Skip to main content
x
ፈረንሣይን የፈተነው ‹‹የሎው ቬስት›› ተቃውሞ

ፈረንሣይን የፈተነው ‹‹የሎው ቬስት›› ተቃውሞ

ፈረንሣውያን በነዳጅ ዘይት ላይ የተደረገውን የግብር ጭማሪና የኑሮውን ውድነት በመቃወም ለአራት ተከታታይ ሰንበቶች በዋና ከተማዋ ፓሪስና በተለያዩ ከተሞቿ ‹‹የሎው ቬስት›› (አንፀባራቂ ጃኬት) በመልበስ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ያለው ተቃውሞ ከአራት ሳምንት በፊት ቅዳሜና እሑድን እየጠበቀ የተካሄደ ቢሆንም እንዳለፈው ሳምንት ግን የዓለም አቀፍ ሚዲያ መነጋገሪያ አልነበረም፡፡ እሑድ ለተቃውሞ የወጡ ፈረንሣውያን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን እያወገዙ ተሽከርካሪዎችን ሲያጋዩና የሕንፃዎችን መስተዋት ሲሰባብሩ  ተስተውለዋል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ባለፈው ቅዳሜ ብቻ 125 ሺሕ የሚጠጉ ፈረንሣውያን  ጎዳናዎች በተቃውሞ አጥለቅልቀዋል፡፡ ከ1,700 በላይም ታስረዋል፡፡ ተቃውሞውን ለመመከት ደግሞ 89 ሺሕ ያህል ፖሊሶች ተሰማርተዋል፡፡

በተቃውሞው ምክንያት ኤፍል ታወርን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ተዘግተው ውለዋል፡፡ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ቡርኖ ለማሪ ሁኔታውን ‹‹የማኅበረሰብና የዴሞክራሲ ቀውስ›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ሚኒስትሩ የተዘረፉና ከጥቅም ውጭ የሆኑ የንግድ ተቋማትን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ለንግዳችንና ለኢኮኖሚያችን መቅሰፍት›› ሲሉ ተቃውመው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አደጋ እንደጣለ አክለዋል፡፡

በተለይ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ለተቃውሞ የወጡባት ፓሪስ በተቃውሞው ክፉኛ ተመትታለች፡፡ የሕንፃ መስተዋቶች ረግፈዋል፣ መኪኖች ተቃጥለዋል፣ ሱቆች ተዘርፈዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሰንበቶች የአሁኑ በርካታ ውድመት የደረሰበት፣ በርካቶችም በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለያዩ ከተሞች የወጡበት ነበር፡፡ ሆኖም ለተቃውሞ ከወጣው ሕዝብ አንፃር የደረሰው ጉዳት ብዙ አይደለም ተብሏል፡፡

የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን የቪስ ለድሬን ተቃውሞውን ያባባሱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው ብለዋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ቅዳሜ ፈረንሣይን አስመልክተው ትዊት ማድረጋቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ በትዊታቸውም ፓሪስ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የደረሰችበት ስምምነት በአገሪቱ ለተከሰተው ተቃውሞ ምክንያት ነው ማለታቸውን አስታውቋል፡፡ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ማክሮንም ‹‹ትራምፕ በሕዝባችን ጉዳይ ጣልቃ አይግቡ›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

አመፁ ለሳምንታት በየሰንበቶች ሲካሄድ እምብዛም ምላሽ ለመስጠት ያልወጡት ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ ከትናንት በስቲያ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም መለስተኛ የደመወዝ ጭማሪና የታክስ ምሕረት እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡

‹‹ተቃውሞው ጥልቅና በብዙ አቅጣጫ ሲመዘን ሕጋዊ ነበር›› ያሉት ፕሬዚዳንት ማክሮን ተቃዋሚዎች የፈጸሙትን ውድመት ግን አውግዘዋል፡፡ ዝቅተኛ ጡረታ ተከፋዮች ላይ ተጥሎ የነበረው የግብር ጭማሪ እንደሚነሳ፣ የትርፍ ሰዓት ሥራዎች ግብር እንደማይጣልባቸው እንዲሁም በዓመት መጨረሻ ሠራተኞች ከሚያገኙት ጉርሻ (ቦነስ) ላይ ግብር እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡ ሆኖም በሀብታሞች ላይ የተጣለው ግብር እንደማይነሳ አሳውቀዋል፡፡

