Skip to main content
x
‹‹ፍላጎቴ አርሶ አደሩ ጥሩ ገበያ እንዲያገኝና ምርቱ ጥራት እንዳለው እንዲመሰከርለት ነው››

‹‹ፍላጎቴ አርሶ አደሩ ጥሩ ገበያ እንዲያገኝና ምርቱ ጥራት እንዳለው እንዲመሰከርለት ነው››

አቶ በለጠ በየነ፣ የአግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር

አቶ በለጠ በየነ የብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በ1969 ዓ.ም. ፋፋ የምግብ ድርጅት ሲመሠረት ጀምሮ በተመጣጠነ ምግብ ማቀነባበር ዙሪያ ተሳትፈዋል፡፡ ከ1985 ዓ.ም. ወዲህ በዚሁ ዘርፍ የግል ድርጅት በመክፈት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከሆላንድ በንግድ ሥራና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ እንዳላቸው የነገሩን አቶ በለጠ፣ ሴኔጋል በነበራቸው ቆይታ በሥነ ምግብ ዙሪያ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ ፋፋን ከመመሥረት ጀምሮ የምግብ ይዘትና ጥናት ላይ መሥራታቸው ለአሁኑ ስኬታቸው መነሻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምግብ ከማቀነባበር ባለፈ የግብርና ምርቶችን ጥራት የሚያረጋግጥ ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ አቋቁመዋል፡፡ በሥራዎቻቸው ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ማጥናት የጀመሩት መቼ ነው?

አቶ በለጠ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በንግድ ሥራ ትምህርት በ1965 ዓ.ም. ተመርቄ ከመውጣቴ በፊት ሦስተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ የኢትዮጵያ የምግብ ጥናት ድርጅት የገበያ ክፍል ኃላፊ ሆኜ መሥራት ጀምሬ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ የገበያ፣ የምግብ ዓይነትና ዋጋ እንዳውቅና ለምርምር የሚያገለግሉ ግብአቶችን እንድረዳ አግዞኛል፡፡ ከዚህን ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ማጥናት ችያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ምግቦች ይዘትና ዋጋ የሰሜን፣ የምዕራብና የደቡብ፣ የአፋርና የሱማሌ፣ የማዕከላዊና  የሸዋና አካባቢው የምግብ ሥርዓት መስመር ይዘው፣ ተመርምረው፣ ለተመራማሪዎችም ለተመጋቢውም የካሎሪና የፕሮቲን ይዘቱ እንዲታወቅ ሠርተናል፡፡ በተለይ እናቶች ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያበሉ ለማስቻል የጃንሆይ መንግሥት አዋጅ ማውጣቱ የኢትዮጵያ የምግብ ጥናት ድርጅትን ለመመሥረት አግዞናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የምግብ ጥናት ድርጅት ያበረከተው አስተዋፅኦ ምን ነበር?

አቶ በለጠ፡-  እንደማኅበረሰቡ አካባቢና ለሕፃናት አመጋገብ ተጨማሪ ምግብ ምን ጥቅም አለው? የትምህርት ቅቡልነታቸውን፣ ጤንነታቸውን ለመጨመር በሚል የምግብ ምርምር የሚካሄድበት ክፍል ነበረው፡፡ በተደረገው ምርምር መሠረት ፋፋ ተገኝቷል፡፡ በ1969 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የተባለውን የሕፃናት ምግብ ፋብሪካ ፋፋ የምግብ ድርጅት አቋቋመች፡፡ በስዊድን ዕርዳታና እኔ እመራው የነበረው የምግብ ጥናት ድርጅቱ ባደረጉት ጥረት የፋፋ ምግብ ድርጅት ተቋቁሟል፡፡ በወቅቱ በአገሪቱ ከሚገኙት 158 ፋብሪካዎች በልዩ ሁኔታ ዕቃዎቹ ከቀረጥ ነፃ ገብተውና ከገበሬዎች እህል እየተገዛ በመጀመሪያ 12 ሺሕ ቶን፣ በ1977 ዓ.ም. 24 ሺሕ ቶን፣ ሥራዬን በ1982 ዓ.ም. ስለቅ 33 ሺሕ ቶን በዓመት ያመርት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ጨርቃ ጨርቅ ኮርፖሬሽንም አገልግለው ነበር፡፡ ፋፋን ለምን ለቀቁ?

አቶ በለጠ፡- በደርግ ጊዜ ድርጅቱን ጥሩ አስተዳድረው ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ምርት የውጭ ገበያ ዋጋው እያነሰ ስለመጣና ኤክስፖርት እንዲያገግም በዘርፉ እንድሠራ ስለተፈለገ ልምዴን ይዤ የጨርቃ ጨርቅ ኮርፖሬሽን የኤክስፖርት ማናጀር ሆንኩ፡፡ ለሁለት ዓመት ሠርቼ ነው በ1985 ዓ.ም. መጀመሪያ የለቀኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ነው በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ በግል መሥራት የጀመሩት?

አቶ በለጠ፡- አዎ፡፡ ከሦስት ጓደኞቼ ጋር ሆነን እኔ በዕውቀቴ እነሱ በገንዘብ አድርገን የፋፋን ዓይነት ድርጅት ‹‹ጤና ምግብ አምራቾች ብለን መሠረትን፡፡ ይህ የተመጣጠነ ምግብ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያቀርብ ነበር፡፡ ድርጅቱ እየተስፋፋ ሄዶ ከአኩሪ አተር ምግብ የምንሠራበትን ደረጃ አስተዋውቀናል፡፡ ፋሚክስ ፕላስ ማለትም በ10 ደቂቃ የሚበስል፣ 15 ዓይነት ቫይታሚኖችን ይዞ የሚመረትና ለልጆች አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት የሚረዳና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚያግዝ ‹‹በርታ›› የሚባል ምግብ በሰፊው አምርተናል፡፡ ለዩኒሴፍ ትልቅ አቅራቢም ጤና የምግብ ድርጅት ነበር፡፡ ለዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅትም በድርቅ ለተጎዱ ሕፃናትና አዋቂዎች የሚሆን አምርተናል፡፡ በ1993 ዓ.ም. አካባቢ ህሊና ገንቢ ምግቦች ድርጅትን መሠረትኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ህሊና ገንቢ ምግቦች የግልዎት ነው? ምን ዓይነት ምግቦች ያመርታል?

አቶ በለጠ፡- ይኼኛውን ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የመሠረትኩት፡፡ ህሊና የሚያመርተው አዲስ ምግብ ነበር፡፡ ምንም ሌላ ተጨማሪ ምግብ የማያስፈልገውና እጅግ ለተጎዱ ሕፃናት የሚሆን ከኦቾሎኒ የሚዘጋጅ ምግብ ነው፡፡ የፈረንሣይ ሳይንቲስቶች የሠሩት ምግብ ነው፡፡ ከኦቾሎኒ የሚሠራ ሲሆን፣ ዩኒሴፍም እየገዛን ነበር፡፡ ይህን ምግብ የሠራነው ምግብ ጥናት ድርጅት እያለሁ አብሮኝ ይሠራ የነበረ ሰው ምግቡን ኢትዮጵያ መሥራት ትችላለህ ብሎ ባደረገልኝ ድጋፍ ነው ለገጣፎ ላይ ፋብሪካው የተከፈተው፡፡ የኦቾሎኒ ቅቤው 23 ዓይነት ቫይታሚን አለው፡፡ ነፍስ አድን ነው፡፡ ኤችአይቪ ያለባቸውን ሰዎች ሲዲፎር ያስተካክላል፣ ከቫይረሱ ጋር ለሚወለዱትም ገንቢ ምግብ ነው፡፡ የታመሙ ቶሎ እንዲያገግሙ ይረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ገበያው ላይ አለ?

አቶ በለጠ፡- መንግሥትና ዩኒሴፍ እየገዙ ለጤና ጣቢያዎች ይሰጣሉ፡፡ ሦስት ዓይነት ምርት አለው፡፡ በምግብ እጥረት በጣም እና በትንሹ ለተጎዱ የሚሆን ነው፡፡ አሁን ደግሞ የንጥረ ነገር ይዘቱን ወደ 70 ከፍ በማድረግ ‹ድንቡጭ› የሚል እየሠራን ነው፡፡ ይህ ከሽምብራ፣ ከ23 ዓይነት ቫይታሚንና ከወተት የሚሠራ ነው፡፡ ከሶያና ከኦቾሎኒም ድንቡጭ ይሠራል፡፡ በአዮዲን የበለፀገ በቂ ጨው ስለሌለም ጣፎ ጨው እናመርታለን፡፡ ህሊና የምግብ ድርጅት ላይ እኔና ቤተሰቤ 51 በመቶ ድርሻ ሲኖረን ፈረንሣዮች ደግሞ 49 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ዩኒሴፍ ምርታችንን ስለሚገዛ በየዓመቱ የፋብሪካችንን ጥራት ኦዲት ያደርጋል፡፡ የምናመርታቸው ምግቦች በሙሉ በዘረመል ምሕንድስና ከበቀሉ አዝዕርት ነፃ ናቸው፡፡ ግብዓቶቹ የሚገዙትም ከአገር ውስጥ አርሶ አደሮች ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከጤፍ የሚዘጋጅ ፍሌክስ (እንደ ኮርን ፍሌክስ) ለመሥራትም ዝግጅት ላይ ናችሁ፤

