Skip to main content
x
የቅዱስ ላሊበላ የታደጉን ድምፆች
መንግሥት ለላሊበላ ቅርሶች ትኩረት እንዲሰጥ በከተማዋ የተደረገው ሰላማዊ ሠልፍ

የቅዱስ ላሊበላ የታደጉን ድምፆች

‹‹ታሪክና ቅርስ እየፈረሰ አዲስ ታሪክ አይሠራም፣ ቅርሳችን ሲፈርስ እያየን ዝም አንልም፣ ላሊበላን መታደግ ኢትዮጵያን መታደግ ነው. . .›› እነዚህንና መሰል ኃይለ ቃሎችን በሰሌዳ ይዘው በላሊበላ ከተማ ሠልፍ የወጡ ያስተጋቡት ድምፅ ነው፡፡

ከአሥራ አንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በአራቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ተብሎ የተደረገው ጊዜያዊ የብረት መጠለያ ከአምስት ዓመት በላይ በመቆየቱ ለቅርሱ ሥጋት መደቀኑን ተከትሎ ነው ኅብረተሰቡ ሠልፍ የወጣው፡፡ ግዙፍ ብረቶችን የተሸከሙት ምሰሶዎች ቦታቸውን እየለቀቁ በመሆኑ በቅርሱ አናት ላይ የተላለፉት ከባድ ብረቶች በነፋስ ኃይል ተገፍተው ቢወድቁ ቅርሱን ይጎዱታል በሚል ሕዝቡ ሥጋት ላይ እንዲወድቅ ያደረገው፡፡

እሑድ መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በላሊበላ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ ከከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ ከአጎራባች ወረዳዎች ከቡግና፣ ከብልብላ፣ ከሰቆጣና ከሌሎች አካባቢዎች ከ47 ሺሕ በላይ ሠልፈኞች መውጣታቸውን የሠልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምስጋን አዱኛው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አሳሳቢ የሆነው የላሊበላ ቅርስን ለመታደግ እንዲቻል ለሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል ተቋማት አቤቱታ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑንም ሰብሳቢው ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

በመንግሥቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮና የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ በ2000 ዓ.ም. የተሠሩት መጠለያዎች ለአምስት ዓመታት ብቻ እንዲቆዩ ቢታሰብም ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት መቆየታቸውና መጠለያዎቹን የደገፉት የብረት ምሰሶዎች መሬቱን እየሰነጣጠቁ በመሆኑ እንዲነሱ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በየካቲት 2010 ዓ.ም. መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ጥላው እንዲነሳ መወሰኑን ለአስፈላጊ ጥገናም 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ሚኒስቴሩ ይፋ ቢያደርግ የብረት ጥላዎቹን የማንሳት ሥራ መቼ እንደሚጀመር አልተገለጸም ነበር፡፡

በወቅቱ እንደተገለጸው፣ በላሊበላ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ቅርሶች መካከል እነ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ መርቆሪዎስ በዕድሜ ብዛት በደረሰባቸው ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት እየተፈረካከሱ ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ቅርሱን ለመጠገን የተወሰዱ ዕርምጃዎች አንፃራዊ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ወደተባባሰ ችግር እያመሩ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡

ዓምና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ለአደጋ የተጋለጡ ቅርሶችን በዘላቂነት ለመታደግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው። አገራዊ ቅርሶችን በዘላቂነት ለመጠገን የሚያስችል ‹‹የቅርስ ፈንድ›› የተሰኘ የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ኃላፊነት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ወስዶ እየሠራ ነው። ማዕቀፉ በዋናነት ለቅርስ ጥገና የሚሆን ፋይናንስ ማሰባሰበን ያለመ እንደሆነም ተመልክቷል።

የቅርስ ጥገና በርካታ መዋለ ንዋይ በመጠየቁ ከመንግሥት በተጨማሪ ሌሎችም እንዲሳተፉበት እንደሚደረግ፣  በቀጣይም አደጋ ላይ ያሉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በሙሉ ለመጠገን የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የሚሠራ አገራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋምም የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር  ማሳወቁ ይታወሳል።  