ተቃውሞው በኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ጫና

የፈረንሣይ ኢኮኖሚ ለሳምንታት በዘለቀውና ብዙ የንግድ ተቋማትን ባወከው ‹‹የሎው ቬስት› ተቃውሞ ምን ያህል እንደተጎዳ ለመግለጽ ገና ቢሆንም፣ ላፓሪዝያን ጋዜጣ እንዳሰፈረው፣ 50 መኪኖች መቃጠላቸው፣ በርካታ ሱቆች መውደማቸውና አንዳንዶቹ መዘረፋቸው ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያመጣል፡፡ የከተማዋ ባለሥልጣናትም ውድመቱ በሚሊዮን ፓውንድ እንደሚገመት መግለጻቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በኅዳር 17 ቀን 2018 ተቃውሞው ከተጀመረ ወዲህ ቸርቻሪዎች ብቻ 1.1 ቢሊዮን ዶላር ማጣታቸውን ሮይተርስ አስታውሷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ሚስተር ለማሪ፣ የምግብ ቤቶች ንግድ ከ20 በመቶ እስከ 50 በመቶ ውድቀት እንደገጠመው መሰንበቻውን ተናግረዋል፡፡

የአነስተኛና መካከለኛ ንግድ ኮንፌዴሬሽን በበኩሉ፣ አባላቱ አሥር ቢሊዮን ዩሮ ማጣታቸውን አስታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 በ40 ሚሊዮን ጎብኚዎች የተጎበኘችውና ሪከርድ ውስጥ የገባችው ፈረንሣይ በአገሪቱ የተከሰተው አመፅ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋን ያሽመደምደዋል ተብሏል፡፡

ፈረንሣይን የፈተነው ‹‹የሎው ቬስት›› ተቃውሞ

የሎው ቬስት ሙቭመንት ምንድን ነው?

 የየሎው ቬስት ሙቭመንት (ተቃውሞ) የተጀመረው መንግሥት በናፍጣ ላይ የቀረጥ ጭማሪ በማድረጉ ነበር፡፡ የፈረንሣይ ተሽከርካሪዎች በብዛት የሚጠቀሙት ናፍጣ ሲሆን፣ ከሌሎች የነዳጅ ዓይነቶች ሲነፃፀርም በዝቅተኛ ዋጋ የሚሸጥ ነበር፡፡ ባለፉት 12 ወራት ብቻ የናፍጣ ዋጋ በ23 በመቶ ጨምሯል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ማክሮንም ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በናፍጣ ላይ 6.5 ሳንቲም፣ በፔትሮል ላይ 2.9 ሳንቲም እንደሚጨመር ማሳወቃቸው ነበር የየሎው ቬስት ተቃውሞን የቀሰቀሰው፡፡

ፕሬዚዳንት ማክሮን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ መምጣቱን በመኮነን በፎሲል ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ግብር መጣል የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የተቃውሞ ሠልፉ ‹‹የሎው ቬስት›› የተባለበት ምክንያት ተቃዋሚዎች በፈረንሣይ የተሽከርካሪዎች ሕግ መኪና ውስጥ ማስቀመጥ ግድ የሆነውን  አንፀባራቂ ጃኬት ለብሰው በመውጣታቸው ነው፡፡

የፈረንሣይ መንግሥት ለ2019 ጥሎት የነበረውን የነዳጅና የኤሌክትሪሲቲ ግብርን ጭምር ለመተው የተስማማ ቢሆንም ተቃውሞው ሌላ ጥያቄም አንግቧል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ መሥፈርቶች እንዲላሉ፣ የደመወዝና የጡረታ ክፍያ እንዲሻሻልና የታክስ መጠን እንዲቀንስ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ማክሮንም ደመወዝ ለመጨመር የታክስ ጭማሪን ለመሰረዝ ቃል ገብተዋል፡፡

ፈረንሣይን የፈተነው ‹‹የሎው ቬስት›› ተቃውሞ

የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሚሊዮኖችን ይታደጋል ተባለ

የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መተግበር በአየር ብክለት ሳቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት የሚሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለማዳን እንደሚረዳ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ሰሞኑን በኮፐንሃገን እየተደረገ ባለው የድርጅቱ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (ኮፕ 24) ይፋ ባደረገው ሪፖርት፣ የፓሪሱን ስምምነት በመተግበርና የአየር ብክለትን በመቀነስ እ.ኤ.አ. በ2050 በየዓመቱ የሚቀጠፉ ሚሊዮኖችን ማዳን ይቻላል፡፡

ከአየር ብክለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና እክሎችን ለማከም ከሚወጣው ወጪም የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር የሚወጣው እንደሚያንስም ገልጿል፡፡