Skip to main content
x
‹‹የግሉ ዘርፍ የሚያቀርባቸውን መፍትሔዎች በመጠቀም በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል››

‹‹የግሉ ዘርፍ የሚያቀርባቸውን መፍትሔዎች በመጠቀም በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል››

ሰርጂዮ ፒሜንታ፣ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ምክትል ፕሬዚዳንት

ሰርጂዮ ፒሜንታ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የተቋሙን የአፍሪካና የመካከኛው ምሥራቅ የኦፕሬሽን ሥራዎች እንዲመሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዓለም ባንክ የግሉ ዘርፍ ክንፍ የሆነው ይህ ተቋም የልማት ፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን በማቅረብ፣ በተለይም የግል ዘርፉን በመደገፍ የሚታወቅ የዓለም ባንክ አካል ነው፡፡ በአፍሪካና በመካከኛው ምሥራቅ ብቻ 600 ሠራተኞች ያሉትን ተቋም የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የማማከርና የኢንቨስትመንት ተልዕኮዎችን አቀናጅተው በመምራት እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ፈንድ ማንቀሳቀስ የሚችሉ ቁልፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ ግለ ታሪካቸው እንደሚሳየው፣ በኮርፖሬሽኑ አሁን ያላቸውን ደረጃ ከመያዛቸው ቀደም ብሎ በአይኤፍሲ የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የአግሪ ቢዝነስና የአገልግሎት ዘርፎችን በዓለም ደረጃ የሚያስተዳድሩበት የኃላፊነት ድርሻም ነበራቸው፡፡ ሚስተር ፒሜንታ የዓለም ባንክን እ.ኤ.አ. በ1996 ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ፣ በፈረሣንይ መንግሥት የፋይናንስ ሚኒስቴር ሥር በሚተዳደረው የመንግሥት ግምጃ ቤት ባልደረባ ነበሩ፡፡ ባንክ ናሽናል ደ ፓሪስ (ቢኤንፒ) የተሰኘው የፈረንሣይ መንግሥት ባንክንም አገልግለዋል፡፡ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመንግሥት፣ ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ ከዓለም ባንክና ከኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ከመጡባቸው ጉዳዮች መካከል አይኤፍሲ ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያውለው ከዓለም የልማት ማኅበር የተመደበለትን የሁለት ቢሊዮን ዶላር ፈንድ የተመለከተው አንደኛው እንደሆነ በተለይ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ መተግበር ስለጀመረው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ማዕቀፍ፣ አይኤፍሲ በኢትዮጵያ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት፣ በተለይም በኢትዮጵያ ከፀሐይ ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመርቱ በሚታሰቡ ፕሮጀቶች ዙሪያ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ትግበራ ሒደት የመንግሥት ተቋማት የድርድር አቅማቸው ምን ያህል ብቃት እንዳለውና በሌሎችም ነጥቦች ላይ ሚስተር ሰርጂዮ ፒሜንታን ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግሮ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ያመጣዎ ጉዳይ ምንድነው? ጉብኝትዎ በምን ላይ ያተኮረ ነበር?

ሚስተር ፒሜንታ፡- ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት አገሪቱ በጣም ጠቃሚ በመሆኗና በአፍሪካ ከሚካሄደው የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ብዙ ነገር ቢታይም፣ ካለው ድህነትና መልካም አጋጣሚ አኳያ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ከሚሠለፉት አገሮች የመጀመርያዋ ነች፡፡ የመጣሁት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮችንና የልማት አጋሮችን ብሎም እዚህ ያሉ የሥራ ባልደረቦቼን ለማግኘት ጭምር ነው ድጋፍ ማድረግ ብቻም ሳይሆን፣ ሁላችንም በጋራ የተሳሰርንበትና የተግባባንበት ጉዳይ ላይ በመሥራት አይኤፍሲ የኢትዮጵያን ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ እንዴት እንደሚደግፍና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ነው የመጣሁት፡፡

ሪፖርተር፡- የትራንስፎርሜሽን ጉዳይን ካነሱ ዘንዳ በኢትዮጵያ በርካታ ለውጦች እየተስዋሉ ነውና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከአይኤፍሲ ምን እንደሚፈልጉ ቢገልጹልን? ከዓለም ባንክስ ምንድነው የሚጠይቁት?