የቅዱስ ላሊበላ ገጽታ

‹‹. . .የምገልጽበት ቋንቋ የለኝም፡፡ የዚህን ክቡር ሰው፣ ከሁሉም መሬታውያን በጥበብም ሆነ በሥነ ጽድቅ የከበረ ላሊበላ ከአንድ ደንጊያ፣ ከአንድ አለት ፈልፍሎ አሥር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀው ዐቢይ ሥራ የምገልጽበት ልሳን የለኝም::›› ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በዛጒዬ ሥርወ መንግሥት ዘመን በላስታ ላሊበላ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያከናወናቸው የቅዱስ ላሊበላን ገድል በኋላ ዘመን ላይ የጻፈው ደራሲ ውሳጣዊ ስሜቱን የገለጸበት ነበር፡፡

የነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሥራ አስደናቂነት ለመግለጽ ቃል እንዳነሰው እነዚህ ላሊበላ ባንድ ቋጥኝ ያሠራቸው፣ ሰሎሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበጥልም አመስጥሯል፡፡ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን ጭምርም በመግለጽ ሰው ሁሉ እየመጣ ባይኑ እያየ ሊያደንቃቸው የሚገባ መሆኑንም ‹‹በላሊበላ እጅ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ግብረ ሕንፃዎችን ለማየት የሚፈቅድ ይምጣና በዓይኖቹ ይይ (ይምጻእ ወይርአይ በአዕይንቲሁ) ነበር፤›› ያለው፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ኑቢያ አክሱም ዛጒዬ›› በሚባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የቅዱስ ላሊበላን ገድል የጻፈው ጸሐፊ ምንም ያህል የተሳሳተው ነገር የለም፡፡ የነዚህን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ የተመለከቱ የውጭ አገር ሰዎች እሥፍራው ድረስ እየመጡ ባይናቸው እያዩ ተደንቀዋል፡፡ ከተመለከቱትም ውስጥ ይኼን የመሰለ በቋጥኝ ውስጥ እየተፈለፈለ የተሠራ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዓለም አለመኖሩን የገለጹም ብዙ ናቸው፡፡

‹‹አዲሲቱ ኢየሩሳሌም›› የሚል ተቀጽላ ያገኙት የመካከለኛው ዘመን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዐረፍተ ዘመኑ ካገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የብዙዎች ጎብኚዎችን፣ ተሳላሚ ምዕመናን ቀልብ መያዝ ችለዋል፡፡ በዚህም ሳይገደብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት- ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገብ መሥፈር ችለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ አስደናቂ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ገናና የሆኑት ካንድ አለት ተፈልፍለው የታነፁት ናቸው፡፡ የአገሪቱ የክርስትና መነሻ መዲና ከሆነችው አክሱም ደቡባዊ አቅጣጫ በተለያዩ መንገዶች 240 ኪሎ ሜትር እስከ 394 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቅዱስ ላሊበላ ከተማ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ትውፊትን በግሩም ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በጉያዋ የያዘችው ላሊበላ በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በየወቅቱ የሚዘልቁባት የሚሳለሙበት ሥፍራ ናት፡፡

በታሪክ እንደሚወሳው የከተማዋ የመጀመሪያ መጠሪያ ሮሃ ሲሆን 12ኛው ምዕት ዓመት የነገሠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ያነፀው እርሱ በመሆኑ ከተማዋ ስሙን አግኝታለች፡፡

11 አብያተ ክርስቲያናት በሦስት የተለያዩ ሥፍራዎች ሲገኙ፣ ስድስቱ በሰሜን አቅጣጫ፣ አራቱ በሊባ (ደቡባዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሆነው የሚገናኙበት መስመር አላቸው፡፡ 11ኛው ቤተ ክርስቲያን ቤተ ጊዮርጊስ ብቻውን ተነጥሎ ነው ያለው፡፡

በሰሜናዊ ክበብ የሚገኙ (1) ቤተ መድኃኔዓለም (2) ቤተ ማርያም  (3) ቤተ መስቀል (4) ቤተ ደናግል (5) ቤተ ሚካኤል (6) ቤተ ጎልጎታ ሲሆኑ፤ በሊባ በኩል (7) ቤተ አማኑኤል (8) ቤተ አባ ሊባኖስ (9) ቤተ መርቆርዮስ (10) ቤተ ገብርኤልና ቤተ ሩፋኤል ይገኛሉ፡፡ በምዕራባዊ አቅጣጫ ለብቻው ያለው ከላይ ወደታች ተፈልፍሎ የታነፀው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፡፡