Skip to main content
x

አዋሽ ኢንሹራንስ 140 ሚሊዮን ብር አተረፈ

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ክሲዮን ማኅበር በ2010 ዓ.ም. ከታክስ በፊት (ያልተጣራ) 140 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 128 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ፡፡

ኩባንያው የ2010 ዓ.ም. ሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው መረጃ፣  በተጠናቀቀው ዓመት ያስመዘገበው የተጣራ ትርፍ ከ2009 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ46 በመቶ ብልጫ ታይቶበታል፡፡ ይህ የትርፍ መጠንም ከፍተኛ ትርፍ ካስመዘገቡ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተርታ አስቀምጦታል፡፡

ኩባንያው በጠቅላላ መድን ሥራ 604.6 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም 11 በመቶ ዕድገት እንደታየበት ያመለክታል፡፡ በሕይወት መድን ሥራ ዘርፍም ከ69.5 ሚሊዮን ብር በላይዓረቦን ገቢ በማሰባሰብ 27 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በሁለቱም የሥራ ዘርፎች በጠቅላላው 674.1 ሚሊዮን ብር ዓረቦን  ገቢ በመሰብሰብ 12.5 በመቶ ዕድገትማሳየት በቅቷል፡፡

ኩባንያው በጠቅላላ መድን ሥራ ዘርፍ ብቻ 246.66 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ በማስተናገዱ፣ ከዚህ ውስጥ 74 በመቶ ወይም 233.97 ሚሊዮን ብር በሞተር የሥራ ዘርፍ ብቻ ያጋጠመውካሳ ጥያቄ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ የካሳ ክፍያ መጠኑ በመቶኛ ሲሰላ የ57 በመቶ የክፍያ ጥያቄውን ሬሾ የያዘ በመሆኑ፣ ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑ ኩባንያው ይጠቅሳል፡፡ በጠቅላላ የመድን ሥራ ዘርፍና በሕይወት ኢንሹራንስ የሥራ ዘርፍ የሰበሰበው የዓረቦን  ገቢ ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለተከታታይ ዓመታት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን የሚገልጸው የኩባንያው መረጃ፣ የገበያ ድርሻውን እያሰፋ መምጣቱ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱና በኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል እንዳስቻለው ያመለክታል፡፡

ኩባንያው ከመድን ሥራው ባሻገር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮችም በመሰማራቱ፣ በ2010 ዓ.ም. መዋዕለ ነዋዩን ስላፈሰሰባቸው የኢንቨስትመንት ዓይነቶች አስታውቋል፡፡ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች 60.3 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል በቦሌ ፍለ ከተማ በመገንባት ላይ የነበረውን ባለአራት ወለል ጅምር ሕንፃ 51 ሚሊዮን ብር መግዛቱ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በልደታ ፍለ ከተማሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል የቤት ግዥ ፈጽሟል፡፡ 1.6 ሚሊዮን ብር ከሁለት ተቋማት አክሲዮኖችን ገዝቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ‹‹ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ›› ለተሰኘው ሶፍትዌር  ግዥ 4.7 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የአውቶሜሽን ፕሮጀክቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ችያለሁ ብሏል፡፡

የአጠቃላይ ኢንሹራንስ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ፕሮግራምን ውጤታማ ለማድረግ በመዲናችንና በመላው አገሪቱ የሚገኙ ቅርንጫፎችን ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ በመረጃ መረብ በማስተሳሰር በኢንዱስትሪው ፈር ቀዳጅና እጅግ የተሳካ ተግባር እንዳከናወነም የኩባንያ መግለጫ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የተቀናጀና ቀልጣፋ አገልግሎት ለተጠቃሚው በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኩባንያው ቋሚ ሠራተኞች ብዛት 514 የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም 50.2 በመቶ ወይም 258ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ኩባንያው ሁለት አዳዲስ ቅርንጫፎችንና አራት አገናኝ ቢሮዎችን ከመክፈቱም በተጨማሪ እስከተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ድረስኩባንያው ቅርንጫፍ መሥሪቤቶች ብዛት አንድ የሕይወት ዓብይ ቅርንጫፍን ጨምሮ 46 ያደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህ በተጨማሪ አራት አገናኝ ቢሮዎችም ያሉት በመሆኑ አጠቃላይ የአገልግሎት መስጫዎቹ ብዛት 50 ደርሰዋል፡፡ በተጨማሪም የኩባንያው የሽያጭ ወኪሎች ብዛት 470 በላይ በመድረሱ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ማመላከቻ አድርጎታል፡፡ እስካለፈው ሰኔ ድረስ የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 277.13 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ የሀብት መጠኑም ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ታኅሳስ 23 ቀን 1987 ዓ.ም. ተመሥርቶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በምሥረታው ወቅት የነበሩት ባለአክሲዮኖች ብዛትም 456 ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን 1285 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት የኩባንያው  መረጃ ይጠቁማል፡፡