Skip to main content
x
የትራኮማውን ጫና ለማርገብ

የትራኮማውን ጫና ለማርገብ

ፍሬድ ሃውሎስ ፋውንዴሽን መቀመጫውን በአውስትራሊያ ያደረገ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መከላከል በሚቻሉ ሕመሞች የሚመጣውን ዓይነሥውርነት ለመግታት ይሠራል፡፡ በኢትዮጵያም ከ100 ሺሕ ለሚልቁ የትራኮማ ሕሙማን ቀዶ ሕክምና አድርጓል፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እያደረገ በሚገኘው እንቅስቃሴ ዙሪያ የድርጅቱ ግሎባል ሊድ ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አሊሰን ሂልን ሳሙኤል ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ፍሬድ ሃሎውስ ፋውንዴሽን ቢያብራሩልን?

አሊሰን ሂል፡- ፋውንዴሽኑ ዓለም አቀፍ ሲሆን፣ ሊታከሙ በሚችሉ ሕመሞች የሚከሰተውን ዓይነሥውርነት ለመከላከል ይሠራል፡፡ ሥራውን የሚያከናውነውም ከመንግሥት፣ ከአጋር ድርጅቶችና ከሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ነው፡፡ በዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ25 በላይ ለሚሆኑ አገሮች ትራኮማን የመከላከል ኢንሽየቲቭ ወስደን አንተገብራለን፡፡ ሥራችንም የድርጅቱ መሥራች የሆኑትንና ጊዜያቸውን ሊታከም ሊታከም እየቻለ ባለመሆኑ ዓይን የሚያጠፋውን ትራኮማ ለማስቆም ሲሠሩ የቆዩትን ፕሮፌሰር ፍሬድ ሃሎውስ ዓላማ የተከተለ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ዶክተሮችን፣ ነርሶችንና አጋር ሠራተኞችን በማሠልጠን ጠንካራ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት እንዲኖር ሠርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ እየሠራን ያለነው በኦሮሚያ ክልል ትራኮማን በማጥፋቱ ላይ ነው፡፡ ከትራኮማ ባለፈም ለዓይን ጤና ጠንቅ የሆኑትን ችግሮች0 ለመከላከል የሚሠራውን ሥራ እናግዛለን፡፡ ከ26 ዓመታት በፊት በአውስትራሊያ የተመሠረተው ፋውንዴሽኑ አሁን ላይ ግንባር ቀደም ከሆኑትና የዓይን ጤና ላይ ከሚሠሩት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተርታ ተሰልፏል፡፡

ሪፖርተር፡- የፋውንዴሽኑ ቡድን አባላት በኦሮሚያ ክልል የትራኮማ ቀዶ ሕክምናን አድርጓል፡፡ በተያዘው ዓመት መጀመርያም 100 ሺኛውን ቀዶ ሕክምና አከናውናችኋል፡፡ ስለሥራው ቢያብራሩልኝ?

አሊሰን ሂል፡- ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር 100 ሺኛውን የትራኮማ ቀዶ ሕክምና ባለፈወ ሰኔ አከናውኗል፡፡ ተጠቃሚዋም በኦሮሚያ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሚኖሩት የ80 ዓመቷ ከምሩ አብደላ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል 27 ሚሊዮን ሰዎች በትራኮማ የመጠቃት አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ 150 ሺሕ ያህሉ ደግሞ ቀዶ ሕክምና ካላገኙ የዓይን ብርሃናቸውን የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩን ለማጥፋት ጠንካራ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ድረስ ያሉ ለውጦች ምን ይመስላሉ?

አሊሰን ሂል፡- ኢትዮጵያ በዓለም የትራኮማ ጤና ችግር ካለባቸው ቀዳሚ አገሮች ተርታ ናት፡፡ ትራኮማ ልንከላከለው የምንችል ነገር ግን ከባድ ሕመም ያለው የዓይን በሽታ ነው፡፡ 76 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ትራኮማ በብዛት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ናቸው፡፡ 800 ሺሕ ያህል ደግሞ ዓየነሥውር የመሆን አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ፋውንዴሽኑ በኢትጵዮያ ያለው ትልቁ ፕሮጀክት ከመንግሥት፣ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮና ከአጋሮች ጋር በመተባበር ቀዶ ሕክምና የሚጠብቁ ሕሙማንን በአንድ ሦስተኛ በመቀነስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሕሙማን ከዓየነ ሥርውርነት መታደግ ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ሥራውን በኦሮሚያ ስንጀምር 150 ሺሕ ሰዎች ለቀዶ ሕክምና ወረፋ እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ችግሩን ለማቃለል ጠንክረን ሠርተናል፡፡ እንቀጥልበታለንም፡፡ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን እንደርስላቸዋለን፡፡ ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት በተጨማሪም ከዩኤስኤአይዲ ከእንግሊዙ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት፣ ከአርቲአይ ኢንተርናሽናል፣ ከሄለን ኬለር ኢንተርናሽናልና ከሌሎችም አጋሮቻችን ጋር ተባብሮ ባይሠራ ኖሮ አሁን ለደረስንበት ዕድገት አንበቃም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በተያዘው ሳምንት ትኩረት ባልተሰጣቸው የቆላ በሽታዎች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኔትወርክ ኮንፍረንስ አለ፡፡ በኮንፍረንሱ የሚነሱ ጭብጦች ምንድን ናቸው?

