Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ዲፕሎማት ስልክ ይደውላሉ

ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ዲፕሎማት ስልክ ይደውላሉ

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰላም ወዳጄ፡፡
 • ጠፍተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያው የእኛን ሥራ እያወቅከው?
 • እሱማ አሁን የባሰ ሥራ እንደሚበዛብዎት አውቃለሁ፡፡
 • ይኸው ለውጡን ለማሳለጥ ከፍ ዝቅ እያልን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በእርግጥ ስለለውጡ እኛም ከጎናችሁ ነን፡፡
 • ምን ነካህ ለውጡ ያለእናንተ ድጋፍ የትም አይደርስም፡፡
 • ስለእሱማ አያስቡ፣ ሁሌም ከጎናችሁ ነን፡፡
 • እሱንማ እኛም እናውቃለን፡፡
 • ለመሆኑ ለውጡ እንዴት እየሄደ ነው?
 • እንደምታየው አገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ደፋ ቀና እያልን ነው፡፡
 • በእርግጥ እያደረጋችሁት ያለው ለውጥ አበረታች ነው፡፡
 • አዲሱን የሚኒስትሮች ሹመት መቼም በሚገባ ተከታትለኸዋል፡፡
 • እያንዳንዱን ነገር ነው የምከታተለው፡፡
 • ታዲያ እንዴት አገኘኸው?
 • በእውነት ሴቶችን ወደ ሥልጣን ለማምጣት ያላችሁን ቆራጥነት አድንቄዋለሁ፡፡
 • ስማ ገና ከዚህ በላይ ትገረማለህ፡፡
 • በምን?
 • ከዚህም በላይ ሴቶችን ወደ ሥልጣን ለማምጣት ወሰነናል፡፡
 • እሱማ የአገሪቱን ፕሬዚዳንትም ሴት ማድረጋችሁ የቆራጥነታችሁ ማሳያ ነው፡፡
 • ብንችልማ ሙሉ ለሙሉ የመንግሥትን ሥልጣን ለሴቶቹ ሰጥተን ብንገላገል ይሻለናል፡፡
 • ከዚያ ከሚኒስትርነት ወደ ወንዶች መብት ተሟጋችነት ይቀየራሉዋ?
 • መቼም ቀልደኛ ነህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለውጡ ግን በሌላ በኩል እያሳሰበኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰበህ?
 • በቃ ሥርዓተ አልበኝነት በየቦታው ነው የሚታየው፡፡
 • ያው አለቃችን እንዳሉት ታፍኖ የነበረ ሰው ሲለቀቅ ብዙ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
 • አይ ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር አንዳንድ ቦታዎች የምናያቸው ሁኔታዎች በአስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጣቸው አሳሳቢ ይመስሉኛል፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ዛሬ ታዲያ ከየት ተገኙ?
 • አንድ ነገር ላማክርህ ብዬ ነው፡፡
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ጓደኛዬ በጡረታ አገለልነውና እናንተ ጋ ልከነው ነበር፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • ያው የኃላፊነቱን ቦታ በወጣቶች እየተካነው ስለሆነ እሱ እናንተ ጋ ቢመጣ ይሻላል ብለን ነው የላክነው፡፡
 • ታዲያ ምን ልርዳዎት?
 • እናንተ ግን አንቀበለውም ብላችሁታል፡፡
 • እ. . . ክቡር ሚኒስትር ለአምባሳደርነቱ የላካችሁትን ግለሰብ ነው?
 • አዎን ወዳጄ፡፡
 • ያው እንደሚያውቁት ክቡር ሚኒስትር፣ ሁሌም አምባሳደሮች ሲሾሙ በራሳችን የማጣራት ሥራ እናከናውናለን፡፡
 • ታዲያ ምን አግኝታችሁበት ነው?
 • ከፍተኛ የሆነ የማስፈጸም ችግር እንዳበት ተረድተናል፡፡
 • እዚህ ጋ እንዳትሳሳት፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰውዬ እንዲያውም ከፍተኛ የሆነ የማስፈጸም ብቃት ነው ያለው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደምታውቀው እኛ እንደ አገር የመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ እየሠራን ነው፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • ሰውዬው ከአገራችን በፊት በግሉ ከእነሱ አገሮች ተርታ መሠለፍ ችሏል፡፡
 • እ. . .
 • እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን ከድህነት ወለል በታች አንስቶ እሱ የደረሰበት ደረጃ አድርሷል፡፡
 • ምን ይቀልዳሉ?
