Skip to main content
x
‹‹ኢትዮጵያ አገሬን እናድናት ብለን ከተነሳን ሁሉም ችግሮቻችን ይወገዳሉ››

‹‹ኢትዮጵያ አገሬን እናድናት ብለን ከተነሳን ሁሉም ችግሮቻችን ይወገዳሉ››

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ አንጋፋ ፖለቲከኛ

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የ88 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ በምዕራብ ወለጋ ቦጂ ዲርመጂ አካባቢ የተወለዱት አቶ ቡልቻ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና አሜሪካ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል፡፡ በሕግ ዲግሪ አላቸው፡፡ በንጉሡ ዘመን የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በዓለም ባንክ በቦርድ ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አምባሳደር በመሆንም ሠርተዋል፡፡ አቶ ቡልቻ ከደርግ ውድቀት በኋላ የመጀመርያ የግል ባንክ የሆነውን አዋሽ ባንክን ለማቋቋም ግንባር ቀደም አደራጅና የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡ በፖለቲካውም ዓለም በተለይ የፓርላማ አባል በመሆን ይሰጡዋቸው በነበሩ አስተያየታቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተባለውን ፓርቲ እንዲቋቋም በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ዕድሜያቸው የገፋ ቢሆንም ዛሬም ጉልበት አለኝ ብለው ስለሚያምኑ፣ በዚህ ዕድሜያቸው የሚሳካላቸው ከሆነ ፓርላማ የመግባት ምኞት ጭምር እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ አቶ ቡልቻ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮችን የሚመለከቱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ የእስካሁኑን የሕይወት ጉዞዋቸውንና ወቅታዊውን የአገሪቱን የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በመንተራስ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሕይወት ጉዞዎ ለመጀመር እስኪ ታሪክዎን በአጭሩ ይንገሩን?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ የተወለድኩት በምዕራብ ወለጋ ቦጂ ዲርመጂ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ እዚያው ቦጂ ዲርመጂ ውስጥ ከጣሊያን በፊት የተማሩ አስተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከጣሊያን ተደብቀው የሚያስተምሩ ስለነበሩ እነሱ ቤት ውስጥ ሀሁ አስተማሩኝ፡፡ እዚያው በነበረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቄሶችና ዲያቆኖች አማርኛ አስተማሩኝ፡፡ ማንበብና መጻፍ አስተማሩኝ፡፡ በኋላ መንግሥት ትምህርት ቤት ከፈተ፡፡ በዚያን ወቅት 12 ዓመቴ ነበር፡፡ ከአንደኛ ክፍል እስከ ሦስተኛ ክፍል እዚያው መንደሬ ውስጥ ተማርኩ፡፡ ወደ 16 ዓመቴ አካባቢ ደግሞ ከጓደኞቼ ጋር ወደ አዲስ አበባ እንሂድ ተባባልንና አዲስ አበባ መጣን፡፡ አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ ግን ፈፅሞ ትምህርት ቤት መግባት አቃተን፡፡ ምክንያቱም በሚገባ አማርኛ አናውቅም፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች እኛን ለመመደብ ተቸገሩ፡፡ ለመመደብ አማርኛ መቻል አለብህ፡፡ እኛ ደግሞ አማርኛ በደንብ አናውቅም፡፡ ስለዚህ ወደ አገራችሁ ሂዱና አማርኛ ተምራችሁ ተመልሳችሁ ኑ አሉን፡፡ በአገራችን እንኳን አማርኛ ልንማርበት ሰው ሁሉ የሚናገረው ኦሮሚኛ ነው፡፡ እንደተባለው ትንሽ ትንሽ አማርኛ ተማርንና ተመልሰን አዲስ አበባ መጣን፡፡  

ሪፖርተር፡- አማርኛ ተምሮ ለመምጣት ምን ያህል ጊዜ ወሰደባችሁ?