አሊሰን ሂል፡- እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ የኒግሌክትድ ትሮፒካል ዲስስ ኔትወርክ ትራኮማን ጨምሮ ተገቢ ትኩረት ያልተሰጣቸው በሽታዎችን ለመከላከል ፎረም ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በዘርፉ የሚሠሩ እርስ በርስ ይማማራሉ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ላይ ልምድ ይለዋወጣሉ፣ ልምድ መለዋወጡ የተሠሩና ያልተሠሩ ሥራዎችን ለማወቅና ዕርዳታ ሰጪዎች፣ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቱ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ለማስገንዘብ ይረዳል፡፡ ትኩረት ያልተሰጣቸው በሽታዎች ልንከላከላቸውና ሊታከሙ የሚችሉ ቢሆንም በዓለም በተለይ በገጠራማ ሥፍራ ከሚኖሩት ከቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ድሆችን አጥቅቷል፡፡ እንደኛ ያለ ፋውንዴሽንና ሌሎችም ችግሩን ለመዋጋት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ የድህነት መገለጫ የሆኑት በሽታዎች የተዘነጉትን ሕዝቦች እንዳያጠቁ ያለውን የጤና ሥርዓት ማሻሻልና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ላይ ለመምከር ከ500 በላይ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ኮንፍረንስ ይታደማሉ፡፡ በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል አዲስ ስትራቴጂና ስልት ያስፈልገናል፡፡ ግንዛቤ መፍጠርም እንዲሁ፡፡ ፋውንዴሽናችን ልምዱን ያካፍላል፡፡ ሥራውን ውጤታማ የሚያደርጉ ልምዶችንም ከኮንፍረንሱ ይቀስማል፡፡ የዓመቱ ኮንፍረንስ ጭብጥ “Reaching the Last Billion” [የመጨረሻው ቢሊየነኛው ላይ መድረስ] የሚል ነው፡፡ ዓላማው በበሽታዎቹ አደጋ ውስጥ ያሉ ድሆችን መድረስ ነው፡፡ እነዚህ የችግሩ ተጋላጮች ድሆችና የተዘነኑም ናቸው፡፡ በአብዛኛውም አርብቶ አደሮች፣ የተፈናቀሉ፣ ሰላም በሌለበት ሥፍራ የሚኖሩ ሲሆኑ በተለይ ከትራኮማ ጋር ተያይዞ ሴቶች ከወንዶች አራት እጥፍ ያህል ተጋላጭ ናቸው፡፡ እነዚህን የመድረስ ዓላማ ያነገበ ኮንፍረንስ እናካሂዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የቀዶ ሐኪም እጥረት መኖሩን ያወሳል ይኼንን ችግር በተለይ በገጠራማ ሥፍራዎች እንዴት መሙላት ቻላችሁ?

አሊሰን ሂል፡- የፋውንዴሽኑ መሥራች ፍሬድ ሃሎውስ ሁልጊዜም አስተማሪዎችን ማስተማር የሚለው አባባልን ጠብቀው ነው ያቆዩት፡፡ ይህ ፍልስፍናቸው በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም የምናከናውነው ሥራ የሚቃኝበት ነው፡፡ እኛም ቀዶ ሕክምና ስናደርግ የአገር ውስጥ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን፣ የዓይን ሐኪሞችን፣ የማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞችንና አስተማሪዎችን እናሠለጥናለን፡፡ ይኼን በማድረግ በኢትዮጵያ ትራኮማን ለመከላከል ተፅዕኖ እየፈጠርን ነው፡፡ በ2017 ፋውንዴሽኑ 24 የተቀናጀ የዓይን ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በትራኮማ ቀዶ ሕክምና አሠልጥነናል፡፡ ከ53 ሺሕ በላይ የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎችንና አስተማሪዎችን አሠልጥነናል፡፡ እነዚህ ትራኮማን ለማጥፋት ለምንሠራው ሥራ ወሳኝ አጋሮች ናቸው፡፡ ይኼንን በማድረግ በዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ሴፍ (SAFE) ፕሮግራም ቢገለጹልኝ?

