Skip to main content
x

ጋዜጣዊ መግለጫ ወይስ ራስን ማጋለጫ?

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

በአገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ እየተካሄደ ስለመሆኑ አሌ አይባልም፡፡ የለውጡ ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ደግሞ በተደራጀ የመንግሥት ሀብት ዝርፊያና በከባድ የሰብዓዊ መብቶች ድፍጠጣ ወንጀሎች ተጠርጥረው በተያዙትና ፍርድ ቤት በቀረቡት በርካታ ቀደምት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ሥራ መሪዎችና ቱባ የደኅንነት ባለሥልጣናት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የቅርብ ክትትል ተካሂዷል ከተባለውና ጭማቂው ብቻ በመገናኛ ብዙኃን ሲነበብ ከተደመጠው የወንጀል ምርመራ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የደሃዎች ደሃ የሆነችው ምስኪን ምድር ከድህነት ያወጣታል ብቻ ሳይሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዘምኖ ሰማይ ላይ ይሰቅላታል ተብሎ በ2002 ዓ.ም. በተቋቋመውና በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሥር በሚተዳደረው አገር በቀል የልማት ድርጅት አማካይነት አንጡራ ሀብቷን ያለ ርህራሔ ተዘርፋለች፡፡

ሜቴክ እየተባለ በአህፅሮት የሚጠራው ይህ ድርጅት አንዳንዶች እንደሚሉት አገር ለመለወጥ ታስቦ በቅንነት የተመሠረተ ነበር ቢባል እንኳ፣ ከወታደራዊ ማዕረግ ውጪ ይህ ነው የሚባል የንግድና የኢንዱስትሪ ተቋማት ሥራ አመራር ዕውቀቱም ሆነ ልምዱ ባልነበራቸውና በሌላቸው የጦር ሹማምንት የሚመራና ለከት ለሌለው ምዝበራ የተመቻቸ ተቋም ሆኖ ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን ተንተርሶ የአገራችን ይፋና ድብቅ እስር ቤቶች በርገድና ወለል ተደርገው ሲከፈቱ፣ በወንጀል ምርመራና እርማት ስም በንፁኃን ዜጎች ላይ ለዘመናት ሲፈጸሙ የቆዩና ከዘግናኝነታቸው የተነሳ ተወዳዳሪ የሚገኝላቸው የማይመስሉ እጅግ አስነዋሪና አሳፋሪ የሰቆቃ ድርጊቶች ገሀድ ሆነዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የቀድሞዎቹን የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ሹማምንትና ሙያተኞች ጨምሮ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታና ሃይማኖት ሳይመርጥ ቁጥር ሥፍር በሌላቸው ወገኖቻችን ላይ በአረመኔያዊነት ለተፈጸመው ለዚህ ዓይነቱ ግፍና መከራም ግንባር ቀደም ኃላፊነት መውሰድና በፍርድ አደባባይ መልስ መስጠት ያለባቸው አያሌ ተጠርጣሪዎች፣ በተመሳሳይ የሕግ አስከባሪዎች የተቀነባበረ ዕርምጃ መያዛቸው አልቀረም፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በሥልጣን ላይ ከወጣ ገና የጫጉላ ጊዜውን ያልጨረሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ይኼንን ያልተጠበቀ የሚመስል ጨከንና ኮምጠጥ ያለ ዕርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ሕግና ሥርዓትን አላስከበረም፣ ሙሰኞችንና የሰብዓዊ መብት ገፋፊዎችን ታግሷል፣ ተለሳልሷል. . .  እየተባለ በብዙ ወገኖች ዘንድ ክፉኛ ተወቅሷል፣ ከዚያም አልፎ በአቅመ ቢስነት ተወንጅሏል፡፡ አይ መሬት ላይ ያለ ሰው ነበር ያለው ዘፋኙ? በእርግጥ ለዚህ የተቻኮለ ወቀሳና ትችት በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበራቸው ምላሽ ቀድሞ እንደለመድነው ሰዎችን አስሮ ከማጣራት ይልቅ፣ አጣርቶ ማሰሩ ይሻላል ብለን ነው የሚል ነው፡፡ ሰውየው ለዚህ እውነት አላቸው እላለሁ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ (4) እንደተደነገገው የሚያበረታታውም ይህንኑ ነው፡፡

