Skip to main content
x

ጠንካራ የፌዴራሊዝም ጥናት ተቋም የማቋቋም ፋይዳ

በተስፋዬ ጎይቴ

ማንኛውም መንግሥት አገሩን የማስተዳደር ኃላፊነት ተረክቦ በሥልጣን ላይ  በሚቆይበት ዘመን አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ሕጎች ያወጣል፣ ተቋማትን ይፈጥራል፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን ለማስፈጸምና ፖሊሲና ስትራቴጂውን ለማሳካት አይጠቅሙኝም ያላቸውን ተቋማት ደግሞ ያፈርሳል፡፡ በአጠቃላይም አደረጃጀቶችን በራሱ አምሳል ይቀርፃል፡፡

በተለይም በአፍሪካ አገሮች በተደጋጋሚ እንደሚታየው የፖለቲካ ሥርዓቶች ወይም መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር ተቋማት ይቀያየራሉ፡፡ ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላኛው ተሻጋሪ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችና ከመንግሥት ወደ መንግሥት የሚተላለፉ አደረጃጀቶች እምብዛም አይደሉም፡፡ የሰከነ አደረጃጀትና አሠራር ያላቸው ዘላቂ ተቋማትን በመፍጠር ረገድ ብዙ ጊዜ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ እዚህም እዚያም ጉምጉምታዎች የሚታዩትም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት በዓለም ላይ የሚታየው ተለዋዋጭ ሁኔታና ፈጣን ዕድገትም ለዚህ ጉዳይ አስተዋጽኦ አላደረገም ማለት አይቻልም፡፡

በአገራችን ዘውዳዊው አስተዳደር አልፎ ሶሻሊዝም ሲተካ አንዳንድ ተቋማት ‹‹አያስፈልጉንም›› ተብለው ፈርሰዋል፡፡ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ ከርዕዮተ ዓለሙ ጋር እንዲጣጣሙ እየተደረገ ከስያሜቸው ጀምሮ ቅርፅና ይዘታቸው ተቀይሯል፡፡ በዚህም ሥርዓት አዲስ የተፈጠሩና ለአገሪቱ እምብዛም ፋይዳ የሌላቸው ተቋማት የመኖራቸውን ያህል በርካታ ጠቃሚ ተቋማትም ተፈጥረዋል፡፡ በሁሉም ሥርዓቶች ውስጥ ይብዛም ይነስ ጥሩ የታሪክ ውቅሮች እንደታዩት ሁሉ፣ መጥፎ ጠባሳዎችም ነበሩና ጥሩ ወይም መጥፎ ሥርዓት ብሎ በጅምላ መፈረጅ የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡

ከ1960ዎቹ ጀምሮ በነበሩት አምስት አሥርት ዓመታት ውስጥ በባህልና ቱሪዝም፣ ከተማ ልማት፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ግብርና፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ ፋይናንስ፣ ወዘተ መሥሪያ ቤቶችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የተደረጉትን የአደረጃጀትና የስያሜ ለውጦች እንኳን ማየቱ ለተነሳንበት ርዕስ ጉዳይ አብነት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የተነሳሁበት ጉዳይ ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡

በዘመነ ሶሻሊዝም (በ1970ዎቹ አጋማሽ አካባቢ) ለአገሪቱ እጅግ አስፈላጊ ነው በሚል ዕሳቤ አዲስ ከተፈጠሩት ተቋማት ውስጥ በአዋጅ የተቋቋመውና በሽግግሩ ዘመን መጀመሪያ የመፍረስ ፍርድ የተበየነበት፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ለዚህ ጉዳዩ ዋነኛ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ኢንስቲትዩት ሲቋቋም እንዲያከናውናቸው በአዋጅና ከዚያም በተከታታይ በወጡ የተለያዩ መመሪያዎች ከተሰጡት ግዙፍ ዓላማዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን ማየቱ፣ ተሞክሮው በአገራችን መሰል ተልዕኮ ተሰጥቶት ለሚደራጀው ተቋም ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚህም፡-

  • ከተቋሙ ስያሜም መገንዘብ እንደሚቻለው የብሔረሰቦች ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ አሠፋፈር፣ መልክዓ ምድር፣ አንድነትና ልዩነት፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ወዘተ ጥናት ማካሄድ፣
  • የሕገ መንግሥትና ልዩ ልዩ ማስፈጸሚያ ሕጎች ጥናት፣
  • የአድያማት ወይም የአስተዳደርና ራስ ገዝ አካባቢዎች /ክልላዊ አደረጃጀት/ እና በየደረጃው የሚዋቀሩ ሸንጎዎች ወይም የሕዝብ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ጥናት፣
  • የአገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ጥናት፣ ዝግጅትና ማስፈጸም፣
  • ጥናቶቹ በሚመለከተው አካል ፀድቀው በተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡

ለተቋሙ በመንግሥት ከተሰጠው ለየት ያለና ጥልቅ የሆነ ስትራቴጂካዊ ኃላፊነት አንፃር በወቅቱ የሚኒስትር ማዕረግ በነበራቸው የበላይ ኃላፊና የምክትል ሚኒስትር ማዕረግ በተሰጣቸው ምክትል ዋና ኃላፊ እንዲመራ መደረጉም፣ ለተቋሙ ለተሰጠው ትኩረት አመላካች ነገር አለው፡፡ ለተቋሙ ከተሰጡት ዋና ዋና ተግባራት ጋር የተጣጣመ የውስጥ አደረጃጀትም ተፈጥሮለታል፡፡ አገሪቱ ያፈራቻቸውና አንቱ የተባሉ ምርጥ ምሁራን (አንዳንዶቹ ከሥርዓቱ ጋር ተቃርኖ ቢኖራቸውም እንኳን የመስመር ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ)፣ ለጋራ አገራቸው ለኢትዮጵያ ‹‹በሙያቸው›› የጎላ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ወደሚችሉበት ወደዚያ ኢንስቲትዩት እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

