Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር በስልክ እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር በስልክ እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ነው፡፡ ልብሳቸውን ሲያስተካክሉ ሚስታቸው አገኟቸው]

 • ምነው ሽር ጉድ አበዛህ?
 • ጉዞ አለብኝ፡፡
 • የምን ጉዞ?
 • ወደ አውሮፓ መሄዴ አይቀርም፡፡
 • ምን ልታደርግ ነው አውሮፓ የምትሄደው?
 • አንቺ ግን ሚዲያ መከታተል ተውሽ?
 • ኧረ እከታተላለሁ፡፡
 • ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውሮፓን ሊጎበኙ መሆኑን አልሰማሽም?
 • ከእሳቸው ጋር አብረህ ልትጓዝ ነው?
 • እህሳ፡፡
 • ማን ጋብዞህ?
 • በዚህ  ጉዞ ላይ የሚሳተፉት በሥርዓቱ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው ስለሆኑ፣ እኔም ለዚያ ነው የተጋበዝኩት፡፡
 • የሥርዓቱ ወሳኝ ሰው ነኝ እያልከኝ ነው?
 • እሱ ብቻ ሳይሆን አውሮፓን እንደ ቤቴ ስተመላለስኩባት እንደ እኔ ዓይነት የጉዞ ልምድ ያለው ሰው መሄዱ አይቀርም ብዬ ነው፡፡
 • በነገራችን ላይ በዚህ በለውጥ መንግሥት ያላግባብ ወጪ አያወጣም፣ በተለይም የውጭ ጉዞ ወጪ ይቀነሳል ስትሉ አልነበር እንዴ?
 • እሱማ አላስፈላጊ ጉዞዎች ተቀንሰዋል፡፡
 • ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚሄደው ባለሥልጣን አልበዛም?
 • እዚህ ላይ አንድ ነገር መሳሳት የለብሽም፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • አንዳንድ ጉዞዎች ከፍተኛ ወጪ ቢኖራቸውም፣ ገቢያቸውም በዚያው ልክ ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • አየሽ ምንም እንኳን መንግሥት ለእንደዚህ ዓይነት ጉዞዎች ከፍተኛ ወጪ ቢያወጣም፣ በኋላ ላይ ጉዞው ፍሬ ሲያፈራ አገራችን በትልቁ ነው የምትጠቀመው፡፡
 • እንዴት እንደምንጠቀም አብራራልኝ እስኪ?
 • ለምሳሌ እኔን ልትወስጂኝ ትችያለሽ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ፈረንሣይ በምንድነው የምትታወቀው?
 • በብዙ ነገር ትታወቃለች፡፡
 • እስኪ አንዱን ጥሪልኝ?
 • ለምሳሌ ሽቶ አንዱ ነው፡፡
 • በጣም ጥሩ ሽቶን መውሰድ እንችላለን፡፡
 • እሺ፡፡
 • አሁን እኔ እንደ ዲፕሎማት ስለምሄድ ሻንጣዬ አይፈተሽም፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ አንድ ሁለት ሻንጣ ሽቶ ይዤ ብመጣ እዚህ ምን ያህል እንደማተርፍ አስቢው፡፡
 • ወይ ጉድ?
 • ከዚህ ጉዞ ብቻ ለእኔ ሦስት ሺሕ ዶላር ቢወጣ፣ እኔ ስመለስ እስከ 20 ሺሕ ዶላር ላተርፍ እችላለሁ፡፡
 • መቼ ይሆን ከዚህ አስተሳሰብ የምትላቀቀው?
 • ይኼ በግለሰብ ደረጃ የሚገባው ብቻ ነው፡፡
 • ሌላ ምን አለ?
 • ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥትን ወክለው እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
 • ይኼማ ለአገር የሚጠቅም ነው፡፡
 • እኮ እንደነገርኩኽ አገሪቱም ሆነ እኔ የምንጠቀምበት ጉዞ ነው፡፡
 • ዞረህ ዞረህ ከራስህ አታልፍም በቃ?
 • ስሚ እኔ ሲያልፍልኝ ነው አገሪቱ የሚያልፍላት ብዬ ብዙ ጊዜ ነግሬሻለሁ፡፡
 • ይኼ አካሄድ ግን ብዙ የሚያዘልቅህ አይመስለኝም፡፡
 • ይኸው እያዋራሽኝ ስለጉዞው ኢሜይል ተላከልኝ፡፡
 • ምን ይላል?
 • እንዴ?
 • ምነው?
 • ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ከሚሄዱት መሀል ስሜ የለም፡፡
 • ውይ ሽቶህ የእንትን ሽታ ሊሆን ነው፡፡
 • የምን ሽታ?
 • የውኃ ሽታ!

[ክቡር ሚኒስትሩ የዲስፕሊን ግድፈት የተገኘበትን አማካሪያቸውን ከሥራ ለማሰናበት ቢሯቸው አስጠሩት]

 • በድጋሚ ስላገኙኝ አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንም ችግር የለውም፡፡
 • ጉዳዬን አጣሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • በሚገባ ነው ያጣራሁት፡፡
 • ምን አገኙ ታዲያ?
 • ግኝቴማ ከዲስፕሊን ኮሚቴ ውጤት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ስማ በተደጋጋሚ ቢሮ የምትገባው እየጣጠህ ነው፡፡
 • ወድጄ አይደለም እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የቢሮ ዲሲፕሊን አታውቅም እንዴ?
 • ሱስ ስላለብኝ እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ከመጠጥ ሱስህ ባለፈ ሌሎችም ሱሶች አሉብህ አይደል?
 • ጫትም እቅማለሁ፡፡
 • የሚገርመው በሥራ ሰዓት ከቢሮ እየወጣህ ጫት ቤት ነው የምትውለው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ጫት ቤት ብሄድም ሥራዬን እዚያም ሆኜ እሠራለሁ፡፡
 • ጫት ቤት ሆነህ እንዴት ነው እዚህ ያለውን ሥራ የምትሠራው?
 • ክቡር ሚኒስትር ፋይሎቹን ጫት ቤት ይዤ ሄጄ ከዚያ ሥራዬን እሠራ ነበር፡፡
 • ይህ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡
 • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በዚያ ላይ ቢሮ ውስጥ ከበርካታ ሰዎች ጋር ትጣላለህ፡፡
 • እኔ እኮ ትንሽ ከነኩኝ ስለምናደድ ነው፡፡
 • በዚህ ፀባይህ የተለያዩ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰሃል፡፡
 • ምን ላድርግ በተፈጥሮዬ ቁጡ ስለሆንኩ ነው፡፡
 • ስለዚህ አንተን ወደዚህ መሥሪያ ቤት የምትመለስበት ምክንያት አላገኘሁም፡፡
 • ኧረ ጥሩ ምክንያት አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ዘመኑ እኮ የፍቅርና የመደመር ነው፡፡
 • ቢሆንም ከአንተ ዓይነቱ ሥርዓተ አልበኛ ጋር ፍቅርና መደመር አይሠራም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሌላ ምክንያትም አለኝ፡፡
 • ምንድነው?
 • ከሥራ በታገድኩበት ወቅት ስለመሥሪያ ቤታችን ዋነኛ ተቆርቋሪ ነበርኩ፡፡
 • ነገርኩህ እኮ እንደ አንተ ዓይነቱ ሥርዓተ አልበኛ መሥሪያ ቤታችን እንዲኖር አልፈልግም፡፡
 • ምን እያሉኝ ነው ታዲያ?
 • እኔም ከሥራህ እንድትታገድ ወስኛለሁ፡፡
 • ችግር የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ በስምህ ያሉትን ንብረቶች በአስቸኳይ አስረክብ፡፡
 • ለስቴፕለርና ለወረቀት ደግሞ ምን ችግር አለው?
 • ላፕቶፕም በስምህ እንዳለ አይቻለሁ፡፡
 • ስለእሱም አይጨነቁ አስረክባለሁ፡፡
 • ሌላም በስምህ የተመዘገበ ዕቃ አይቻለሁ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ማከሮቭ ሽጉጥ፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱንም ሽጉጥ አስረክብ፡፡
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • ለዚህ ጥያቄዎ ምላሼ አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • ትጥቅ አልፈታም!

[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን ቢሮ አስጠሯት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አለቃችን መቼም በአገሪቱ እያደረጉ ያለውን ሪፎርም አይተሻል?
 • የቱን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሴቶችን ወደ ሥልጣን በማምጣት ያደረጉትን ለውጥ ነዋ፡፡
 • በጣም ነው የተደሰትኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በመሥሪያ ቤታችን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ፈልጌያለሁ፡፡
 • ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኛ መሥሪያ ቤት የበር ጥበቃ ስትመለከቺ ወንድ ብቻ ነው፡፡ በየቢሮው ብትገቢ ወንድ ነው፡፡ ሾፌሬ ወንድ፣ ጋርዶቼ ወንድ፣ አማካሪዎቼ ወንድ፣ ብቻ ምን አለፋሽ ሁሉ ቦታ ወንድ ብቻ ነው ያለው፡፡
 • እ. . .