አቶ ቡልቻ፡- አንድ ሦስት ዓመት ፈጀ፡፡ ከዚያ በኋላ መደበኛ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ጊምቢ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ አምስተኛ ክፍል እንደደረስኩ እንደገና አዲስ አበባ መጣን፡፡ ግን አሁንም ትምህርት ቤት መግባት አቃተን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደገና? ለምን?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ እንደገናም አቃተን፡፡ ምክንያቱም መማር የሚገባን ዘመድ ቤት ተቀምጠን ነው፡፡ ይህ ካልሆነ የምንማርበት ትምህርት ቤት አዳሪ መሆን አለበት፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤት ለመግባት ደግሞ ከባድ ሆነ፡፡ ትምህርት ቤት ለመግባት ያኔ ሰው ማወቅ ነበረብህ፡፡ እኔ ተማሪ ነኝ፡፡ ስለዚህ ተመልሼ ጊምቢ ሄድኩ፡፡ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት በአቅሜ አስተማሪ ሆንኩ፡፡ እዚያ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ስጨርስ አቃቂ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ አቃቂ ስገባ የመጨረሻው አሥረኛ ክፍል ነው፡፡ እዚህም አስተማሪ ሆንኩ፡፡ እዚሁ እያለሁ አንድ ሦስት ዓመት በኮሪስፖንዳስ (በተልኮ) ችሎታው ባላቸው አስተማሪዎች እየተማርኩ ለኮሌጅ ራሴን አዘጋጀሁ፡፡ በጣም ጥረት የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ራሴን ለኮሌጅ ካዘጋጀሁ በኋላ ያኔ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ይባል ወደ ነበረው ሄድኩ፡፡ የኮሌጁን ፕሬዚዳንት አግኝቼ ታሪኬን ነገርኩት፡፡ አባቴን በልጅነቴ ጣለያን ስለገደለብኝ በደንብ የረዳኝ የለም፡፡ እንደ ምንም ተጣጥሬ እዚህ ደርሻለሁና ተቀበለኝ አልኩት፡፡ ወረቀቶችህን በሙሉ አምጣ አለኝ፡፡ አመጣሁና ሰጠሁት፡፡ እሱም ከመጀመርያ ዓመት ኮሌጅ የተሻለ ዝግጁነት አለህ አለኝ፡፡ ተቀበለኝና ገባሁ፡፡ አራት ዓመት ተምሬ በኢኮኖሚክስ ቢኤ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ ከዚያ በኋላ መንግሥት ወደ አሜሪካ ላከኝ፡፡ ሰርኪውዝ የሚባል ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ በወቅቱ ግን ኮርኔል ነበር የላኩኝ፡፡ እዚያ ስደርስ ግን ጓደኞቼ ሰርኪውዝ ይሻላል ሲሉኝ እዚያ ገባሁ፡፡ ሁሉ ነገር መንግሥት ነው የሚከፍለው፡፡ ሰርኪውዝ ሄጄ ሁለት ዓመት ተምሬ በኢኮኖሚክስ ዲግሪ ይዤ ተመለስኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ሥራ የጀመሩት የት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- ከተመለስኩ በኋላ የገባሁት ገንዘብ ሚኒስቴር ነበር፡፡ ያኔ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ ይልማ ደሬሳ ይባላሉ፡፡ አንተዋወቅም ነበር፡፡ ለእሳቸውም የተወለድኩበትን ቦታ፣ የተማርኩትን ትምህርትና እንዴት እዚህ ደረጃ እንደደረስኩ ታሪኬን በሙሉ ነገርኳቸው፡፡ አቶ ይልማ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁትን ልክ እንደ እኔ እየጠሩ ኢንተርቪው አድርገው ይቀጥራሉ፡፡ እኔንም ኢተርቪው ካደረጉ በኋላ እኛ ጋ ትሠራለህ አሉኝ፣ ቀጠሩኝ፡፡ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በተማርኩት ትምህርት ገንዘብ ሚኒስቴር እሠራለሁ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ምክንያቱም ትምህርቴ ከኢኮኖሚ፣ ከፋይናንስና ከባንክ ጋር ስለሚያያዝ በዚህ መሥሪያ ቤት ተቀጥሬ እሠራለሁ እንዳልኩት ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከአቶ ይልማ ጋር ገንዘብ ሚኒስቴር ለዘጠኝ ዓመታት ሠራሁ፡፡    

ሪፖርተር፡- በገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ድርሻዎ ምን ነበር? ኃላፊነትዎስ ምን ድረስ ነበር?

አቶ ቡልቻ፡- ከዳይሬክተርነት እስከ ምክትል ሚኒስትርነት ሠርቻለሁ፡፡ እንዲያውም በአጭር ጊዜ ረዳት ሚኒስትር፣ ከዚያም ምክትል ሚኒስትርነት ቦታ ደረስኩ፡፡ ያኔ የእኔ የኃላፊነት ቦታ ከፍ እያለ ሲመጣ አንዳንድ ሰዎች አቶ ይልማ ቡልቻን ወደ ላይ ያወጡት የአንድ አገር ልጆች ከወለጋ ስለሆኑ ነው ይሉ ነበር፡፡ እንዲያውም፣

‹‹ቡልቻ ደመቅሳ

ይልማ ደሬሳ፣

እኛሳ. . . እኛሳ?!. . .›› ተብሎ እስከ መተረት የተደረሰበትን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ ግን እዚያ መሥሪያ ቤት እኔና እሳቸው ብቻ ነበርን ኦሮሞ፡፡ ለማንኛውም በዘጠኝ ዓመት የገንዘብ ሚኒስቴር ቆይታዬ በጣም ብዙ ሥራ ነው የሠራሁት፡፡ አቶ ይልማም ወዲያው ነበር ከጃንሆይ ጋር ያስተዋወቁኝ፡፡ እሳቸውም ጥሩ ሠራተኛ አገኘሁ አሉ፡፡ እኔ አልተኛም፡፡ እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት እሠራ ነበር፡፡ ዘጠነኛ ዓመት ላይ አዲስ ሚኒስትር ተሾሙ፡፡ አቶ ማሞ ታደሰ ይባላሉ፡፡ እሳቸው ሲመጡ እኔ የምሠራውን እሳቸው ይሠራሉና ቦታ ልፈልግ ብዬ ወጣሁ፡፡ እሳቸው ወጣት ናቸው፡፡ የአቶ ማሞን መምጣት እንደሰማሁ ወዲያውኑ እኔ ዓለም ባንክ ለመግባት ፈለግኩ፡፡ እዚያ ለመግባት የፈለግኩት ደግሞ ቀደም ብሎ በዓለም ባንክ ውስጥ ኢትዮጵያን ወክዬ በቦርድ አባልነት እንድሠራ አቶ ይልማ ከመሄዳቸው በፊት እኔን ስለጠቆሙ ነው፡፡ የዓለም ባንክ አባል የሆኑ የአፍሪካ አገሮች አፍሪካን በዓለም ባንክ ውስጥ በቦርድ አባልነት የሚወክል አንድ አባል ተሰባስበው መርጠው ነው የሚልኩት፡፡

እንግዲህ በዓለም ባንክ ቦርድ ውስጥ እንደ ድርሻህ ነው የምትወከለው፡፡ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይና የመሳሰሉት አንዳንድ የቦርድ አባል ይወከላሉ፡፡ የአፍሪካ አገሮች ግን አሥር አሥራ አምስት ሆነው አንድ ወኪላቸውን በቦርዱ ውስጥ ይወክላሉ፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ በዓለም ባንክ ሊሠራ ይችላል ተብሎ ከኢትዮጵያ እንድወክል የተደረግሁት እኔ ነበርኩ፡፡ በቦርዱ ውስጥ ለመሥራት እንድችልም  አፍሪካውያኑን ምረጡኝ ብዬ ጻፍኩላቸው፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ አባል የሆነችው ጣሊያን ከኢትዮጵያ እንደወጣ ነው፡፡ ግን የቦርድ አባል አስመርጣና ልካ አታውቅም፡፡ ምክንያቱም ያኔ ለራሷም የሚሆን በቂ ሠራተኛ አልነበራትም፡፡ በእኔ ጊዜ ግን ይቻል ነበር፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ እኔን ተክተው ሊሠሩ የሚችሉ ስለነበሩ ነው፡፡ ለማንኛውም የዓለም ባንክ የቦርድ አባል ሆኜ ገባሁ፡፡ በቦርድ አባልነት አራት ዓመት ሠራሁ፡፡ ከዚያ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሥልጣን ያዘ፡፡ በዓለም ባንክ በቦርድ አባልነት የማከናውነው ሥራ የመንግሥት ነውና እኔም ከዚያ ወጣሁ፡፡

