Skip to main content
x
የኢሕአዴግ ነገር ብዙ ያነጋግራል!

የኢሕአዴግ ነገር ብዙ ያነጋግራል!

የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከረቡዕ መስከረም 23 ቀን እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማ ሐዋሳ ይካሄዳል፡፡ መሰንበቻውን የግንባሩ አራት ብሔራዊ ድርጅቶች በጉባዔያቸው የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴዎች ምርጫ በማድረግ፣ በአመዛኙ አዳዲስ አመራሮች ወደፊት አምጥተዋል፡፡ ሁለቱ የስያሜና የዓርማ ለውጥ ሲያደርጉ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ በነበራቸው ስያሜና ዓርማ ቀጥለዋል፡፡ የአሁኑ የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ የሚካሄደው ኢትዮጵያን ለአራት ዓመታት ያህል በከፍተኛ ግለት ሲንጣት በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት፣ አዲስ የለውጥ ጉዞ ተጀምሮ በርካታ ነገሮች እየተለወጡ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግ የሚመካባቸው ስኬቶች ቢኖሩትም፣ ነገር ግን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባሩ ከመጠን በላይ ሆኖ ሕዝባዊ አመፅ እንዲቀሰቀስና በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ አሁንም ድረስ በየቦታው በሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ምክንያት፣ ንፁኃን እየተገደሉና እየተፈናቀሉ የአገር ሰላም እየደፈረሰ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ጉባዔ ላይ የሚቀመጠው፡፡ ትዕግሥትና ብልኃት የሚያሻበት ወሳኝ ወቅት ላይ ስለሚገኝ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡

ኢሕአዴግ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተሳነው፣ በውስጡ ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብና ድርጊቶች ከመጠን በላይ እየሆኑ በመምጣታቸው እንደሆነ ራሱ በተደጋጋሚ አምኗል፡፡ በተለይ በተከታታይ ያደረጋቸውን የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማዎች ሲያበቃ እንዳስታወቀው ለሕግ የበላይነት መጥፋት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለሙስና መንሰራፋት፣ ሕዝብን አገልግሎት በመንፈግ ለምሬት በመዳረግና ለመሳሰሉት አስከፊ ድርጊቶች ዋነኛ ምንጩ ራሱ ኢሕአዴግ ነበር፡፡ ሕዝባዊ አመፁ እየገፋ ሲሄድና አገሪቱ ወደ ቀውስ ስታመራ ከአንዴም ሁለቴ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር ለመምራት መሞከሩ፣ አመፁ የበለጠ እንዲጋጋልና ቀውሱም እንዲባባስ አድርጓል፡፡ የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ውጤታማ መሆን ባለመቻሉም በመጨረሻ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለ17 ቀናት በሩን ዘግቶ ካደረገው ግምገማ በኋላ፣ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች ለደረሰው ጥፋት ሁሉ አመራሩን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድም የአመራር ለውጥ ተደርጎ ከመጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግንባሩን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ በኢሕአዴግ ምክር ቤት ተመርጠዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዕርምጃዎች ተወስደው የለውጡ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ መንገድ ይቀራል፡፡ በጥልቀት መነጋገር ይገባል፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ በአሁኑ ጉባዔ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ሲቀመጥ፣ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ትግል እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ‹‹ካለፉት ጥፋቶች ትምህርት ወስደን፣ የአገራችንን መጪ ዘመን ብሩህ እንዲሆን ከፊታችን ያሉትን አማራጮች ለይተን በመመካከር ቀጣይ ዕርምጃዎችን ለመንደፍ ተነስተናል፡፡ የተጋረጡብን ችግሮች ከባድ ቢመስሉም፣ ተስፋ ሰንቀን ወደፊት ለመራመድ ለጀመርነው ጉዞ የዚህ ጉባዔ ሚና ከፍተኛ ነው፤›› ያሉት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹…በእርግጥ በሁሉም ጉባዔዎች እንደሚደረገው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በዋናነት በ10ኛው ጉባዔ መግባባት የተደረሰባቸውን አቅጣጫዎች አፈጻጸምን በተመለከተ የበላይ አመራሩ ግምገማ ለጉባዔ ተሳታፊ አባላት የሚቀርብበት፣ ከዚያም በመነሳት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ የሚያስቀምጥበት ይሆናል፡፡ ጉባዔተኛው ከበላይ አመራሩ የሚቀርብለትን መነሻ በመያዝ ባለፉት 27 ዓመታት እንደ ድርጅት ያካሄደውን ጉዞ በመገምገም፣ አገራችን የምትገኝበትን የትግል መድረክ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገራችንን ወደ አዲስ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫ ሊያሸጋግር እንደሚችል የታመነበት አቅጣጫ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መንገድ መሄድ ከተቻለ ጥሩ ነው፡፡

