Skip to main content
x
በተጠናቀቀው 2018 ትኩረት ያገኙ ዘገባዎች

በተጠናቀቀው 2018 ትኩረት ያገኙ ዘገባዎች

የፈረንጆቹ ዓመተ 2018 አመፆች፣ ጦርነቶች፣ ስምምነቶች፣ አደጋዎችና ሌሎችንም ክስተቶች አስተናግዷል፡፡ ዓመቱ ለማብቃት የሳምንት ያህል ዕድሜ ሲቀረው፣ በዓመቱ በዓለም መነጋገሪያ የተባሉ ክንውኖች በየመገናኛ ብዙኃኑ ተዘግበዋል፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ብሎገሮች እንደራሳቸው ዕይታ ዋና ነበሩ ያሏቸውን አትተዋል፡፡

የአሜሪካው ፔንታጎን ብሔራዊ የደኅንነት ስትራቴጂ መንደፉ፣ ደቡብ ኮሪያ የክረምት ኦሊምፒክ ማዘጋጀቷ፣ አሜሪካ በኢየሩሳሌም ኤምባሲ መክፈቷና ማወዛገቡ፣ በጃፓንና በአውሮፓ ኅብረት መካከል የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት መፈረሙ ከዓመቱ ክንውኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ሩሲያ ኢንተርኮንቲኔንታል ኑክሌር ክሩዝ ሚሳኤልን ጨምሮ አዳዲስ የመድፍ የጦር መሣሪያዎችን ማስተዋወቋም የ2018 ዓብይ ጉዳይ ነበር፡፡

ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ካገኙ ጉዳዮች አንዱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ አቀጣጥለውታል የተባለው ‹‹የንግድ ጦርነት›› ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 መጀመርያ አሜሪካ ከውጭ በሚገቡ የማጠቢያ ማሽኖችና በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ቁሳቁሶች እንዲሁም ለአሜሪካ ደኅንነት ሥጋት ነው በማለት በብረታ ብረትና በአሉሚኒየም ላይ የጣለችው ታሪፍ አወዛጋቢ ሆኖ ከርሟል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ምርቶቿን በብዛት በምታቀርበው ቻይና ምርቶች ላይ የጣሉት ከፍተኛ ታሪፍ በተለይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አሜሪካ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ 50 ቢሊዮን ዶላር ያህል የታሪፍ ጭማሪ በማድረጓ የተፈጠረው የንግድ ጦርነት ቻይናን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ገበሬዎችንና አምራቾችንም አቃውሷል፡፡ በአሜሪካ የንግድ ጉድለቱ ከመስፋቱም በተጨማሪ የአሜሪካ ገበሬዎችና አምራቾች ወደውጭ ከሚልኩት ምርት ላይ ኪሳራ እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

ወደ አሜሪካ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ታሪፍ የመጫኑን ያህል የአውሮፓ ኅብረትና ቻይናም በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣላቸው ሁለቱንም ወገኖች ነበር ያወዛገበው፡፡ በመሆኑም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተጨማሪ ታሪፍ ላለማድረግ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ከቻይና ጋር የገቡትን የንግድ ውዝግብ ለማርገብም በኅዳር 2018 ለ90 ቀናት የሚቆይ ስምምነት አድርገዋል፡፡

እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ያቀረበችው ጥያቄም የ2018ም አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ 2018 ለጠቅላይ ሚኒስትሯ ተሬሳ ሜይ ፈታኝ ነበር፡፡ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት መውጣት ላይ ሁለቱም ወገኖች ከመግባባት ላይ የደረሱ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ተሬሳ ሜይ ግን ምክር ቤታቸውን (ሐውስ ኦፍ ኮመናቸውን) ማማለል ተስኗቸዋል ተብሏል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ እየተባባሰ ስለመምጣቱም በ2018 ትኩረት ተሰጥቶት ተዘግቧል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ሳይንቲስቶች ላለፉት ሦስት አሠርታት ያህል ድምፃቸውን ቢያሰሙም የአየር ንብረት ለውጥ መወያያ ከመሆን ባለፈ ብዙም ወደ ተግባር ሳይገባ ዓመቱ እየተገባደደ ነው፡፡ ዘንድሮም እንደከረሙት ዓመታት ሁሉ ሰደድ እሳትን፣ ጎርፍን  ሪከርድ ያስመዘገበ ሙቀትንና አውሎ ንፋስን አስተናግዷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጡን ለመግታት ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቅ የጋዝ መጠን እንዲቀንስ ምክረ ሐሳብ ቢያቀርብም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የቀረበውን ሪፖርት፣ ‹‹አላምነውም፤›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

በአሜሪካና በኢራን መካከል የነበረውን የኑክሌር ስምምነት አሜሪካ ያፈረሰችውም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡንግ የገቡትን የቃላት ጦርነት ረገብ አድርገው ፊት ለፊት መገናኘታቸው የዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ነበር፡፡

