Skip to main content
x

ለፍርድ ቤቶችና ለፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ጥናት ይቅደም

በበዛወርቅ ሺመላሽ

‹‹ፍርድ ቤት ያጣውን የሕዝብ አመኔታ ለመመለስ›› በሚል ርዕስ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዳራሽ ቅዳሜ ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ ስብሰባውን የመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ አመራሮች ሲሆኑ፣ ተሳታፊዎቹ ደግሞ በአብዛኛው ጠበቆችና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡

ለውይይት መነሻ የሚሆን መግለጫ በጠበቃ መታሰቢያ ቀርቦ ነበር፡፡ ርዕሱም ‹‹ዳኝነትና የጠበቆች ዕይታ›› የሚል ነው፡፡ እኔ አሁን ዓላማዬ በዕለቱ ስለተካሄደው ውይይት ሪፖርት ለማቅረብ ሳይሆን፣ አንዳንድ ተሳታፊዎች ባቀረቧቸው ሐሳቦች ላይ አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡ በአቶ መታሰቢያ የቀረበው መግለጫ አጠቃላይ ሆኖ ጠበቆች ስለፍርድ ቤት ያላቸውን ‹‹ፐርሰፕሽን›› የሚጠቁም እንጂ፣ በምርምር ላይ የተመረኮዘ ባለመሆኑ በእሱ ላይ የምለው የለም፡፡

ብዙ ተናጋሪዎች የመናገር ዕድል አግኝተው የማያውቁ እስኪመስል ድረስ በፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የችሎታ ማነስ እንዳለባቸው፣ ጉቦኞች እንደሆኑ፣ ባለጉዳዩንም ሆነ ጠበቃውን እንደማያከብሩ በመጥቀስ ሰፊ ትችት አውርደውባቸዋል፡፡ ጥቂት ተናጋሪዎች ግን አጠቃላይ ከሆነ የጅምላ ንግግር መቆጠብ እንዳለብን፣ ዳኛ ሲባል ሁሉም ጉቦኛ እንዳልሆነ በመጥቀስ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

እንደሚታወቀው እንደዚህ ዓይነት ብሶት መልቀሚያ መድረክ ሲከፈት በሌላው ተናጋሪ ተመስጦ የመነዳት (የመዝለል)፣ ‹‹የመንጋ›› አካሄድ አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ ‹‹የዝለል እንዝለል›› ድባብ በሰፈነበት ጊዜ ቆም ብሎ ‹‹ለምን?››፣ ‹‹እንዴት››፣ ‹‹ምን ማስረጃ አለ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ከብዙ ስህተቶች ያድናል፡፡ [እዚህ ላይ በወታደራዊ መንግሥት ዘመን በኅዳር 1967 ዓ.ም. እነዚያ 60 ባለሥልጣናት ያለ ፍርድ በሞት እንዲቀጡ እጅ በማንሳት ሲወሰን ‹ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ለምን አይታይም?› ብሎ ኮሎኔል ብርሃኑ ባይህ ያቀረበውን ሐሳብ ጉባዔው ቢቀበለው ኖሮ ከስህተት ይዳን እንደነበር ያስታውሷል]፡፡ እስኪ የሚከተሉን ነጥቦችን አንስተን እንመርምራቸው፡፡

ፍርድ ቤት የሕዝብ አመኔታ አጥቷል መባሉ እውነት ነውን?

ይኼ መነሻ ሐሳብ ‹‹ፕሬሚስ›› ትክክል ወይም እውነት ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለ? ምን ጥናት ተደርጎ ነው እዚህ መደምደሚያ ላይ የተደረሰው? ይልቅስ ራሳችን ይኼን አባባል እዚህም እዚያም ስንዘራ ተቋሙ የበለጠ ስሙ እንዲበላሽ፣ የበለጠ አመኔታ እንዲያጣ ከሚያደርገው በቀር የሚያሻሽለው እንደማይሆን መገንዘብ አለብን፡፡

ደግሞም ፍርድ ቤት በተቋምነቱ መከበር አለበት እላለሁ፡፡ ልክ መንግሥት፣ ልክ ቤተ ክህነት፣ ልክ መስጂድ መከበር እንዳለበት ሁሉ፡፡ ተቋማትን ውስጣቸው ካሉ ብልሹ ሰዎች ነጥለን ነው ማየት ያለብን፡፡ ችሎታ የሌለው ዳኛ ካለ፣ ጉቦ የበላ ዳኛ ካለ፣ ሌላ ጥፋት የፈጸመ ካለ ጥፋቱ ተረጋግጦ ከሥራው መወገድ አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ በድፍንፍን፣ እንዲያው በደምሳሳ ፍርድ እንዲህ ነው ብሎ መፈረጅ ወደ ስህተት ያመራል፡፡ ተቋሙ በተቋምነቱ መከበር አለበት፡፡

ደግሞስ ፍርድ ቤት የሕዝብ አመኔታ አጥቷል ካልን፣ ሰው ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ትቶ ሌላ አማራጭ ይዟል ማለት ነው፡፡ ይኼ እውነት አይደለም፡፡ እውነት ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ጠበቃ ቦርሳውን አንጠልጥሎ ወደ ፍርድ ቤት መጉረፉ ይቆም ነበር፡፡ መጉረፉ አላቆመም፡፡

ዳኞች የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡ መባሉ ሕጋዊ ነውን?

