Skip to main content
x
የህልም ዓለም

የህልም ዓለም

መንገድ ሲሻገሩ በፍጥነቱ የሚያውቁት እግርዎት ድንገት ተሳስሮ አደባባይ ላይ ተዘርግተው ያውቁ ይሆናል፡፡ ውድቅት ላይ መዝጊያውን ሰብሮ ከሚገባ ነፍሰ ገዳይ ታላቅ ወንድምዎ ደርሶ እንዲያስጥልዎት ሁለት እጆችዎን እያርገበገቡ ኡ ኡ ማለት ሞክረው ድምፅዎ ወይ ፍንክች አልወጣም ብሎዎትም ይሆናል፡፡ ጓደኛዎ በሱፍ ዘንጠው በተገኙበት ድንቅ ፕሮግራም ላይ ባዶ እግርዎን ግልገል ሱሪዎ ላይ ምንም ሳይደርቡ ተገኝተው መሳቂያ ሆነውማል፡፡ ወይም የሚነዱት ብስክሌት ክንፍ አውጥቶ በሰማይ ላይ አንሳፎዎት ዓለምን ቁልቁል ተመልክተዋል፡፡  ዓመቱን ሙሉ የተማሩበት ክፍል ጠፍቶት ሊያመልጥዎ የማይገባ የክፍል ፈተና አምልጦታል፡፡ ደቂቃ የማይፈጀው የቤትዎ መንገድ አንድ ቀን ጨርሶብዎ ምን ጉድ ነው አሰኝቶታል፡፡ ገና ድክድክ ማለት የጀመረ ሕፃን እያባረርዎት የአገር መሳቂያም ሆነው አልፈዋል፡፡ ከሰማይ ጠቀስ ተራራ ላይ ቁልቁል ተወርውረው ነፍስዎ ከስጋዎ ተላቆ ልብዎ እየደለቀ ነቅተው ህልም መሆኑን ሲያውቁ ፈገግ ወይም እፎይ ብለዋል፡፡

ህልም ሰዎች ካሉበት መነቃነቅ ሳይስፈልጋቸው ከሚያሳድዳቸው አውሬ እንደ ዩሴን ቦልት አፈትልከው የሚያመልጡበት፣ ሲላቸው ደግሞ እንደ ቀንድ አውጣ በደረታቸው የሚሳቡበት፣ ፍቅሩንም ፀቡንም እኩል የሚያስተናግዱበት፣ ምክንያታዊነት ምክንያት የሚያጣበት፣ በደቂቃዎች እንቅልፍ ዓመታት የሚኖሩበት ሚስጥራዊ ዓለም ነው፡፡ ህልም ፈላስፎችን አንድ የሚያደርጋቸው መላምት የሌለው፣ ሕዋን በቁጥጥሩ ሥር ላደረገው ሳይንስ የማይፈታ እንቆቅልሽ፣ በተለያዩ እምነቶች እንኳ ቁርጥ ያለ መልስ የሌለው፣ ትርጉም አለው ብሎ ለማመን፣ የለውም ብሎም ለመደምደም አስቸጋሪ የሆነ ከገሃዱ ዓለም የተለየ ተፈጥሯዊ ሒደት ነው፡፡

ህልም የተረሱ ትዝታዎች፣ የታፈነ ጭንቀትና ፍርኃት፣ እንስሳዊ ፍላጎትና፣ ያልተገራ ተፈጥሯዊ መሻትና እንደ ኦዲፐስ ኮምፕሌክስ (ወንድ ልጅ አባቱን የሚጠላበትና ያልተገባ ወሲባዊ ፍላጎት የሚያድርበት ውስብስብ ባህሪ) የመሳሰሉት ባህሪያትና ኩነቶች የሚከማቹበት የውስጠ ህሊና (ሰብ ኮንሺየስ) ሒደት ነው፡፡ በዚህ የአዕምሮ ክፍል ውስጥ ከሰዎች ሁሉ የተወረሰ ኮንሺየስ የሚባለውን ገሃዱን የአዕምሮ ክፍል የሚመራ የሕይወት ልምድ የሚከማችበትም ነው፡፡ ሰብ ኮንሺየስ አዕምሮ የአንድን ሰው አጠቃላይ ፍላጎትና ባህሪ ቁልጭ አድርጎ የሚንያፀባርቅ ሆኖም በቀላሉ የማይገለጥ ፍፁም ሚስጥራዊነትም አለው፡፡

