ክቡር ሚኒስትር ከአንድ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ጋር ምሳ እየበሉ ነው
[ክቡር ሚኒስትሩ ተክዘው ቴሌቪዥን እያዩ ሚስታቸው ገቡ]
- ሰሞኑን ምን ሆነሃል? ትክክል አይደለህም፡፡
- አገር ላይ የሚሠራውን አታይም እንዴ?
- ምን ተሠራ?
- እኔ ለአገሬ የዋልኩትን ውለታ እንዴት ታይዋለሽ?
- አንተ መቼ ሕይወት ነበረህ? ሙሉ ሕይወትህን ለአገርህ አይደል እንዴ የሰጠኸው?
- ጎሽ ምን ላድርግሽ፡፡ አሁን እኔ መሰናበት ነበረብኝ?
- የምን ስንብት ነው?
- አንቺ ሚዲያ አትከታተይም እንዴ?
- እኔ እኮ ፊልም ነው የሚመቸኝ፡፡
- ታዲያ የአገሪቱ ፖለቲካ ፊልም ከሆነ ቆይቷል እኮ?
- ቢሆንም እኔ የውጭ እንጂ የአገር ውስጥ ፊልም አይመቸኝም፡፡
- አንቺማ ደልቶሻል፡፡
- ምንድነው የሆንከው?
- ይኸው ሕይወቴን የሰዋሁለት ፓርቲ አንቅሮ ተፋኝ፡፡
- ለምን?
- ስሚ ልጅነቴን ብትይ ወጣትነቴን፣ ከዚያም ሲልቅ ጎልማሳነቴንና የሽምግልና ዘመኔን የሰጠሁት ፓርቲ ዝም ብሎ ይሸኘኛል?
- ከሸኙህማ ለአንተም ግልግል ነው፡፡
- ፖለቲካ እኮ ሱስ ነው፡፡
- የምን ሱስ ነው?
- ሴትዮ ፖለቲካ ለእኛ ሁሉ ነገራችን ነው፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- የእኛ ቢዝነስ እኮ ከፖለቲካው ጋር የተጣመረ ነው፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ቢዝነስ ውስጥ የገባነው እኮ ፖለቲካውን በመቆጣጠራችን ነው፡፡
- አሁንም ግን ቢዝነሳችን ጥሩ እየሠራ ነው፡፡
- በዚያ ላይ አሁን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ተሰበሰበ ሲባል እንኳን ከሕዝቡ እኩል ልስማ?
- ምን ችግር አለው ጓደኞችህ አይደሉ ቀድመው ይነግሩሃል፡፡
- አሁን የገባው ኃይል እኮ እኛን ነባሮቹን ማየት ያንገሸግሸዋል፡፡
- እና ከጨዋታ ውጪ ሆኛለሁ ነው የምትለኝ?
- ነገርኩሽ እኮ ሳስበው ራሱ ይጨንቀኛል፡፡
- በቃ ጠቅልለህ ቢዝነሱን ማሯሯጥ ነው የሚሻለው፡፡
- የቢዝነሱ ጨዋታስ መቼ ገባሽ?
- እንዴት ማለት?
- ቢዝነስ እኮ ያለ ፖለቲካ አይሠራም፡፡
- ምን አገናኛቸው?
- ረሳሽው እንዴት ስንት የመንግሥት ሥራ ያለ ጨረታ እንደምንሠራ?
- አሁን ተወዳድረን እንሠራለና?
- ተወዳድረንማ ማሸነፍ ብንችልማ በፊትም እንወዳደር ነበር፡፡
- ምን እያልከኝ ነው ታዲያ?
- ከፖለቲካው ከወጣሁ ከቢዝነሱም እንደምወጣ አትጠራጠሪ፡፡
- ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያስጠላው፡፡
- ስለዚህ ቢዝነሳችንም ያልቅለታል ማለት ነው፡፡
- ታዲያ ምን ተሻለ?
- ወደ ፖለቲካው በአገኘሁት መንገድ መመለስ አለብኝ፡፡
- ይኸው አንቅረው ተፉኝ እያልክ አይደለ እንዴ?
- እሱማ ልክ ነሽ ግን ሌላ መንገድ መፈለግ ነዋ፡፡
- ሌላ ምን ዓይነት መንገድ?
- እኔማ አንድ ነገር እያሰብኩ ነበር፡፡
- ምን?
- ባቋቁም ምን ይመስልሻል?
- ምንድነው የምታቋቁመው?
- አዲስ ፓርቲ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር አንድ ሆቴል ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ምንድነው ደብሮሃል?
- እንዴት አይደብረኝ?
- ምን ሆንክ?
- እንደ ዕቃ ተጠቅመው ሲጥልዎት እያየሁ እንዴት አይደብረኝ?
- እስኪ አታስታውሰኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ በጣም እየተጨነቅኩ ነው፡፡
- ምንድነው ያስጨነቀህ?
- ቢዝነሶቻችንን ሳስባቸው ዝም ብዬ በቀን ራሱ መቃዠት ጀምሬያለሁ፡፡
- ምንድነው የሚያስቃዥህ?