ከዓለም ባንክ እንደወጣሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ለመሥራት አመለከትኩ፡፡ ወዲያው ተቀበሉኝ፡፡ ለ17 ዓመታት በተባሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሠራሁ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አምባሳደር ሆኜ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሠራሁ፡፡ ዕድሜዬ ለጡረታ ሲደርስም ጡረታ ወጣሁ፡፡ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ኢሕአዴግ ገብቷል፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ አዋቂ ኢትዮጵያውያንን ጋብዞ ነበር፡፡ በአገሪቱ ሁኔታ ላይ ለመምከር ያስተላለፈው ግብዣ ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙ አዋቂ ኢትዮጵያውያን መጡ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የተናገርነውና ያሰብነው ሁሉ ፉርሽ ሆነ፡፡ አልተቀበሉንም፡፡ ከዚያ በኋላ ሕገ መንግሥት መፅደቅ አለበት አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን አፀደቁ፡፡ እኔ በምመረጥበት አካባቢ ኢሕአዴግ ኩማ ደመቅሳ ሊመረጥ ይፈልጋል ብሎ ወሬ አሠራጨ፡፡ የእኔ አባት በአካባቢው ይታወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ ኩማ ደመቅሳ ብለው ለወረዳው ሁሉ ነገሩ፡፡ በኋላ ወደቅኩ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ላይ አልተሳተፍኩም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተረቀቀው እነሱ እንደሚሉት በፓርላማ በተወከለ ሕዝብ ነው፡፡ በጭራሽ! የእነሱ ሰዎች ናቸው ሕገ መንግሥቱን ያፀደቁት፡፡ ከዚያ በኋላ እነሱ ስሜን በሌላ ስም እንደጠሩት ገብቶኛል፡፡ ከፍተኛ ጥረት አድርጌ የእኔን ወረዳ አዳረስኩ፡፡ እኔ ነኝ ቡልቻ ደመቅሳ፣ የደመቅሳ ሰንበቶ ልጅ ነኝ ብዬ ነው፡፡ እንደዚያ ብዬ ሄጄ ተመረጥኩ፡፡ ፓርላማ ገባሁ፡፡ ብዙ ለፋሁ፡፡ ከአቶ መለስ ጋርም እከራከር ነበር፡፡ እሱ ኮሙዩኒስት አይደለሁም ብሎኛል፡፡ ነገር ግን የሚሠሩት እንደ ኮሙዩኒስት ነው፡፡ እንደ ኮሚኒስት ብቻ ቢሆን እንኳን ጥሩ ነበር፣ ግን አይደለም፡፡ መንግሥትና ፓርቲ የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ ኢሕአዴግ ሆነው ፓርቲው የሚሠራው ለብቻ የመንግሥት የሚመስል ነገር አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የሚመስል ከሕዝብ ጋር የሚሠሩት ሥራ አለ፡፡ የሚወዱትን ያቀርባሉ፡፡ የሚጠሉትን ያርቃሉ፡፡ የሚሠሩት በሚስጥር ነው፡፡ ገንዘብ የሚበደሩት በሚስጥር ነው፡፡ ድብቅ ነው፡፡ በኋላ ይህንን ሁሉ የማየው ውጭ ሆኜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወቅቱን የአገሪቱን ለውጥ እንዴት ያዩታል? በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተመራ ያለውን ለውጥና ወቅታዊን የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዴት ይገመግሙታል?

አቶ ቡልቻ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሲሾሙ እኔ አሜሪካ ነበርኩ፡፡ እሳቸው ሲሾሙ ልጆቼን ለማየት እዚያ ሄጄ አራት ወር ሆኖኝ ነበር፡፡ እኔ ወደዚህ ስመጣ ደግሞ እሳቸው አሜሪካ ነበሩ፡፡ ግን ውጭ በነበርኩበት ጊዜ የተደረገውን ለውጥ ስሰማ በጣም ደስ አለኝ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የደስታዎ ምንጭ ምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡- ኢትዮጵያ አዲስ ሕይወት አገኘች ብዬ ነው የተደሰትኩት፡፡ እሳቸው አሜሪካ ሲሄዱ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡ እዚህ ከመጣሁም በኋላ እጅግ ደስ አለኝ፡፡ ምክንያቱም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አቅጣጫቸው ሁሉ ጥሩ ነው፡፡ አነጋገራቸው ጥሩ ነው፡፡ የሚናገሩትና የሚሠሩት ነገር ሁሉ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ዓብይ አህመድን እኔ ብቻ ሳልሆን ሰው ሁሉ ወዷቸዋል፡፡ እኔም ወደድኳቸው፡፡ እኔ የፖለቲካ ፍላጎት አለኝ፡፡ ነገሮችን እከታተላለሁ፡፡ ከአሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እየተሠራ ያለውን ሥራ ስመለከት እጅግ በጣም አስደስቶኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለ ለውጥ ይደረጋል ወይም ይፈጠራል ብለው ገምተው ያውቃሉ?