አንድ ሰው ሰብ ኮንሺየስ አዕምሮው ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ አይችልም፡፡ ‹‹ሰብ ኮንሺየስ አዕምሯችን ውስጥ ምን እንደሚካሄድ አናውቅም፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሰውየው ድርጊት ይንፀባረቃል፡፡ ለምሳሌ የምላስ ወለምታ የሰውየውን አንኮንሺየስ አዕምሮ የሚያስበውን በጥቂቱም ቢሆን ምልክት ይሰጣል፡፡ ወይም ደግሞ በራሱ ጥፋት መገኘት ካለበት ሰዓት አርፍዶ ሲገኝ ሳያውቀው ሰበብ በመደርደር ማርፈዱን ምክንያታዊ ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ይህንን የሚያደርገው ከራሱ ዕውቅና ውጪ ሰብ ኮንሽየስ አዕምሮው ነው፤›› የሚሉት በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሐኪሙ ዮናስ ላቀው (ዶ/ር)  ናቸው፡፡ በሰብ ኮንሽየስ አዕምሮ ውስጥ ምን እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ መንገዱን የሚመራው ዋናው መንገድም ህልም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ተመራማሪዎች ህልም ሥውሩን የሰብኮንሽየስ አዕምሮ ክፍል ነፀብራቅ ወይም አቅጣጫ ተቋሚ መንገድ ነው ሲሉት፣ በሌላው ወገን ያሉት በተለይም በቀደሙት ጊዜያት የነበሩ በርካቶች ህልም መፃኢ እድልን ከወዲሁ የሚያሳይ የተፈጥሮ መስታወት ነው ይሉታል፡፡ ወደውና ፈቅደው አስበውበት የማይገቡበት የህልም ዓለም ከእንቅልፎ እስኪነቁ ድረስ ሁሉም እውነት ነው፡፡ በህልሞ ሚሊየነር ሆነው የማይዛቅ ሀብት ባለቤት ሆነው ይቦራቃሉ፣ በገንዘቡ ድህነትን ድል ሲነሱ የሚሰማዎን ደስታ ያጣጥማሉ፡፡ ነብር አይተው ክው ይላሉ፡፡ ትዳሮን ፈትተው ያዝናሉ፣ አልያም በትዳሮ ላይ ማግጠው ያፍራሉ፡፡ በስለት ተወግተው ለሞት የሚያደርስ ስቃይ ያስተናግዳሉ፡፡ በህልሞ የሚናፍቁትን ዶሮ ወጥ ጎርሰውም ያጣጥማሉ፡፡

የዘርፉ ተመራማሪዎችም ህልም ከገሃዱ ዓለም ጋር ተመሳሳይነት ያለው የምስልና የድምፅ ምልልስ ያካተተ ብቸኛው በእንቅልፍ ወቅት የሚከሰት ሳይኮሎጂካል እንቅስቃሴ ነው ይሉታል፡፡ አላሚው ሳያውቀው አንድ ገፀ ባህሪን ወክሎ የሚጫወትበት ምናባዊ ዓለም ነውም ይሉታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በሌላ ዓለም ላይ የሚገኘውን የዓላሚውን ሕይወትና ውጣ ውረድ የሚቃኝበት ሚስጥራዊ መንገድ ነው የሚል እሳቤ ያራምዳሉ፡፡ ህልም መሠረተ ቢስና የማይጨበጥ ቅዠት ነው የሚሉም አሉ፡፡

