Skip to main content
x
‹‹በዕርዳታና በበጀት ብቻ የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት ችግር አይፈታም›› አቶ ሰልፊሶ ኪታቦ፣ በኢትዮጵያ የወተር ኦርግ ዳይሬክተር

‹‹በዕርዳታና በበጀት ብቻ የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት ችግር አይፈታም›› አቶ ሰልፊሶ ኪታቦ፣ በኢትዮጵያ የወተር ኦርግ ዳይሬክተር

አቶ ሰልፊሶ ኪታቦ በኢትዮጵያ የወተር ኦርግ  ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ወተር ኦርግ ከተቋቋመ 25 ዓመታትን ያስቆረጠ ሲሆን፣ በ13 አገሮች ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በንፁህ ውኃና መፀዳጃ ቤት ተደራሽነት ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የራሱን ቢሮ ከፍቶ መሥራት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ያልሞላው ቢሆንም ኬንያ በሚገኘው ቢሮ በኩል ግን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ወተር ኦርግ፣ ማት ዴመን በተሰኘው ታዋቂው የሆሊውድ አክተርና በውኃ ኢንጂነሩ ጌሪ ዋይት ጥምረት የተመሠረተ ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱ ግለሰቦች በውኃ ዙሪያ የሚሠሩ የተለያዩ ሁለት ድርጅቶችን ይመሩ ነበር፡፡ ጌሪ ዋይት ወተር ፓርትነርስ የሚባል፣ ማት ዴመን ደግሞ ኤችቱኦ (H2o) አፍሪካ የሚባል ድርጅት መሥርተው ሲሠሩ ቆይተው እ.ኤ.አ. በ2009 ተጣምረው ወተር ኦርግን መሠረቱ፡፡ ወተር ኦርግ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዳይሬክተሩን አቶ ሰልፊሶ ኪታቦና አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ወተር ኦርግ በኢትዮጵያ የራሱ ቢሮ ሳይኖረው ኬንያ በሚገኘው ቢሮ በኩል በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥራዎችን ሠርቷል? ምን አይነት አሠራርስ ይከተላል?

አቶ ሰልፊሶ፡- እ.ኤ.አ. 2004 አካባቢ ብቅ ብለው በትግራይ ክልል ብዙ ቦታዎች ላይ የውኃ ጉድጓዶች ቆፍረዋል፡፡ በአማራ ክልልም እንደዚሁ 100 የሚሆኑ የውኃ ጉድጓዶች ተቆፍሯል፡፡ ይህ የተደረገው እኔ ከገባሁ በኋላ ስለሆነ በደንብ አስታውሳለሁ፡፡

በዕርዳታና በመንግሥት በጀት ብቻ ዓለም ላይ ያለውን የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት ችግር አይፈታም፡፡ ስለዚህ ሌላ ዘዴ መፈጠር ነበረበት፡፡ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት የሚበጅተው በቂ አይደለም፣ በቂ ዕርዳታም ከውጭ አይገኝም፡፡ ወተር ኦርግ ይህንን ውስብስብ ችግር ለመፍታት አዲስ ሐሳብ ያመነጨ ድርጅት ነው፡፡ ደሃ በሚባለው ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ነገር ግን ያለባቸውን የመፀዳጃ ቤትና የውኃ አቅርቦት ችግር ጥቂት ድጋፍ  ተደርጎላቸው መፍታት የሚችሉ ሰዎችን ለይቶ በማውጣት ራሳቸው ለችግራቸው ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ ነው፡፡ ደሃን፣ ያለው ደሃና የሌለው ደሃ በሚል ለሁለት እንከፍለዋለን፡፡ በዓለም ላይ በቀን ከሦስት ዶላር በታች የሚያገኝ ሰው ደሃ ይባላል፡፡ እኛ አገር ግን በቀን 90 ብር የሚያገኝ ሰው ደሃ አይባልም፤ ቢያንስ ራሱን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ደሃ የሚባለውን የማኅበረሰቡን ክፍል ለሁለት በመክፈል ከታች ያለውን መንግሥትና የዕርዳታ ድርጅቶች እንዲያግዙት በማድረግ፣ የተሻለው ደሃ ግን ያለበትን ችግር በራሱ መቅረፍ እንዲችል መንገድ ማመቻቸት የወተር ኦርግ መርህ ነው፡፡ በዚህ መርህ መሠረት ወተር ኦርግ በዓለም ላይ በሚገኙ 13 አገሮች ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ በእነዚህ አገሮች ሲሠራ ፖሊሲያቸው በሚፈቅደው መጠን ባንኮችን በማስተባበር ብድር ይሰጣል፡፡ በእኛ አገር ፖሊሲው ስለማይፈቅድ የብድር ገንዘብ ማቅረብ አልተቻለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የብድር ፖሊሲ ለውኃ አቅርቦት ምን ያህል የተመቸ ነው?