አቶ ቡልቻ፡- በፍፁም፡፡ እገምት የነበረው ኢሕአዴግ እንደገና ይመረጣል፣ የፈለጉትን ሰዎች ይሾምና ይቀጥላሉ ብዬ ነበር፡፡ እንዲያውም ወደ አሜሪካ ልጆቼን ለመጠየቅ ሄጄ እዚያው ለመቆየት አስቤ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም የሚለወጥ ወይም የተለየ ነገር አይኖርም ከሚል ግምት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! ምንም ለውጥ አይኖርም ብዬ ነው፡፡ ከዚያ ስለእነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የሰማሁት ሁሉ ስላስደሰተኝ ወዲያው ዕቃዬን ጠቅልዬ ልጆቼን ጤና ይስጥልኝ ብዬ ተመልሼ መጣሁ፡፡ ሐሳቤ ግን እዚያው ልጆቼ ዘንድ ለመቆየት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በዚሁ ሰበብ ማለት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! በዚሁ ሰበብ ነው ተመልሼ የመጣሁት፡፡ ስሄድ ግን እዚያ ለመቆየት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- kጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር በአካል ተገናኝተው ተነጋግረው ያውቃሉ?

አቶ ቡልቻ፡- አላገኘኋቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጡን ብዙዎች እንደተቀበሉት በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡ እርስዎም በዚህ አምናለሁ ብለዋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች አሉ፡፡ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ ያለው ግጭት መነሻ ምንድነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ቡልቻ፡- እኔ ይህ ሁሉ ችግር አይቀጥልም ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ አባባሌ ምክንያት አለኝ፡፡ እኔ አሁንም በኦሮሞ በኩል አለሁኝ፡፡ በኦሮሞ በኩል ያለው የአሁኑ ግርግር ይጠፋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት? ይህንን እርግጠኛ የሆኑት እንዴት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሚባለውን ድርጅት አለቃቸውን አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ ዳውድ ኢብሳን ማለት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! ከአስመራ እንደመጡ ኢሊሌ ሆቴል ሄጄ ሰላምታ ሰጥቼ ጥያቄ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ እንዴት ነው? እንደ ግንቦት ሰባት ወይም እነ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በመጡበት መንገድ ነው አይደል የመጣችሁት? አልኳቸው፣ እሳቸውም አዎ አሉኝ፡፡ ሰላም ፈጥራችሁ፣ የአሁኑ እንቅስቃሴ አካል ለመሆን በሰላም አይደል የመጣችሁት? ብዬም ጠየኳቸው አዎ አሉኝ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ሁላችንም በሰላም ለመሥራት እንችላለን? ለዘመናት የተመኘነውን አብረን እንሠራለን ማለት ነው? ብዬም ስጠይቃቸው አዎ ልክ ነው አሉኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ነገሩን ሳየው ቶሎ ቶሎ እንደነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ መሆን አልቻሉም፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎ ስሰማ ደግሞ ኧረ ትጥቃቸውን አልፈቱም አሉ፡፡  እንዴት? ብዬ ገረመኝ፡፡ ከአቶ ዳውድ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአቶ ዳውድ ጋር ከሚሠሩ አመራሮች ዘንድ ሁሉ እየደወልኩ ጠየቅኩ፡፡ ጓደኞቹን ጭምር ስጠይቅ መሣሪያችንን እየፈታን ነው ይላሉ፡፡ ግን አሁንም ሳይ አይፈቱም፡፡ እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ስታይ ደግሞ እየተዘጋጁ ነው፡፡ የሚሠሩትን በየቀኑ እንሰማለን፡፡ የእነኝህን ግን አንሰማም፡፡ በኋላ በቦረና በኩል አንዳንድ እንቅስቃሴ አለ፣ ይታኮሳሉ፣ ሰው ይሞታል አሉ፡፡ በሁኔታው ተገርሜ ይህንን የሚያደርገው ማነው ስል ያገኘሁት መልስ እዚያ የሚንቀሳቀሱት ኦነጎች ናቸው ይሉኛል፡፡ በጣም አስደነቀኝ፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልናገር፡፡ እነዚህ ሰዎች ወለጋ ነው የተወለዱት፡፡ እኔም እዚያው ነኝ፡፡ ብዙዎቻችን እንተዋወቃለን፡፡ አካባቢያችን አይራራቅም፡፡ ቢበዛ ሁላችንም ጊምቢ አውራጃ ውስጥ ነንና እንተዋወቃለን፡፡ ያኔ ከነበሩ ሰዎች ማለትም በእኔ ዕድሜ ከነበሩት ጋር ገና ከጅምሩ ስንጫወት እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም ልንጀምር ነው፣  ኦሮሞን ነፃ እናወጣለን አሉ (እኔ ከእነሱ በዕድሜ እበልጣለሁ)፡፡ አይ እኔ በዚህ አላምንም አልኳቸው፡፡ ለምን ብለው ሲጠይቁኝ ነፃ ማውጣት ሳይሆን፣ ባይሆን በኢትዮጵያን ሕይወት ተፅዕኖ መፍጠር ነው እንጂ መውጣት የለብንም አልኳቸው፡፡ መሸሽ የለብንም አልኳቸው፡፡ በዚህ ልዩነት ፈጠርን በዚህ ልዩነታችን እስካሁን ቆየን፡፡