በህልም ዙሪያ የተለያዩ መላምቶች የተሰጡና እየተሰጡ ቢሆንም አንዱም ግን ድምዳሜ ላይ አልደረሰም፡፡ ታዋቂው ኒውሮሎጂስት ሲግመንድ ፍሬውድና ሌሎች ህልም የሰብኮንሺየስ አዕምሮ ክፍል ሚስጥራዊ መግቢያ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ ሕፃናት ከሁለት ዓመታቸው ጀምሮ ህልም ያያሉ፡፡ እስከ ስድስት ዓመታቸው ድረስ የሚያዩዋቸው ህልሞች በርከት ያሉና አስፈሪ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አንድ ሰው በአንድ ሌሊት ከአራት እስከ ስድስት ህልሞችን ያያል፡፡ በከባድ ትኩሳት ውስጥ ሆነው የሚሰቃዩ፣ አልያም አንዳንድ ህልም የሚከለክሉ መድኃኒቶችን ከሚወስዱ ሰዎች በስተቀር ሳያልም የሚያድር የለም፡፡ ያዩትንና ማየታቸውን የማያስታውሱ ግን ብዙ አሉ፡፡

‹‹የምናያቸው ህልሞች ማንነታችንን ይገልጻሉ፡፡ በህልም ውስጥ እኛ በውል የማናውቃቸው ድብቅ ምኞታችን፣ ፍርኃታችን፣ ጭንቀታችን ሌሎችም ማንነታችንን የሚያሳዩ ነገሮች ይታዩናል፤›› የሚሉት ዶ/ር ዮናስ፣ አብዛኞቹ ህልሞች የሚቀዱት ከቀን ውሎ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ቀን ከአለቃው ጋር የተጋጨ በህልሙ ጥቁር ውሻ ሲያባርረው ሊያይ ይችላል፡፡ አልያም ተምሳሌታዊ መልዕክት ሳይኖረው ቀን ያጋጠመውን ሁሉ በህልሙ ደግሞ ሊያይ ይችላል፡፡

ህልም እሩዕያ (ለራዕይ የቀረበ)፣ ሁሉም (ህልም)፣ ቅዠት በሚል ለሦስት እንደሚከፈሉ የሚናገሩት ኡስታዝ አብዱረዛቅ ነጋሽ ደግሞ ህልሞች ከፈጣሪና ከሰይጣን የሚመነጩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ እሩዕያ የሚባለው የህልም ዓይነት ከፈጣሪ የሚሰጥና ነብያቶች አንዳንዴ ደግሞ በእምነታቸው ጠንካራ ለሆኑ ሰዎች ይታያል፡፡ በእሩዕያ መፃኢ እድል ወይም ሰዎች ከሚሠሩት ወንጀል እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ ማስጠንቀቂያ ይተላለፋል፡፡

ቅዠት እንደስሙ ጭብጥ የሌለው የሚያዩት ታሪክም እርስ በርሱ የሚጋጭ አልያም እንዲህ ነው የማይሉት አይነት ነው፡፡ ‹‹ሁሉም›› የሚባለው ደግሞ በሰዎች ላይ ጭንቀት የሚፈጥሩና የማይጨበጡ ህልሞች የሚታዩበት በሰይጣን አቀናባሪነት የሚቀረፁ ህልሞች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው ህልም ሰዎች ከመተኛታቸው በፊት ማድረስ የሚገባቸውን ፀሎት ሳያደርሱ ሲተኙ የሚከሰት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ብዙ ሰዎችን የሚያስቸግረው ህልም ከሰይጣን የሚመጣው ነው፡፡ ፀሎት አድርጎ መተኛት ግን ከአስፈሪ ህልሞች ይጠብቃል፤›› ብለዋል፡፡