አቶ ሰልፊሶ፡- የብድር ፖሊሲው ለውኃ አቅርቦት ያስቀመጠው የብድር መጠን በቂ አይደለም፡፡ ለውኃ ብድር ተብሎ በፖሊሲ የተቀመጠው መጠን ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ባላውቅም በጣም ትንሽ እንደሆነ ግን አውቃለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የውኃ ችግር ለመቅረፍ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የሚመድበው ዓመታዊው በጀት ግን የዚህን 30 በመቶ እንኳን አይሆንም፡፡ መንግሥት ዘላቂ የልማት ግቦች ብሎ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል ንፁህ የመጠጥ ውኃን በየቤቱ የማድረስ ተልዕኮ ይገኝበታል፡፡ ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚሄድበት አቅጣጫ ጥሩ ሆኖ ሳለ ግብ ለመምታት ግን በቂ ገንዘብ የለውም፡፡ ስለዚህ ከዕርዳታ ድርጅቶች የሚገኘውን ድጋፍ፣ የራሱን በጀት እንዲሁም ከተለያዩ አካላት የሚገኘውን ገንዘብ አቀናጅቶ ችግሩ ለጠናበት ደሃ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለተሻለው ደሃ ግን ብድር በማመቻቸት ራሱን እንዲችል ማድረግ አይነተኛ አማራጭ ነው፡፡ እኛ የምንሠራው በዚህ መንገድ ሆኖ ሳለ አሠራራችንን ለመረዳት የሚቸገሩ ሰዎች ደሃውን ማኅበረሰብ የማይወጣው ዕዳ ውስጥ ልትከቱት ነው ይሉናል፡፡ እኛ የምንለው ግን የተሻለ ገቢ ያለው ደሃ ብድር አግኝቶ መንግሥትን ሳይጠብቅ ራሱን እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ደሃ ናቸው ከተባሉ የማኅበረሰቡ ክፍል ውስጥ ከአብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች የተሻለ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮች አሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ውኃ ከፍላችሁ አስገቡ ቢባሉ ለማስገባት ዝግጁ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የምትከተሉት መርህ ውጤታማ ስለመሆኑ በተግባር ያሳያችሁት ነገር አለ?

አቶ ሰልፊሶ፡- ሞጆ አሁን ለኛ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ የሞጆ ከተማ የውኃ አገልግሎት ቢሮ 24 ኪሎ ሜትር ድረስ የውኃን ተደራሽነት ለማስፋት ነበር የዓመት በጀት ይዞ የነበረው፡፡ ማኅበረሰቡ ተጨማሪ የውኃ ዝርጋታ ሲጠይቅ የተያዘው በጀት ለ24 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው ከዚያ በላይ መሥራት አንችልም ይላል፡፡ በወተር ኦርግ በኩል የተደራጁ የሞጆ ነዋሪዎች ግን መተባበር ፋይናንስ ከሚባለው ተቋም ወደ 700 ሺሕ ብር ተበድረው ስድስት ኪሎ ሜትር ውኃ ስበው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ያደረጉት 150 ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር ምን ያህል የመንግሥትን ሸክም ሊያቀል እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ስድስት ኪሎ ሜትር ማለት የማንንም በጀት በማይጠይቅ መልኩ አንድ አራተኛ የሚሆነውን የከተማውን ሸክም መከፋፈል ማለት ነው፡፡ የዚህን ዓይነት ሞዴል ነው እንድገም የምንለው፡፡ ወተር ኦርግ በአንድ ዓመት ውስጥ ማይክሮ ፋይናንሶችን በማስተባበር ወደ 18.6 ሚሊዮን ብር ለውኃና ለሥነ ፅዳት ዘርፍ እንዲያበድሩ አድርጓል፡፡ በዚህ ወደ 22,500 ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የመንግሥትን በጀት ሳይነካ ከ22 ሺሕ ሰዎች በላይ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህንን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለውም ሦስት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በሰጡት ብድር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት 38ቱም ማይክሮ ፋይናንሶችና 18ቱ ባንኮች አብረው ቢሠሩ ከመንግሥት ላይ የሚያወርዱት ሸክም ቀላል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ውኃ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ 70 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ብድር ቢመቻችልን ውኃ የማስገባት አቅም አለን እንደሚሉም ባለፈው አዳማ ባዘጋጃችሁት ዐውደ ጥናት ላይ ገልፃችኋል፡፡ በዚህ ረገድ ያካሄዳችሁት ጥናት አለ?

