Skip to main content
x
ረሃብን በ2030 ዜሮ ለማድረግ

ረሃብን በ2030 ዜሮ ለማድረግ

ረሃብን በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ2030 ለማጥፋት አገሮች፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት መረባረብ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም በየአገሮች መሻሻሎች እየታዩ፣ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ፣ ረሃብን የማጥፋት ዘመቻው እየጎለበተና ረሃብ እየቀነሰ መጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ረሃብ መልሶ እያገረሸ ነው፡፡ ረሃብን በ2030 የማጥፋት ዓለም አቀፍ ዕቅዱን ‹‹ዜሮ ሃንገር ወርልድ በ2030›› ለማሳካትም ሥጋት ሆኗል፡፡ ሆኖም መንግሥትና በዘርፉ የሚሠሩ አካላት ችግሩን ለመፍታት እየተረባረቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ የዓለም የምግብ ቀን በየዓመቱ ሲከበርም ረሃብን ዜሮ የማድረግ አጀንዳ ይነሳል፡፡ ትናንት ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ38ኛ ጊዜ የዓለም የምግብ ቀን ተከብሯል፡፡ ቀኑ በኦሮሚያ ምሥራቅ ሸዋ ዞን በሎሜ ወረዳ በሎሜ አዳማ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየንና በአባል አርሶ አዳሮች የተሠሩ ምርጥ ዘር ማባዣና የኢንዱስትሪ ግብዓት የሆኑ ሰብሎች ልማት ቦታዎች ላይ የመስክ ጉብኝት በማድረግ የተከበረ ሲሆን፣ ከበዓሉ አስቀድሞ ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ደግሞ በዓለም አቀፍ የምግብ ቀን በዓል አከባበር ዙሪያ በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ድርጅት በኢትዮጵያ ተወካይ ፋቱማ ሰኢድ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና ተወካይ ስቲቭ ዌር ኦማሞ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ መግለጫውን የተከታተለችው ምሕረት ሞገስ እንደሚከተለው አቀናብራዋለች፡፡  

ጥያቄ፡- ረሃብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ የነበረ ቢሆንም መልሶ አገርሽቷል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

ፋቱማ ሰኢድ፡- ረሃብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ከ815 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እጥረት አለባቸው፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥን ተከትለው የሚከሰቱ ችግሮች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ፣ የእኩልነት አለመኖርና ተያያዥ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህም ረሃብን በ2030 ለማጥፋት ማለትም ‹‹ዜሮ ሃንገር በ2030›› የሚለውን የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት አጀንዳ ለማሳካት ታይቶ የነበረውን ተስፋ ተገዳድረውታል፡፡

ጥያቄ፡- ችግሩን ለመቅረፍ የአገሮች ሚና ምን ሊሆን ይገባል?