ሰዎች ዓይናቸው ሲከደን ማለም መጀመራቸውንና የሚያልሙት አስፈሪ ይሁን ሰላማዊ መሆኑን ማወቅ የማይታሰብ ነበር፡፡ ለሳይንስ ምስጋና ይድረሰውና በአሁኑ ወቅት ሰዎች ማለም ሲጀምሩ በዓይናቸው እንቅስቃሴ ማወቅ አስችሏል፡፡ አንድ ሰው ማለም የሚጀምረው እንቅልፍ ከወሰደው ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው፡፡ ልክ ማለም ሲጀምር በልብ ምቱና በአንዳንድ የአካል ክፍሎቹ ላይ ለውጦች ይስተዋላሉ፡፡

የተከደነው ዓይኑ ሶኬቱ ውስጥ እንዳለ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጀምራል፡፡ የሚያየው ህልም እንቅስቃሴ የበዛበት እንደሆነ የዓይኑም እንቅስቃሴ በዚያው መጠን ፈጣን ይሆናል፡፡ እንቅስቃሴ ያልበዛበት እንደሆነ ደግሞ በተቃራኒው የተረጋጋ ይሆናል፡፡ የአይኑ እንቅስቃሴ የሚተላለፉትን ምስሎች ቀርፆ ያስቀራል፡፡ የምስሉን መዋቅራዊ ቅርፅም በዓይኑ እንቅስቃሴ መለየት ይቻላል፡፡

ምሁራን የደረሱበት የምርምር ደረጃ እዚህ ድረስ ነው፡፡ አንድ ሰው ማለም መጀመሩን እንጂ ምን እያለመ እንደሆነ አላሚው እንጂ ሌላ የማይደረስበት ሚስጥር ነው፡፡ የአንድ ሰው ህልም ውስጥ ቢኖሩም የሚያውቀው የህልሙ ባለቤት አላሚው ብቻ መሆኑ በምክንያት የማይተማመኑበት የህልም ሕግ ነው፡፡ ህልምን ማጋራት የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያልመልሰው፣ ጠቢባን በመላምት ደረጃ እንኳ የሚስተካከል ቀመር ያላገኙለት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ንስር አሞራ ከደመና በላይ ሲንሳፈፉ፣ እንደ ቅጠል ገንዘብ ከመሬት ሲለቅሙ፣ ጦርነት መሀል ገብተው የሚሆኑትን ሲያጡ እያለሙ መሆኖ ትዝ ይሎትና መዝናናት ድብብቆሽ መጫወት፣ አልያም መባነንን ይመርጣሉ፡፡ የህልሞ ደራሲ ይሆኑና ታሪኩን ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ይጠመዝዛሉ፡፡ አንበሳውን ከተኛበት ቀስቅሰው ይሮጣሉ፣ ሲሎት ደግሞ ነቅተው ፈገግ ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን በህልም ውስጥ እያለሙ መሆኑን የሚያውቁበት የህልም ዘውግ ‹‹ሉሲድ›› ይሰኛል፡፡

የሉሲድ ህልምን ጽንሰ ሐሳብ ህልምን በአንደኛው ሰው የህልም ዓለም ውስጥ ገብቶ አብሮ የማለም ጽንሰ ሐሳብን ያጣመሩ የሆሊውድ ፊልሞች ያልተነካውን ጉዳይ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሊኦናርዶ ዲካፕሪዮ መሪ ተዋናይ ሆኖ የሚተውንበትን እ.ኤ.አ. በ2010 የወጣውን ኢንሴፕሽንን ማንሳት ይቻላል፡፡ የአንድን ሰው ህልም ለሌላ ማጋራት የሚያስችል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰዎችን በተለይም የትልልቅ ድርጅቶችን ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን ህልም ሲሰርቁና፣ ሌላ ህልም በአዕምሯቸው ውስጥ ሲጨምሩ የሚያሳይ ፊልም ነው፡፡ በዚህ ፊልም ውስጥ ተዋናዮቹ ህልሞችን መቆጠጠር ብቻ ሳይሆን በህልም ውስጥ ሌሎች ህልሞችን ሲያልሙ፣ የራሳቸውን ከተማ ሲገነቡ ይታያሉ፡፡    