- ቢዝነሶቻችንን በእርስዎ ተገን ነበር የሚንቀሳቀሱት እኮ?
- አውቃለሁ ግን ችግር የለውም፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- በሩን ሲዘጉብን ሌላ በር ሠርተን መግባት ነዋ፡፡
- አልገባኝም?
- አዲስ ፓርቲ እናቋቁማለን፡፡
- እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሰውዬ በዚህ ጊዜ ቀልድ አይቀለድም፡፡
- ታዲያ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋሙ እንደ ቢዝነሱ ቀላል ይሆናል ብለው ያስባሉ?
- እንዲያውም እኛ ያልነካነው ቢዝነስ እሱ ነው፡፡
- እንዴት?
- ምንም ፖለቲካ የማያውቁት አይደሉ እንዴ ፓርቲ እያቋቋሙ ቢዝነስ ሲሠሩ የነበሩት?
- እሱስ እውነትዎን ነው፡፡
- አየህ እንደ እኛ ዓይነቱ በፖለቲካ ምራቁን ዋጥ ያደረገ ሲይዘው ቢዝነሱ እንዴት አሪፍ ሊሆን እንደሚችል አስበው፡፡
- እኔማ ግራ ገብቶኝ ነው፡፡
- ምኑ ነው ግራ የገባህ?
- እንዴት ነው ፓርቲ የምናቋቁመው?
- ስማ እኔ እኮ ከልጅነቴ ጀምሮ ያደግኩበትና ጥርሴን የነቀልኩበት ቢዝነስ ነው፡፡
- ያው ያኔ እኮ በትጥቅ ትግል ነው እናንተ ፖለቲካውን የተቀላቀላችሁት፡፡
- እሱማ ያለፈበት ፋሽን ነው ሲባል አልሰማህም?
- ክቡር ሚኒስትር አሁን እኮ የሐሳብ የበላይነት ያለው ፖለቲካ ነው ማሸነፍ የሚችለው?
- ለእሱስ ቢሆን መቼ እናንሳለን?
- ያው ፋሽን አልፎብዎታል ብለው እኮ ነው ያሰናበትዎት ብዬ ነው፡፡
- ስማ አዲስ ስትራቴጂ ይዘን ነው ጠንካራ ፓርቲ የምንመሠርተው፡፡
- ምን ዓይነት ስትራቴጂ?
- መቼም በርካታ ሰዎች ይህን ለውጥ እንደማይደግፉት ታውቃለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ሰው ሁሉ ተደምረናል እያለ እኮ ነው?
- እንዳይመስልህ በርካታዎቹ የተደመሩት አማራጭ ስለሌላቸው በግዴታ ነው፡፡
- እንደዚያ ነው ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ነገርኩህ እኮ በተለይ አብዛኛው የቢዝነስ ሰው ጥቅሙ በአንድም በሌላም ስለሚነካበት ለውጡን አይደግፈውም፡፡
- ግን ሁሉም ተደምሬያለሁ ነው የሚለው፡፡
- እነዚህን ሰዎች እኮ እኛው ሀብታም ያደረግናቸው ስለሆነ አሁን ውለታቸውን መመለስ አለባቸው፡፡
- እንዴት አድርገው?
- በቃ ባላቸው ሀብት እኛን በመደገፍ ጠንካራ ፓርቲ እንድናቋቁም ያደርጉናል፡፡
- የእኔ ሥራ ታዲያ ምንድነው?
- እነዚህን ሰዎች ታሰባስባለህ፡፡
- እነ ማንን?
- ያኮረፉትን ነጋዴዎች!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጡረታ ከወጣ ሌላ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- የደበርዎት ይመስላል ክቡር ሚኒስትር?
- እንዴት አይደብረኝ?
- ምነው?
- እኛ ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለን ይህችን አገር 11 በመቶ አሳድገን፣ ዓለም ሁሉ ካስጨበጨብን በኋላ ዝም ብለው ሲያሰናብቱን እንዴት አይደብረኝ?
- ኧረ በዚሁ ይለፍልን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ?
- ክቡር ሚኒስትር መቼም በሥልጣናችን ዘመን ያልፈጸምነው ሙስና እንደሌለ ያውቃሉ፡፡
- ስማ የፈለገ ቢሆን አገራችንን እኮ በዓለም መድረክ ያስወደስን መሆኑን አትርሳ፡፡
- ቢሆንም አለመታሰራችን በራሱ ጥሩ ነው፡፡
- አሁንም ለራስህ ካልታገልክ በኋላ መቼ ይቀርልሃል?
- የሰሙት ነገር አለ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል ሲባል አልሰማህም?
- እሱስ እውነትዎትን ነው፡፡
- ስለዚህ ተደራጅተን በመታገል መብታችንን ማስከበር አለብን፡፡
- የምን ትግል ነው?
- ደርግን የሚያህል ኃይል ታግለን ማሸነፋችንን አትርሳ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ደርግን እኮ ያሸነፍነው እኛ ሳንሆን ሕዝቡ ነው፡፡
- እኛ ግን ሁሌም እኛ ነን ያሸነፍነው እያልን ነው የምናወራው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ልብዎ ግን አሁንም ትልቅ ነው፡፡
- ማለት?