አቶ ሰልፊሶ፡- ወተር ኦርግ እዚህ አገር ሥራ ከመጀመሩ በፊት ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ጥናቱ የተደረገው ባልሳሳት እ.ኤ.አ. 2014 አካባቢ ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሌላ ጥናት እያስጠናን ነው፡፡ በወቅቱ ጥናቱ ሲደረግ  የብድር አገልግሎት ቢመቻችለት ውኃ የማስገባት ፍላጎት አላችሁ ወይ? ተብለው የተጠየቁ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አምስት የማይክሮ ፋይናንሶችም ጥናት አካሂደው ይህንን እንዲያረጋግጡና የዋሽ ብድርን በፖርትፎሊዎአቸው እንዲያስገቡ አድርገናል፡፡ የተለያዩ አበዳሪ ተቋማት የውኃና የመፀዳጃ ቤት ለማስፋፋት የሚሰጥ ብድር ኮንሰምሽን ሎን ነው ከየት አምጥተው ይከፍላሉ በሚል ለማበደር ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ እኛ ግን እነዚህ የተሻሉ ደሃዎች ስለሆኑ መክፈል ይችላሉ እንላቸዋለን፡፡ ማይክሮ ፋይናንሶች እኛ ስላልናቸው ግን አይደለም ብድር የሚሰጡት፡፡ አስፈላጊውን የገበያ ጥናት እንዲያደርጉ እኛ ገንዘብ ሰጥተናቸው ያለውን የገበያ ሁኔታ ካዩ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የኛ ሚና ተቋማቱ ጥናት እንዲያደርጉ ማገዝ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ነው፡፡ ለእያንዳንንዱ ጥያቄ የገበያ ጥናት ማድረግ አይጠበቅብንም ፍላጎቱ እንዳለ በጥናት ተረጋግጧል ቀጥታ መግባት ይቻላል፡፡ ብቸኛው ነገር መንግሥት በፖሊሲው እንዲደገፍ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አበዳሪ ተቋማትን ለውኃና ሥነ ንፅህና ዘርፍ እንዲያበድሩ የሚገደዱበት ሕግ ይውጣ የሚል አቋም አለዎት?

አቶ ሰልፊሶ፡- በአስገዳጅነት መልክ ይውጣ ማለት አይደለም፡፡ ለዚህ ዘርፍ የብድር ሁኔታ ማመቻቸት በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ተቋማት ወይም ባንኮች ለዚህ ተግባር ሲያበድሩ በአንድ በኩል ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቱን መሠረታዊ ችግር መቅረፍ ነው፡፡ በውኃ ወለድና ተያያዥ በሽታዎች ሳቢያ በዓለም ላይ በየሁለት ደቂቃ አንድ ልጅ ይሞታል፡፡ የትኛውም ድርቅ፣ የትኛውም የምግብ ማጣት ችግር፣ የትኛውም ጦርነት በዚህ ፍጥነት ሕፃን አይገድልም፡፡ ለዚህ ግን በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ባንኮችም ለዚህ ጉዳይ ራሱን የቻለ የብድር አገልግሎት እንዲያዘጋጁ አልተደረገም፡፡ በዓለም ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በዓመት ከ114.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ተግባር ተብሎ በየዓመቱ የሚበጀተው ገንዘብ ግን ከዚህ እስከ አራት እጥፍ ያነሰ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ሊገባደድ 11 ዓመት ለቀረው ዘላቂ የልማት ግብ  እንዴት ነው ከፍጻሜ ሊደረስ የሚቻለው? የኢትዮጵያን ስንመለከት ይህንን የዘላቂ ልማት ግብ ለማሳካት በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል፡፡ እነኝህን አበዳሪ ተቋማት ማሳተፍ ካልተቻለች ግን ይህንን ያህል ገንዘብ ከየት ኢትዮጵያ ከየት ታመጣለች?

ሪፖርተር፡- ያሉት አበዳሪ ተቋማት በሙሉ በዚህ ተግባር ቢሳተፉስ በ11 ዓመታት ውስጥ የዘላቂ የልማት ግቦቹን ማሳካት ይቻላል ብለው ያስባሉ?