ህልም ግላዊም ዓለም አቀፋዊም ባህሪም አለው፡፡ ‹‹ሰብኮንሺየስ አዕምሯችን ሰው በመሆናችን ተመሳሳይ ነው፡፡ በባህልና በተለያዩ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ቢኖርበትም የምናልማቸው ህልሞች መሠረታቸው ተመሳሳይነት አለው፡፡ ይህ አንዱ የህልም ሚስጥራዊ ባህሪ ነው፤›› ይላሉ ዶክተር ዮናስ፡፡ ይህም ህልም ፈቺዎች ሳይቸገሩ ህልሞችን መፍታት እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡ አብዛኞቹ በህልም የሚታዩ ነገሮችም ተምሳሌታዊ ትርጉም አላቸው፡፡ አንዳንድ ህልሞች በአላሚው የግል ሕይወት ላይ የሚያጠነጥኑ በቤተሰቡ፣ አልያም በቅርበት በሚያውቃቸው ሰዎችና ቁሶች ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ፡፡

ህልም በተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ተመራማሪዎች ዘንድ የተለየ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በየማኅበረሰቡና በየግለሰቡ ስለ ህልም ያለው እምነትና እውነታም የተለያየ ነው፡፡ ህልም አናይም የሚሉ አሉ፡፡ የሚያዩትንም ቢሆን ጭብጥ አልባ የምስልና የድምፅ ምልልስ ብቻ አድርገው የሚያስቡም ብዙ ናቸው፡፡ ያለሙትን ሁሉ መልዕክት እንዳለው በማሰብ ካላስፈታን የሚሉ፣ እንደ ህልሙ ዓይነት እየመረጡ ይህ አንዳች መልዕክት ያዘለ ይሆናል በማለት ተምሳሌታዊ ፍቺውን ተከትለው ውሳኔያቸውን የሚያስተካክሉም ጥቂት አይደሉም፡፡

ፀጉር መቆረጥ፣ ጥቁር መልበስና የመሳሰሉት በህልም ሲታዩ የቅርብ ዘመድ ህልፈትን ያሳያሉ፡፡ ከማዕድ መቋደስ፣ ደረጃ መውጣትና የመሳሰሉት ደግሞ የመልካም አጋጣሚ ተምሳሌት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ ግን የቀረቡበት ማዕድ በርበሬ የበዛው እንደሆነ አልያም ከደረጃ ጫፍ ላይ ቁልቁል ወደ ታች ተወርውረው እንደሆነ ያልወደዱት አጋጣሚ በሕይወትዎ ሊያጋጥምዎ እንደሆነ ያምኑ ይሆናል፡፡ በህልማቸው የዱላ ውርጅብኝ ያጋጠማቸው ከባድ ሕመም እንደሚጠብቃቸው ያምናሉ፡፡ ሲጋራ ያጨሱ እንደሆነም ከሰዎች ጋር ሊጋጩ እንደሚችሉ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ጫማዎን አውልቀው ባዶ እግሮን ከሆኑ ምናልባት ትዳሮ ሊፈርስ ይሆናል፡፡ አልያም ጫማ ሲገዙ ካለሙ ትዳር ሊይዙ ይችላሉ፡፡ ሌሎችም በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ምሳሌያዊ አቀራረባቸው ትርጉም የሚሰጣቸው ህልሞች አሉ፡፡

‹‹የኔ ቤተሰቦች ጥሩ ህልም ሲታይ ሲሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እያንዳንዱን ትርጉሙን ባያውቁም በደፈናው ጥሩና መጥፎውን መለየት ይችላሉ፡፡ መጥፎ ህልም ሲታይ ግን በጠዋት ተነስተው አመድ ወደ አፋቸው አስጠግተው እፍፍፍ እያሉ ህልም እልም ህልም እልም ይሉ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ የኔነሽ (ስማቸው ተቀይሯል) ብዙም በህልም እንደማያምኑ ነገር ግን ትርጉም የለውም ብለውም ለመደምደም እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ህልም የሚያልሙት ከስንት አንዴ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አየሁ ከሚሏቸው ህልሞች የተወሰኑትም እውነት ሆነው አይተዋልና ህልም ትርጉም አልባ ነው ለማለት ይቸገራሉ፡፡