ተቋሙ በመላ አገሪቱ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ባለሙያዎቹን አሰማርቶ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወዘተ . . . በሚመለከት የመነሻ ጥናት ሠርቶ የብሔረሰቦች ማወቂያ ዳጎስ ያለ ያልታተመ ጥራዝ አቅርቧል፡፡ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የራስ ገዝና አስተዳደር አካባቢዎች አደረጃጀት ጥናት አካሄዷል፡፡ እንዳለፉት ዓመታት በቋንቋ ወይም በዘር ብቸኛ መሥፈርት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ ተቀባይነት ባላቸው በተለያዩ በርካታ ሳይንሳዊ መሥፈርቶች ላይ ተመሥርቶ ግዛቶችን (አድያማትን) እንደ ባህሪያቸው ልዩ ራስ ገዝ (ለምሳሌ ኤርትራ)፣ ራስ ገዞችና አስተዳደር አካባቢዎች በማድረግ አደራጅቷል፡፡ የኢኮኖሚና መልክዓ ምድር፣ የሕገ መንግሥት፣ የልዩ ልዩ ማስፈጸሚያ ሕጎች፣ እንዲሁም የምርጫ ሥርዓት ጥናቶችን አካሂዷል፡፡ ለሕገ መንግሥትና ለምርጫ ኮሚሽኖችም ሴክሬታሪያት ሆኖ አገልግሏል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ውሳኔ ሕዝብና የሸንጎዎችን ምርጫም በተቋቋሙት ኮሚሽኖቻቸው አማካይነት አስፈጽሟል፡፡

ከመደበኛ ተግባሩ ጎን ለጎን  በበርካታ አገር አቀፍ ግብረ ኃይሎችና ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ፣አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሆኖ በማገልገል ላይ ባለው ሕንፃ ግንባታና ፋሲሊቲዎችን አሟልቶ ለሥራ በማብቃት፣ የብሔራዊ ሸንጎውን መሥራች ጉባዔ አደራጅቶ ሥራ በማስጀመር፣ በሽግግር ወቅት የክልል መንግሥታትን በማዋቀር፣ ለዚህች አገር መሠረታዊ ፋይዳ ያላቸው ሌሎችም በርካታ ጥናቶችን በማካሄድና በማስፈጸም ኃላፊነቱን ለመወጣት የሞከረና ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቶ ጥሩ ስም ያኖረ ተቋም እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ምስክር ነው፡፡

ይህ ኢንስቲትዩት ምናልባትም ከአንድ የአገራችን ነባር ዩኒቨርስቲ ባላነሰ የበሰሉና ዕውቅ የሆኑ ሊቀ ሊቃውንት መገኛ የነበረ ተቋም ነው፡፡ አብዛኞቹም ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የፋኩልቲ ዲን፣ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንና ተመራማሪዎች የነበሩና የዛሬዎቹን የዩኒቨርስቲዎቻችንን ምሁራን ያፈሩ የተከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ኢንስቲትዩቱ በአገራችን ሶሻሊዝም ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ‹‹የደርግ ሥርዓት ዕድሜውን ለማራዘም የፈጠረው ተቋም ነው›› በሚል አስተሳሰብ ላይ በመመሥረት ብዙም ፋታ ሳይሰጠው ከእነ ተሞክሮው በአጣዳፊ እንዲከስም ተደረገ፡፡ በደርግ መንግሥት በወጣ አዋጅ እንደተቋቋመ ሁሉ በሽግግር ጊዜ አዋጅ እንደቀላል ነገር እንዲፈራርስ ሆነ፡፡ አፈር ብቻ ሳይሆን ጥቁር ድንጋይ ተጫነበት፡፡ ያኔ የነበረውን ሒደት የሚያውቁት ያውቁታል፡፡ ለብዙዎችም ቁስል ሆኖ ያለፈና ዛሬ በእጅጉ ልንማርበት የሚገባ ታሪክ ነው፡፡ አንድ መንግሥት የገነባውን ሌላው ሲተካ የማፍረስ፣ አንዳንዴም በጣም የሚጠቅሙንን ተቋማት እምብዛም ከማይጠቅሙን መለየት ያለመቻል የአመለካከት ችግር ወይም አባዜ ተደጋግሞ ይታያል፡፡

