Skip to main content
x
ሳዑዲ አሜሪካ በአገሬ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች ስትል አወገዘች
(ከግራ) የሳዑዲው ልዑል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማንና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ሳዑዲ አሜሪካ በአገሬ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች ስትል አወገዘች

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት፣ በየመን ላይ በጥምር ለከፈተው ጦርነት የጀርባ አጥንት ሆና ስትደግፍ የነበረችው አሜሪካ ከጦርነቱ ራሴን አገላለሁ ማለቷን አወገዘ፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ ሴኔት የአሜሪካ መንግሥት ሳዑዲ ዓረቢያ የምትመራውን ወታደራዊ ጥምረት መደገፍ የለበትም በሚል ሰሞኑን ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ሳዑዲ ከወዳጇ አሜሪካ ጋር የቃላት ጦርነት ገብታለች፡፡

የመንን በበታተነው ጦርነት ለምትሳተፈው ሳዑዲ ዓረቢያ አሜሪካ ወታደራዊ ዕገዛ ማድረግ የለባትም ብሎ የአሜሪካ ሴኔት ውሳኔ ከማሳለፉም ባለፈ ደራሲ፣ ጋዜጠኛና የዋሽንግተን ፖስት ዓምደኛ በሆነው ጀማል ካሾጊ ግድያ የሳዑዲውን ልዑል አልጋ ወራሽ ወቅሷል፡፡

የሳዑዲ መንግሥት በበኩሉ የአሜሪካውን ሴኔት ውሳኔ ‹‹በውሸት ውንጀላ ላይ የተመሠረተ ጣልቃ ገብነት›› ሲል አጣጥሎታል፡፡

የሴኔቱ ውሳኔ ምናባዊ እንጂ ሕግ የመሆኑ ጉዳይ ያጠራጥራል ያለው ዘገባው፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳዑዲ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ለመገሰጽ ያህል እንደተወሰነ ገልጿል፡፡

ሴናተሮቹ ኑሮውን በአሜሪካ ባደረገው የሳዑዲው ተወላጅ ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያሳዩት ቸልተኝነት አስቆጥቷቸዋል ተብሏል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ ኢስታምቡል እንደተገደለ የተነገረውን ጋዜጠኛ ካሾጊ ያስገደለው የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሰልማን ነው የሚል እምነት እንዳለው የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ አሳውቆ ነበር፡፡

ሳዑዲ አሜሪካ በአገሬ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች ስትል አወገዘች
የዕርዳታ ድርጅቶች ለየመናውያን የምግብ ዕርዳታ እያቀረቡ ነው

 

ሆኖም ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሲአይኤን ሪፖርት አጣጥለው ነበር፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የአሜሪካ ዋና ወዳጅ እንደሆነች በመግለጽም ገደብ እንዲጣልባት የተነሱ ጥያቄዎችን ተቃውመዋል፡፡ በዚህ ተበሳጭቷል የተባለው ሴኔቱ፣ ለሳዑዲ የሚደረግ ወታደራዊ ዕገዛ እንዲቋረጥ ቢወስንም፣ በአሁኑ ሳምንት ተጨማሪ ውይይት ይደረግበታል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ ሴኔቱ ይህንን ውሳኔ ቢያሳልፍም አብላጫው መቀመጫ በሪፐብሊካኑ በተያዘበት በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ አይገመትም፡፡ ምናልባት ከ2019 በኋላ ዴሞክራቶች አብላጫ ወንበር ሲይዙ ሁኔታዎች ሊቀያየሩ ይችላሉ፡፡

በሳዑዲ ለሚመራው ጥምር ኃይል አሜሪካ የቁሳቁስና የደኅንነት ዕርዳታ መሣሪያም ትሸጣለች፡፡ 60 በመቶ ያህሉ የሳዑዲ የጦር መሣሪያዎች ከአሜሪካ የሚገቡ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ከአሜሪካ በተጨማሪ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ስፔን፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ካናዳ፣ ቱርክና ስዊድን ለሳዑዲ የጦር መሣሪያ ሸጠዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 በየመን በተቀሰቀሰው ጦርነትም ሳዑዲን ጨምሮ ስምንት የሱኒ ሙስሊም ተከታይ አገሮች ከሁቱ ሙስሊም በመቃረን የሚያደርጉትን ጦርነት አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ይደግፋሉ፡፡

በየመን ደግሞ በጦርነቱ ሳቢያ ከ29 ሚሊዮን ሕዝብ 18 ሚሊዮኑ ለከፋ ረሃብ ተጋልጧል፡፡ የቀሩትም ቢሆኑ በረሃብ ውስጥ እንደሚገኙ ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት አስታውቋል፡፡ የመናውያኑ ጦርነቱ ከሚቀጥፋቸው ባለፈም በበሽታ እየሞቱ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ድርጅቶች እንደሚሉት በየመን ባለው ጦርነት ከ2015 እስከ 2017 ብቻ ከ8,000 እስከ 14,000 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 5,000 ያህሉ ሰላማዊ ሰዎች ናቸው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በአገሪቱ በተከሰተው ረሃብ 50 ሺሕ ያህል ሞተዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡

የሱዳኑ ኦማር አልበሽር የሶሪያ ጉብኝት

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሶሪያ ጦርነት ውስጥ ከገባች ከስምንት ዓመት ወዲህ ሶሪያን በመጎብኘት የመጀመርያው የዓረብ ሊግ አገር መሪ ሆነዋል፡፡

አልጀዚራ እንደሚለው፣ ፕሬዚዳንት አልበሽር እሑድ ሶሪያ ደማስቆ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አልአሳድ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በአገሮቹ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የመከሩ ሲሆን፣ በአንዳንድ የዓረብ አገሮች በሚታየው ቀውስ ላይም ተወያይተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሶሪያ በቀጣናው የነበራትን ወሳኝ ሚና መልሳ እንደምትቀዳጅና ድንበሮቿን አስጠብቃ እንደምትኖር ለዚህም ሱዳን ከጎኗ እንደምትቆም መናገራቸውም ተገልጿል፡፡ ሆኖም የፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር የሶሪያ ጉብኝት ዓላማ ግልጽ እንዳልሆነ አልጀዚራ አስፍሯል፡፡

የሱዳኑ ኦማር አልበሽር የሶሪያ ጉብኝት