እስከዛሬ ከማይረሷቸው ህልሞች አንዱን እንዲህ አስታውሰዋል፡፡ በየዓመቱ የሚሄዱበት የፃድቃኔ ማርያም ገዳም ውስጥ ጋደም እንዳሉ ያዩት ነው፡፡ በህልማቸው ያዩት ታናሽ እህታቸው ስትሞትና የሚይዙት የሚጨብጡን አጥተው ሲያለቅሱ ነበር፡፡ ‹‹ከህልሜ የነቃሁትም እየጮህኩ ነበር፡፡ ሁኔታዬ በዙሪያዬ ያሉትን አስደንግጦ ስለነበር ምን ሆንሽ አሉኝ፡፡ ያየሁትን ነገርኳቸውና አዘኑ፡፡ ህልሜ በግልጽ የታየኝ ለመፍታትም የማያስቸግር ነበር፤›› የሚሉት ወይዘሮዋ፣ ጤናማ የነበረች እህታቸውን በሞት የተነጠቁት ህልሙን አይተው ብዙም ሳይቆዩ ነበር፡፡ አንዲት ጓደኛቸውም ባዶ እግራቸውን ሲሄዱ በህልሟ ታይቷት ትዳራቸውን እንደሚፈቱ ነግራቸው ነበር፡፡ ከባለቤታቸው የተፋቱትም ተጋብተው አምስት ዓመታት ያህል እንኳን አብረው ሳይኖሩ ነበር፡፡ ሌሎችም እንዲህ መሬት ጠብ ያላሉ ህልሞች አልመውም ታልሞላቸውም ያውቃል፡፡ ለዚህም ስለ ህልም ጉዳይ ሲጠየቁ ደፍረው እንዲህ የሚሉት ነገር የለም፡፡

አብዛኞቹ ህልሞቹ መልዕክት እንዳላቸው የሚሰማው አንድ ወጣትም ህልሞቹን እንደማስጠንቀቂያ ወስዶ ድርጊቱን ያጤናል፣ እንደ መልካም ዕድል አመላካች አድርጎም የበረታል፡፡ ለጓደኝነት ካሰባት ወጣት ወይም በጓደኝነት አብራው ካላች ወጣት ጋር በሚኖረው አብሮነት የማይደሰት ከሆነ መልዕክቱ ቀድሞ በህልሙ ይታየዋል፡፡ አብዝቶ ፀሎት በማድረግ የህልሙ መልዕክት በተቃራኒው እንዲሆን ጥረት ያደርጋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ደጋግሞ ተመሳሳይ ህልም የሚታየው ከሆነና በገሃዱ ዓለምም አንዳንድ ምልክቶች ሲታዩት ህልሙን ተቀብሎ የጓደኝነት ሐሳቡን ይተዋል፣ አብረው ከሆኑ ለመለያየት ይወስናል፡፡

ከዚህም ባሻገር ለዓመታት የለፋበት ሥራ ውጤቱ አደገኛ መሆኑን በህልሙ ታይቶት ሙሉ ለሙሉ እንዳወደመው ይናገራል፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውን ጽሑፍ ማዘጋጀት የጀመረው ከዓመታት በፊት ነው፡፡ በሆነው ባልሆነው አቋሙ የሚበታተንበት፣ ወደ ነፈሰበት የሚነፍሰውን ወጣት መስመር ያስይዛል ብሎ ያሰበው መጽሐፍ እንደ የልምዣት ልብወለድ ረዥም ነበር፡፡ ጽሑፉ ሊገባደድ መደምደሚያው ላይ ሲደርስ ህልም ይታየዋል፡፡