የጋዜጠኛና የዋሽንግተን ፖስት ዓምደኛ ትውልደ ሳዑዲ ዓረቢያዊው ጀማል ካሾጊ መገደልም መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል፡፡ ጋዜጠኛ ካሾጊ አሟሟት ላይ የተለያዩ ምርመራዎች እየተከናወኑና መረጃዎች እየተለቀቁ ቢሆንም ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም፡፡

2018 መጥፎ ነገር ብቻ የተዘገበበት ሳይሆን መልካም ነገር የተሰማበትም ነበር፡፡ ይህ መልካም ዜና የመነጨው ደግሞ ከኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት ነበር፡፡

ዶ/ር ዓብይ ‹‹በሰላም መልዕክተኛነታቸው ዓለምን አስደምመዋል›› ሲል የ2018 ዋና ዋና አጀንዳዎችን በብሎጉ ያሰፈረው የአሜሪካ ፖለቲካና መንግሥት ነክ ጉዳዮች ኤክስፐርት፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት የጥናቶች ዳይሬክተር፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና ብሎገሩ ጀምስ ኤም ሊንድሴይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን፣ ሁለቱም አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን በየአገሮቹ መክፈታቸው፣ በዓመቱ ከተከናወኑ መልካም ጉዳዮች በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በአገር ውስጥ ለውጥ እያከናወኑ መሆኑ፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና በአገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ምክንያት መሆናቸውም ተወስቷል፡፡

ኤርትራ ከሶማሊያና ጂቡቲ ጋር የነበራትን ውዝግብ በሰላም ለመፍታት ከስምምነት መድረሷ፣ ለዚህም የተባበሩት መንግሥታት ጥሎባት የነበረው የጦር መሣሪያ ገደብ መነሳቱ ተዘግቧል፡፡ በተያያዘም የዶ/ር ዓብይ የሰላም አጀንዳ ብልህ የፖለቲካ አመራር የተባለ ሲሆን፣ ይህም ዕድል ታክሎበት የአፍሪካ ቀንድን ሰላም ለማረጋገጥና የቀጣናውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል፡፡

የመንና ቬንዙዌላ ሰብዓዊ ቀውስን ያስተናገዱበት ዓመትም ነበር፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት 2.3 ሚሊዮን የቬንዙዌላ ዜጎች ከአገሪቷ ተሰደዋል፡፡ ለዚህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ በአግባቡ አለማስተዳደር ዋና ምክንያት ነው፡፡

የየመን እርስ በርስ ጦርነት በ2018 አራተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በየመን ያለው ሰብዓዊ ቀውስ በዓለም ሁሉ ካለው የከፋ ነው ተብሏል፡፡ 14 ሺሕ ያህል የመናውያን በእርስ በርስ ጦርነት ሞተዋል፡፡ ጦርነት በፈጠረው ረሃብ 50 ሺሕ ያህል ዜጎች ሞተዋል ተብሎም ይገመታል፡፡ በየመን ያለውን ረሃብ የሚያስቃኙ ፎቶዎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቢለቀቁም፣ ጦርነቱን ያስቆመ አንድም አካል የለም፡፡ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በኮንጎ፣ በሶሪያና በደቡብ ሱዳን ያለው ሰብዓዊ ቀውስም እ.ኤ.አ. በ2018 የቀጠለ ነበር፡፡   

የኑሮ ውድነት ያስነሳው ተቃውሞ

በሱዳን የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል በሚል ለተቃውሞ የወጡ ሱዳናውያን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ ከሥልጣን ይውረዱ የሚል አጀንዳ ማንሳታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን የያዘው ተቃውሞ የተጀመረው በአትባራ ከተማ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተስፋፍቷል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስና መሣሪያ መተኮሳቸውንና 12 ሰዎች መሞታቸውንም ዘገባው ያሳያል፡፡ ተቃዋሚዎችም ሕንፃዎችን ሲከቡና በየጎዳናው ጎማ ሲያቃጥሉ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ታይተዋል፡፡

የዳቦ ዋጋ ከ0.02 ዶላር ወደ 0.06 ዶላር መጨመሩ፣ ከባንክ የሚወጣ ገንዘብ ላይ ገደብ መጣሉ፣ የኤቲኤም ማሽኖች አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ የማይሰጡ መሆኑ ተቃዋሚዎች ካነሷቸው ጥያቄዎች ይጠቀሳሉ፡፡

​​በተጠናቀቀው 2018 ትኩረት ያገኙ ዘገባዎች
ሱዳናውያን በዳቦና በነዳጅ ዘይት ላይ የተጣለውን የዋጋ ጭማሪ ተቃውመዋል