አቶ ሰልፊሶ፡- ግቡን ለመምታት ያግዛል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ እገዛው በምን ያህል መጠን ቢሆን ግቡን መምታት ይቻላል የሚለው ግን መሰላት አለበት፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው አካሄድ፣ ባለው ገንዘብና በሚኬድበት ፍጥነት የምንቀጥል ከሆነ ግቡን በጥቂቱም እንኳ ለማሳካት ከባድ ይሆናል፡፡ ወተር ኦርግ ባመጣው አካሄድ መቀጠል ከተቻለ ግን በ11 ዓመታት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን ዕቅድ ማሳካት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማቅረብ ይከብዳል፡፡ በዕርዳታም አይገኝም፡፡ በአጠቃላይ ማወቅ ያለብን ነገር መንግሥት የሚያገኛቸው ዕርዳታዎች በዓመት የሚፈለገውን ሁለት ቢሊዮን ዶላር መሸፈን የሚችል አይደለም፡፡ አበዳሪ ተቋማትን በማሳተፍ የሚገኘው ገንዘብ ግን የዕርዳታ ተቋማት ከሚሰጡት፣ መንግሥት ከሚበጅተው በብዙ እጥፍ የበለጠ ነው፡፡ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ማግኝት ባይቻልም መንግሥትና የዕርዳታ ተቋማት ከሚሰጡት ቢያንስ በአራት እጥፍ የበለጠ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ወተር ኦርግ ለራሳቸው የማያንሱ ደሃዎችን መልምሎ ብድር እንዲያገኙና ችግራቸውን በራሳቸው እንዲቀርፉ መንገዱን የማመቻቸት ሥራ በኢትዮጵያ ይሠራል ብለዋል፡፡ በሌሎቹ አገሮች የሚሠራቸው ሥራዎችን የሚያከናውነው ተመሳሳይ አካሄድን ተጠቅሞ ነው? ወይስ የተለየ አካሄድን ይጠቀማል?

አቶ ሰልፊሶ፡- ከአሜሪካና ከኬንያ እየተመላለሱ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚሠሩትን የውኃ ጉድጓድ የመቆፈር፣ መፀዳጃ ቤት ተደራሽ የማድረግ ሥራ ሰርቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በህንድ፣ ፊሊፒን፣ ኢንዶኔዥያ፣ ባንግላዴሽ ውስጥ በሰፊው እየሠራ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ህንድ ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ በሁሉም አገሮች ላይ የሚከተለው ይህንኑ አካሄድ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አገሮች አሠራሩ ቀጥታ ከባንኮች ጋር እንዲያያዝ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህንን አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ትልቁ የማይክሮ ፋይናንሶች ችግር ግን ለማበደር ፈቃደኛ ቢሆኑም የሚያበድሩት ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ያጣሉ፡፡ ፖሊሲው ቢፈቀድልን ወተር ኦርግ ከሌሎች ባንኮች ጋር በማገናኘት ይህን ገንዘብ ተደራሽ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ለሁሉም የልማት መስኮች ብድር ለማድረስ በቂ ገንዘብ የለንም ይላሉ፡፡ ይህ ችግር ከረሃብም፣ ከድርቅም ከምንም የበለጠ ገዳይ ስለሆነ ወደ ከፋ ድህነት የሚገፋም ስለሆነ እያንዳንዱ ባንክ ለውኃና ሥነ ፅዳት መስክ የማበደር ግዴታ አለበት የሚል ቀጭን ትዕዛዝ መንግሥት ቢሰጥ መፍትሔ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ባንኮችም እኮ በነፃ አይደለም የሚሰጡት፡፡ እስካሁን እንደታዘብነውም ለውኃና ሥነ ፅዳት መስክ የተሰጠው ብድር ከ99.9 በላይ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ከተሰጠው የጊዜ ገደብ ቀድመው ብድራቸውን የሚመልሱም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ትልቁ ችግር ውኃ ካለበት ቦታ ረዥም ርቀት በቱቦ ስቦ ወደየቤቱ የማስገባቱ ሒደት ከበድ ያለ ወጪን መጠየቁ ነው፡፡ ውኃ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ውኃን ቤታቸው ድረስ ስቦ ለማስገባት ምን ያህል ገንዘብ ይበደራሉ?