ሚስተር ፒሜንታ፡- ባለሥልጣናቱ በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ እንደሚፈልጉና በአገሪቱ የልማት ጉዳይ ምን ዓይነት ለውጥ መምጣት እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ ከዓለም ባንክ የሚፈልጉት በአገሪቱ የልማት ሒደት ላይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ነው፡፡ ከአይኤፍሲ በተለይ የሚፈልጉት ደግሞ ልምድና የድጋፍ ሥልቶቹን በመጠቀም የግሉን ዘርፍ እንዲያግዝላቸው ነው፡፡ አገሪቱ ብዙ ድጋፍ የሚያስፈልገው የግል ዘርፍ አላት፡፡ ከመንግሥት ዘርፍ አኳያ ሲታይ የግሉ ዘርፍ ብዙ ድጋፍና እገዛ የሚሻ ነው፡፡ በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችን በምናይበት ጊዜ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ ችግሮች ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ መንግሥታቱ ለልማት የሚያስፈልጋቸው በቂ ሀብት ባይኖራቸውም፣ የግሉ ዘርፍ በለውጥና በልማት ሒደት ውስጥ ትልቅ ተዋናይ ስለመሆኑ ግን ይገነዘባሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ ውሱን ድርሻ በያዘባቸው አገሮች ውስጥ በርካታ ዕድሎች መኖራቸው የታመነ ነው፡፡ በኢትዮጵያም እየታየ ያለው ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ፕሮግራም በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንደመሆኑ አይኤፍሲ በየትኞቹ መስኮች ላይ ቅድሚያ በመስጠት ይሳተፋል?

ሚስተር ፒሜንታ፡- የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍና አገሪቱን ሊደግፍ የሚችልባቸው በርካታ መስኮች አሉ፡፡ አንደኛው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት በጣም ጠንካራው መፍትሔ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉም አካላት ዕውቀትና ክህሎታቸውን በመጠቀም ተወዳዳሪ በሆኑባቸው መስኮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው፡፡ በአይኤፍሲ በኩል የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሞዴል አተገባበርን በንቃት በማበረታታት በመላው ዓለም ስኬታማ እንቅስቃሴ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር መንግሥታት በምን አግባብ የመንግሥትና የግል ዘርፉን አጋርነት ማዋቀር እንደሚገባቸው፣ ለአጋርነት ማዕቀፉ ምን ማሟላት እንደሚያስፈልጋቸው፣ በምን ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ፣ ብሎም ከአይኤፍሲ ወገን በሁለቱ አካላት ግንኙነት ሒደት ወቅት እንበልና መንግሥት የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍባቸው የሚፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በማማከር፣ በሁለቱ መካከል ለሚኖረው ግንኙነት መዋቅሩን በመዘርጋትና ጥራትና ብቃት ያላቸው ኩባንያዎች ከግሉ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚያስችል ቅድመ ታሪካቸው የታወቁና ሌሎች መመዘኛዎችን የሚያሟሉትን ለመመልመል የሚረዳ እገዛ እናደርጋለን፡፡ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር በአጋርነት እንዲሳተፉ የሚያስችል ሞዴል ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን በተመለከተ በቅርቡ 6.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የኤሌክትሪክ ኃይልና የመንገድ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ በፕሮጀክቶቹ በአብዛኛው የግሉ ዘርፍ እንደሚገባቸው ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ አካላት ከአይኤፍሲ ለዚሁ ጉዳይ የፋይናንስ ድጋፍ የጠየቁበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን?