‹‹በልጅነታችን እንጫወትበት የነበረውን የሽቦ መኪና እየነዳሁ ነው፡፡ ዋናውን መንገድ ስቼ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ እገባለሁ፡፡ ከዚያም ከየአቅጣጫው አውሬ ይከበኛል፡፡ እጮሀለሁ፣ በመኪናው ለማምለጥ እሞክራለሁ በቃ ከባድ ጭንቅ ውስጥ ሆኜ ነቃሁ፡፡ የጀመርኩት ፕሮጀክት የሕፃን ጨዋታ ሳይሆን አገርን የሚያጠፋ ነገር እንደሆነ ገባኝና ሊገባደድ የቀረውን መጽሐፍ ወዲያውኑ አንስቼ እሳት ለኮስኩበት፤›› በማለት ህልሞቹን እምን ድረስ እንደሚያምንባቸው ይናገራል፡፡

ህልም እንደ ፈቺው ነው ከሚባለው አባባል በስተጀርባ ተምሳሌታዊ ፍቺ ያላቸው ነገሮች አንዳንድ ጊዜ ትርጉማቸው አብዛኞቹ ከሚስማሙበት ውጪ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ትናንት ሌሊት ያዩት አስፈሪ ህልም ተምሳሌታዊ ፍቺው ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡  ቀን ላይ ያባነኖት ቅዠት መልዕክት አዘል ታሪክ ይኖረዋል፡፡ እግር በእግር የሚከታተሎት ጥቁር እባብ እንደ ህልሙ ዓይነት ጠላት መሆኑ ቀርቶ ጠባቂዎ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌባ ሲያፈርሰው ያዩት መኖሪያ ቤቶ ፍቺው ነፃ መውጣቶን አልያም ደግሞ የቤተሰቦ መበተን ሊሆን ይችላል፡፡ አልያም ደግሞ ህልሞ ወጥ የሆነ ታሪክ ቢኖረውም ፍቺው ምንም ላይሆን ይችላል፡፡ አልያም ያዩት ከባድ የሚመስል ህልም እንደ ተሰጠው ፍቺ ሳይሆን አልመው ያለፉት ከንቱ ድራማ ሆኖም ይሆናል፡፡

በዚህ ረግድ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች መልዕክት የሌለው ህልም የለም ቆይቶም ቢሆን ዕውን ይሆናል ይላሉ፡፡ ኡስታዝ አብዱረዛቅ ደግሞ መልዕክት አዘል የሚባለው ህልም ለጥቂቶች የተሰጠ እንደሆነ፣ አብዛኞቹ የሚያዩት ህልም ግን ከሰይጣን የሚመጣ ማደናገሪያ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ዋናው ነገር የታለመው ህልም ከሰይጣን የመጣ ‹‹ሁሉም›› መሆኑንና ከፈጣሪ የመጣውን ‹‹እሩዕያ›› መለየቱ ላይ ነው፡፡ ‹‹ህልም አይተን ስንባንን ተገቢውን ፀሎት አድርሰን ደግመን ስንተኛ በድጋሚ ያየነው ህልም ከመጣ እሩእያ ነው ማለት ነው፡፡ ካልመጣ ግን ሁሉም ነው፤›› የሚሉት ኡስታዙ እሩዕያ ከሆነ ግን በአዋቂዎች እንደሚፈታ ይናገራሉ፡፡

ህልም የሰውን ማንነት ያንፀባርቃል የሚሉት ዶ/ር ዮናስ፤ ከዚህ ባለፈ ትርጉም ሊኖረውም ላይኖረውም እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይህንንም በህልማቸው ያዩዋቸውና በዕውን ያጋጠማቸውን በተቃራኒው ደግሞ በህልማቸው ያዩት ግን እንዲሁ ያለፈን ጉዳይ በማስታወስ ነው፡፡