አቶ ሰልፊሶ፡- አነስተኛ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ውኃን ከዋናው ምንጭ ወደ ቤታቸው ለማስገባት ከ6,000 እስከ 12,000 ብር የሚሆን ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ ገጠር ላይ የሚገኙ ደግሞ በእጅ ፓምፕ የሚሠሩ የውኃ ጉድጓዶችን እስከ 12,000 ብር ተበድረው ይሠራሉ፡፡ በዓመት ለሚከፍል ገበሬ ገንዘቡ ብዙ አይደለም፡፡ ውኃ ተደራሽ በሆነባቸው አካባቢዎች ውኃ እየጠፋ ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ ተበድረው የውኃ ታንከር ይገዛሉ፡፡ እስከ 4,000 ሊትር የሚይዝ ታንከር ገዝተው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ለዚህም የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል የሚመቻቸችበት ሥራ ይሠራል፡፡ ውኃ ቤት ድረስ በቧንቧ መጣ ማለት ንፁህ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የመጀመርያው የዘላቂ ልማት ግብ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በአቅራቢያው ወይም ደርሶ መልስ 30 ደቂቃ በማይፈጅ ርቀት ውስጥ ውኃ እንዲያገኝ ማስቻል የሚል ግብ ተይዞ ነበር፡፡ ይህንን በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማሳካት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ደግሞ በእያንዳንዱ ግቢ ውስጥ የ24 ሰዓት ንፁህ የውኃ አቅርቦትና ንፁህ የመፀዳጃ ቤት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚል ግብ ነው የተያዘው፡፡ ይህንን አሳካለሁ ብላም ኢትዮጵያ ፈርማለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ከ100 ሚሊዮን በላይ ሆኗል፣ የዘላቂ የልማት ግቡም ሊጠናቀቅ 11 ዓመታት ብቻ ናቸው የቀሩት፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ታዲያ ደሃ ተብለው ከተጠቃለሉት ውስጥ አቅሙ ያላቸውን ለይቶ በብድር ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሥራ ካልተሠራ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ በቀሩት ዓመታት ውስጥ የተገባውን ቃል እንዴት መሙላት ይቻላል? ይህ የማይታሰብም ነው፡፡ ህንድ ውስጥ አመርቂ ውጤት እየታየ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በግላቸው በዚህ ፕሮጀክት ላይ አብረው ስለሚሠሩ ነው፡፡ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው ‹‹ንፁህ ኢንዲያ›› የሚል ዘመቻ ስለተካሄደ ነው፡፡ ፊሊፒን ውስጥም እንደዚሁ ነው፡፡ መንግሥት በየቤቱ ቧንቧ በመዘርጋት ፈንታ ምንጩን ማዘጋጀት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ሰዎቹ ራሳቸው ናቸው ባንቧ ቤት ድረስ ውኃ ስበው የሚያስገቡት፡፡ ማስገባት ላልቻለው ደግሞ መንግሥት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ እንደዚያ እየተደጋገፍን እንግፋ ነው የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከባድ የውኃ ችግር ያለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ሰልፊሶ፡- ይህንን የመሰለ የዳሰሳ ጥናት እኛ አልሠራንም፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ንፁህ ውኃን በየቤቱ የማስገባት ተልዕኮ ከ40 በመቶ በላይ ይቀረዋል፡፡ የዓለም የመፀዳጃ ቀን ባወጣው ሪፖርት መሠረት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት የለውም፡፡ ከፍተኛ ችግር ካለባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡ ይህ ገንዘብ ማጣት ብቻ ሳይሆን ከባህሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር መፍታት የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ መስክ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑና የሆኑ ተቋማት አካሄዳቸውን ለውጠው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ ተደራሽነት ችግር የለባቸውም በሚባሉ የአገሪቱ ክፍሎች ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የውኃ ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ ብዙ ጊዜ ይጠፋል፣ አንዳንዴም ደግሞ ንፁህ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ሰልፊሶ፡- ውኃ በሚፈልገው መጠን እንዳይገኝ እንቅፋ የሚገጥመው ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ ነው፡፡ ውኃ የትም አገር ችግር ሊሆን ይችላል ነገር ግን ቅድሚያ ተሰጥቶት ጥሩ ዕቅድ ወጥቶለት ስለሚሠራ ችግር አይሆንም፡፡ እኛ አገር የባለሙያም ችግር አለ፡፡ የውኃ መስመር የሚዘረጋው ሰው በቂ ዕውቀት ከሌለው መስመር መዘርጋት ቱቦ በመግጠም ብቻ ሊመስለው ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ውኃን መንግሥት ስለሚያቀርብ ዋጋው ትንሽ ስለሆነም ማኅበረሰቡ ውኃ ሲባክን ዝም ብሎ ነው የሚያየው፡፡ ውኃ ሲፈስ እያየ የእከሌ ነው ምን አገባኝ የሚል ብዙ ሰው አለ፡፡ ቱቦ ፈንድቶ ውኃ ሲባክን እያየ ሪፖርት የማያደርግ ብዙ ነው፡፡ ለውኃ ዋጋ አንሰጥም፡፡ ውኃ ግን ዋጋ ያለው ሸቀጥ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ለዚህ ነው እኛ የውኃና የመፀዳጃ ቤት አቅርቦት ጉዳይ ከባንክ ጋር እንዲያያዝ የምንፈልገው፡፡