 ሚስተር ፒሜንታ፡- በበርካታ አገሮች ውስጥ የግል ዘርፍ በኤሌክትሪክ ኃይል ማልማት ሥራ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ይታያል፡፡ ይህ የመጀመርያው የተሳትፎ ደረጃ ሲሆን፣ በአብዛኛውም የግሉ ዘርፍ ለተሳትፎ የሚገባው በዚህ ወቅት ነው፡፡ የሥርጭትና የማስተላለፍ ሥራዎችም አልፎ አልፎ በግሉ ዘርፍ ሲተዳደሩ ማየት ይቻላል፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥ የመንግሥትና የግሉ የጋራ የኢነርጂ ዘርፍ ተሳትፎ ስለሚታይ፣ ጠንካራ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካል በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ ለአገሪቱ የሚያስፈልገውን ተጠቃሚነት በማስገኘቱ ላይ ቁጥጥር የሚያደርግበት አሠራር አለ፡፡ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል መስክ የወደፊት ትልቅ ተስፋ አላት፡፡ ይሁንና ቀላል የማይባለው የሕዝብ ቁጥር የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኝም፡፡ ለዚህ ሕዝብ እንዴት ነው የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚቻለው? ለሚለው ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ አማራጮችንና መፍትሔዎችን ማየት ይጠበቅብናል፡፡ የግል ወይም የመንግሥት ኢንቨስትመንት ያስፈልግ እንደሆነ ማየት አለብን፡፡ አይኤፍሲ በአፍሪካ በርካታ የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ አድርጓል፡፡ በግል የለሙትም፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የለሙትም በኮርፖሬሽኑ በተገኘ ፋይናንስ የተከናወኑ በርካቶች ናቸው፡፡ የዓለም ባንክ ውስጥ የሚሠሩ አጋሮቻችንና የሥራ ባልደረቦቻችንም እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ላይ ያግዙናል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ ተዋናዮች ሊያግዝ የሚችል የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ ከሆነ ስለዚህ ሊነግሩን የሚችሉት ጉዳይ አለ?

ሚስተር ፒሜንታ፡- መንግሥትንና እዚህ ያሉ አጋሮቻችንን አነጋግረናል፡፡ ፍላጎታችን በዚህ አገር ውስጥ የምናከናውን ተግባር ይበልጥ ማሳደግ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ብዙም አከናውነናል፡፡ እየመጡ ካሉ ለውጦች አኳያም ከእስካሁኑ የበለጠ ብዙ መሥራት እንፈልጋለን፡፡ የተወሰነ ፕሮግራምና የተወሰነ ገንዘብ ይዘን አይደለም የምንመጣው፡፡ ነገር ግን በዚህ አገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ ለማገዝ ጭምር ነው የምንመጣው፡፡ በመሆኑም ይህ ነው የሚባል ይፋ የማደርገው ጉዳይ የለኝም፡፡ ይሁንና ከግሉና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በነበረኝ ምክክር ደስተኛ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ አብረን ልንሠራ የምንችልባቸው በርካታ ዕድሎች አሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚያመጣቸውን መፍትሔዎች በመጠቀም በኢትዮጵያ በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ አንደኛው ቁልፍ ፈተና የሥራ ዕድል መፍጠርና ወጣቶች፣ ሴቶችና መሥራት ለሚችለው የሕዝብ ቁጥር ትርጉም ያላቸው የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ ለማስቻል የሚረዱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን መፍጠር ያስፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ከአፍሪካም አኳያ ሲታይ የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ አቅርቦት፣ ብሎም ከአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ ከመሆን አኳያ በጣም ዝቅተኛ ተሳትፎ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይህንን ሊያሻሽሉ የሚችሉ አዳዲስ ሥልቶችና አካሄዶች አሉ?

ሚስተር ፒሜንታ፡- በጠቀስከው ነጥብ ላይ ለሙሉ ለሙሉ መስማማት ይቸግረኛል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ኦፕሬሽኖችን በኢትዮጵያ አካሂደናል፡፡ የኢትየጵያ የግሉ ዘርፍ በበርካታ መስኮች አብሮን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የተወሰኑትም ከእኛ ጋር ጥሩ የተጠቃሚነት ድርሻ እንዳላቸውና ወደፊትም ብዙ ለመሥራት ካለን ተነሳሽነት አኳያ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ አዳዲስ ሥልቶችና አካሄዶች ወይም አሠራሮችን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ፣ አዳዲስ ሥልቶችን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ማስተዋወቅ እንደጀመርን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡  አዲሱ ሥልት የዓለም የልማት ማኅበር ለግሉ ዘርፍ ያቀረበው አዲስ የተጠቃሚነት መስኮት ብለን የምንጠራው ፕሮግራም ተዘርግቷል፡፡ የዓለም የልማት ማኅበር የዓለም ባንክ የልማት ክንፍ በመሆኑ፣ በደሃ አገሮች ውስጥ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ገንዘብ የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡ ማኅበሩ ለአይኤፍሲ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚነት መስኮት ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ድጋፍ ይሆን ዘንድ ይህ ፈንድ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ኢትዮጵያ ከፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን መሥፈርቶቹን ስለምታሟላ የአገሪቱ የግል ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን ይችላል፡፡ የእኔም አንደኛው የጉብኝት ዓላማ ይህንን ፈንድ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ጋር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ነው፡፡ ከተገኘው ፈንድ ውስጥ ሥጋት ያለባቸውን ፕሮጀክቶች ሥጋታቸው እንዲቀንስ በማድረግ፣ በርካቶች እንዲሳተፉ ለማድረግና በሚሳተፉበት መስክ የሚፈለገውን ተፅዕኖ ለመፍጠር እንዲችሉ የሥጋት ደረጃዎችን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የግሉ ዘርፍ ከሁለት ቢሊዮን ዶላሩ መቼ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ቢገልጹልን?