በወቅቱ ለኢንስቲትዩቱ የተሰጠውን ባለብዙ ፈርጅ ውስብስብ አገራዊ ተልዕኮ ወይም ኃላፊነት የሚረከበው ተቋም ማነው? የፌደራሊዝም ሥርዓት እየገነባን ነው እየተባለ፣ በእውነት ይህች ባለብዙ ብሔር ብሔረሰብ የሆነች በኃውርታዊት አገር ለብዝኃነቷና ለብዝኃ ባህሏ መበልፀግ ይህንን መሰል ተቋም አያስፈልጋትም ወይ የሚለውን ጉዳይ እምብዛም ያሰበበት አልነበረም፡፡ እንዲያውም ተቋሙ ይጠቅመኛል ብሎ ለፈጠረው ለዚያ የሶሻሊዝም ሥርዓት ሳይሆን ፌደራሊዝምን አሰፍናለሁ፣ የራስ በራስ አስተዳደርን አረጋግጣለሁ ብሎ ለተነሳው ለዚህ ሥርዓት ይበልጥ አስፈላጊ ይሆን ነበር እላለሁ፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም፡፡ ያኔ በደንብ ታስቦበት፣ ተመክሮበት፣ ጥናትን መነሻ አድርጎ የተወሰደ ዕርምጃ ቢሆን ኖሮ ባልከፋ ፡፡ የዚህ ዓይነት ተቋም ቢኖረን ኖሮ የፌደራሊዝም ቅኝት እንደተውሶ ልብስ ወይም በሰው እጅ እንደሚያምርና ሲይዙት እንደሚያደናግር ከበሮ ዓመታቱም አዘፋፈኑም እንዲህ መግቢያ መውጫውና መላቅጡ ጠፍቶን ባልዳከርን ነበር፡፡

እናም የጠቃሚ ድርጅት ዶፍ ዝናብ ወይንም ውሽንፍር በድንገት እንደመጣበት እንደ አገር ቤቱ የጉልት ገበያ በሚያሳዝን ሁኔታ በአንድ ጀንበር ተበተነ፡፡ ግዙፉ የምሁራን ማዕከል አውሎ ነፋስ እንዳበነነው አቧራ በነነ፡፡ ይህም ሆኖም ግን በወቅቱ በነበረው የአስተሳሰብ ሁኔታ አካሄዱ ስህተት ነበር ተብሎ በድፍኑ ሊኮነን አይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የሥርዓቱ ባህርይና የአመለካከት ጉዳይ ነውና፡፡ ዛሬ ላይ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ጉድለቶችን መነጋገር ግን ተገቢ ነው፡፡ ለተጀመረው ለውጥ ምሥጋና ይግባውና ከስሜታዊነት ተላቀን የሁለት አሥርት ዓመታት ተኩል ጉዟችንን ቆም ብለን ሰከን ባለ መንገድ ወደኋላ እንድናስብ፣ ከጉዳታችንም እንድንማር ዕድል አግኝተናል፡፡ ሁላችንም ዕድሉን ከተጠቀምንበት ማለቴ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በብዙ ውስብስብ ብሔረሰባዊ ጉዳዮችና የፌደራል ሥርዓቱን ጉዞ ቆልፈው በያዙ ችግሮች ውስጥ አልፈናል፣ አያሌ ፈተናዎችን አስተናግደናል፡፡ በሽግግሩ ወቅት ገና ሥርዓቱን በእግሩ ማቆም እንደተጀመረ በአጎራባች ክልሎች መካከል እዚህም እዚያም ተከስተው የነበሩትን የድንበር ውዝግቦችና የይገባኛል ጦሶች እናስታውስ፡፡ በየትኛውም ወገን ይሁን የስንት ንፁኃን ዜጎች ሕይወት እንደ ጠቦት ጭዳ ሆነ? ስንት መንደሮች፣ መኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ተቃጠሉ፣ ምን ያህል ንብረት ወደመ ድምር ውጤቱስ በአገራችን ላይ ምን አስከተለ? ችግሩ አናታችን ላይ የወፍ ጎጆ ሠርቶብን ሙጭጭ ብሎ ይዞን ዛሬም ድረስ አልለቀቀንም፡፡ እንደ ኮሶ ተጣብቶን ሲከተለን ቆይቷል፡፡ የዛሬው ዓይነት የዘር ሐረግን እየቆረጡ መቆራቆስ ደግሞ አስከፊ የተባለውን የደርግ አገዛዝን ጨምሮ ባለፉት ሥርዓቶች ሁሉ እምብዛም የገነነ ወይም ሥር የሰደደ አልነበረም፡፡ ታዲያ ችግሩ ይህንን የፖለቲካ ሥርዓት ተከትሎ ለምን መጣ ብለን ደፍረን እንፈትሸው፡፡ ተከራክረን እንማማርበት፡፡ ለሚነሱ ሐሳቦች አሉታዊ ትርጉም መስጠት የአዕምሮ ብልሽት ወይም የአስተሳሰብ ክስረት ነው፡፡ ሳንፈራ እንነጋገር፡፡ ያለዚያ አንዱ ሲገነባ ሌላው ሲያፈርስ፣ አንዱ ሲያቃጥል ሌላው ንብረቱ ብቻ ሳይሆን ቆሽቱም ሲቃጠል፣ አንዱ ሲገፋ ሌላኛው እንደተገፋ ልንቀጥል ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ያልተወገደ ችግር አለ፡፡ ሰበቦች አያዋጡንም፡፡

