Skip to main content
x
25 ዓመታት በባዮጄኒክ ውበት አጠባበቅ

25 ዓመታት በባዮጄኒክ ውበት አጠባበቅ

የፊት፣ የእጅና እግር ውበት አጠባበቅ አገልግሎት በማዕከል ደረጃ እምብዛም በማይሰጥበት ወቅት ነበር የባዮጄኒክ ስፓ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት፡፡ የዛሬ 25 ዓመት የባዮጄኒክ ስፓ አገልግሎት ሲጀምሩ ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩባቸውም ያስታውሳሉ፡፡ ወ/ሮ ሙሉእመቤት ገብረ ሥላሴ የባዮጄኒክ ስፓና የሥልጠና ማዕከል መሥራችና ባለቤት ናቸው፡፡ ሥራውን የመሠረቱበትን 25ኛ ዓመትም ባለፈው ሳምንት አክብረዋል፡፡ በባዮጄኒክ የፊት ቆዳ ንፅህና አጠባበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የነበርዎትን ሥራ ትተው አሜሪካ ለመሄድ ያነሳሳዎት ምን ነበር?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- ከዛሬ 26 ዓመታት በፊት አሜሪካ የሄድኩት በውስጤ የነበረውን የውበት በተለይም የፊት አጠባበቅ ትምህርት ለመማር ነው፡፡ በወቅቱ በአገራችን ምንም ዓይነት በዘርፉ የሚሰጥ ትምህርት አልነበረም፡፡ የውበት አጠባበቅ ትምህርቱን ስጨርስ እዚያው መልካም ሥራ አግኝቼ የነበረ ቢሆንም ፍላጎቴ አገሬ ተመልሼ ለወገኖቼ ማገልገልና ማስተማር ስለነበር አሜሪካ ብዙም ሳልቆይ ተመለስኩ፡፡ ሴቶችም ወንዶችም ውበታቸውን የሚጠብቁበትና በሙያ የታገዘ ማዕከል መክፈት ዓላማዬ ነበርና ማዕከሉን በኢትዮጵያ ከፈትኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ በውበት አጠባበቅ ዙሪያ መሥራት ፈተና አልነበረም?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- በጣም ከባድ ነበር፡፡ ፍቃድ ከማውጣት ጀምሮ ዕቃዎችን ማስገባትና ቤት መከራየትም ከባድ ነበር፡፡ ዋናው ፈተና ‹‹Skin Care Center›› ብዬ ለመሥራት ስነሳ በዚህ ዘርፍ ንግድ ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዘርፉ ግንዛቤም አልነበረም፡፡ የቆዳ አጠባበቅ ማዕከል ለመክፈት ስነሳ እንደዚህ ዓይነት የስራ ዘርፍ የለም ተብሎ ብዙ ተመላልሻለሁ፡፡ ለምን ከአሜሪካ ተመልሼ መጣሁ? ያልኩበት ጊዜም ነበር፡፡ ንግድ ፈቃድ ለማውጣት ሰባት ወር ከተመላለስኩ በኋላ የፀጉር ሥራ በሚለው ሥር እንድሠራ ተፈቀደልኝ፡፡ በአሜሪካ የቆዳ አጠባበቅ ራሱን የቻለ ዘርፍ ነው፡፡ ከቆዳ ሕክምና ጎን ለጎን ቢሄድም ሕክምና አይደለም፡፡ ውበት አጠባበቅ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ፍቃድ የማግኘቱን ውጣ ውረድ አልፈው ሥራውን ሲጀምሩ የኅብረተሰቡ አቀባበል እንዴት ነበር?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- ከብዙ ድካም በኋላ የሥራ ፈቃድ አግኝቼ ስጨርስ ማሽኖቹን ማስገባቱና ታክሱ ከባድ ነበር፡፡ ዕቃውን የሚያውቁ ባለሙያዎች አለመኖራቸው ችግር ነበር፡፡ ይህን ሁሉ አልፈን ሥራውን ስንጀምር ደግሞ ስለውበት አጠባበቅ ግንዛቤው የለም፡፡ እኔ፣ አንድ ረዳትና አንድ አስተናጋጅ ሆነን ነበር ሥራው የተጀመረው፡፡ አንድ ሰው ከመጣ ደስታ ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ግን መቀጠል ከባድ ሆነ፡፡ በመሆኑም ግንዛቤ ለመፍጠር የሴት ማኅበራትን ፈልጌ ማናገር ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ ልማድ ወንዶችን ማምጣት ከባድ ነበር፡፡ የሴት ነጋዴዎች ማኅበር አባላት ሲሰበሰቡ ተንቀሳቃሽ አልጋና የውበት መጠበቂያ ቁሳቁስ በመያዝ ሥራዬን ማሳየት ጀመርኩ፡፡ ስብሰባ ባለበትና በየትምህርት ቤቶች እየዞርኩ ስለሥራው ማስረዳትን ተያያዝኩት፡፡ በዚያው ሥራው እየታወቀና እየተለመደ መጣ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ዜጎችም ማእከሉ በመከፈቱ ደስተኛ ነበሩ፡፡ ቀስ በቀስ ተጠቃሚዎችም እየበዙ መጡ፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ አሜሪካ ተምረው ስለመጡ ሙያውን ይዘዋል፡፡ በኢትዮጵያ የውበት አጠባበቅ በተለይም በፊት ቆዳ አጠባበቅ ዙሪያ ባለሙያ ማግኘት አልተቸገሩም?