- አሁን በዚህ ዕድሜያችን ጫካ ገብተን ታግለን እናሸንፋለን ብለው ነው?
- እሱማ ፋሽኑ ያለፈበት አካሄድ ነው፡፡
- ታዲያ እንዴት ነው የምንታገለው?
- አሁን ትግላችን ፋሽኑን የተከተለ መሆን አለበት፡፡
- ፋሽኑ ምንድነው?
- የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ነዋ፡፡
- ለቀቁ ልበል ክቡር ሚኒስትር?
- ከሥልጣን እንዳስለቀቁኝማ ታውቃለህ አይደል እንዴ?
- ኧረ እኔ በአዕምሮ ለቀቁ ወይ ነው ያልኩት?
- ምን እያልክ ነው?
- እንዴት ብለን ነው አዲስ ፓርቲ የምናቋቁመው?
- ከዚያ ውጪ የምናሸንፍበት መንገድ የለም፡፡
- ለመሆኑ ምን ዓይነት ፓርቲ ነው የምናቋቁመው?
- የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሴቶችን በማስጠበቅ የኒዮሊብራል አስተሳሰብን ድባቅ የሚመታ ፓርቲ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የአገሪቱ ሕዝብ ከ70 በመቶ በላይ ወጣት ከመሆኑ ባሻገር፣ ይህን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና እንደማይቀበለው መቼም ለእርስዎ አላስረዳዎትም፡፡
- የእኛ አባላት የተለቀሙና የተነጠሩት እንጂ ወጣቶቹ አይደሉም፡፡
- ወጣቱን ሳንይዝ የምን ፓርቲ ነው?
- ነገርኩህ እኮ በአመራር ብቃታቸው የሚታወቁና በአገሪቱ ፖለቲካ ምራቃቸውን የዋጡትን ነው የምንፈልገው፡፡
- እኮ እነማንን ልንይዝ?
- ነባሮቹን!
[ክቡር ሚኒስትር ከአንድ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ጋር ምሳ እየበሉ ነው]
- ዛሬ ለምን እንደፈለግኩህ ታውቃለህ?
- ለምን ነበር የፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰሞኑን እንደ እኔ በጡረታ ከተሰናበቱ ጓደኞቼ ጋር ተገናኝቼ ነበር፡፡
- በቀጣይ ምን ሊሠሩ አሰቡ?
- በእሱ ጉዳይ ላይ እንድንመካከር አይደል እንዴ የጠራሁህ?
- እኔ እኮ በእናንተ መልቀቅ ቅር ብሎኛል፡፡ በቀጣይ ለእኛም አስቸጋሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡
- ምኑ ነው የሚያስቸግራችሁ?
- ከእናንተ ጋር ስንሠራ እኮ ትዕዛዝ እንቀበላችኋለን ከዚያ እሱን ማስፈጸም ነበር፡፡ አሁን ግን ዴሞክራሲ እየተባለ ከማን ጋር ልንሠራ ነው? ስለዚህ በጣም ያስፈራኛል፡፡
- ምኑ ነው የሚያስፈራህ?
- ነገ የእናንተ ዕጣ እኛም ጋ ይመጣል፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ያው በቀጣይ የእኛም ተቋም ሪፎርም መደረግ አለበት ተብሎ እኛም መሰናበታችን ይቀራል?
- ስለዚህ በጊዜ መጠቃቀም ይኖርብናል፡፡
- ምን አስበው ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ለእኔ እኮ ፖለቲካ ሕይወቴ ነው፡፡ ከልጅነት እስካሁን ድረስ ከፖለቲካ ውጪ ምን አውቃለሁ?
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎስ በደህና ጊዜ ቢዝነሷንም ተቀላጥፈዋታል፡፡
- ያለ ፖለቲካው ቢዝነሱ የለም፡፡
- ታዲያ ምን አሰቡ?
- አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ላቋቁም እያሰብኩ ነው፡፡
- የምን ፓርቲ ነው?
- አገሪቱ እኮ በቋፍ ላይ ነው ያለችው፡፡
- እሱስ እውነትዎትን ነው፡፡
- ስለዚህ እንደኛ ዓይነቱ በሳል አመራር ፖለቲካውን ሊመራው ይገባል፡፡
- ምን ዓይነት ፍልስፍና ያለው ፓርቲ ሊያቋቁሙ ነው?
- አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚያራምድ ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ፓርቲዎች ሁሉ ከዚህ ፍልስፍና እየወጡ ዴሞክራሲ እናራምዳለን በማለት ስያሜያቸውን እየቀሩ እኮ ነው፡፡
- እኛም ስያሜያችን ውስጥ ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል መጠቀም እንችላለን፡፡
- ለመሆኑ የፓርቲው ስያሜ ምንድነው የሚለው?
- ቀ.ሥ.ና.ዴ.ፓ!
- ምን ማት ነው?
- የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ!