Skip to main content
x
ዳያስፖራው በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሊሳተፍባቸው የሚችሉ አማራጮች ቀረቡ

ዳያስፖራው በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሊሳተፍባቸው የሚችሉ አማራጮች ቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለዳያስፖራው ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት አገር አቀፍ የዳያስፖራ የውይይት መድረክ፣ ዳያስፖራው በተለያዩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፎች እንዲሰማራ አማራጮች ቀረቡ፡፡

ዳያስፖራው በከተማ ልማት ዘርፍ በአማካሪነት፣ በጥናትና ምርምር፣ በከተማ ግብርና፣ በከተማ ፅዳት፣ በውበትና አረንጓዴ ልማት፣ በቤቶች ልማት ዘርፍ፣ በሪል ስቴት፣ በአፓርትመንት፣ በግንባታና በኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ በአርክቴክትነት፣ ሕንፃ ግንባታ አማካሪነት፣ በኮንትራክተርነት፣ በኮንስትራክሽን ማሽንና ግብዓት አቅራቢነት፣ በከተማ መንገድ ግንባታና በጌጠኛ መንገድ (ኮብልስቶን) መሳተፍ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ዓርብ ታኅሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል የተዘጋጀውን የውይይት መድረክ የታደሙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር ዓባይ እንደገለጹት፣ እጅግ ኋላ ቀር የነበረችው አዲስ አበባ አሁን እያደገች ቢሆንም የተለያዩ ችግሮች አሉባት፡፡

‹‹የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በተለይ በከተማ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ዕውቀት እንዳለው እንገነዘባለን፤›› ያሉት አቶ ጃንጥራር ከተሜነት ያለ ፅዳት፣ ያለ ቤትና ያለ መሠረተ ልማት ሊመጣ አይችልምና ዳያስፖራው ዕውቀቱንና ገንዘቡን በሚኒስቴሩ በተቀመጡ አማራጮች ላይ እንዲያፈስ ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 25.7 በመቶ የከተማ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች፣ ከ16 እስከ 18 በመቶ የሚሆነው ወጣት በየከተማው ሥራ ፈላጊ መሆኑን በመግለጽም የከተማ አጀንዳ ያገባኛል ማለት ከዳያስፖራውና ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ባቀረባቸው የልማት አማራጮች ላይ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የተጠየቁት ዳያስፖራዎች በአብዛኛው የግል ችግራቸውን ነበር ያነሱት፡፡

በአክሰስ ሪል ስቴት የገጠማቸውን ውዝግብ፣ በ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤቶች በቅድሚያ ሙሉ ለሙሉ የከፈለ ያገኛል የተባለው አለመፈጸሙ፣ ካቻምና ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ 150 ቤተሰቦች ቤት ማጣታቸውና ሌሎችም ግላዊ አጀንዳዎች ተነስተዋል፡፡

መድረኩን የመሩት አቶ ጃንጥራር፣ ‹‹የግለሰብ ችግር አይፈታ የሚል አቋም ባይኖረኝም በኢትዮጵያ ሳይበሉ የሚያድሩ፣ የተቸገሩ፣ መግቢያ ያጡና እንደ እሳት የሚያቃጥል ችግር የሚያነሱ ነዋሪዎች ባሉበት አገር ዳያስፖራው የእኔ የቤት ችግር ብቻ ይፈታ ብሎ ያምናል የሚል ግምት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

በከተሞች አብዛኛው ሕዝብ ቤት ፈላጊ መሆኑን ዳያስፖራው በራሱ በኩል እንደሚጠይቅ በማውሳትም ሁለቱን አጣጥሞ ለመሄድ ይሠራል ብለዋል፡፡

‹‹የቀን ሥራ ላይ ተሰማርቶ ማደሪያ የሚቸግረው ባለበት አገር አንድን ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር እንደማይኖርና የአገሪቷን ችግር ለመቀየር አብሮ መሥራት ይገባል እንጂ፣ የሌላው ችግር አይመለከተኝም የሚል ይኖራል ብዬ አልገነዘብም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ችግሮችን በአቅማችን እንፍታ፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ዳያስፖራው የሚያጋጥሙትን ችግሮች በሚመለከታቸው አካላት በኩል ለመፍታት እንደሚሠራም አክለዋል፡፡

ወደፊት ሊሳተፉ በሚችሉት ዘርፍ ላይ ብዙም ግብዓት ያልሰጡት፣ ዳያስፖራዎች በግል ጉዳያቸው ላይ ቢያተኩሩም፣ ሚኒስትሩ ግን መንግሥት ለዳያስፖራው ጥሪ ያቀረበው ችግሮችን አብሮ መፍታት በሚቻልበት ላይ ለመሥራት ጭምር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለዳያስፖራው ጥሪ ያቀረቡት አገሪቷ ያሉባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አብሮ ለመፍታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹አገራችንን አብረን እንገንባ፣ ያላችሁን ዕውቀት አገራችሁ ላይ አፍስሱ ሲባል ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር የተመቻቸ አለመሆኑን ተገንዝባችሁ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የቤት ጥያቄ የጎላበት የዳያስፖራው ውይይት ለተያዘው አጀንዳ ትኩረት ባይሰጥም፣ ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር ግን መንግሥት በልዩ ሁኔታ ካስቀመጣቸው ዘርፎች በስተቀር ዳያስፖራው መሬት በሊዝ ጨረታ ሊያገኝ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙት ፍሰሐ ጽዮን መንግሥቱ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ሁሉም ቤት ለመሥራት ይጠይቃል፣ እኔ ግን የሰውን ጭንቅላት መገንባትና አመለካከት መቀየር ላይ መሠራት አለበት እላለሁ፤›› ብለዋል፡፡