የ1983 ዓ.ም. ለውጥን ተከትሎ የብሔር ካርዶች ያለገደብ እየተመዘዙ የልዩነቶቻችን መንስዔ ወይም ግድግዳ ሲሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በተደራጀ መልኩ ምክር የሚሰጡን ጥብቅ ሐሳብ ያላቸውና የምናዳምጣቸው ልሂቃን ስብስብ ቢኖረን ኖሮ ችግሩ በእንጭጩ ሊቀጭ ይችል ነበር፡፡ የጥፋቱ ምንጭ ምንና ማን እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ከታወቀም በኋላ ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ ግዴታ ነው፡፡ መንግሥት በፍቅር ልናከብረው ካልሆነም በመንግሥትነቱ ልንፈራው ይገባል፡፡ ያለንበት ሁኔታ ሊታወቀንና ሕመሙ ሊሰማን ይገባል የምለውም ለዚህ ነው፡፡ የፖለቲካ ትኩሳቶችን ሊያበርዱ፣ የተዛቡ አስተሳሰቦችን መስመር ሊያስይዙ፣ ለሥርዓቱ ሳያሸረግዱ፣ ለቁንጥጫውና ለኩርኩሙ ሳይንበረከኩ ልክ አይደላችሁም የማለት በአቅም ላይ የተመሠረተ ድፍረት ወይም ወኔ ያላቸው ምሁራን የታደሙበት ማዕከል በዘላቂነት ቢኖረን ኖሮ ምንኛ በተጠቀምን ነበር፡፡ አሁን ይህንን መሰል ተልዕኮ እንዲፈጽም እየተደራጀ ያለው ተቋም ያለፈውን ተሞክሮ ታሳቢ ቢያደርግ ይጠቅማል ብዬ በማሰብ ነው ይህንን አስተያየቴን ለአንባቢያንም ለመንግሥትም አትኩሮት ያቀረብኩት፡፡ ግዙፉ ችግር እንዳይደገም በማሰብ የታየኝን ካቀረብኩ የዜግነት ግዴታዬን ተወጣሁ፡፡ መቀበል ያለመበቀል የመንግሥት ፋንታ ነው፡፡

ልብ እንበል! አንድን የፖለቲካ ሥርዓት እኛ መገንባት ስላማረን ወይም እንዲሁ ዓይናችን ደስ ስላለው ብቻ የምንሞክረው የገበጣ ጨዋታ አይደለም፡፡ የትኛውን መርጬ ብመገብ ይሻለኛል የሚሉት የተደረደረ የቡፌ ምግብም አይደለም፡፡ በሌሎች ላይ ስላማረ ብቻ የትኛውን መርጬ ገዝቼ ልልበስ የሚባልበት ቡቲክ ውስጥ የተሰቀለ ልብስ ወይም ሌሎች ስለዋኙበት ዓይን ተጨፍኖ ተዘሎ የሚገባበት ባህርም አይደለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ‹‹ያላዋቂ ሳሚ›› መሆንን ያስከትላል፡፡ ዕርምጃው አገር አልሚ ወይም አጥፊ፣ ትውልድ ገዳይ ወይንም ትውልድ አብቃይ ሊሆን ይችላል፡፡ ፀጉራሞች ፀጉራቸውን ስለተከረከሙ መላጦች ፀጉር መከርከም ሊያምራቸው አይገባም፡፡ ምርጫው ለእነርሱ አይሆንማ፡፡ የእኛ ነገር እንዲህ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ሲገነባ በማመዛዘን፣ አሻግሮ በማየት ላይ የተመሠረተ የተለየ ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡

ታዲያ ያኔም ቢሆን (ከ1974 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም) የነበሩት ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ተቋም ምሁራንም ቢሆኑ ምክራቸው በሙሉ በሥርዓቱ ተቀባይነት አግኝቷል የሚል ተላላ እምነት የለኝም፡፡ ሐሳባቸው ሲፈለግ የሚወሰድ ሳይፈለግ የሚጣል እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦችንም አቅርበው ውድቅ እንደተደረጉባቸው ይታወሳል፡፡ የተናገሩት፣ የጻፉት ሁሉ ተቀባይት ቢያገኝ ኖሮ ሥርዓቱም ያየነው ዓይነት የመፍረስ አደጋ ውስጥ አይወድቅም ነበር፡፡ የሌሎችን ሐሳብ ወይንም ምክር የማያዳምጥ ግለሰብ፣ በድን፣ ተቋምም ሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ተንገዳግዶ ወደ መውደቅ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ እረኛውን ለማሳደድ ከመሄድ ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ብሎ እረኛው የነገረንን መፈጸም ይመረጣል፡፡

እናም የዚያ ተቋም ስብስቦች ሙሉ በሙሉ በይደመጡም እንኳን በወቅቱ በርዕሰ ብሔሩ ጭምር ከፍተኛ ከበሬታ ተሰጥቷቸው የነበሩ አንቱ የተባሉ ምሁራንን ለማሰባሰብ ተችሎ ነበር፡፡ ዘር፣ ሃይማኖትና ቀለም ሳይለዩ ለአንድ ዓላማ የተሰባሰቡ ጠበብት፡፡ ታዲያ በወዲህኛው ሥርዓት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እነዚያ አገር ያፈራቻቸው ምሁራን ለደንታችሁ ተባሉ፡፡ ቀስ በቀስ መዋያና ማደሪያ ሥፍራቸውን መፈለግና ጥጋቸውን መያዝ ጀመሩ፡፡ እንደማያገለግል አሮጌ ቁና ወደ ዳር ተወረወሩ፡፡ ይህን ጊዜ ነገሮችም እንዳልነበሩ ሆነው ተቀያየሩ፡፡ ያለፈውን እንዲያው በጅምላ የመፈረጅ፣ የራስን ንግግሮች ብቻ የማድመጥ፣ የራስን አስተሳሰብ ብቻ የማራመድ፣ እኔ ብቻ አውቃለሁ የማለት አባዜ ቀስ በቀስ ሥር ሰደደ፡፡ ከፍ ብሎ የተጠቀሱት የክልል ለክልል፣ የብሔር ለብሔር መቆራቆሶች እያደር አገረሹ፡፡ ለአስታራቂም አስቸገሩ፡፡ መደማመጥ ከመዝገበ ቃላት ጠፋ፡፡ እንደ ደርግ ጊዜ ሁሉ የራሱን የፖለቲካ ፓርቲ ሰንበቴ የማይጠጡ ሰዎችን ሐሳብ  በፍጹም የማያስተናግድ አግላይ ሥርዓት ተፈጠረ፡፡ ሚዛኑና ወንፊቱ ብቃት ላይ ሳይሆን ለሥርዓቱ ባለው ‹‹ታማኝነት›› ላይ ብቻ ተመሠረተ፡፡ የትናንት ከትናንት ወዲው ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡ እነሆ ደርግም በመጨረሻ ውጤቱን አገኘው፡፡ ብቻ ከእንግዲህ ከዚህ ያውጣን አቦ!! ግን ዛሬም ቢሆን ይህንን እውነት ተቀብለው ወደ አዕምሮቸው ለማይመለሱ ክቡራን ሐሳውያን መሲሆች አዝንላቸዋለሁ፡፡ ይዘውን አዘቅት ውስጥ እንዳይገቡም እሠጋለሁ፡፡