የዳኞችን ነፃነት ለማረጋገጥ ተብሎ ዳኞች ከሥራቸው የሚገለሉባቸው ምክንያቶች በሕገ መንግሥቱ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ የዳኛው የጡረታ ዕድሜ ሲደርስ፣ የሥነ ምግባር ጥፋት ሲፈጽም፣ በገዛ ፈቃዱ ሥራውን ሲለቅ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ እኛ የሕግ ባለሙያዎች ይህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ መከበር አለበት ብለን ነው አቋም መያዝ ያለብን፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነት ይከበር›› እያልን ለመጮህም የሞራል ብቃት የሚኖረን ያንን አቋም ስንይዝ ነው፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ታዲያ ከላይ በጠቀስኩት ቀን በተካሄደው ስብሰባ አንዳንድ ተሳታፊዎች ‹‹ዳኞች በፈቃዳቸው ሥራውን ይልቀቁ›› የሚል ሐሳብ ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል፡፡ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፡፡ ዳኛው በራሱ አነሳሽነት ራሱ ፈልጎ ሥራውን ይለቃል እንጂ፣ በበሌላ አካል ጥያቄና ግፊት ሥራውን እንዲለቅ ቢደረግ ‹‹በፈቃደኝነት›› ተፈጸመ ይባላል? ይህ አካሄድ በሕግ ባለሙያ ይመከራል? (እዚህ ላይ የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የአቶ ዳኜ መላኩ ቦታ መልቀቅ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ አይዘንጋ)፡፡

የሕግ ባለሙያው ሲገመገም

ዘፋኙ ጨርሶታል፡፡ አንዱ ጣት ወደ ሌላ ሲጠቁም ሦስቱ ጣቶች ወደ ራስ ይጠቁማሉ፡፡ የሕግ ባሙያዎች ስብስብ ራሱ (ማኅበሩ ጭምር) እንደ ተቋም ስለሚቆጠር፣ እዚህም ተገቢ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሕግና ሥርዓት ጠብቀው የሚሠሩ ጠበቆች ያሉትን ያህል ከመሥራት ይልቅ ማውራት (ማማት)፣ ገንቢ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ ማፍረስ የሚመርጡ አሉ፡፡ አዳዲስ ዕውቀት በየዕለቱ ለመጨበጥ ከመሞከር ይልቅ፣ በዚያችው በለመዷት በድሮዋ መንገድ መጓዝን የሚመርጡ ጠበቆች አሉ፡፡ በደላላ የሚጠቀሙ፣ ከዳኛው ጋር ቀረቤታ አለኝ በሚል ሰበብ ሥራ የሚቀበሉ እንዳሉ በስብሰባው ዕለትም ተጠቁሟል፡፡ የችሎታ ማነስ ጉዳይም ሊነሳ ይገባል፡፡ ተናገር ብትለው ቀኑን ሙሉ መናገር የሚችል፣ ሁለት ፓራግራፍ (በእንግሊዝኛ ይቅር) በአማርኛ አስተካክለህ ጻፍ ብትለው ግን ግራ የሚገባው አይጠፋም፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ጣቶች ወደ ጠበቃው መቀሰራቸውን አንርሳ ለማለት ነው፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች (ከብዙ በጥቂቱ)

ሀ) የዳኛ ዕድሜ

ወጣት (ከልምድ በየዕለቱ ከምናየው) ለዳኝነት ሥራ ብቁ አይደለም፣ ብዙ አላየም፣ ብዙ አላሸተተም፣ ስሜታዊነት ያጠቃዋል፡፡ የዳኝነት ሥራ ብስለትና ሚዛናዊነት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ለዳኝነት ሥራ የሚታጭ ሰው ዕድሜው ቢያንስ 35 ዓመት የሞላ ሊሆን ይገባል፡፡

ለ) በቂ ሥልጠና

ዳኛ ከመሾሙ በፊት ከሕግ ዲግሪ በተጨማሪ በቂ የሥራ ልምድ የጨበጠ፣ እንዲሁም በሕዝብ ግንኙነት፣ በክርክር ጭብጥ አያያዝ፣ በፍርድ አጻጻፍ ወዘተ. በቂ ሥልጠና የተሰጠው ሰው መሆን ይገባዋል፡፡