ሚስተር ፒሜንታ፡- ተስፋ የማደርገው በቅርቡ ተጠቃሚ መሆን እንደሚጀምር ነው፡፡ ይሁንና ገና ጅምር ሒደቱ ላይ በመሆናችን ገንዘቡን ጥቅም ላይ በማዋሉ ረገድ ገና ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን አስፈላጊውን ፈንድ በአግሪ ቢዝነስ ላይ ማዋል እንደሚቻል እናስባለን፡፡ ለማኑፋክቸሪንግ መስክ መንግሥት ለኢንዱስትሪዎች በተለይም ወደ ውጭ ምርቶቻቸውን ለሚልኩና የውጭ ምንዛሪ ለሚያስገኙ ኩባንያዎች ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ እኛም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚውል ፈንድ ማቅረብ እንደምንችል እናስባለን፡፡ እንዲህ ላሉት ዘርፎችና ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደምንችል ይታሰባል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ቢሊዮን ዶላሩ ውስጥ ለኢትዮጵያ የሚውለው መጠን ምን ያህል እንደሆነ ቢጥቀሱ?

ሚስተር ፒሜንታ፡- ገንዘቡ መመዘኛውን ለሚያሟሉ አገሮች የሚውል ነው፡፡ በአገር ደረጃ ተመድቦና ተከፋፍሎ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ የድጋፍ መስኮቱን በሚቻላት መጠን እንድትጠቀምበት፣ ትልቁን ፈንድም በዚህ አገር ለማዋል እንዲቻል እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ማዕቀፉ እንመለስ፡፡ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የግሉና የመንግሥት አጋርነት ሥርዓት ውስጥ ተሳትፎ ማድረጉ የታወቀ ነው፡፡ አይኤፍሲ በኢትዮጵያ የግልና የመንግሥት አጋርነት ሥርዓት ውስጥ ስላካሄዳቸው ተግባራት ቢጠቅሱልን?

ሚስተር ፒሜንታ፡- አሁን ባለው ደረጃ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎ አላደረግንም፡፡ የዓለም ባንክ በግልና በመንግሥት የአጋርነት ሥራዎች ውስጥ፣ በተለይም በሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ዘርፉን እንዴት መምራትና መቆጣጠር እንደሚቻል የሚያግዙ ሥራዎችን በመሥራት ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ዕውን የሚያደርግበትን ሒደት አግዟል፡፡ የግልና የመንግሥት አጋርነት ክፍል እንዲቋቋም ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ መንግሥት በተወሰኑ ዘርፎች ውስጥ የግሉ ዘርፍ መሳተፍ ስለሚችልባቸው መንገዶች ይፋ አድርጓል፡፡ በአጋርነት የሚለሙ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡ እኛም እነዚህ ዘርፎችን በንቃት እየተከታተልን ድጋፍ መስጠት በምንችልባቸው ላይ ለመሳተፍ ፍላጎቱ አለን፡፡ አንዴ መንግሥት የግሉ ዘርፍ እንዲገባ ከወሰነ እኛም የግሉ ዘርፍ በምን አግባብ እንደሚገባ፣ ምን መሥራት እንደሚችልና እንደሚጠበቅባቸው፣ ምን ያህል ሥጋት ያለባቸው መስኮች ውስጥ መሳተፍ እንደሚችልና መንግሥትም ከግሉና ከመንግሥት አጋርነት ፕሮጀክቶች ገቢ ማግኘት ስለሚችልባቸው ጉዳዮች ድጋፍ ማድረግ እንችላለን፡፡ እንዲህ ባሉት መስኮች ላይ ሥራ መሥራት እንደምንችል እንጠብቃለን፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የአይኤፍሲ ቡድን ከመንግሥት ጋር በመነጋገር፣ ድጋፍ ልንሰጥባቸው የምንችላቸው ፕሮጀክቶች የትኞቹ እንደሆኑ በመለየት ሒደት ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ባለሙያዎች የግሉና የመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍ የመጨረሻውን ተጠቃሚ ይበልጡን ለወጪ የሚዳርግና ተጎጂነቱን የሚያባብስ ሥርዓት እንደሆነ ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ ለአብነትም ኩባንያዎች በኤሌክትሪክ ኃይል መስክ ለመሳተፍ ድርድር ሲደረጉ ከነበሩባቸው ነጥቦች አንደኛው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ይሻሻል በሚለው ላይ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህም በኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ላይ የዋጋ ጭማሪ በማስከተል ተጠቃሚው ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም በራሳቸው ኃይል አልምተው ለመንግሥት ለመሸጥ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለው የታሪፍ ዋጋ ለምርት ከሚወጣውም ያነሰ ነው በማለት ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም እርስዎ የግልና የመንግሥት አጋርነት እንዲህ ያሉ ጫናዎችን አያመጣም ይላሉ?