 • ብቻ ምን አለፋህ አገሪቱ 11 በመቶ እንድታድግ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የነበረው እሱ ነው፡፡
 • እና ምን እያሉ ነው?
 • እኛም እናንተ ጋ የመደብነው እናንተም ከእኛ ተምራችሁ እንደ እኛ የምታድጉበትን መንገድ ያሳያችኋል ብለን ነው፡፡
 • አሁን አረጋገጡልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምኑን?
 • የወሰነው ውሳኔ ትክክል መሆኑን፡፡
 • ምን ነካህ ወዳጄ ከእሱ እኮ ብዙ ትማራላችሁ እያልኩህ ነው?
 • ከእሱ የምንማረው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • ሌብነት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከጸሐፊያቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምነው የከፋሽ ትመስያለሽ?
 • መቼም የእኔን ሥራ ከእርስዎ የበለጠ የሚረዳው የለም፡፡
 • አልገባኝም?
 • ያው በሥራዬ ላይ ምንም ዓይነት ግድፈትና ችግር ታይቶብኝ አይታወቅም፡፡
 • እሱስ ጥሩ ሰው ነሽ፡፡
 • እኔ አንድም ቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል የእርስዎን የራስ ምታት ለማቅለል ሁሌም ተግቼ ነው የምሠራው፡፡
 • ይኼንን ሁሉ ለምንድነው የምትነግሪኝ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሥራዬ ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም፡፡
 • ሰርተፊኬት ፈልገሽ ነው?
 • ይኼማ በሰርተፊኬት የሚታለፍ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ደመወዝ ጭማሪ ነው?
 • ደመወዝ ጭማሪም አይደለም፡፡
 • የደረጃ ዕድገት ነው የፈለግሽው?
 • የተግባባን አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን እያልሽ ነው ታዲያ?
 • አሁን በአገሪቱ እየመጣ ያለው ለውጥ እንዴት እንደመጣ ያውቃሉ?
 • በዋናነት ሕዝቦች ጭቆና በቃኝ ስላሉ ነዋ፡፡
 • እንዳይመስልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ በምንድነው የመጣው?
 • እኔ ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ለእመብርሃን ሻማ አበራ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • ይኼው እሷም ፀሎቴን ሰምታ ግማሹን ካቢኔ ሴት አድርጋዋለች፡፡
 • እ. . .
 • ምን እሱ ብቻ ክቡር ሚኒስትር? ፕሬዚዳንት ሴት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሴት ናቸው የተሾሙት፡፡
 • የለውጡ ዋና ተጠያቂ እመብርሃን ናት እያልሺኝ ነው?
 • እንደዚያ ሳይሆን የለውጡ ውጤት ያስደስታል እያልኩዎት ነው፡፡
 • ስለዚህ ምን ይደረግ?
 • እኔም የዚህ ለውጥ አካል መሆን አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡
 • ለመሆኑ አንቺ ትምህርትሽ ምንድነው?
 • እንደሚያውቁት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ዲግሪ አለኝ፡፡ ማስተርሴንም ጀምሬ ኃላፊነት ስለበዛብኝ ነው ያቋረጥኩት፡፡
 • ታዲያ ዲግሪ ይዘሽ ነው የምትንጫጪው?
 • መቼም ከእርስዎ የፌክ የተልዕኮ ዲግሪ ይሻላል፡፡
 • ምንድነው ያልሽው?
 • ሰምተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እ . . .  
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ልምዱም አለኝ፣ ብቃቱም አለኝ፣ ከእርስዎ የምፈልገው ሪኮመንድ እንዲያደርጉልኝ ነው፡፡
 • ለምንነት?
 • ለሚኒስትርነት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር ምንድነው?
 • ምነው ወዳጄ?
 • በየሄድኩበት የእርስዎ ስም እኮ በጥሩ አይነሳም፡፡
 • አልገባኝም?
 • የመንግሥት ችግር በተወራ ቁጥር የእርስዎ ስም ሳይነሳ አይቀርም፡፡
 • ስማ ተረቱን አታውቀውም እንዴ?
 • የምን ተረት?
 • ውሾቹም ጩኸታቸውን ይቀጥሉ፣ ግመሎቹም ጉዟቸውን አያቋርጡም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ለምንድነው ሁሌ ከብልሹ አሠራር ጋር ስምዎ የሚነሳው?
 • የምን ብልሹ አሠራር ነው?
 • ይኼው መሥሪያ ቤትዎ በዘርና በወንዝ ብቻ ነው ሥራ የሚሠራው፡፡
 • ምንድነው የምትለው?
