Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዳያስፖራ ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዳያስፖራ ጋር እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቁርስ እየበሉ እያወሩ ነው]

 • ቶሎ ቶሎ ብዪ እንጂ?
 • ሰሞኑን ምግብ አልበላ ብሎኛል፡፡
 • ምን ሆንሽ?
 • ጊዜው የምን መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
 • የፍቅርና የመደመር ጊዜ ነዋ፡፡
 • ለእኛ ግን የፀብና የመቀነስ ጊዜ ነው፡፡
 • ምን እያልሽ ነው?
 • የግብር ጊዜ መሆኑን ረሳኸው እንዴ?
 • ደረሰ አይደል?
 • ስማ ይኼን ጊዜ ተጠንቅቀን ካላለፍን እኮ እንዳልኩህ የምንቀነስበት ጊዜ ነው፡፡
 • ማን ነው የሚቀንሰን?
 • ግብራችንን በአግባቡ ካልከፈልን ልንቀነስ እንችላለን፡፡
 • ታዲያ እንዴት እየሆነልሽ ነው?
 • ይኸው ቀን ተሌት ደፋ ቀና ብዬ ነገሮችን እያስተካከልኩ ነው፡፡
 • እኛ እኮ ደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች ስለሆንን መጠንቀቅ አለብን፡፡
 • እንግዲህ በተሰማራንባቸው ዘርፎች ያሉት ድርጅቶቻችን ግብራቸውን እንዲከፍሉ እያስደረኩ ነው፡፡
 • ስለዚህ የተሰማራንባቸው ሁሉም ዘርፎች አዋጪ ናቸው ማለት ነው?
 • በማኑፋክቸሪንግ፣ በሰርቪሱና በሪል ስቴቱ አሁንም ጥሩ እየሠራን ነው፡፡
 • ሁሉም ነገር አስተማማኝ ነው ልበል?
 • እኔማ እንደፈራሁት አይደለም፣ ምክንያቱም ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱ ካሳለፈችው ችግር አንፃር እኛም ችግር ውስጥ መሆን ነበረብን፡፡
 • ይኼ እኮ አስደሳች ዜና ነው፡፡
 • የሚገርምህ ለሪል ስቴት የሰጡንን ቦታ አልገነባችሁበትም ብለው ሊነጥቁን ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ግን እንደ ምንም ብዬ አስጥዬዋለሁ፡፡
 • አንቺ እኮ ጀግና ነሽ፡፡
 • ብቻ ከተሰማራንባቸው በአንደኛው ዘርፍ ጥሩ አልሠራንም፡፡
 • በየትኛው ዘርፍ?
 • ባለፈው ትንሽ ደከም ብለንበታል ያልኩህ ዘርፍ ነዋ፡፡
 • እስኪ አስታውሽኝ የቱ ነበር?
 • የማዕድን ዘርፉ ላይ በጣም ተዳክመናል፡፡
 • ለምን ተዳከምን?
 • ለእሱማ በሚዲያም እንደሰማኸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉት፡፡
 • ምንድናቸው ምክንያቶቹ?
 • የአካባቢው ወጣቶች በአንድ በኩል አላሠራ ብለውናል፡፡
 • ለምንድነው አላሠራ ያሉት?
 • ከዘርፉ እኛ ተጠቃሚዎች አልሆንም እያሉ ነው፡፡
 • ድርጅታችን የሚቀጥረው የአካባቢውን ወጣቶች አይደል እንዴ?
 • እነሱ የሚፈልጉት መቀጠር ብቻ አይደለም፡፡
 • ሌላ ምን ይደረግላቸው?
 • የማዕድኑ ባለቤት እኛ ስለሆንን እኛ ራሳችን እናውጣ ነው የሚሉት፡፡
 • ምን?
 • የሚገርምህ እኛም ይኼንኑ አውቀን የተወሰነ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርገን ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን አሉ?
 • ሙሉ ለሙሉ እኛ ካልያዝነው መሥራት አትችሉም እያሉ ነው፡፡
 • አሁንስ ሥርዓተ አልበኝነቱ በዛ፡፡
 • ስማ አገሪቷን በሙሉ ሥርዓት አልበኛ አይደል እንዴ የወረራት?
 • መንግሥት ግን ምን እየሠራ ነው?
 • እሱ ጥያቄ እኮ አንተን ነው የሚመለከተው፡፡
 • አሁንስ በዛ፡፡
 • ስለዚህ ሥርዓተ አልበኝነቱ ከባድ ስለሆነ መሥራት አልቻልንም፡፡
 • መንግሥት እያለማ እንደዚህ ዓይነት ሥርዓተ አልበኝነት አይሠራም፡፡
 • ስማ ውኃ እየዘጉ ገንዘብ አምጡ የሚሉ አካላት እንዳሉ አልሰማህም?