ሚስተር ፒሜንታ፡- ጫና ማምጣት የለበትም፡፡ ሊያመጣም አይገባም፡፡ የግልና የመንግሥት አጋርነትን በአግባቡ ካዋቀርከው የግሉ ዘርፍ በሚገባበት ወቅት የራሱን ልምድ፣ ዕውቀትና ክህሎት ይዞ በመምጣት የምርት ወጪን ለመቀነስ የሚረዱ ሥራዎችን እንዲተገብር ያስችለዋል፡፡ የኢነርጂ ዘርፍ የታሪፍ ቅናሽ የሚያሳየው በመንግሥት ስለሚደጎም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ሰው ዋጋውን ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ተጠቃሚው ላያስተውለው ይችላል፡፡ ነገር ግን ታክስ ሲከፍል ሊያየው ወይም ሊገነዘበው ይችላል፡፡ ምክንያቱም የድጎማው መጠን በጨመረ ቁጥር ታክስ ሊጨምርበት ስለሚችል ነው፡፡ ነገር ግን የግልና የመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍን በመፍጠርና የግሉ ዘርፍም በሚገባ እንዲሳተፍ ሲደረግ ዋጋዎች ይቀንሳሉ፡፡ ሌሎችም ወጪን ሊቀንሱ የሚችሉ አሠራሮች ይተገበራሉ፡፡ በኢነርጂ ዘርፍ ‹‹ስኬሊንግ ሶላር›› የተሰኘ ፕሮግራም በመተግበር ትልቅ ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ይህንን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለመተግበር ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ ስኬሊንግ ሶላር ከዓለም ባንክ ጋር በአጋርነት የሚካሄድ ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም መሠረት ሥጋት የሚታይባቸውን ሁኔታዎች በመቀነስ፣ የግሉ ዘርፍ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ በመሳተፍ እንዲመጣ የምናደርግበት ነው፡፡ ሥጋቶች በመቀነሳቸው የዓለም ባንክም ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችንና ደረጃቸውን የጠበቁ ሰነዶችን ብሎም ሌሎችም ሒደቶችን ስለሚያግዝ፣ ሁሉም አካላት በእኩል ደረጃና ወጥ በሆነ አሠራር መሠረት የሚሳተፉበት መድረክ ያገኛሉ፡፡ ተጫራቾች እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል እናምርት ብለው መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን በዛምቢያ ዓይተነዋል፡፡ በሶላር ኢንርጂ መስክ ስድስት የአሜሪካ ሳንቲም በሰዓት ኪሎ ዋት አወር ለተገልጋዩ ማቅረብ ተችሏል፡፡ በሴኔጋልም ከዚህ ባነሰ ዋጋ በአምስት የአሜሪካ ሳንቲም አንድ ኪሎ ዋት አወር ማቅረብ ተችሏል፡፡ እነዚህ በጣም ዝቅተኛ ክፍያዎች ናቸው፡፡ የሶላር ኃይልን ጨምሮ በየትኛውም አካባቢ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል የምርት ዋጋ ደረጃ ካየህ፣ በስኬሊንግ ሶላር ፕሮግራም አማካይት የሚተገበረው ላይ ዝቅተኛ ዋጋ እንደሚጠየቅበት ትገዘነባለህ፡፡ እንዲህ ካለው ርካሽ ዋጋ ተጠቃሚው ተገልጋዩ በመሆኑ የተመረው ምርት ለኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያው ይቀርብለትና እንዲያሠራጨው ይደረጋል ማለት ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ መፍትሔዎች በምትጠቀምበት ጊዜ በአግባቡ የተዋቀሩና ተፈላጊውን ጥቅም እንዲያስገኙ በሚገባ የተደራጁ ከሆኑ ዋጋን ዝቅ እንዲል በማድረግ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁሉም በተመጣጣኝ ታሪፍ እንዲዳረስ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- የግልና የመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍ ሲነሳ አንደኛው ጥያቄ የመንግሥት ተቋማት የመደራደር ብቃትና አቅም ምን ያህል ነው የሚለው ጉዳይ ይነሳል፡፡ በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ከግል ኩባንያዎች ጋር የሚደራደሩበት ብቃትና ደረጃ እንዴት ይታያል?