እነሆ እርሳቸው እንዳሉት የማጣራቱ ሥራ በከፊልም ቢሆን በመጠናቀቁ ተጠርጣሪዎች በብርቱ እየተለዩና ከየተደበቁበት እየተለቀሙ በመያዝና ለፍርድ በመቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ያልተያዙትም ቢሆኑ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል፡፡ በሌላ አነጋገር እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ሥር ያልዋሉት ተጠርጣሪዎች፣ በማናቸውም ጊዜና በየትኛውም ሥፍራ ታድነውና ተገደው ሊያዙና ፍርዳቸውን ሊቀበሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ እጅግ በከበደና ዓለም አቀፍ ፀባይ ባለው ወንጀል ተጠርጥረዋልና የመንቀሳቀስ ነፃነታቸው በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተገደበ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን ጸሐፊ አብዝቶ የሚገርመው መንግሥት የወሰደውን ኃላፊነት የተሞላበት ዕርምጃ ተከትሎ፣ የተጠርጣሪዎችን አያያዝና ማንነት በሚመለከት ከየአቅጣጫው የሚወርደው ሙሾና ያለማቋረጥ የሚፈሰው የአዞ ዕንባ ነው፡፡ በመሠረቱ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ራሳቸውን የመከላከል ዕድል አግኝተው እንዲሰሙና በገለልተኛ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ መወትወት የአባት ነው፡፡ ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሔር አባሎች በመሆናቸው፣ ልዩ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሎ ያለበቂ ማስረጃ ጥብቅና የቆሙ መስሎ መታየቱ ግን በጩኸቴን ቀሙኝነት ያስጠረጥራል፡፡

የሕግ ልዕልናን ለማረጋገጥና ለዜጎች የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት አቅም ተስኖት ቆይቷል የተባለው የፌደራሉ መንግሥት እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውና ተባባሪዎቻቸውን ከያሉበት እያደነ በቁጥጥር ሥር ሲያውልና ለፍርድ ሲያቀርብ፣ ክልላዊ መንግሥታትና አብዛኛው ማኅበረሰብ ያለውን ድጋፍና አብሮነት ያላንዳች ማወላወል ገልጸዋል፡፡ ዘር ከልጓም ይስባል ሆኖበት ነው መሰል በዚህ ረገድ የትግራይ ክልል ብቻ በአቋም የተለየበትን የተድበሰበሰና አደናጋሪ መግለጫ ማውጣቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

ሰሞኑን ደግሞ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር መንበር ላይ የተቀመጡት ከእግዜር የከበዱ ሰው የአገር ውስጥ ፕሬስ ጠርተው በይፋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ነገሩን ከሚገባው በላይ በማጦዝ ይበልጥ እንዲወሳሰብ አድርገውታል፡፡ እንደርሳቸው ግምገማ ከሆነ ሌሎች መሰል ድርጅቶችና የሥራ አካባቢዎች እያሉ የሁለቱ ተቋማት፣ ማለትም የሜቴክም ሆነ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ተለይቶ በተናጠል መመርመርና የሥራ መሪዎቻቸው በሙሰኝነትና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋል ትግራይን ከማንበርከክና የትግራይን ሕዝብ ከማሸማቀቅ ጋር ይያያዛል፡፡ ሆኖም ይህ ከእውነት የራቀ ነገር ለእውነት የቀረበ ቢሆን እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክፍልና አካል የሆነው የትግራይ ሕዝብ ከውስጡ የወጡ ሐሳውያነ መሲህ፣ በተደራጀ የመንግሥት ሀብት ሌብነትም ሆነ የሰው ልጅን በማሰቃየት ወንጀሎች ተጠርጥረው ስለተያዙ ብቻ ለምን እንደሚንበረከክና እንደሚገፋ ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡

በእርግጥ ሰውየውን ወደዚህ የተሳሳተ ድምዳሜ የወሰዳቸው በወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት ሰዎች መካከል የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር ጎላ ብሎ መገኘቱ እንደሆነ በቀላሉ ለመገመት አያዳግት ይሆናል፡፡ የዚህም ምክንያት ቢሆን ታዲያ ያን ያህል ሚስጥረ ሥላሴ አይደለም፡፡ ቀድሞውኑ ፍትሐዊ ባልሆነና በተዛባ የኃላፊነት ድልድል ሳቢያ ከያዙት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሥልጣንና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የተነሳ፣ ዙሪያ መለስ ተፅዕኖ የማድረስ ዕድል የነበራቸው እነርሱ ብቻ በመሆናቸው ነው፡፡ ያም ቢሆን ታዲያ ከሌላ ዘውግ የሆኑ ሌሎች ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ተባባሪዎች አልተደመሯቸውም ማለት አይደለም፡፡

በዚህ ጸሐፊ አስተያየት ክቡርነታቸው የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተቀመጡበትን ሕዝባዊ መንበረ ሥልጣን የማይመጥንና የመሪነት ብቃታቸውን ለድርድር የሚያቀርብ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እመራዋለሁ የሚሉትን ኩሩ የትግራይ ሕዝብ የማገናዘብ ችሎታ ሳይቀር ክፉኛ የማጣጣል አባዜም ተጠናውቶት አስተውዬበታለሁ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ የሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውን በካቴና ታስሮ ከሔሊኮፕተር መውረድና በአደባባይ መታየት በተናጠል አንስተው አድራጎቱን በፅኑ ተቃውመዋል፡፡ በመሠረቱ በስም የጠቀሷቸው የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ ወደ ፍርድ ቤት የመጡት ራሳቸው ፈቅደው ሳይሆን በኃይል ተገደውና በሕግ አስከባሪዎች ተይዘው ነው፡፡ ይልቁንም ተጠርጣሪው እንደተያዙ የተነገረን ለአገሪቱ አንደኛው ጠረፍ በቀረበ አካባቢ መሆኑ ሲታይ ወደ ጎረቤት አገር ለመሸሽ እየሞከሩ፣ ወይም ቢያንስ እያውጠነጠኑ አልነበረም ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ አንፃር የሰውየውን አደገኛነት ከወዲሁ መገመትና ባያያዛቸው ወቅት ምናልባት ተበሳጭተው፣ በራሳቸውም ሆነ በሌላው ሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከል ሁለት እጆቻቸውን በካቴና አስሮ ወደ ፍርድ ቤት የማድረሱ አሠራር ያን ያህል እንግዳና ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡

ለነገሩ ያንን ጋዜጣዊ መግለጫ በትክክል ተከታትለነው ከሆነ በፌዴራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለውና ሊኖር የሚገባው ሕገ መንግሥታዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይህ በሥልጣን ላይ ከሚገኘው የክልሉ አመራር አልፎ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

እንደዚያ መግለጫ ከሆነ ከአሁን በኋላ የፌዴራሉ መንግሥት ሕግ አስከባሪ ኃይሎች ትግራይ ክልል ውስጥ ገብተው በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን የመያዝና ለፍርድ የማቅረብ መብት የላቸውም፡፡ በግልባጩ ስናየው ትግራይም ብትሆን ወንጀል የፈጸሙና በጉያዋ የተሸሸጉ ልጆቿን ለፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት አሳልፋ በመስጠት ረገድ አትተባበርም፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ በአንድ አገር ውስጥ የተለያዩ እርከኖችን መሠረት አድርገው በተቋቋሙት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት መካከል መስኩን የሚገዛው ዓለም አቀፍ ሕግ ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ፣ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ሊያስፈልገን ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የዘውግ ተኮር ፌዴራሊዝማችን ትሩፋቱ፡፡

በመሠረቱ የወንጀል ሕግን ጨምሮ የፌዴራሉ ሕግ ተፈጻሚነት መላ ክልሎቿን የሚሸፍን ነው፡፡ ሄዶ ሄዶ ትግራይ ላይ ሲደርስ ተፈጻሚነቱ ሊቋረጥ አይችልም፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይኼንን እውነታ በመቃረን እመራዋለሁ የሚሉትን ክልል ከፌዴራላዊው ኅብረት የማፋታት ዕቅድ ካላቸው፣ በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ሊነግሩን ይገባል፡፡ ያም ቢሆን ባፈተተ የሚወሰን የግል ጉዳያቸው አይደለም፡፡