 • ይኼማ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
 • ሕዝቡ ግራ ተጋብቶ ነው ያለው፡፡
 • መንግሥት እያለ ግራ መጋባት አያስፈልግም፡፡
 • ሕዝቡማ መንግሥት እንዳለ ያውቃል፣ ግራ ያጋባው ሌላ ነገር ነው፡፡
 • ምንድነው ግራ ያጋባው?
 • ብዛታችሁ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የቤት ውሻ ፈልገው የእንስሳት ሐኪም ጋ ይሄዳሉ]

 • ጤና ይስልኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • በጣም ነው የደነገጥኩት፡፡
 • ምን አስደነገጠህ?
 • በቲቪ ብቻ ነበር የማውቅዎት፡፡
 • ዛሬ በአካል እንተዋወቃለና፡፡
 • ምን ልርዳዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ነገር እንድታማክረኝ ፈልጌ ነበር፡፡
 • ምን ይሆን ክቡር ሚኒስትር?
 • ውሻዬ ጠፋችብኝ፡፡
 • ከእርስዎ ግቢ እንዴት ልትጠፋ ትችላለች?
 • ለምን አትጠፋም?
 • ማለቴ ያው ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት ግቢ ስለሆነ ልታመልጥ አትችልም ብዬ ነዋ፡፡
 • እሱማ ውሻዋም ቤቷ ውስጥ በሰንሰለት ታስራ ነው የምትውለው፡፡
 • ታዲያ እንዴት ልትጠፋ ቻለች?
 • እኔማ ብዙ እየጮኸች ስትበጠብጠኝ ትንሽ ትናፈስ ብዬ ብለቃት በራ ጠፋች፡፡
 • ለነገሩ ብዙ ጊዜ የሚታሰሩ ውሾች ሲለቀቁ በዚያው በረው ይጠፋሉ፡፡
 • እኔማ ባለቀኩዋት ብዬ ተፀፀትኩ፡፡
 • ባይለቁዋት ደግሞ አውሬ ትሆንና የበጠሰች ዕለት አታስተርፍዎትም ነበር፡፡
 • እኔም እኮ እሱን ፈርቼ ነው የለቀኩዋት፡፡
 • ታዲያ ምን ልርዳዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን መቼም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ሰምተሃል?
 • አልሰማሁም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኸውልህ እሳቸው አራት ዓይነት ውሻዎች እንዳሉ ነግረውናል፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ አራቱም ዓይነት ውሻዎች እንዲኖሩኝ እፈልጋለሁ፡፡
 • ምን ምንድን ናቸው?
 • የመጀመርያው lap dog የሚሏት ናት፡፡
 • እሺ፡፡
 • እንደዚህ ዓይነቷን ውሻ እግርህ ላይ አድርገህ እያሻሸህ የምታጫውታት ናት፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለዚች ውሻ ስም አውጥቼላታለሁ፡፡
 • ማን ሊሏት ነው?
 • ቆንጂት፡፡
 • ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሁለተኛው ደግሞ attack dog የሚሉት ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • እንዲህ ዓይነቱ ውሻ ደግሞ ጠላትህን የሚያጠቃልህና የሚያስፈራራልህ ነው፡፡
 • በጣም ጥሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለዚህም ውሻ ስም አውጥቼለታለሁ፡፡
 • ማን አሉት?
 • ሺፈራው፡፡
 • ሌላኛውስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሦስተኛው ደግሞ guide dog ይባላል፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼ ደግሞ እኔ ዓይነ ሥውር ባልሆንም ብቻዬን ወክ ሳደርግ ይዤው የሚመራኝና የምኩራራበት ውሻ ነው፡፡
 • ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለእሱም ስም አውጥቼለታለሁ፡፡
 • ማን አሉት?
 • መኩሪያ፡፡
 • የመጨረሻውስ ክቡር ሚኒስትር?
 • አራተኛው ደግሞ watchdog ይባላል፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የዚህ ውሻ ዋነኛ ሥራ ደግሞ ግቢዬን ነቅቶ መጠበቅ ነው፡፡
 • ማን ሊሉት ነው ይኼን ውሻ?
 • ዓይናማው ነው የምለው፡፡
 • ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን እነዚህን አራት ውሻዎች የት እንደማገኛቸው ትጠቁመኛለህ?
 • አራቱም የሚገኙት አንድ ቦታ አለ፡፡
 • የት ነው?
 • ሚዲያ ውስጥ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከመሥሪያ ቤታቸው የሕዝብ ክንፍ አደረጃጀት ኃላፊ ጋር ቢሯቸው ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እየሄድንበት ያለው መንገድ በጣም እያስፈራኝ ነው፡፡
 • የትኛው መንገድ?
 • ክቡር ሚኒስትር በየቦታው እኮ የግጭትና የረብሻ ወሬ ነው የሚሰማው፡፡
 • ይህ ምን እንደሚጠቁም ታውቃለህ አይደል?