ሚስተር ፒሜንታ፡-  በእኛ በኩል ጥያቄው ከአቅም ግንባታ ጋር የሚያያዝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ የመንግሥት ተቋማት አሉ፡፡ እኛም የበለጠ ልናግዛቸው የምንችለበት ዕድል ስላለን ደስተኞች ነን፡፡ የልማት ተቋም እንደ መሆናችን መጠን የኢትዮጵያን ልማት ለማገዝ ነው የመጣነው፡፡ በእኛ በኩል የተቋቋመው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ቡድንም ይህንኑ በመወጣት ላይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቡድኑ ከኩባንያዎች ጋር አይደራደርም፡፡ ነገር ግን በድርድር ሒደቱ ላይ መንግሥትን ያግዛሉ፡፡ የሚመጡት ኩባንያዎች የሚያቀርቧቸው በርካታ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከልክ ያለፈ ማበረታቻ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ የድርድር ሰነድ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እኛ መንግሥትን የምንመክረው ደረጃውን የጠበቀና ተቀባይነት ያለው፣ ብሎም በዓለም ዙሪያ የሚተገበር መነሻ የድርድር ማዕቀፍ እንዳለና በዚያ መሠረት እንዲደራደር እናግዘዋለን ማለት ነው፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ተደራዳሪ የመንግሥት ተቋማት ግልጽ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ ሥርዓትን በድርድር ሒደቱ ላይ እንዲተገብሩ እናግዛቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የስኬሊንግ ሶላር ፕሮግራም ካነሱ አይቀር አራት ያህል ፕሮጀክቶች በመንግሥት ለግሉና ለመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍ ተለይተው እንዲለሙ የሚያስታውቅ መረጃ ወጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ተሳትፏል ማለት ነው?

ሚስተር ፒሜንታ፡- በኢትዮጵያ የስኬሊንግ ሶላር ፕሮግራምን አይኤፍሲ ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቶቹ በጠቅላላው 500 ሜጋ ዋት ከፀሐይ ኢነርጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገኘት የሚያስችሉ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ምዕራፍ በ250 ሜጋ ዋት ኃይል ይጀመራል፡፡ በሚጠናቀቅበት ጊዜም በአፍሪካ ትልቁ የሶላር ኢንርጂ ፕሮጀክት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እስካሁን በጥሩ ደረጃ እየተጓዘ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁና እንዲሳተፉ በሚጠይቀው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ አስፈላጊውን ሥራ በማጠናቀቅ ለጨረታ ሒደቱ እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ አዋጭና ተስማሚ ዋጋ ያላቸውን ሥራዎች በማቅረብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተጠቃሚ እንደምናደርግ ተስፋ አለን፡፡ አዋጭ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከሌለ አነስተኛ ኩባንያዎችን ማገዝ አይቻልም፡፡ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በአዋጭና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ካልተቻለ ግለሰቦችም የየራሳቸውን የንግድ ሥራዎች በመፍጠር እንዲሳተፉ፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ፋብሪካዎችና ሌሎችም ተቋማት ውጤታማ ሆነው እንዲሠሩ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡  የኢነርጂ አቅርቦት በጣም ወሳኝና መሠረታዊ አገልግሎት በመሆኑ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ቁጥሮችን ስንመለከትበት በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪል ኃይል አቅርቦት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህንን ለማሻሻል በጋራ መሥራት የምንችልባቸው መፍትሔዎች ላይ በመንቀሳቀስ፣ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እንዲኖር ለማስቻል የምናግዛባቸው ሰፊ መስኮች አሉ፡፡