 • ታዲያ ሴቶቹ የት አሉ?
 • እኔን አንድ ብለው መጀመር ይችላሉ፡፡
 • ምን መሰለሽ ከአንቺ ውጪ ቡና የምታቀርብልኝ ልጅ ብቻ ነው የማየው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ምናልባት እርስዎ ስለሚያውቋቸው ይሆናል እንጂ ሌሎችም ሴቶች አሉ፡፡
 • ስሚ ለእኔ አሁን የማንቂያ ደወል ነው የተደወለልኝ፡፡
 • የምን ደወል?
 • የአገራችን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የካቢኔያችን ግማሽ ሴቶች መሆናቸው በጣም ጥሩ የማንቂያ ደወል ነው፡፡
 • ምን ሊያደርጉ ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለዚህ የእኛም መሥሪያ ቤት የኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በሴቶች መያዝ አለባቸው፡፡
 • የኃላፊነት ቦታ ግን አቅም ባለው ሰው እንጂ በፆታ መሆን አለበት ብለው ያምናሉ?
 • ምን ነካሽ ከዚህ በፊት ሹመት በታማኝነት እንጂ በብቃት መቼ ሆኖ ያውቃል?
 • እ. . .
 • ስለዚህ አሁን ደግሞ ለለውጥ ያህል በፆታ ብናደርገው ምን ችግር አለው?
 • ማለቴ የኃላፊነት ቦታ ብዙ ውሳኔዎች ስለሚሰጥበት ብቃት የግዴታ ነው ብዬ ነዋ?
 • ስሚ የእኔ ዋና ዓላማ ታሪክ መሥራት እንጂ ሌላው አያሳስበኝም፡፡
 • ምን?
 • ስለዚህ ጋርዶቼ በሙሉ ሴቶች ይደረጉልኝ፡፡
 • እንዴት ይሆናል ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ችግር አለው? የጋዳፊ ጋርዶች ሴቶች አልነበሩ? ስለዚህ የእኔም ስም ከእሱ ጋር በታሪክ እየተነሳሁ ከታወስኩ ምን እፈልጋለሁ?
 • ካሉ ምን ይደረጋል?
 • እሱ ብቻ ሳይሆን ሾፌሬም ሴት ትሁንልኝ፡፡
 • እ. . .
 • ነገርኩሽ እኮ ዓላማዬ ታሪክ መሥራት ነው፡፡
 • የሚያዋጣ ግን አልመሰለኝም፡፡
 • ስሚ ቢቻልማ እኔም ብቀይር ደስ ይለኛል፡፡
 • ምንድነው የሚቀይሩት?
 • ፆታዬን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር በስልክ እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ምንድነው የምሰማው?
 • ምን ሰማህ?
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ እኮ ነው?
 • ምንድነው የምታወራው?
 • የእርስዎ ግን በዛ፣ እኔ ራሴ ማፈር ጀመርኩ፡፡
 • ምኑ ነው ያሳፈረህ?
 • በየቦታው የሌብነትና የሙስና ችግር ካለ የእርስዎ ስም እኮ ነው የሚነሳው፡፡
 • ስማ ሪፎርሙን የማይቀበሉ አካላትን ወሬ ዝም ብለህ ማስተጋባት የለብህም፡፡
 • እንዴት?
 • ከማንም በፊት መደመሬን ታውቃለህ?
 • እሱማ ልክ ነው፡፡
 • አየህ በፊት እነሱ ሲሰርቁ ዝም በማለቴ አሁን ያጋልጠናል ብለው ስለሚፈሩ ነው እንደዚህ ስሜን የሚያጠፉት፡፡
 • አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ ምን ሰምተህ ነው?
 • ከተማ ውስጥ ስም አልባ ከሆኑት ሕንፃዎች መካከል ሁለቱ የእርስዎ ናቸው ይባላል፡፡
 • ለእዚህ ነው እኮ እያሳሳቱህ ነው ያልኩህ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ከእነሱ ውስጥ አራት ነው ያሉኝ፡፡
 • ይኼን ነበር የፈራሁት፡፡
 • ምን ነካህ አገሪቱ በ11 በመቶ እያደገች እኛ ካላደግን ምን ትርጉም አለው?
 • ለማንኛውም አካሄድዎ ትክክል አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አካሄዴማ ትክክል ለመሆኑ አትጠራጠር፡፡
 • ብቻ የእኔ ፀሎት አንድ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • አወዳደቅዎትን. . .
 • እ. . .
 • ያሳምርልዎት!