ሐ) ጠንካራ የኢንስፔክሽን መምርያ

ዳኞች ሕጉን ተከትለውና ምርኩዝ አድርገው ስለሆነ ሥራቸውን ማከናወን የሚገባቸው፣ ይኼን በትክክል ስለመሥራታቸው የሚቆጣጠር ጠንካራ የ‹‹ኢስፔክሽን›› መምርያ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡

መ) አጥኚ ቡድን (ግብረ ኃይል) ማቋቋም

ዛሬ ፍርድ ቤቶች የሚገኙበትን ሁኔታና የፍትሕ አሰጣጡን ችግሮቹንም ጭምር በአጠቃላይ መርምሮ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ የሚፈለግ ከሆነ፣ ቅዳሜ ከተካሄደው ዓይነት ውይይት የረባ ነገር አይገኝም፡፡ ምክንያቱም በዚያ ዓይነት መድረክ የግል ብሶቶች ብቻ ናቸው የሚቀርቡት፡፡ ታይቷል፡፡ ከዚያ ይልቅ አንድ አጥኚ ቡድን (ግብረ ኃይል) ተቋቁሞ የሥራ መመርያ ‹‹ተርም ኦፍ ሬፈረንስ›› ተሰጥቶ ለምሳሌ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብ ቢያደርግና ያ እንደቀረበ አጀንዳ ተይዞ ውይይት ከተካሄደ በኋላ፣ ሊወሰድ ይገባል የሚባለው ዕርምጃ ላይ ውሳኔ ቢተላለፍ ያን ጊዜ የረባ ነገር፣ የተጨበጠ ነገር፣ ፍሬ ያለው ነገር፣ ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ነገር ይገኛል፡፡ የቅዳሜው ዓይነት ውይይት ግን ተበትኖ ነው የሚቀረው፡፡

ሠ) የጠበቆች አስተዳደርን ከዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አውጥቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር እንዲሆን ማድረግ

የጠበቆችን አስተዳደር በሚመለከት አንዳንድ ተሳታፊዎች ኬንያ ያለውን ዓይነት ወይም አሜሪካ ያለውን ዓይነት ‹‹ባር አሶሲዬሽን›› በሕግ ቢቋቋም፣ ያጋጠሙ ችግሮች ሁሉ መፍትሔ እንደሚያገኙ አድርገው ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይኼም እንዲሁ ዘለን የምንገባበት ሊሆን አይገባም፡፡ እኛ ጠበቆች በቡድን ሆነን ‹‹ሎው ፈርም›› አቋቁመን የመሥራት ልምድ (አንድ ወይም ሁለት ሊኖሩ ይችላሉ) እንኳን ገና አላዳበርንም፡፡ ‹‹ጄኔራል ፕራክቲሺነር›› እንደሚባለው ሐኪም ዓይነት ነን፡፡ በአንድ ወይ በሁለት የሕግ ዘርፍ የጠለቀ ዕውቀት እንድንጨብጥ አልሆነም፡፡ የሙያ ብቃታችንን ለማሳደግ ጉጉት የለንም፡፡ እንደ ‹‹አንግሎ ሳክሰን›› ጠበቃ ‹‹አግሬሲቭ›› መሆን ሲገባን አይደለንም፡፡ ተጋፊነት፣ ተጋፋጭነት ይጎድለናል፡፡ አካሄዳችንም፣ አረማመዳችንም ‹‹ጎመን በጤና›› ዓይነት ነውና፡፡ ገና ብዙ ብዙ ይቀረናል፡፡

ማኅበር የሚያቋቁም አዋጅ ከመጠበቅ ይልቅ (በግዴታ የማኅበር አባል መሆን የማይፈልጉ ስላሉ) መጀመርያ የጠበቆችን አስተዳደር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት እጅ አውጥቶ፣ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር እንዲሆን ማድረግ፣ ቀጥሎ የጠበቆች የዲሲፕሊን ኮሚቴ አወቃቀር ውስጥ ብዙ ጠበቆች እንዲካተቱ ማድረግ፡፡ ከሥር ከሥር ደግሞ የጠበቆችን ሙያ (ዕውቀትና ክህሎት) ማሳደግ ዋና ነገር በመሆኑ፣ በየሁለት ወይም በየሦስት ዓመቱ ፈተና እየተሰጠ (ጠበቃው ፈተናውን ለማለፍ ሲል ስለሚያጠና) ፈተናውን ያለፈ ብቻ በሙያው እንዲቆይ ማድረግ፡፡ በዚህ መንገድ ከተሄደ ብዙ ማሻሻል እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን ይቻላል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያና ጠበቃ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