አቶ በለጠ፡- የጤፍ ፕሮጀክት ብዙ ዓመት ሳጠናበት የቆየሁት ነው፡፡ የሕፃናት ምግብ ለመሥራት ነው ያቀድነው፡፡ ለገጣፎ ላይ መሬት አግኝተናል፡፡ ብድር አግኝተንም ማሽኖች እየገዛን ነው፡፡ ይህ ባብዛኛው ለውጭ ገበያ ቢሆንም ለአገር ውስጥም የሚቀርብ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያላቸው የግብርና ምርቶች እያቀነባበራችሁ ቢሆንም በአብዛኛው የምታቀርቡት ለውጭ ገበያ ነው፡፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የኢትዮጵያውያንም ችግር ነው፡፡ በርካታ የቀነጨሩ ሕፃናት በኢትዮጵያ ስለመኖራቸውም ይነገራል፡፡ መሬቱ ታጥቦ የሚመረቱ ምርቶች የንጥረ ነገር ይዘታቸው እየቀነሰ መሆኑም ከዚህ ቀደም ተነግሯል፡፡ ይህ በሆነበት ያቀነባበራችሁትን ምግብ ለምን ለአገር ውስጥ ገበያውም አታቀርቡም?

አቶ በለጠ፡- እውነት ነው፡፡ ፋፋ ሲጀመር ጀምሮ አለሁኝ፡፡ ፋፋ፣ ጤናና በርታ ሲቀነባበሩ ሁሉ አለሁኝ፡፡ በእርግጥ በፊት እኔ ነበርኩ፡፡ አሁን ግን በርካታ ድርጅቶች ተመሥርተዋል፡፡ ተመሳሳይ ምርቶችን እያቀነባበሩ ነው፡፡ የውጭ ድርጅቶችም ይገዟቸዋል፡፡ ዩኒሴፍ ለምሳሌ ከእኛ ድርጅት ቢገዛ አብዛኛውን የሚያቀርበው እዚሁ ነው፡፡ የተቀነባበረው ውጭ ቢሄድም ጥሬ ዕቃው የሚገዛው ከአገራችን አርሶ አደር ነው፡፡ ኦቾሎኒ በብዛት እንገዛለን፡፡ ሌሎችንም ጥሬ ዕቃዎች በብዛት እንገዛለን፡፡ በእሴት ሰንሰለት ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እኛ እየደረሰ እኛ ደግሞ ሸጠን ዶላር እናመጣለን፡፡ የእኔ ዓላማ አርሶ አደሩ ጥሩ ገበያ እንዲያገኝና የሚያመርተው ጥራቱን ስለመጠበቁ እንዲመሰከርለት ነው፡፡ በአገራችን አፍላቶክሲን አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ኦቾሎኒው ኪሎ እንዲያነሳ ውኃ እየነከሩ እያቀረቡልን ችግር ይገጥመን ነበር፡፡ አርሶ አደሮችን አሰባስበንና ከአንድ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር ሆነን ኦቾሎኒ አምራቾቹን አሠለጠንን፡፡ አሁንም ከምርት መሰብሰብ በፊት ስለሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ በሚፈለፈልበት ጊዜ በእጅ ስለሆነ የመጀመሪያው የኦቾሎኒው ቅርፊት እንዲነሳ ውኃ ውስጥ ይዘፈዝፉት ነበር፡፡ ይህ ለአፍላቶክሲን (ሻጋታ) መፈጠር አንዱ ምክንያት ስለሆነ መፈልፈያ እንዲጠቀሙ፣ ከተፈለፈለ በኋላ በአግባቡ እንዲደርቅ እያሠለጠንን ነው፡፡ በርበሬ ላይም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ባልጠበቀ መልኩ የተሰበሰበ ምርትን አዘጋጅተው ለውጭ የሚልኩ ሰዎች አልቅሰዋል፡፡ በኮንቴየነር የላኩት በጥራት ችግር ምክንያት አክስሯቸዋል፡፡ ለምሳሌ ምሥራችንን ሽምብራችንን ብንወስድ ከእኛ አገር ወጥቶ እየፀዳ ስንት ጊዜ ተገለባብጦ ይሸጣል፡፡ ሽምብራችን ከዚህ ሲወጣ እስራኤል ደርሶ ያበቃ ይመስለናል፡፡ ግን እውነታው ከዚያም ተገለባብጦ አሜሪካ ድረስ መግባቱ ነው፡፡ የእኛ የግብርና ምርት ከዘረመል የፀዳና ኦርጋኒክ ስለሆነ በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ የውጭ ድርጅቶችም የእኛን የተፈጠሮ ጥራጥሬ ለመውሰድ ይጠይቁናል፡፡ እኛ ግን አገራችን ውስጥ የሚበላ ይጠፋል ብለን ጥያቄያቸውን እያቀዘቀዝን ነው፡፡ ሆኖም የእኛ ከዘረመል ምሕንድስና የፀዱ ኦቾሎኒ፣ ሽምብራ፣ ምስርና ሌሎች ምርቶች በውጭው ዓለም ተፈላጊ ናቸው፡፡ አሜሪካውያን ኦቾሎኒያቸው በዘረመል ምሕንድስና የበቀለ ስለሆነና ከዚህ የሚሠራው የኦቾሎኒ ቅቤ አለርጂ እየሆነባቸው ስለመጣ እየተውት፣ በዚያ ምትክ የእኛን ሽምብራ እየወደዱት ነው፡፡ ከሽምብራ የሚሠራ ሁሙስ የተባለ ምግብ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ኮሜርሻል ፋርሚንግ (ንግዳዊ እርሻ) ብትገባ ብለን በየጊዜው የምንወተውተው ባለን መሬት ላይ በደንብ አምርተን ሕዝባችንም ራሱን መግቦ ለውጭ ገበያም እያቀረብን የውጭ ምንዛሪን እንድናገኝና የሕዝቡ ኑሮ እንዲለወጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሜርሻል ፋርሚንጉ ላይ ምን ይመከራሉ?

አቶ በለጠ፡- የሚያዋጣንና የጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ ፕሮግራምም ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ መግባቱ ነው፡፡ ለዚህ ግብርናውን ማዘመንና ሰፋፊ እርሻዎችን ማረስ አለብን፡፡ ትናንሽ ግድቦች እየሠራን ገበሬውን ተጠቃሚ ማድረግ አለብን፡፡ ይህ ሲሆን ከጤና ጥበቃ ጋር አብሮ መሥራትና ወባውን ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ ከቆላማ ቦታ ወባውን አጥፍቶ በዓመት ሦስቴ ማምረት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን የግብርና ምርት ቆልተንና አንፍረን እንኳን ብንሸጥ በውጭ ዓለም ተፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ግን መጀመርያ ደረጃ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ምርቶቻችንን በማፅዳት፣ ደረጃ በመስጠትና ጥራት በመጠበቅ ብዙ ዶላር ማምጣት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርጋኒክ አተር፣ ባቄላ ምስር…እያልን ጥራቱን ጠብቀንና አሽገን ብንሸጥ እንችላለን፡፡ የእኛ ምስር በጣም ተወዳጅ ነው፡፡ አትክልቶቻችን ሁሉ ጣማቸው ተወዳጅ ነው፡፡ የተፈጥሮ ስለሆኑ ያለብዙ ቅማመ ቅመም የሚጣፍጡ ናቸው፡፡ ብዙ ዕድል ነው ያለን፡፡ ከዚህ ጋር አብሮ የሚታቀደው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ላቦራቶሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን ምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ጥራትን እንዴት ያዩታል?

አቶ በለጠ፡- በየገበያው የሚቀርቡ የተቀነባበሩ ምግቦች አሉ፡፡ የአፍላቶክሲን ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ወተትን ብናይ አብዛኛው አርቢ የሚያበላው የኑግ ጭማቂ ነው፡፡ ምግባቸው ከአፍላቶክሲን የፀዳ እንዲሆን መሥራት አለብን፡፡ ኅብረተሰቡ መጠየቅ፣ አምራችና አቅራቢውም የሚቀርበው ምግብ ምን ያህል የኅብረተሰቡን ጤና የጠበቀ ነው ብሎ መሥራት አለበት፡፡ ጥራት ላይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የምግባችንን ጥራት ካልጠበቅን ጉዳቱና ለሕክምና የሚወጣው ወጪ ያንኑ ያህል ነው፡፡ ምግብ አቀነባባሪዎች አዘጋጅተው የጥራትና የደኅንነት ፍተሻ ማስደረግ አለባቸው፡፡ እኔ ያቋቋምኩት ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የምግብ ጥራትን ይመረምራል፡፡ ደረጃ መዳቢዎችም የምርመራ ሥራ ይሠራል፡፡ ውኃ ላይ ለምሳሌ በብሌስ በኩል 29 ዓይነት ምርመራ እንሠራለን፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ እኛ ጋር የሚመጡትም በራሳቸው የሚተማመኑ ብቻ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ደረጃዎችን የመስጠት መብት አለን፡፡ ድርጀቶች በእኛ አስመርምረው ጥራታቸውን ጠብቀው ከተገኙ ውጭም ቢልኩ ተቀባይነት አላቸው፡፡ የውጭው ዓለም የሚሠራበትን የጥራት ደረጃ መስፈርትና ቴክኖሎጂ ተከትለን እየሠራን ነው፡፡ በዚህም ምንም እንኳን ድርጅቱን ከፍተን ለሁለት ዓመት ያህል ብዙ ላኪዎች ያልመጡልን ቢሆንም፣ አሁን እየመጡና ራሳቸውንም አገራቸውንም ከኪሳራ እየታደጉ ነው፡፡ ጥራቱ ተጠብቋል ተብሎ የላኩት ዕቃ ውጭ ደርሶ ደረጃውን አልጠበቀም ተብሎ ሲመለስ ያለው ኪሳራ ቀላል አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ ላኪውም አገሪቷም እንዳትከስር ተባብረን ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች ለውጭ ገበያ እናቅርብ ነው የምንለው፡፡ ብዙዎች የላኩት ዕቃ ተመልሶ ሲመጣና ኪሳራ ውስጥ ሲገቡ ደረጃውን የጠበቀ ምርመራ ለማግኘት እኛ ጋር መምጣት ጀምረዋል፡፡ ከኪሳራ አዳንከን ብለው የሚያመሰግኑኝም በርካቶች ናቸው፡፡ እኛም የምርመራ፣ የፍተሻና ሰርተፍኬት መስጠት አቅም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ጥራት ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ሠራችሁ?

አቶ በለጠ፡- ዘንድሮ ሕዝቡ ስለጥራት ጉዳይ እንዲገነዘብ 1.2 ሚሊዮን ብር መድበናል፡፡ ለሚቀጥለው ዓመት ሁለት ሚሊዮን ብር ይዘናል፡፡ በዚህ መልኩ ማኅበረሰቡ ስለሚገዛውና ስለሚመገበው ምግብ ምንነት እንዲጠይቅ በተለያዩ ዘዴዎች እናስተምራለን፡፡ ስለምግቡ ደኅንነት ማወቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ያለዎትን ልምድ ለማካፈል ከማን ጋር ይሠራሉ?

አቶ በለጠ፡- ላቦራቶሪው በመከፈቱ ብቻ ምሁራን ለጥናት እየመጡ ነው፡፡ ከጂማ፣ ከባህር ዳር፣ ከሐዋሳና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንሠራለን፡፡ ባሉን ሦስት ድርጅቶችም 450 ሠራተኞች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ለየትኞቹ ምርቶች የላብራቶሪ ምርመራ ታደርጋላችሁ?

አቶ በለጠ፡- ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ የግብርና ምርቶችና ምግቦችን የጥራት ደረጃ ለመፈተሽ የተቋቋመ ኩባንያ ነው፡፡ የግብርናንና የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችን መደገፍ፣ የምግብ ደኅንነትን ማረጋገጥና ሸማቹን ለመጠበቅም ይሠራል፡፡ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸውን እንዲጨምሩ ማስቻልም የሥራው አካል ነው፡፡ የአገራችን ምርቶች በላቦራቶሪያችን አንዴ ተመርምረው ካለፉ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ተቀባይነት አላቸው፡፡ ኩባንያው የባዮሎጂካል ላቦራቶሪ፣ የኬሚስትሪ ላቦራቶሪ እንዲሁም የምርት ሰርተፍኬሽን ክፍሎች አሉት፡፡ በተመጣጠነ ምግብ፣ በምግብ ደኅንነት፣ በመልካም የአመራረት ሥርዓትና በላቦራቶሪ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ምግብና የምግብ ግብዓቶች፣ በውኃ በአልኮልና በለስላሳ መጠጦች ላይ ፍተሻ እንሠራለን፡፡ የጥራት ማረጋገጫ እንሰጣለን፡፡ ማር፣ ውኃ፣ የምግብ ዘይት፣ የኦቾሎኒ ቅቤ፣ የተቆላና ተቆልቶ የተፈጨ ቡና፣ ጁስ፣ ካችአፕና ድልህ የጥራት ደረጃ ምርመራና የጥራት ሰርተፍኬት ከምንሰጥባቸው ምርቶች ይጠቀሳሉ፡፡