በመጨረሻም የፌደራሉ መንግሥት ትግራይን ለይቶ ለማጥቃት የውጭ ኃይል ጭምር ተጠቅሟል ሲሉ ሰውየው ያሰሙት ተጨማሪ ውንጀላ ሌላው ግር የተሰኘሁበት ጉዳይ ነው፡፡ እምብዛም ያልተብራራው ይህ ‘የመሸ በከንቱ’ አሉባልታ የጋዜጣዊ መግለጫቸው ክፍልና አካል ባይሆን ምንኛ በወደድኩ ነበር፡፡ ጭራሹኑ የመግለጫውን ደረጃ አሳንሶ ከመንግሥታዊ መግለጫነት ይልቅ ራስን ወደ ማጋለጫነት ያሸጋገረባቸው ይመስለኛል፡፡ ለምን እንደሆነ ለጊዜው ግር ሊያሰኝ ቢችልም ይዛመዱኛል ያሏቸው ተጠርጣሪዎች አያያዝ ክፉኛ አበሳጭቷቸዋል፡፡ ቁጭት አሳድሮባቸዋል፡፡ በእርሳቸው አነጋገር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ከፍትሕ ይልቅ ፖለቲካ የተጫነው፣ ወይም የተጣባው በመሆኑ እንደማይቀበሉት ብቻ ሳይሆን፣ መስተካከል እንዳለበት ጠቅሰው ከዚህ የተነሳ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው እንደማይሰጡ ከወዲሁ ማስፈራሪያ የታከለበት ፍንጭ እስከ መስጠት ደርሰዋል፡፡

እዚህ ላይ ክቡርነታቸው በውል ያልተገነዘቡት አንድ ጥሬ ሀቅ እንዳለ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ እሳቸው ያን ያህል ከቁብ ባይቆጥሩትም የፌዴራሉ ዓቃቤ ሕግ በአገር ሰላም፣ በዜጎቿ ደኅንነትና የጋራ አገልግሎት በሚሰጡ አንጡራ ሀብቶቿ ላይ የሚቃጡ ወይም የተፈጸሙ ከባድ የምዝበራና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ወንጀሎችን የሚመረምረውና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ አቅርቦ የሚያስቀጣው ግፍና በደሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በደረሰባቸው ሰለባዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ሕዝብ ስም ነው፡፡ ስለሆነም ይኼንን ኃላፊነት አቃሎ ማየት ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ለመገዳደር መሞከር አፈጻጸሙን ከጅምሩ እንደማሰናከል ይቆጠራል፡፡ ይህ ፍትሕን የማደነቃቀፍ ሙከራ ራሱን ችሎ በወንጀል ኃላፊነት ማስቀጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለእኔ እንደሚገባኝ ከሆነ አሁንም ገና የአንድ አገር ልጆች ነንና ለመፃኢው ዕድላችን በእጅጉ የሚበጀው እርስ በርስ ተቀራርቦ በጨዋነት መመካከሩና በሠለጠነ መንገድ መተራረሙ እንጂ፣ ማዶ ለማዶ የጎሪጥ እየተያዩ አታካችና ፍሬ ቢስ መግለጫዎችን ከርቀት መወራወሩ አይደለም፡፡ እንደ ወትሮው ሁሉ ዓለማችን ዛሬ በከባድ የሙስና ወንጀል ለተከሰሱና በሰብዕና ላይ ወሰን ተሻጋሪ ወንጀሎችን ፈጽመው ከአንድ ሥፍራ ወደሌላው በህቡዕ እየተሹለከለኩ ለመኖር፣ ሰይጣናዊ ምኞት ለተጠናወታቸው እኩያን ደኅንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ መሸሸጊያ የማቅረብ አቅም የላትም፡፡

ከዚህ ባልተናነሰ ምክንያት በዘመናዊው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከባድ የሙስና ወይም የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ወንጀሎች ይቅርና ማናቸውም ዓይነት ወንጀል ቢሆን፣ ዋና ፈጻሚውን ብቻ ሳይሆን በአነሳሽነት፣ በሞካሪነት፣ በረዳትነትና በአባሪ ተባባሪነት ደረጃዎች ጭምር የተሳተፉትን ወገኖች ሁሉ በተጠያቂነት እንደሚያስቀጣ መታወቅ አለበት፡፡ በሥራ ላይ ያለውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አናቅጽት 27፣ 32፣ 36፣ 37ና 39 ድንጋጌዎች በዝርዝር ይመለከቷል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