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- ሥራው እየበዛ ሲሄድ የተገነዘብኩት ብቻዬን እንደማልዘልቀው ነው፡፡ ዓላማዬም ለመሥራትና ለማስተማርም ስለነበር የሥልጠና ማዕከል ለመክፈት ተነሳሁ፡፡ ውጭ ተምረን አገር ውስጥ ዕውቀት ካላስተላለፍን ጥቅም ስለሌለው ከ13 ዓመታት በፊት በራሴ ኢንቨስትመንት የማሳጅ፣ የሜካፕና የፊት አጠባበቅ ሥልጠና ማዕከል  ከፈትኩ፡፡ በመጀመርያም 43 ተማሪዎች አገኘሁ፡፡  ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ ከ1,500 በላይ አስተምሯል፡፡ ከሠለጠኑት ከእኔ ጋ የሚሰሩና በተለያዩ ተቋማት የገቡ እንዲሁም የራሳቸውን የከፈቱ አሉ፡፡ እኛም ሦስት ቅርንጫፍ ከፍተናል፡፡ ከሦስት ሠራተኞች ተነስተን 85 ደርሰናል፡፡ ስኬታማ ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ሥራ የጀመርንበትን 25ኛ ዓመት ማክበር መጀመራችን አስደስቶኛል፡፡ የውጭ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያንም የባዮጄኒክ ስፓ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለ25 ዓመታት በባዮጄኒክ ስፓ አገልግሎት ለ13 ዓመታት ደግሞ በሥልጠና ሰርታችኋል፡፡ ባዮጄኒክ ወይም የባዮጄኒክ የውበት አጠባበቅ ምን ማለት ነው?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- የባዮጄኒክ ውበት አጠባበቅ ማለት በተፈጥሮ ዕፅዋት የሚሠሩ ቅባቶችን ተጠቅሞ የሰው ፊት ማፅዳትና ማዋብ ማለት ነው፡፡ ፀጉርና ሰውነታችንን እንደምንታጠብና እንደምናፀዳው ሁሉ ፊትም በደንብ መፅዳት አለበት፡፡ ማፅዳት ሲባል እንዲሁ በውኃ ብቻ ተለቃልቆ መውጣት አይደለም፡፡ ሲፀዳ የደረቀ የቆዳ ክፍል እስከሚወገድ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ የሚሆኑ ከዕፅዋት የተቀመሙ መታጠቢያዎች አሉ፡፡ ከታጠቡ በኋላ ደግሞ የፀሐይ መከላከያን ጨምሮ የሚቀቡ  ቅባቶች አሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው የሞቱ የፊት ቆዳ ሴሎች በየ28 ቀኑ ታጥበው መወገድ ስላለባቸው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የፊት ቆዳ ቀዳዳ ስለሚደፈን ፊት ያረጃል፣ ይጎሳቆላል፡፡  ቀዳዳው በተደፈነ ፊት ላይ የትኛውም መዋቢያ ቢቀባ ፊትን ከማርጀት አይከላከለውም፡፡ ፊት በሥርዓቱ ከተፀዳ እያማረ ይሄዳል፡፡ ብዙ የኢትዮጵያ ወጣቶች መድኃኒትነት ያላቸውን ቅባቶች ይቀባሉ፡፡ ይህ መቅረት አለበት፡፡ እያንዳንዱ በተፈጥሮ ቆንጆ ቆዳ እያለው የሚያቀላና ቀለም የሚቀይር የሚቀባም አለ፡፡ መድኃኒትነት ያላቸውና ያለሐኪም ትዕዛዝ ፊት ላይ የሚቀቡ ቅባቶች ፀሐይ ሲነካቸው ፊትን ያበላሻሉ፡፡ የማድያት አንዱ መንስዔም ይኼው ነው፡፡ ወቅት ጠብቆ ለምሳሌ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ማድያት ከእርግዝና በኋላ በራሱ ይጠፋል፡፡ ለዚህ ተብሎ በገዛ ፈቃድ መድኃኒትነት ያላቸውን ቅባቶች መቀጠም አያስፈልግም፡፡ ብዙ መድኃኒትነት ያላቸው የፊት ቅባቶች አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ግንዛቤው ስለሌለ ብዙዎች ከገበያ እየገዙ ይጠቀማሉ፡፡ መንግሥት ይህን ለማስቆም መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ የአሁኑ ትውልድ መረጃ የማግኘት ዕድል አለው፡፡ ኢንተርኔት ተጠቅሞ ማንበብ ይችላል፡፡ ቆዳ እንዴት እንደሚጠበቅና የሚቀቡት ቅባት ውስጥ ያለውን ኬሚካል ጥቅምና ጉዳት ማንበብና ማወቅ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው በታዳጊ ወጣትነት ዕድሜ የሚከሰተውን ብጉር በማፅዳት ማዳን ይቻላል፡፡ ብጉር ያለበትን ሰው አፅድተን ሕክምና ካስፈለገ ወደ ቆዳ ሐኪሞች እንልካለን፡፡ ከቆዳ ሐኪሞች ጋር የሥራ ግንኙነት አለን፡፡ ፊት አፅድተን ሕክምና የሚፈልግ መሆኑን ስናውቅ ወደ ሐኪም የምንልክበትን አሠራር ዘርግተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ውበትና የፊት አጠባበቅ ሲነሳ ሁሌም የሴቶች ጉዳይ ተደርጎ ይወራል፡፡ እንደ ባለሙያ ምን ይመክራሉ?