አንድ ጉዳይ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግ በተፈጸሙ ጥፋቶች ምክንያት፣ በሕዝብና በአገር ላይ ከባድ ፈተና አጋጥሟል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በተደጋጋሚ ለኢሕአዴግ ዕድሉን ሰጥቶታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሕዝብ ሲፈጸሙ የነበሩ ታሪካዊ ስህተቶች እንዲታረሙ ሕዝብ ዕድል መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይኼንን ታሪካዊ ዕድል በሰከነ ሁኔታ ልንጠቀምበት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ እንደሚታወቀው እሳቸው የድርጅቱንና የመንግሥትን አመራር ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከባድ ስህተቶችንና በደሎችን ለማረም በርካታ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የለውጡ ምዕራፍ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዜጎች ከእስር ተለቀዋል፡፡ በስደት ይኖሩ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤተ ተመልሰዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲከፈት የሚረዱ ተጨባጭ ዕርምጃዎች እየታዩ ነው፡፡ ቢያንስ ሕዝብና ድርጅቱን ሆድና ጀርባ ያደረጉ ድርጊቶች እየተቀረፉ መግባባት እየተፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ሕዝብ ከድርጅቱ የሚጠብቃቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በአባል ድርጅቶች መካከል በይፋና በህቡዕ የሚደረጉት የአይጥና የድመት ዓይነት ማድፈጦች ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ ከዚህ ጉባዔ ምላሽ ይጠበቃል፡፡ በነበረበት ሁኔታ መቀጠል አይቻልምና፡፡

የድርጅቱ ውስጠ ዴሞክራሲና አወቃቀር የራሱ ጉዳይ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ መንግሥትን የሚመራ በመሆኑ ግን በአመራር ጥራትና በሕዝባዊነት ላይ የሚታየው ድክመት አገርን እየጎዳ ነው፡፡ በተለይ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ደንታ የሌላቸውና የአመራር ክህሎት የጎደላቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ድርጅት፣ የተዓማኒነትና የቅቡልነት ጥያቄ ቢነሳበት አይገርምም፡፡ ስኬቴ ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ከመጠን በላይ ሲኩራራ የነበረ ድርጅት ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የፈጸሙ፣ በሌብነት በከፍተኛ ደረጃ የሚጠረጠሩ፣ ለአገር ደንታ የሌላቸው፣ ወዘተ አባላትና አመራሮች ይዞ የት ድረስ ይጓዛል? ኢሕአዴግ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ድርጅት ሆኖ መቀጠል የሚችለው፣ የዘመኑን ትውልድ የለውጥ ፍላጎት ለመምራት የሚያስችለው ቁመና ላይ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ በደመነፍስ ሳይሆን በአመርቂ ዕቅድ ላይ ካልተመሠረተ ዋጋ የለውም፡፡ ዕቅዱ ቢነደፍም ለውጤታማነቱ በፅናት መሥራት የሚችል አመራር ከሌለ ቢከፍቱት ተልባ ይሆናል፡፡ ለሕዝቡና ለአገሪቱ የሚጠቅም ነገር ይፈለጋል ሲባል፣ ጉባዔው በራሱ ፋይዳ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው፡፡ ፋይዳ እንዲኖረው ደግሞ ከሕዝብ ፍላጎት ተፃራሪ የሆኑ የምንቸገረኝ ወይም የማናለብኝ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት ሕዝብንና አገርን ዋጋ አስከፍለዋል፡፡

የኢሕአዴግ አባል ደርጅቶች ወደ ጉባዔው ሲገቡ ትከሻ ለትከሻ እየተላከኩ ወይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ እንደሚታየው በነገር እየተጠዛጠዙ ከሆነ፣ የሐሳብና የተግባር አንድነት ከቶውንም ሊኖር አይችልም፡፡ ሌላው ቢቀር መጪው አገራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ለውጡ በሰላምና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ካልቻሉ፣ እንኳን አገር የመምራት ኃላፊነት ለመወጣት የድርጅቱ ህልውናም አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ ተወደደም ተጠላ የተጀመረው ለውጥ በስኬት ተከናውኖ ወደ መጪው ምርጫ ማዝገም የሚቻለው፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግ ውስጣዊ ልዩነቶችን አቻችሎ ኃላፊነቱን ሲወጣ ነው፡፡ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ባልሆነበት፣ ሞትና መፈናቀል እየተለመዱ በመጣበት፣ ዴሞክራሲያዊ ባህል ባልተለመደበት፣ ዛሬም እንደ እባብ ካብ ለካብ መታያየት ባልተተወበት አገር ውስጥ መፈረካከስ ከተጀመረ ማቆሚያ የሌለው ቀውስ ይፈጠራል፡፡ ትናንት የሠራቸውን ኃጢያቶች ተናዞ አይደገመኝም ያለ ድርጅት፣ ትርምስ እንዳይፈጠር ጠንክሮ ቢሠራ ሕዝብና አገር ይጠቀማሉ፡፡ ካሁን በኋላ ወደኋላ ለመመለስ መሞከር ግን ኪሳራው ከባድ ነው፡፡ የኢሕአዴግን ነገር ስንነጋገርበት ተነግረው የማያልቁ ብዙ ችግሮች ስላሉ፣ ሰከን ብሎ ሕዝብና አገርን ማሰብ ይገባል!