክቡር ሚኒስትር?
- ትዕዛዜ ሳይከበር እንዴት ልረጋጋ?
- የትኛው ትዕዛዝ?
- ከዚህ በፊት መመርያ አላወጣንም?
- የምን መመርያ?
- ማንም ሰው እኔን ሳያስፈቅድ ፊልድ እንዳይወጣ አላልኩም?
- ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ይኼ መመርያ የወጣው ለጨዋታ ነው?
- ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምንድነው ተፈጻሚ ያልሆነው?
- እየተፈጸመ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አያውቅም ብለህ ልትጫወትብኝ ነው?
- እኔ እንደዚህ ዓይነት ንቀት ለእርስዎ የለኝም፡፡
- ታዲያ ይኼን ወጪ አይተኸዋል?
- የቱን ወጪ ክቡር ሚኒስትር?
- ለፊልድ የወጣውን ወጪ ነዋ፡፡
- ተመልክቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ካቀረብክልኝ ወጪ ከ30 በመቶ በላይ ነው እኮ?
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ መመርያውን ከማውጣታችን በፊት ከነበረው በላይ ሆኗል እኮ ወጪው?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
- መመርያውን ለመተግበር ምንድነው ያስቸገረህ?
- መመርያውንማ ተግባራዊ አድርጌዋለሁ አልኩ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ይላይ ይኼ? ወጪውን ዓይተኸዋል?
- ክቡር ሚኒስትር ሪፖርቱን በደንብ ያነበቡት አልመሰለኝም?
- ይኸው ፊት ለፊት እያየሁት አይደል እንዴ?
- በደንብ ቢያዩትማ እንደዚህ አይጮሁብኝም ነበር?
- ይኼ ለፊልድ የወጣ ወጪ አይደለም እያልከኝ ነው?
- እሱማ ነው፡፡
- ታዲያ እኔ ሳላውቅ ይኼ ሁሉ ወጪ እንዴት ይወጣል?
- ክቡር ሚኒስትር ወጪውንማ በሚገባ ያውቁታል፡፡
- እኔ እኮ እስከ ዛሬ ማንም ፊልድ እንዲወጣ ፈቅጄ አላውቅም፡፡
- እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ማን ፊልድ ወጥቶ ነው ይኼ ሁላ ወጪ?
- እርስዎ!
[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ኢትዮጵያን መቼም እንደጠበቅካት አይደለም ያገኘሃት አይደል?
- አዎ እንደጠበቅኳት አይደለም ያገኘኋት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ብዙ ለውጥ አለ አይደል?
- በጣም ብዙ ለውጥ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የአገሪቱ ልማት፣ ዕድገትና ሥልጣኔ አላስደነቀህም?
- የምን ዕድገት? የምን ልማት? የምን ሥልጣኔ?
- አሁን በሚገባ ነው ያረጋገጥኩት፡፡
- ምንድነው ያረጋገጡት?
- እናንተ ዳያስፖራዎች ጨለምተኛ መሆናችሁን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለእኔ የታየኝ ዕድገት ሳይሆን አገሪቱ የኋሊት መሄዷን ነው፡፡
- ድሮም ጨለምተኛ ናችሁ እኮ፡፡
- ሰሞኑን አገሪቱ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር አላስተዋሉትም ማለት ነው?
- ምን እያልክ ነው?
- ለምን ሌላ ቋንቋ ተናገርክ ተብሎ ሰው የሚገደልባት አገር የምን ሥልጣኔ ነው ያለው?
- እ. . .
- ክቡር ሚኒስትር ለምን ለየት ያለ ልብስ ለበስክና ለምን ለየት ያለ ምግብ በላ ተብሎ ሰው ሲገደል እያየን ስለልማት ያወራሉ?
- ስማ ይህች አገር የሦስት ሺሕ ዓመት ታሪክ ያላት ናት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፈረንጆቹ ከዛሬ 500 ዓመት በፊት በሚጣሉበት ነገር እየተጣላን ስለዕድገትና ስለልማት እንዲሁም ስለሥልጣኔ ማውራት አንችልም፡፡
- እስኪ ቀና ለመሆን ሞክር፡፡
- ነገርኩዎት ክቡር ሚኒስትር አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ፣ በሚለብሰው ልብስና በሚበላው ምግብ እየለያዩ የሚያጋድሉበት አገር ዜጋ ነኝ ለማለት አፍራለሁ፡፡
- እ. . .
- ስለዚህ ኢትዮጵያ የሦስተኛ ዓለም አገር መሆን አይገባትም፡፡
- እሱማ ካደጉት አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ወጥረን እየሠራን ነው፡፡
- ወዴት ወዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ኢትዮጵያ መመደብ ያለባት ሌላ ዓለም ውስጥ ነው፡፡
- የትኛው ዓለም?
- አራተኛው ዓለም!