ሪፖርተር፡-  በእርስዎና በእነሱ መካከል የተፈጠረው ይኼ ልዩነት አሁንም ድረስ አለ ማለት ነው?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! በዚህ ልዩነታችን እስካሁን ቆየን፡፡ ያኔ እኔ ዓለም ባንክና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ስሠራ አሜሪካ ይመጣሉ፡፡ እጋብዛቸዋለሁ፡፡ እንነጋገራለን፡፡ ግን ይህ ልዩነታችን አለ፡፡ ይህ ልዩነት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በቃ! መጀመርያ ላይ በአቅሜ ዕርዳታ ሁሉ አደርግላቸው ነበር፡፡ እነሱ ብርቱ ብርቱ ሰው ነበራቸው፡፡ አሁንም አቶ ዳውድ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አልተስማማንም፡፡ እንግዲህ አሁን ደግሞ ወለጋ ላይም ጦርነት አለ፡፡ ይዋጋሉ፡፡ ይህ ድርጊት እጅግ በጣም ያሳዘነኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ውስጥ እያጋጠመ ያለው ግጭት ይረግባል ብለውኛል፡፡ እንዴት ይህንን ሊሉ ቻሉ?

አቶ ቡልቻ፡- መርገቡ አይቀርም፡፡ ይረግባል፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ችግር እርግጠኛ ነኝ ይረግባል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኦዴፓም ሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ለሰላም እየሠሩ ስለመሆናቸው እየገለጹ ነው፡፡ በአንፃሩ ግን ኦነግ ይህንን እየተቀበለ አይደለም ይባላል፡፡ ይህ ችግር ካልተፈታ የበለጠ ችግር እንደሚፈጠር የሚሠጉ አሉ እኮ?

አቶ ቡልቻ፡- እሱን እኮ ነው እያልኩህ ያለሁት፡፡ ይህ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ይሞታል፡፡ ሰላም ይፈጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ማረጋገጫ አለ?

አቶ ቡልቻ፡- ኦሮሞን እኔ አውቃለሁ፡፡ የኦሮሞን ሳይኮሎጂና የኦሮሞን ፖለቲካ አውቃለሁ፡፡ ይህ የእኔ እምነት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲሁ ሎጂኩን ስታይ ምንም መሆን አይችልም፡፡ አይሆንማ! ዓብይ አህመድ እየሠሩት ባለው ነገር ኦሮሞ ደስ ብሎታል፡፡ አጨብጭቦ ነው የተቀበላቸው (እያጨበጨቡ)፡፡ አንድ ነገር ልንገርህ ድሮ ኦሮሞ ኦነግን ይወድ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ልክ ነው፡፡ ይወዱታል፡፡ እኔ ራሴ በስሜት ብከታተለውም  መስመሩን ግን አልቀበልም፡፡ ስለዚህ ኦሮሞ ከኢትዮጵያ መገንጠል አይፈልግም፡፡ ባይሆን ኃይል ለማግኘት ይፈልጋል፡፡ መሪ ለመሆን ይፈልጋል እንጂ በጭራሽ መገንጠል አይፈልግም፡፡ በጭራሽ! እንዴት ይሆናል? ኢትዮጵያ አዲስ አገር ትሆናለች? ወይስ ትበታተናለች? ይህ በፍፁም አይሆንም፡፡ ይህንን እንኳን እኛ ዓለም አይቀበለውም፡፡ ስለዚህ የኦነግ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ታዲያ? ካልከኝ እኔ እርግጠኛ ነኝ እነሱም ትጥቅ ይፈታሉ፣ ችግሩም ይፈታል፡፡ እነሱም ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ አሁን ያለው ግጭትና አለመረጋጋት ከስሞ ወደ ሰላማዊ መንገድ ይመለሳል፣ ግጭቱም ጊዜያዊ ነው እያሉኝ ነው? የሚያሳስብ አይደለም?