 • ምንድነው የሚጠቁመው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሥራህን በአግባቡ እየተወጣህ አለመሆንህን ነዋ፡፡
 • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይህ ሁላ ረብሻና ግጭት ያለው ከፍተኛ የሆነ የሐሳብ ልዩነት በሕዝቡ ዘንድ ስላለ ነው፡፡
 • አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ በአንድ ለአምስት አደረጃጀቱ ለምንድነው የሐሳብ ልዩነቱን ማጥፋት ያልቻላችሁት?
 • እኛ ምን እናድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ማለት ነው?
 • ሕዝቡ ታፍኗል ምናምን ብላችሁ ነፃ ለቀቃችሁትና አስተሳሰቡን ልንቆጣጠረው አልቻልንም፡፡
 • ስማ የልማታችን መሠረት የሆነው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ እየተጣሰ ሌሎች ባዕድ አስተሳሰቦች በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ እየሰረፁ ነው፡፡
 • በዚህ ምክንያት አይደል እንዴ እየተቸገርን ያለነው?
 • ሁሌም የልማታችን ሞዴል እንደሆነችው ቻይና ሕዝቡ አንድ ዓይነት ሐሳብ እንዲኖረው ማድረግ አለብን፡፡
 • ሕዝቡ አንድነት ማለት አንድ ዓይነትነት አይደለም እያለ ሊቀበለን ፈቃደኛ አይደለም፡፡
 • በዚህ ከቀጠልን አንድነታችን ይፈራርሳል፡፡
 • ታዲያ ምን ተሻለን ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደነገርኩህ ሕዝቡ ለግጭትና ለረብሻ እየተነሳ ያለው ከእኛ መርህ ውጪ የሆኑ ሐሳቦች አዕምሮ ውስጥ ገብተው ስላቆሸሹት ነው፡፡
 • እሱማ ግልጽ ነው፡፡
 • ስለዚህ በአስቸኳይ እነዚህን ቆሻሻ ሐሳቦች ከሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ማስወገድ አለብን፡፡
 • የጨነቀኝ እኮ እሱ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑ ነው የጨነቀህ?
 • የሐሳብ ልዩነቱን እንዴት ማስወገድ እንችላለን?
 • እሱን የምንችለው አንድ ነገር በማድረግ ነው፡፡
 • ምን በማድረግ?
 • Brainwash!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ዳያስፖራ ጋር እያወሩ ነው]

 • አገሪቱን ለመድካት?
 • ይህች የምትለመድ አገር አትመስለኝም፡፡
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ሁሉም ነገር ያስፈራል፡፡
 • ባለፈው የመጣኸው በብዙ መነሳሳት አልነበር እንዴ?
 • እኔማ አመጣጤ ባለኝ ሀብትና ዕውቀት አገሬን አገለግላለሁ ብዬ ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ተፈጠረ?
 • አሁንማ ሐሳቤን ቀይሬያለሁ፡፡
 • ለምን?
 • ክቡር ሚኒስትር በቆይታዬ አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች ቴአትረኞች መሆናችሁን ተረድቻለሁ፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • የምታወሩትና የምታደርጉት የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት ነው ያለው፡፡
 • ስማ ነገሮችን እየጠበቅክ ያለኸው በምትኖርበት አገር ስታንዳርድ ነው እንዴ? ይኼ እኮ አፍሪካ ነው፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉም ነገር የሚሆነው ቀስ በቀስ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ሳይኖርና ማንም ጎረምሳ ተነስቶ በሚወስንበት አገር ገብታችሁ ኢንቨስት አድርጉ ስትሉ አታፍሩም?
 • ነገርኩህ እኮ ተባብረን ተቋም እንገንባ አይደል እንዴ ያልነው?
 • ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ሥርዓተ አልበኝነት በሰፈነበት አገር እንዴት መተባበር እንችላለን?
 • ምን ይደረግ ነው የምትለው?
 • ክቡር ሚኒስትር አብዛኛው ሰው በአቋራጭ የሚከብርበትን መንገድ ነው እኮ የሚፈልገው፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ባለፉት ዓመታት አገሪቱ 11 በመቶ አድጋለች ምናምን የምትሉት ምንም ትርጉም እንደሌለው ተረድቻለሁ፡፡
 • በአንዴ እንደዚህ አትማረር፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ አድጋለች ምናምን የምትሉትን ቀልድ ብትተውት ያወጣችኋል፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • በቅርቡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 27 በመቶ ሕዝብ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት ይፋ አድርጓል፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ስለዚህ ላለፉት 27 ዓመታት ሕዝቡን ስታሳድጉት አልነበረም፡፡
 • ታዲያ ምን ስናደርገው ነበር?
 • ስታሳብዱት!