Skip to main content
x
የኢታብ ኩባንያ ባለቤት ሞተው ተገኙ
ነፍስ ሔር አቶ እስክንድር ተስፋዬ

የኢታብ ኩባንያ ባለቤት ሞተው ተገኙ

በደቡብ ክልል በሐዋሳ ከተማ የሚገኘው ኢታብ ሳሙና ፋብሪካ ባለቤት አቶ እስክንድር ተስፋዬ፣ ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት በመኖሪያ ቤታቸው ሞተው ተገኙ፡፡

አቶ እስክንድር ምንም ዓይነት የጤና ችግር እንዳልገጠማቸውና መደበኛ ሥራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበር፣ አንድ የሥራ ባልደረባቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የ40 ዓመት ጎልማሳ የነበሩት አቶ እስክንድር ሐዋሳ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ባልታወቀ ምክንያት ሕይወታቸው አልፎ መገኘቱን ባልደረባቸው ገልጸዋል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ የሟችን አስከሬን ለምርመራ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ጳውሎስ ሆስፒታል እንደላከ ታውቋል፡፡

አቶ እስክንድር ታዋቂ የሆነው ኢታብ ሳሙና ፋብሪካን በ1993 ዓ.ም. መመሥረታቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ ሠራተኞች በማስተዳደር ላይ እንደነበሩ ባልደረባቸው ተናግረዋል፡፡

 የደቡብ ክልላዊ መንግሥት ገቢዎች ቢሮ የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ ታማኝና ቀዳሚ ግብር ከፋይ በማለት ላለፉት አምስት ዓመታት በተከታታይ ለአቶ እስክንድር ሽልማት ማበርከቱን የገለጹት የሥራ ባልደረባቸው፣ አቶ እስክንድር በሐዋሳና በአካባቢዋ በሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ሥራ እንደሚታወቁ ጠቁመዋል፡፡