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! እንዳልኩህ ነው፡፡ ግጭቱ ለተወነ ጊዜ የሚፈጠርና የሚቀር ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ድሮው ተጨቁነን እንኖራለን እያለ አይደለም፡፡ አሁን አዲስ ነገር ተፈጥሯል፡፡ እኛም እንደ አማራ፣ ትግሬ፣ ሶማሌና በአጠቃላይ ቀሪው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተደባልቀን በሰላም እንኖራለን የሚል ፍላጎት ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ጊዜ ይውሰድ እንጂ ሰላም መፈጠሩ የማይቀር መሆኑን ብዙዎች ያምናሉ፡፡ እርስዎም በዚህ እምነትዎ የፀና ነው፡፡ ይህ ከሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?

አቶ ቡልቻ፡- ፖለቲካው ከተስተካከለ ኢትዮጵያን ለመርዳት የሚፈልጉ አገሮች አሉ፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያን ለመርዳት ትፈልጋለች፡፡ ግን ጉዳያችሁን አስተካክሉ ነው የሚሉት፡፡ ፖለቲካችሁን አስተካክሉ ነው የሚሉት፡፡ ለቀደሙት መንግሥት ሁሉ ብለዋል፡፡ እኔ በደንብ አውቃለሁ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን በደንብ አውቃለሁ፡፡ የበፊቶቹና አሁንም ያሉት ጭምር የሚናገሩትን እሰማለሁ፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አሜሪካኖች ኢትዮጵያን መርዳት እንደሚፈልጉ ያውቃሉ፡፡ አሜሪካ ከረዳችን ደግሞ ሁሉም ይረዱናል፡፡ እንግሊዝና ፈረንሣይ ሁሉ ሊረዱን ይፈልጋሉ፡፡ ግን እኛ ቤታችንን ማስተካከል አቃተን፡፡ ቤታችን ከተስተካከለ ዕርዳታው ይጎርፋል፡፡ በነገርህ ላይ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ቢቀጥል ኖሮ እስካሁን አገራችን ሌላ ትሆን ነበር፣ ትበለፅግ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ በምን ያህል እየሄደ እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ ያኔ ይመጣ የነበረውን ገንዘብ አውቃለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ ያለውን አነባለሁ፣ አስተውላለሁ፡፡ አንድ ሰው ሲታመም ዶክተሮች ተሰብስበው ብዙ ነገር ይሠሩ የለም? ሕመምተኛውን ለማዳን ይሞክራሉ፡፡ አሜሪካኖችም ይሞክራሉ፡፡ አንድ የማውቃቸው ሰው እዚህ ላይ ናቸው፡፡ እኛ ግን መዳን አቃተን፡፡ መድኃኒት ትንሽ ትንሽ ይሰጡናል፡፡ እኔ ብዙዎቹን የአፍሪካ አገሮች አውቃለሁ፡፡ ከእነዚህ አገሮች ብዙዎቹ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ለምሳሌ ጋናን ውሰድ የቆየች አገር ነች፡፡ ሁሉም ሰው ጋና ጋና ይላል፡፡ አውሮፓውያን ሠራተኛ እንኳን የሚፈልጉት ከጋና ነው፡፡ ታንዛኒያ እንኳን ከእኛ የተሻለች ሆናለች፡፡ እኛ ቤታችንን ብናፀዳ የሚከፈቱ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሲረዱ ደግሞ ትንሽ ትንሽ አይደለም፡፡ ለትምህርት ቤትና ለኤችአይቪ ማገዝ ብቻ አይደለም፡፡ በሰፊው ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ከዕርዳታ ባሻገር ግን ኢኮኖሚያዊ ጉዳይስ እንዴት መታየት አለበት? የአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ወዴት ይሻገራል?

አቶ ቡልቻ፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ የሚችል ነው፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች በረሃ አይደለንም፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች የተፈጥሮ ፀጋ አላጣንም፡፡ ውኃ እንኳን የሌላቸው አንዳንድ አገሮች አለ፡፡ እኛ ግን ውኃ፣ መሬትና በጣም ጎበዝ የሆነ ገበሬ አለን፡፡ ከረዳነው ያድጋል፡፡ ይህ ለአትክልት ውኃ ማጠጣት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን መርዳት በትንሽ በትንሽ ሳይሆን በብዛት መርዳት ቶሎ ፍሬ እንደሚያመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡   

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዴት ቢቃኝ ውጤታማ ይሆናል ብለው ያስባሉ?