እዚህ ላይ ያኔ ኢንስቲትዩቱ መርጦ አሰባሰቧቸው ከነበሩት የአገራችን ዕንቁ ምሁራን መካከል ለአብነት ያህል አንዳንዶቹን ብጠቅስ ለተነሳሁበት ጭብጥ አብነት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የታሪክ አሻራ ነውና ከልብ እንድታዳምጡኝ ፈቃዳችሁን እጠይቃለሁ፡፡ እነ ዶ/ር እሸቱ ጮሌ፣ ዶ/ር አስመላሽ በየነ፣ ዶ/ር ፋሲል ናሆም፣ ዶ/ር ያየህይራድ ቅጣው፣ ዶ/ር አሻግሬ ይግለጡ፣ ዶ/ር አሰፋ መድሃኔ፣ ዶ/ር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል፣ ዶ/ር ግርማ ወልደ ሥላሴ፣ ዶ/ር ላጲሶጌ. ዴሌቦ (ፕሮፌሰር)፣ ዶ/ር ዲበኩሉ ዘውዴ፣ ዶ/ር ክንፈርግብ ዘለቀ፣ አቶ ኃይሉ ወልደ አማኑኤል (አምባሳደር)፣ አቶ ወርቅነህ ሰፊ፣ አቶ ሥዩም ወልዴ፣ አቶ ታዬ ወርቁ፣ አቶ ጀነነው አየለ፣ አቶ ተሾመ ወልደ ሰማያት፣ አቶ ልዑል ሰገድ እርቅይሁን፣ አቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ሌሎችም በርካታ የተቋሙና የብሔረሰብ መምርያ ስመጥር ምሁራን በአሁኑ ጊዜ አንዳቸውም በዚያ ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የሉም፡፡

ከተጠቀሱት አንዳንዶቹ ደግሞ ኢንስቲትዩቱንና የረጅም ጊዜ ራዕያቸውን በልባቸው እንደቀረፁ በቁጭት አልፈዋል፡፡ ዛሬ በሕይወት አናገኛቸውም፡፡ ከሞቱ በኋላ እንኳን በማርሽ ባንድ የመታጀብ ዕድል ባይሰጣቸውም ከእነ ክብራቸው ተሸኝተው ላይመለሱ ርቀው ሄደዋል፡፡ በሕይወት ያሉትም ቢሆኑ ይህንን ግዙፍና ጥልቅ አገራዊ ተልዕኮ የሚወጣ (የሚተካ) ሌላ ተቋም ያለመፈጠሩ ያንበግባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግን ልትጠራቸው፣ አታኩርፉ፣ የይቅርታ ጊዜ ነውና ሥርዓቱን ይቅር ብላችሁ ኑ፣ ታደጉኝ፣ ከልባችሁ ተሳተፉ፣ ለሁሉም ልጆቼ እኩል ነኝና ከእንግዲህ በፓርቲ ወይም በሃይማኖት ወይም በዘር የተነሳ መገለል የለም ልትላቸው የጀመረች ይመስለኛል፡፡

እናንተስ ውድ አንባብያን! እነዚህ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን አገሩን እንደሚወድና የሩቁን አሻግሮ የማየት፣ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሐሳብ የማፍለቅ አቅም እንዳለው ጤነኛ ዜጋ ዱካ አልባ ሆነው ሲቀሩ አያሳዝንም ትላላችሁ? ጎበዝ! ያለ መደማመጥን ያህል ክፉ ነቀርሳ የለም፡፡ ስለዚህ ነው እኮ  ወቅቱ አሁንና አሁን ነው የምለው፡፡ ‹‹ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው፡፡›› የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ መናበብ ካቃተን ግን ኋላ ይቸግረናል፡፡ እንወቅበት፡፡

በአገራችን ስትራቴጂካዊ በሆኑ ብሔራዊ ጉዳዮች በተለይም በፌዴራሊዝም፣ በሕገ መንግሥት፣ በብሔረሰቦችና በክልሎች ጉዳይ ላይ ለፌደራል መንግሥቱ በተለይም ለሁለቱም ምክር ቤቶችና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕውቀትና በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥልቅ ሐሳብ የሚያመነጭ የተሟላ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ በገለልተኛነት የሚያማክር፣ እንዲህ እንዲያ ቢሆን ይሻላል የሚል ሐሳብ ያለው ለመንግሥት ቅርብ የሆነ ድርጅት ነው ሊፈጠር የሚገባው፡፡ ለውጣችን፣ አሠራራችን ሁሉ ግለሰባዊ ስሜታዊ ሳይሆን ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡ በበርካታ ዓይነት የእውቀት ዘርፎች ብቃት ያላቸው ምሁራን የተሰባሰቡበት፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮዎች እየቀመረ የሚያቀርብ፣ የኢትዮጵያን ቀሚስና ሱሪ በልኳ የሚሰፋ፣ የተጠናከረ (ራሱን የቻለ) ተቋም ያለመኖሩ ጉዳቱ እያደር እየታየ ነው፡፡ የሚፈጠረው ኮሚሽን ጊዚያዊ ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ብቻ ሳይሆን ዓላማ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ ተቀርፆለት በዘላቂ ተቋምነት በአዋጅ መቋቋም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ 