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- የዛሬ 25 ዓመት ሥራ ስንጀምር የፊት ንፅህናንና ውበትን መጠበቅ የሴቶች ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ አሁን ግን ወንድም ሴትም እኩል የፊቱን ውበት የሚጠብቅበትን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ የፊት ቆዳ ጥሩ መሆን ዕይታን ጥሩ ያደርጋል፡፡ የፊት ቆዳ አጠባበቅ እንደ ቆዳው ተለያይነት ይለያያል እንጂ፣ ፆታ አይወስነውም፡፡ በኛ ማዕከልም ብዙ ወንድ ተጠቃሚዎች አሉን፡፡ ፊት ብቻ ሳይሆን እጅና እግርም መፀዳት አለበት፡፡ ድሮ ወንድ በማዕከል ደረጃ እጅና እግሩን ሲፀዳ ማየት የተለመደ አልነበረም፡፡ የእጅና የእግር ንፅህናን መጠበቅ ቀለም መቀባት ማለት አይደለም፡፡ የእግር ቆዳ ይደርቃል፣ ፈንገስ ይኖረዋል፣ ሽፍን ጫማ እናደርጋለን፣ የፀሐይ ሙቀት አለ፣ በእግር እንንቀሳቀሳለን፤ ይህ ሁሉ ባለበት ማፅዳት ግድ ነው፡፡ ይህ የራስን ጤንነት እንደመጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም የፊቱን፣ የእጁንና የእግሩን ንፅህና መጠበቅ አለበት፡፡ እኛም የምንሠራው በሠለጠነ ባለሙያ እነዚህን ክፍሎች ማፅዳትና ማስዋብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ክፍሎች ለማፅዳትና ለማስዋብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች አሉ፡፡ የቁሳቁሶቹ ንፅህና አጠባበቅ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- ለእያንዳንዱ መሣሪያ ስቴራላይዘር እዚያው አልጋው አጠገብ አለ፡፡  እያንዳንዱ ሥራ በጥንቃቄ የሚሠራ ነው፡፡ የራሳችንንም ሆነ የደንበኞቻችንን ጤና ፍፁም አስጠብቀን እንሠራለን፡፡ የኛ ማዕከል ሐኪም ቤት ባይሆንም ሐኪም ቤት ያለ የንፅህና አጠባበቅ በሙሉ በማዕከላችን ይተገበራል፡፡ ቆዳን ለመሥራት ንፅህና ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ዓለም አቀፍ መሥፈርትን ተከትለን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የባዮጄኒክ የውበት ጥበቃ አገልግሎት ግንዛቤና ገንዘብ የሚፈልግ ነው፡፡ አቅም ያላቸው እናተ ጋር ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አቅም የሌላቸው እንዴት አድርገው የራሳቸውን የፊት ውበት ሊጠብቁ ይችላሉ?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- ማሠልጠኛ የከፈትነው ሰዎች ሥልጠና እንዲያገኙ ነው፡፡ ስለቆዳ ማወቅ ለሚፈልግም በነፃ ምክር እንሰጣለን፡፡ ምንም ነገር ከመደረጉ በፊት የፊት ቆዳ ዓይነት መታወቅም አለበት፡፡ የሥልጠና ማዕከሉን የከፈትኩትም  ዕውቀቴን ለማካፈል ነው፡፡ ያነሳሽው የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ አቅም ያለው ብቻ ነው እናንተ ጋ የሚመጣው ይሉናል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ማንም ሰው ሊከፍል በሚችለው ዋጋ መገናኛ ላይ ሌላ ማዕከል ከፍተናል፡፡ይህ ማዕከል አገልግሎቱ ከሌሎቹ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ምንም ልዩነት የለውም፡፡ ጥራቱን የጠበቀም ነው፡፡ በዋጋ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህንን ያደረግነው ሰውን ለመጥቀም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሥራው ምን ያህል ኢንቨስት አደረጉ?

ወ/ሮ ሙሉእመቤት፡- የዛሬ 25 ዓመት ወደ 300 ሺሕ ብር ፈጅቷል፡፡