Skip to main content
x
ብሔራዊ ባንክ አገር በቀል አምራቾች ላይ ያወጣውን አግላይ መመርያ እንዲያሻሽል ተጠየቀ
የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ

ብሔራዊ ባንክ አገር በቀል አምራቾች ላይ ያወጣውን አግላይ መመርያ እንዲያሻሽል ተጠየቀ

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሩን እፈታለሁ አለ

አገር በቀል ፋብሪካዎች ከጨዋታ እየወጣን ነው አሉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አገር በቀል አምራቾች አግሏል የተባለውን የውጭ አገር ብድርና ዱቤ ሽያጭ መመርያ እንዲያሻሽል፣ 18 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ጥያቄ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. የውጭ አገር ብድርና የዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ የፈጠረውን ችግርና ሌሎች በፍጥነት መሻሻል አለባቸው የተባሉ አጀንዳዎችን ይዞ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጋር ተወያይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የሚወክላቸው 18 ባንኮች ያበደሯቸው አገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ብድራቸውን መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ስለሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ የውጭ አገር ብድር የዱቤ ሽያጭ መመርያና የውጭ ምንዛሪ ወረፋ አሠራሩን እንዲያስተካክል ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ በተበዳሪዎች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

‹‹በውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ እንዲሻሻል ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርበን ተወያይተናል፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ቁርጥ ያለ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘንም፤›› ሲሉ አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ብድርና ዱቤ ሽያጭ በውጭ ምንዛሪ የሚቸገሩ አገሮች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦታቸውን እስኪያስተካክሉ ድረስ በጊዜያዊነት የሚጠቀሙበት አሠራር ነው፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ያወጣው የውጭ ብድርና የዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ ለውጭ ድርጅቶችና ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ኩባንያዎች ፈቅዶ፣ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት የሚተኩ አገር በቀል አምራቾችን ያገለለ በመሆኑ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡

የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ መመርያ አገር በቀል ፋብሪካዎችና አበዳሪ ባንኮች ላይ ከተጋረጡ ወቅታዊ አደጋዎች ተርታ የተመደበ፣ እንዲሁም አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

የባንኮችም ሆነ የአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች የቅሬታቸው መነሻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገው የውጭ አገር ብድርና የዱቤ ሽያጭ አቅርቦት መመርያ አንቀጽ አራት ላይ የተደነገገው ዋነኛ ነጥብ ነው፡፡

የመመርያው አንቀጽ አራት ኤክስፖርት የሚያደርጉ ኩባንያዎችና በውጭ አገር ባለቤቶች የተቋቋሙ ኢንቨስትመንቶችን ብቻ፣ በተናጠል የውጭ አገር የዱቤ ሽያጭ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ነገር ግን በመስከረም 2005 ዓ.ም. የወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2005 በብድና በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ኢንቨስተሮች ልዩነት ባያደርግም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ያዋጣው መመርያ ቁጥር FXD/47/2017 ግን ልዩነት አድርጓል፡፡ ይህ መመርያ የአገሪቱን አዋጅ የሚቃረን እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ መመርያ በተለይ በሳሙናና በዲተርጀንት ምርት ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ በኬሚካል ኢንዱስትሪ የፕላስቲክ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም የፓልፕና የወረቀት ኢንዱስትሪዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ እየተነገረ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፋብሪካ ባለቤቶች እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ ለዘለቄታው የሚፈታው የወጪ ንግድ ሲያድግ መሆኑን ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣባቸው ስትራቴጂካዊ ገቢ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ሲደረግ ነው፡፡ ነገር ግን የኤክስፖርት ማበረታቻና የገቢ ምርቶችን የመተካት ጥረት በብሔራዊ ባንክ መመርያ ተመጣጥነው አልተስተናገዱም ይላሉ፡፡

ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርቱ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ በመስጠት፣ በኢትጵያውያን ባለሀብቶች አገር ውስጥ የተቋቋሙ ማምረቻዎች ከጨዋታ ውጪ ሊያደርጉ የሚችሉ አሠራሮች በመመርያው ተመቻችተው ተቀምጠዋል በማለት የፋብሪካ ባለቤቶች የችግሩን ጥልቀት ያስረዳሉ፡፡

የፋብሪካ ባለቤቶቹ ጨምረው እንደገለጹት፣ አንድ ዓይነት ምርት የሚያመርቱ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች እኩል አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡ የውጭ ኩባንያዎች የበለጠ ተጠቃሚ በመሆናቸው የውድድር ሜዳው ከመበላሸቱ በተጨማሪ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የፋብሪካዎቻቸውን አክሲዮን ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘም የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ውስን በመሆኑና ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው መሥራት ባለመቻላቸው ሠራተኛ መበተን፣ እንዲሁም በባንኮች የመወረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው እየተናገሩ ነው፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የግል ባንክ ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የውጭ አቅራቢዎች የዱቤ ሽያጭ አገልግሎት ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች መስጠት ልዩነት የለውም፡፡ ዞሮ ዞሮ ክፍያ የሚፈጸመው ከአገሪቱ ግምጃ ቤት ወይም ከባንኮች እንደመሆኑ፣ አገልግሎት መስጠቱ ካልቀረ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች መሆን ነበረበት ብለዋል፡፡

‹‹የውጭ ኩባንያዎች ከራሳቸው ምንጭ የውጭ ምንዛሪ ይዘው መጥተው መሥራት ነበረባቸው፤›› ሲሉ እኚሁ የባንክ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

ሌላው የአገር በቀል አምራቾች ፈተና የሆነው፣ በባንኮች እየተመዘገበ ያለው የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ጉዳይ ነው፡፡ አገር በቀል አምራቾች እንደሚሉት የውጭ ምንዛሪ ወረፋ ምዝገባ የይስሙላ ነው፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች በሚሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ወረፋ በተለያዩ የግል ንግድ ባንኮች ውስጥ በመያዝ ቅድሚያ ሲያገኙ፣ አገር በቀሎች ግን ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ የራሳቸውን ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ የሚያገኙት ከባንኮች የተበደሩ ባለ ኢንዱስትሪዎች ሳይሆኑ፣ በጥሬ ዕቃና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዕቃዎች ሰበብ አስመጪዎች ናቸው፤›› ሲሉ የፋብሪካ ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አሁን ያለውን የተዛባ የውጭ ምንዛሪ ምደባ ለማቃለል አስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚመደበው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነ መቶኛ በቅድሚያ እንዲያስይዙ ማድረግና ባንኮቹ ሁኔታውን እያዩ ለአምራቾች ቅድሚያ በመስጠት እንዲስተናገዱ፣ ይህንንም በየጊዜው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡

እንደ አዲስ እየተዋቀረ የሚገኘው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ላይ የተፈጠረውን ችግር እንደተረዳ አስታውቋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አገር በቀል አምራቾች የውጭ አቅራቢዎች ዱቤ ሽያጭ አሠራር ችግር እንዳመጣባቸው ሚኒስቴሩ ይረዳል፡፡

‹‹ችግሩን በፍጥነት ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁመን ጥናት እያካሄድን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ጥናቱ እየተገባደደ በመሆኑ የተፈጠረው ችግር ይፈታል፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ጨምረው እንደገለጹት፣ ሁለቱ ሚኒስቴሮች (ንግድና ኢንዱስትሪ) ተዋህደው በድጋሚ በአንድ ተቋም እየተዋቀሩ ነው፡፡ የሚኒስቴሩ ትልቁ ትኩረት የአገር ውስጥ አምራቾች ያለባቸውን ችግር መፍታት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