ፋቱማ ሰኢድ፡- ረሃብን የማጥፋት ሥራው ጫና ተፈጥሮበታል፡፡ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ረሃብ ለተወሰነ ዓመታት መቀነስን አሳይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን አገርሽቷል፡፡ ሥር የሰደደ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ ይህም ለዓመታት ቀንሶ የነበረውን የረሃብተኛ ቁጥር እንዲያንሰራራ አድርጎታል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ልምድ እንደሚያሳየው የምግብ ዋስትናንና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ማሻሻል የተቻለው አገሮች በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትና ሕዝቡ ተባብረው በመስራታቸው ነው፡፡ የዓለም መንግሥታት የተስማሙበትን ‹‹ዜሮ ሃንገር በ2030›› ዓላማንና ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት አኅጉሮች፣ አገሮች አጋር ድርጅቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው፡፡ ረሃብን በ2030 ማጥፋት ይቻላል፡፡ በዓለማችን 80 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር የሚኖርና እርሻን በዋነኛነት የኑሮ መሠረትና የገቢ ምንጭ ያደረገ ነው፡፡ ግብርናን ማዘመን ዋናው ረሃብን የማጥፋት ዘመቻ ትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ መንግሥት ባለሀብቶች በግብርናው ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታታትና አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች የማኅበራዊ ዋስትና መርሀ ግብሮችን ማሳደግና የአምራች ገበሬዎችን ምርቶች ከከተማ የገበያ ዕድሎች ጋር ማስተሳሰር ይጠበቅበታል፡፡ አነስተኛ አምራች ገበሬዎች አዳዲስና ዘላቂ የአመራረት ዘዴዎችን በመቀበል ምርታማነትንና ገቢያቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ የእነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጋላጭነት በመቀነስ አዳዲስ የአመራረት ዘዴዎችንና አስተማማኝ የሆኑ የሥራ ዕድል ፈጣሪዎችን ማስተዋወቅ ስኬታማነትን ያረጋግጣል፡፡ የግሉ ዘርፍ ረሃብን በማጥፋት ጥረት ውስጥ የራሱን የጎላ ሚና መጫወት ይችላል፡፡ ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት አስተዋጽኦ በማድረግ፣ የምግብ ብክነትን በመቀነስ፣ ዕውቀትና አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማመንጨትና በማካፈል፣ አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የብድርና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ የምግብ አቅርቦት ጥራትና ደኅንነት በማሻሻል ረሃብን ማጥፋት እንደሚቻል በማስተማር የራሳቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ብቻ በቂ አይደሉም፡፡ በተለይ በእርስ በርስ ግጭትና ስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ኅብረተሰቦች ‹‹ረሃብን እናጥፋ ዘመቻ›› ከዚህም የዘለለ ራዕይ ይዞ የተነሳ ሲሆን በዘላቂነት ሁሉም የሰው ልጆች ሰላማዊ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ነው፡፡ ‹‹ረሃብን እናጥፋ ዘመቻ›› ለየትኛውም የዓለማችን ክፍል፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጤናማና የተመጣጠነ ምግብ እንዲዳረስ በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡ 

ስቲቭ ዌር ኦማሞ፡- ማንኛውም አገር ብቻውን ሠርቶ ረሃብን ዜሮ ማድረግ አይችልም፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከአጋሮቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በረሃብ አደጋ ውስጥ ሆነው አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚፈልጉ ተመጣጣኝ ምግብ እያቀረብን ነው፡፡ በዚህም ረሃብን ዜሮ የማድረጉን ዕቅድ ከምኞት ባለፈ ዕውን ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡  

ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ያለው የረሃብ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ስቲቭ ዌር ኦማሞ፡- ኢትዮጵያ ከዘላቂ ልማት ግቡ ጋር የተቀናጁ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን አስቀምጣለች፡፡ በኢትዮጵያ ቅንጨራ (የዕድሜና የዕድገት አለመመጣጠን) እ.ኤ.አ. በ2000 ከነበረው 60 በመቶ በ2016 ወደ 38 በመቶ ቀንሷል፡፡ ይህ ውጤት ሕፃናት በ2030 የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደምትችል ማሳያ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ‹‹ዜሮ ሃንገር በ2030›› ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል?

ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፡- አዎ ይቻላል፡፡ የሚቻለው ግን በመሥራት እንጂ በማለም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የአመጋገብ አብዮት ያስፈልገናል፡፡ በኢትዮጵያ የምግብና የሰብል ብዝኃነት ቢኖርም ማኅበረሰቡ በተወሰኑ ምግቦች ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ይህ መለወጥ አለበት፡፡ በመንግሥት በኩል ከሕዝባችንና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሥራት፣ ግብርናውንና የእንስሳት ሀብት ዘርፉን በማዘመን፣ ምርታማነትን በመጨመርና ተወዳዳሪነታችንን በማጠናከር በ2030 ረሃብን ዜሮ ለማድረግ የተቀመጠውን ዕቅድ እናሳካለን፡፡  

ጥያቄ፡- እያሽቆለቆለ የነበረው ረሃብ ዳግም ጨምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው መጠን ምን ይመስላል?

ፋቱማ ሰኢድ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለማገርሸቱ መረጃ ወጥቷል፡፡ አገሮችም መረጃ እየሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ግን ለጊዜው የለንም፡፡ መረጃውን ከመንግሥት ጠይቀን ምላሹን እየተጠባበቅን ነው፡፡  

ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ድህነት ለማስወገድ በሚደረገው እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ የአገራችን ብሎም የዓለም ፈታኝና ዋነኛ ችግር የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት የአየር ፀባይ ለውጥ በተከታታይ መከሰት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እየተደረገ ባለው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ የአየር ፀባይ ለውጡ በተለይ በደሃ አገሮች የተፈጥሮ አደጋን በማባባስ፣ የመሬት መራቆትን፣ የውኃ እጥረት እያስከተለ የሚገኝ ችግር ነው፡፡ ይህም በዝናብ ጥገኝነት ላይ ለተመሠረተ ግብርና ልማት ፈታኝ ሁኔታ ነው፡፡ በአገራችን ስናየውም በተከታታይ በተከሰተው ድርቅና ጎርፍ አደጋ፣ እንዲሁም የመሬት መደህየትና መራቆት የምግብ እጥረትን አባብሶታል፡፡ ለአብነት በርካቶችን ለድርቅና ለረሃብ የዳረገውን ያለፉት ሦስት ዓመታት የኢሊኒኖን ክስተት ማንሳት ይቻላል፡፡ ሆኖም ላለፉት 15 ዓመታት የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት ስትራቴጂ አቅጣጫና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመከተል መላው ሕዝባችንን በማሳተፍ የሠራነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተራቆቱ አካባቢዎች የዕፅዋት ሽፋን እንዲጨምርና የጎርፍ ውኃ በአፈር ውስጥ እንዲቆይ በማድረግ ርጥበት የመያዝ አቅም በመጨመሩ የመሬት ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውኃ ለመስኖ ልማት የማዋል አቅማችንን ያሳደገ በመሆኑ በመጀመርያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕድቅ መጀመርያ ላይ ከ853 ሺሕ ሔክታር የማይበልጥ የነበረ የአነስተኛ አርሶ አደሮች በመስኖ የማልማት አቅምን ዛሬ ላይ ከ2.5 (2,579,800) ሚሊዮን ሔክታር በላይ ማድረስ አስችሎናል፡፡

በዚህም ከስድስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረግ የቻለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህም የመቋቋም አቅማችንን በማሳደጉ ኢሊኖ የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ሳያደርስ እንድንቋቋምና እንድናልፍ አስችሎናል፡፡ በዚህም በድርቅ ዓታትም ቢሆን የግብርና ምርትና ምርታማነት እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የተቻለበት ሁኔታ አለ፡፡ በቀጥታ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የምግብ ክፍተት ለመሙላት 7.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲታቀፉ በማድረግ የቤተሰባቸውንና የማኅበረሰቡን ጥሪት የሚገነቡ የልማት ሥራዎች እንዲረዱ በማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ እየሰራን እንገኛለን፡፡

ጥያቄ፡- ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመቋቋም የአረንጓዴ የዕድገት መንገድን በመከተል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ ነው?

ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፡- የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ በማጠናከር የዕፅዋት ሽፋን እንዲጨምር በማድረግ የመሬት ምርታማነት መጨመር፣ የሰልብ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትናንሽ፣ መካከለኛና ትላልቅ የመስኖ ልማት አውታሮችን ማስፋፋት ደንን በመመንጠር ይገኝ የነበረውን የእርሻ ማስፋትን በማስቀረት የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም በማሳደግ በተሻሻለ የግብርና ተረፈ ምርት የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲስፋፋ፣ የአፈር ለምነትና ጤንነት እንዲሻሻል የሰብል ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር፣ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት፣ ናይትሮጂን የሚቆጥቡና ከፍተኛ ምርት ሰጪና ድርቅን የሚቋቋሙ የሰብል ዝርያዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ከግብርና የሚመነጩ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን የሚቀንሱ ቴከኖሎጂዎችን በእርሻ ሥራዎች እንዲካተቱ እየሰራን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የቤት እንስስሳትን ምርትና ምርታማነትን በመጨመርና የአርሶ አደሮችንና የአርብቶ አደሮችን ገቢ በመጨመሩና የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን በመቀነስስ?

ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር)፡- የቤት እንስሳትን ጤና በመጠበቅ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በማሻሻልና ቶሎ በመሸጥ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማፋጠንና የእሴታቸውን ሙሉ ሰንሰለት አትራፊ ማድረግ፣ የአርብቶ አደር የግጦሽ መሬት ላይ እንክብካቤ በማድረግ የዕፅዋት ዓይነትና ሽፋን በማሳደግ ምርታማነቱንና ካርቦንን ከከባቢ አየር የማግለል አቅሙን የማሳደግ ሥራ በመሥራት የአየር ፀባይ ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ እየተራ ነው፡፡