የለውጣችን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ደጋግመው እንደሚነግሩን በታላቋና ገናናዋ፣ ነገር ግን ካንዣበቡባት የውስጥም የውጭም ፈተናዎች ለመላቀቅ በመፍጨርጨር ላይ በምትገኘው አገራችን በምሥራቅና  በምዕራብ፣ በሰሜንና በደቡብ፣ በመሀልና በዳር ችግሮች ሲነሱ የተቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋት መሯሯጡ ከዚህ ወዲያ ማብቃት አለበት፡፡ ከፍ ብሎ ለመጠቆም እንደተሞከረው የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ከውስጥ ባለሙያዎቻቸው በተጨማሪ ለውሳኔዎቻቸው በጥናት ላይ የተመሠረተ የውሳኔ መነሻ ጥናት የሚያቀርብ ቋሚ ተቋም ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ እዚህም እዚያም የሚታዩት ችግሮች በጥናት ዘላቂ ዕልባት ሊያገኙ ይችላሉ የሚል ጽኑ እምነት ሊኖር ካልቻለ ነገራችን ሁሉ ‹‹የእምቧይ ካብ›› ይሆናል፡፡ ልዩነቶቻችን አንደተጠበቁ ሆነው ጠንካራ አገራዊ አንድነት ለመመሥረት የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል የራሱ ባለቤት ያስፈልገዋል፡፡ የመንደር ዘራፌዎች አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡

የቆሸሸ የፖለቲካ ድር፣ ነገሮችን ማጦዝና ማወሳሰብ፣ በስሜት በመነዳት የሌሎችን መብት የራሱ አድርጎ ሕገወጥ በሆነ መንገድ መድፈርና መንጠቅ፣ ሥርዓቱን ለግል መጠቀሚያ ማድረግ፣ ይኼ ሰውና ይኼ ሥርዓት የእኔ ስለሆነ ማንም አይነካኝም ብሎ ከሕግ በላይ መንጠራራት ወንዝ እንደማያሻግር ዓይተነዋል፡፡ አሁንም መቼም ቢሆን አይጠቅመንም፡፡ ከአሮጌውና ከቡቱቷሙ የአስተሳሰብ ሳጥን ውስጥ ሰብረን እንውጣ፡፡ በራሳችንና በአገራችን ላይ መልሰን መዘዝ አናምጣ፡፡ ነገአችንን ገደል አናድርገው፡፡

በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ከትናንሽ ምክንያቶች በመነጨ የሚነሱ ችግሮች ሥር ነቀል መፍትሔ ካልተፈለገላቸው እያበጡና ቁርሾ እየፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ ያመረቅዛሉ፡፡ ከእግር ጥፍር እስከራስ ፀጉር መላ ህዋሳቶችን ይበክላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ ምንጫቸውን ፈልጎ ማድረቅ ይገባል፡፡ ድንገት ቢከሰቱም በሠለጠነና በዘመናዊ መንገድ እንዲፈቱ መደረግ አለበት፡፡ የተንቀጠቀጠውን መሬት ለማቆምና ለማረጋጋት ካስማና ዋልታ ፍለጋ ከመራወጥ መሬቱ እንዳይንቀጠቀጥ አስቀድሞ መፍትሔ መሻት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው፡፡ ለዚህም አሁን እየተደራጀ ያለው ተቋም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና በገለልተኛነት መንፈስ ሥልጡን የሆነና በሳል ሐሳብ የሚያቀርብ፣ ጣልቃ የማይገባበት፣ ሙሉ ኃላፊነት የተሰጠው የጉዳዩ ባለቤት የሆነ ተቋም እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡

ስንዳክርበት ለኖርነው ሥርዓት ሊተርፍ ይችል የነበረው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት በደርግ ዘመን ስለተፈጠረ ብቻ በጥላቻ መንፈስ በግርግር ፈረሰ፡፡ ወገኖቼ ሆይ! በስሜታዊነት ላይ የተመሠረቱ የዚህ ዓይነት ዕርምጃዎች ለአገር መቼም አይበጁም፡፡ ስሜታዊነትና ጥላቻ እኛንና አገራችንን ምን ያህል እንደጎዳን እንይ፡፡ ባሳለፍነው ዘግናኝ ጊዜ ጎጂዎቹም ተጎጂዎቹም እኛው ነን፡፡ ካለፈው በጣም መማር አለብን፡፡ አንዱ ከሌላኛው የበለጠ ተጎድቶ ሊሆን ይችል እንደሆነ ነው እንጂ አብዛኞቻችን ተጎድተናል፡፡ ብዙ ነገሮቻቸውን አጥተው፣ ዕሴቶቻቸውን ተነጥቀው በባሰ ሁኔታ ክፉኛ የደቀቁም እንዳሉግን የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ አሁንም እየተጠቁ ያሉትን ምንዱባን እንድረስላቸው፡፡ አሁን ዘመኑ የምሕረት፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመቻቻል እንጂ የቂም በቀል አይደለም የሚለውን የመሪያችንን ክቡርና ደማቅ ሐሳብ መላ ሕዋሳቶችን ሁሉ የሚያረሰርስ ሐሳብ ነውና፡፡ በሥጋና በደማችን ውስጥ እናስርጸው፡፡ ነገር የሚቆሰቁሰትን፣ እዚህም እዚያም እሳት የሚጭሩትን፣ ጭር ሲል የማይወዱትን ሁሉ በአንድ ቃል በቃችሁ እንበላቸው፡፡ ካልሆነም ዛሬ ማረሚያ ቤቶቻችን ለእነርሱ የሚሆን በቂ ቦታ እንዳለቸውም እናስገንዝባቸው፡፡

ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የሽግግሩ ወቅት የልምድ ዕጦትና የአካሄድ መደበላለቅ ክፍተት በጉልህ የታየበት እንደነበረ ክርክር የሚነሳበት ጉዳይ አይደለም፡፡ (የሚከራከር ካለም ማሳያ ማስረጃዎችን እየጠቀስን በግልጽ እንከራከር) የጠቀስነው ኢንስቲትዩትም የፈረሰው በዚህ መደበላለቅ የተነሳ ቀደም ሲል በነበረው የተዛባ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ለዚህ ሥርዓት ለዚህች አገር ወይም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋታችን ይጠቅማል ወይንስ አይጠቅምም በሚል በጥልቀት ሳይታሰብበት የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የችኮላ ዕርምጃዎች ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ሲወሰዱ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በመሆኑም ዛሬ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ እንደገና በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ ለአገር ጠቃሚ የሆነ ተቋምን ዓይንን ጨፍኖ ማፍረስ ሰው ከመግደል ይተናነሳል ብዬ አላስብም፡፡

ሙስናን በመገናኛ ብዙኃንና በየመድረኮቹ አጋለጣችሁ፣ አርፋችሁ አልተቀመጣችሁም ተብለው ሰዎች ከሥራና ከኃላፊነት የተባረሩባት፣ የፖለቲካ መሥመር ልዩነት ዝንባሌ የታየባቸው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ‹‹ሙሰኞች›› የሚል ታፔላ ተለጥፎላቸው የተንገላቱበት፣ በተቃራኒው ፍጥጥ ያሉ ‹‹ኃያላን ሙሰኞች›› ሽፋንና ተገን አግኝተው የተሸለሙባትና የተሞካሹበት አገራችን ትላንት በተዘፈቀችበት ሁኔታ ትቀጥል የሚል ምኞት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምኞቱ ካለም የማይሳካ ቀቢጸ ተስፋ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ብርሃን ፈንጥቆላታል፡፡ በዚህ ትውልድ ዘመን ወደ ድቅድቅ ጨለማ አትመለስም፡፡ ከመወቃቀስና ከመፈራረጅ ወጥተን የጋራ አገራችንን ወደ መገንባቱ ማተኮር ይሻላል፡፡ የተጎዳዳነውን እየቆጠርንና ቂም እየቆፈርን በቀል ከምናደራ ጊዘያችንን በአገር ግንባታ ላይ ማዋሉ ራሳችንንም ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡

ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ተቋም በዘመኑ በመላው ዓለም በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በኢትዮጵያ ላይ የተሠሩ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፎችን ማሰባሰብ ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ አሃዳዊ መንግሥት ትሁን ፌዴራል?  የየትኛውን አገር የሕገ መንግሥት ቅርፅ እንደ መነሻ እንውሰድ? የፌዴራል አደረጃጀትን የሚከተሉ አገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል? በኃውርታዊነት ምን ዓይነት ጥንቃቄ ይፈልጋል? ራስ ገዝነት ምን  ፋይዳ ወይም ጉዳት አለው? ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት፣ ምንስ ዓይነት የሸንጎዎች አደረጃጀት ለእኛ ይበጀናል? በሚል የተሞካከሩ ጥናቶችና የተደራጁ የሕግ ማዕቀፎችም ነበሩ፡፡ የእኛ ነገር ሆነና እምብዛም ውስጥ ገብቶ ፈትሾ የተጠቀመባቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ እየታየ ያለውን አስፈሪ ነገር ደግሞ መገታት የሚቻለው በጥናት፣ በመከባበርና በመደማመጥ ነው፡፡

ከ1985 እስከ 1987 ዓ.ም. አካባቢ ከየክልሎቹ ድንበሮች ጋር በተያያዘ ይነሱ ለነበሩት ያለ መግባባቶች መፍትሔ ለመፈለግ የረጅም ጊዜ ልምዳቸውን ተጠቅመው ላይ ታች በማለት ቀደም ሲል ፈርሶ የነበረው የዚሁ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ውስጥ ሆነው የተጫወቱት ሚናም መዘንጋት የለበትም፡፡ እዚያ ቤት ውስጥ የነበረው ባለ ብዙ ፈርጅ  ጥልቅ ተሞክሮ ቀላል አልነበረም፡፡ እናም ውሎ አድሮ ምን ዓይነት ማጥ ውስጥ ስንዳክር ነው የኖርነው? ዛሬ በሕይወት ያሉ ጥቂት የተቋሙ ምሁራን እስቲ ከተሞክሯቸው ምን ትመክሩናላችሁ ያላቸው አልነበረም፡፡ ጥላቻ፣ መቃቃር፣ ዘረኝነት፣ መድልኦ፣ ሙስናና የመሳሰሉ የአገራችንን ዕድገት ሰንገው የያዙ (ተጨባጭ ዕድገት የለም የሚል ዕብደት ግን የለኝም) በሽታዎቻችንን ደግሞ ልቅም አድርጎ፣ አራግፎ፣ ቀብሮ መሄዱ በጣም ተገቢ ነው፡፡ የልዩነት፣ የአድልዎ፣ የመለያየት፣ የአፈንጋጭነት፣ የእብሪተኝት ፎረፎራችንን በአገርኛ መድኃኒት ሙልጭ አድርገን ታጥበን እንፅዳ፡፡