አሊሰን ሂል፡- ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ትራኮማን ለማከምና ለማጥፋት ሴፍ የተባለ ስትራቴጂ ነድፏል፡፡ ሴፍ የትራኮማ ተጠቂዎችን ቀዶ ሕክምና፣ በኢንፌክሽን የተጠቁትን ፀረ ተዋሕስያን መስጠት፣ ፊትን መታጠብና በንፁህ አካባቢ መኖርን ጤናን ለመጠበቅና የበሽታውን መተላለፊያ ለመቀነስ ያግዛል ብሎ የነደፈው አሠራር ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የሴፍ ስትራቴጂን በመተግበር ፋውንዴሽኑና የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከ17 ሚሊዮን በላይ ፀረ ተዋሕስያን አሰራጭተናል፡፡ ሆኖም ሕዝቡን ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ደረጃ ሕዝቡ የዓይኑን ደህንነት መጠበቅ አለት፡፡ በየጊዜው የዓይኑን ጤንነት በአካባቢው ባሉ ክሊኒኮች ማረጋገጥም ይጠበቅበታል፡፡ አገሮችም መፀዳጃ መገንባትንና የውኃ አቅርቦት ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሠለጠኑ የጤና ባለሙያዎችና በቂ የጤና መርጃ ቁሳቁስ በሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታ በሽታውን ማጥፋት ቀላል ነው? የናንተ መሪ ቃልም ትራኮማን ማከምና ማዳን ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ዕውን ይሆናል?

አሊሰን ሂል፡- በዓለም በትራኮማ አደጋ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ2011 ወዲህ በግማሽ ቀንሷል፡፡ በ43 አገሮች ከትራኮማ አደጋ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በ157.7 ሚሊዮን ቀንሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ግምት በአሥር ዓመት ውስጥ ትራኮማን ማጥፋት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከመንግሥት፣ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮና ከረጂዎች ጋር የሠራነው ሥራ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ትራኮማን ለማጥፋት ቁርጠኝነት አለ፡፡ በዓለም ካለው የትራኮማ ጫና ኢትዮጵያ 44 በመቶውን ትጋራለች፡፡ የዓለም መንግሥታትም ኢትዮጵያ ላይ ያለውን የትራኮማ ጫና ለማቃለል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በ2017 በዓለም የትራኮማ ጫናን ለመቀነስ ከተሠሩ ቀዶ ሕክምናዎች 75 በመቶው እንዲሁም ከተሰጡ ፀረ ተዋሕስያን 60 በመቶው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ አሁንም በኢትዮጵያ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በጋና ትራኮማን ማጥፋት ተችሏል፡፡ በኢትዮጵያም እናሳካዋለን ብለን እየሠራን ነው፣ ይሆናልም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በዕርዳታ ድርጅቶች ላይ ከሚቀርቡ ቅሬታዎች አንዱ ዕርዳታ ከመስጠት ባለፈ አቅም አይገነቡም የሚል ነው፡፡ የእናንተ ድርጅት ግን ከዚህ ይለያል፡፡ የጤና ባለሙያዎችን ያሠለጥናል፡፡ ቢያብራሩልን?

አሊሰን ሂል፡- የፍሬድ ሃሎውስ ፋውንዴሽን የተገነባው ሌሎችን ማሠልጠን አለብን በሚል መርህ ላይ ነው፡፡ ይህ ፊሎሶፊ በሁሉም አካባቢዎች የምንከተለው ነው፡፡ በተለይ ትራኮማን ከዓለም ለማጥፋት ወሳኙ አስተማሪ የሚሆኑትን በማሠልጠን ነው፡፡ ትራኮማ ሲጠፋ የሠለጠኑትን ወደሌሎች ሕክምናዎች ፊታቸውን አዙረው ይሠራሉ፡፡ በዓይንም ሆነ በሌላ ለመሥራት የሚያስችላቸውን አቅም እየገነባን ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎችን በማሠልጠን በኢትዮጵያ ትራኮማን ለማጥፋት ብሎም የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር እየሠራን ነው፡፡