 • ሰዎች እርስዎ ጋ የሚገቡት በዘር ካልሆነ በስተቀር በብቃታቸው አይደለም፡፡
 • እኔ ስማ ከምንም ነገር በላይ ለብቃት ነው ቦታ የምሰጠው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እውነታው ግን መሥሪያ ቤትዎት በዘርና በወንዝ ተጠላልፎ ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡
 • ይኼ የምቀኛ ወሬ ነው ስልህ?
 • በዚያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ብክነት ነው ያለው፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር የሕዝብና የመንግሥትን ሀብት እንደ ውርስ ንብረት ነው የሚያዙበት ይባላል፡፡
 • መቼም የሚሠራ ሰው ላይ እኮ ወሬ በዛበታል?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህ ጉዳይ እንኳን አፍ ያለዎት አይመስለኝም፡፡
 • እንዴት?
 • ያው ዘመኑ የይቅርታና የፍቅር ነው ተብሎ እንጂ እርስዎ የሚገባዎት ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
 • ምንድነው የሚገባኝ?
 • ጓንታናሞ ነዋ፡፡
 • አንተ ደግሞ ታበዛዋለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ የሙሰኞች አባት ነው የሚባሉት፡፡
 • ምን? አሁን ያልሰረቀ ማን አለ ብለህ ነው?
 • የእርስዎ ግን ከአቅም በላይ ነው፡፡
 • ያው እኔ ነገር ስለሚገንብኝ ነው፡፡
 • በዚያ ላይ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የአፈጻጸም ማነስ ችግር አለብዎት፡፡
 • የተሰጠኝን ሥራ ሁሉ አይደል እንዴ የምፈጽመው?
 • ክቡር ሚኒስትር ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም ያለው እኮ በእርስዎ መሥሪያ ቤት ነው፡፡
 • ምን ላድርግ ታዲያ?
 • እኔማ ልከራከርልዎት ሞክሬ ነበር፣ ግን አሁን ሁሉም ደርሶበታል፡፡
 • ምኑን?
 • ችግርዎን ነዋ፡፡
 • ምንድነው ችግሬ?
 • የአቅም ማነስ!

[ክቡር ሚኒስትሩ እየተገመገሙ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንደ እርስዎ በጣም ወጥ የረገጠ ሰው የለም፡፡
 • ኧረ እኔ ስኳርና ደም ግፊት ስላለብኝ ወጥ የሚባል ነገር በልቼ አላውቅም፡፡
 • ስለማይበሉት እኮ ነው የሚረግጡት፡፡
 • በቃ ግምገማ በጠራችሁኝ ቁጥር ጤንነቴ ይታወካል እኮ?
 • የሚያሳምምዎት ግምገማ መጠራትዎ ሳይሆን ሥራዎ ነው፡፡
 • እሺ ምንድነው? መቼም በልተሃል ምናምን ልትሉኝ እንዳይሆን?
 • እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን እዚህ ውስጥ ያልበላ ሰው አለ?
 • ያልተጠየቁትን አይቀባጥሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አበላልህ ለየት ያለ ስለሆነ ልምድ አካፍለን ብላችሁ ከሆነ በደስታ ነው የማካፍላችሁ፡፡
 • የተጠሩት ሊገመገሙ ነው፡፡
 • ማን ገምጋሚ? ማን ተገምጋሚ ሊሆን ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የተጠሩት ሊገመገሙ ነው፡፡
 • እኮ በምንድነው የምገመገመው?
 • ለምሳሌ የማስፈጸም አቅምዎ እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • በዚህ ያመጡት ምን እንደሆነ ያውቃሉ?
 • ምን አመጣሁ?
 • F
 • ሌላው የሚገመገሙት በሀብት ብክነት ነው፡፡
 • እሺ፡፡
 • በዚህ ምን እንዳመጡ ያውቃሉ?
 • ቆይ ልገምት፡፡
 • እሺ፡፡
 • F?
 • በትክክል፡፡
 • እሺ ቀጥሉ፡፡
 • በመልካም አስተዳደርም ተመሳሳይ ነው ያመጡት፡፡
 • በሁሉም ዘርፍ Flag አውለብልበሃል እያላችሁኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ወዳልተፈለገ የባንዲራ ፖለቲካ ባይገቡ ጥሩ ነው፡፡
 • እሺ ቀጥሉ፡፡
 • በአጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ብቃትዎ ሲገመገም የሚገልጽዎ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • Failure!