ውኃ ሲወስደን መዳከርና ግቻ ለመያዝ እየፈለጉ መልሶ ያንኑ ውኃ መቧጠጥ አይጠቅመንም፡፡ ከትላንቱ ጠቃሚውን ወስደን ጎጂውን ድንጋይ ጭንነበት መጓዝ አለብን፡፡ በስሜት ተነሳስተን የትናንቱን ጠቃሚ ነገር ስናፈርስና አዲስ ስንገነባ የትም አንደርስም፡፡ አሁን የጀመርነው ጉዞ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› ነው፡፡ በተስፋ ላይ ተስፋን የሚያላብስ፣ ነፍስን የሚያሞቅ ለውጥ ነው፡፡ ጤነኛ አዕምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደግፈው፣ ክፍተት ካለም እንዲህ እንዲህ ቢሆን ይሻላል ብሎ በግልጽ ሊናገር ይገባል፡፡ የመደመር ብቻ ሳይሆን የመደማመጥ ወቅት ነው፡፡ የመገፋት ሳይሆን የመታቀፍ ጊዜ ነው፡፡ ዕድሉን እንጠቀምበት፡፡ የሚገነባው ተቋም በጎ የሆኑ ጥረቶችን፣ የተለያዩ ዕውቀቶችን፣ አስተዋጽኦዎችንና አስተያየቶችን የሚያስተባብር ማዕከል መሆን አለበት፡፡ የጋራ አገራችን ናትና ፍላጎትና አቅም ያላቸውን ወገኖች ሁሉ እያሳተፈ መቀጠል እንጂ፣ ሁሉንም ነገር ራሱ ሠርቶ ለመጨረስ አይችልም፡፡ አጥር ሠርቶ በር ዘግቶ ለብቻ መወሰን ይብቃ፡፡

ከዚህ አንፃር ዋናው ማጠንጠኛዬ ካለፉት ክፍተቶቻችን በመማር  ለዚህች አገር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክር ሊሰጥ የሚችል መሰል ተቋም ቢፈጠር ይጠቅማል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለክልል መንግሥታት ሙያዊ (ቴክኒካዊ) እገዛ በማድረግ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ወደፊት ሄደን እንደገና ወደኋላ እንዳንመለስ አሁንም ደጋግሞ ማሰብ ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ፡፡ ‹‹ስትሄድ ያደናቀፈህ ድንጋይ ስትመለስ እንደገና ካደናቀፈህ ድንጋዩ አንተ ነህ›› ይባል የለ? እባካችሁ ከጥርጣሬ አባዜ እንላቀቅ፡፡

የተጀመረውን መሠረታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ሁላችንም ከውስጣችን አምነን መደገፍ ከቻልን የጋራ አገራችን አታዝንብንም፡፡ ለዚህም ኮሚሽኑን በማደራጀት ሒደት ከፍ ብሎ የቀረበውን ሐሳብ ከግምት ማስገባቱ ጠቃሚ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽን ጥረት በማናቸውም መንድ ማገዝ፣ በሙሉ እምነት መሳተፍ፣ ክንዳችንን አስተባብረን እንቅፋቶችን በጋራ ማስወገድ ተስኖን በተቃራኒው ማመንታትና ማወላወል ውስጥ ከገባን አደጋው ከባድ ይሆናል፡፡ ቢያንስ ዛሬ ንፁሕ አየር መተንፈስ ጀምረናል፡፡ የለውጥ ደወል ተደውሏል፡፡ ጉዳዩ የመሪ ወይም የተመሪ፣ ወይም የአንድ ለውጥ አምጪ ተቋም ጉዳይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ከጠባቂነት መላቀቅ የዚህች አገር ዜጎች ሁሉ የጋራ ሐሳብ መሆን አለበት፡፡ በመጠራጠር ሳይሆን በመተማመንና በይመለከተኛል መንፈስ ተጀመረውን ጥረት ለማሳከት እንረባረብ፡፡

የተያዘው ጉዞ አገርን የማዳን፣ ጥላቻንና መተላለቅን የማስቆም፣ ሕዝባችንን ከድህነት የማላቀቅና የነፃነት አየር እንዲተነፍስ የማድረግ ነው፡፡ ከተቻለ ለዚህ ግስጋሴ የሚረዱ፣ ያለፉት 35 ዓመታት ሌሎች መሰል ተሞክሮዎቼን አገርን ለመገንባትና ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር በሚረዳ መንገድ እየመራረጥኩ ለማጋራት ሌላም ጊዜ እቀጥላለሁ፡፡ መስመር የሳቱ ሐሳቦችን አስተላልፌ ከሆነ በማቃናት እንድታግዙኝ ልመናዬን አቀርባለሁ፡፡ ለመተንፈስ ዕድል ለሰጠኝ ለዛሬው ቀንና ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ምሥጋናዬ ይድረስ፡፡ ጽሑፌ የራሴ የግል ሐሳብ መሆኑ ይታወቅ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