አቶ ቡልቻ፡- የኢኮኖሚ ፖሊሲው የሚያስተማምን መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የውጭ መንግሥታት ራሳቸው አይደለም የሚሠሩት፡፡ ነጋዴዎቻቸውን ነው የሚጠቅሙት፣ በራሳቸው ሀብታም ሰዎች ነው የሚጠቀሙት፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ጎበዞች ናቸው፡፡ በጣም አዋቂ ናቸው፡፡ ሀብት ያገኙት ብልህ በመሆናቸው ነው፡፡ እኛ አገር በውርስና በመሳሰሉት ሀብታም የሚሆኑ አሉ፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ አልተማሩም፡፡ ባላገር ጋ ስትሄድ ደግሞ የሚያርሰው ባላገር አልተማረም፡፡ ሁሉን ነገር የሚሠራው ደሃ ነው፡፡ አልተማረም፡፡ ማስተማር ይቻላል፡፡ አሁን ባላገሩን በሰፊው ለማስተማር የሞከረ የለም፡፡ ለባላገሩ ልዩ ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ሥራውን እንዴት ቢሠራ ምርቱ እንደሚያድግ ማስተማር ከተቻለ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ታድጋለች፡፡ አሁን በትንሹ የምንሸጠውን ቡና ሦስት እጥፍ ለምን አናሳድገውም? ሁመራ ያለውን ሰሊጥ በአሥር እጥፍ ለምን አንሸጥም? ዓለም ይፈልጋል፡፡ ሌላው ዓለም ሳይንሳዊ ሥራ ላይ ነው፡፡ መርከብ እየሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ምግብ በርካሽ መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ እኛ ድህነት ለመውጣት የምንችለውን ሁሉ በሰፊው ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ማረስ ያስፈልገናል፡፡ በአቅማችን ፋብሪካዎችን እየከፈትን ከውጭ የምናመጣውን ዕቃ መተካት እንችላለን፡፡ ሰሊጥ፣ ቡና፣ ከብትና ሥጋ በመሸጥ የሚገኘውን ገንዘብ ዕቃ በመግዛት ከማጥፋት ለአገር የሚጠቅሙ ምርቶችን መግዛት ያስፈልጋል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ በእጅጉ ትለወጣለች፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን ለማድረግ ምን ያህል ዕድል አለ? የእርስዎስ ራዕይ ምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡- ለምንድነው ዕድል የማይኖረን? አለን፡፡ ጉልበት ካለ፣ አዋቂ ካለ፣ ለመማር የሚችል ሕዝብ ካለ ለምንድነው የማንለወጠው? ለምንድነው የማናድገው? አንድ ቤተሰብ ውስጥ ጥሩ የተማረ ሰው ሲኖር ፍጥነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ገበሬውን ሰብስበን ማስተማር እንችላለን፡፡ ግን ገበሬው በጆሮው ሰምቶ የተቻለውን ይሠራል እንጂ ማስታወሻ መውሰድ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን ላስተምር ቢል ገበሬው መጻፍ አይችልም፡፡ ማስታወሻ መያዝ ሳትችል መማር አይቻልም፡፡ ስለዚህ የእኛ ሕዝብ መማር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት 27 ዓመታት ብዙ ውዝግቦች እንደነበሩ ሲገለጽ ነበር፡፡ እርስዎም በፓርላማ አለ የሚባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሌለ ነው ማለትዎ ይታወሳል፡፡ ከዚህ አንፃር ያለፈውን ጊዜ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ቡልቻ፡- ያለፈውን ጊዜ በሙሉ ጨለማ አድርጌ አላየውም፡፡ ምክንያቱም እኔ ብዙ ባላገሮችን ዞሬ አይቻለሁ፡፡ የሚገርምህ ብዙ ትንንሽ መንገዶች ከመንገድ ተገናኝተዋል፡፡ ድልድዮች ተሠርተዋል፡፡ በትልቅ የሚወራ ነገር ባይሆንም ትንንሽ ከተሞች ድረስ መንገድ ተሠርቷል፡፡ ትምህርት ቤቶች ተሠርተዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ዜሮ ማድረግ አልችልም፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ብዙ ማድረግ ስትችል ማድረግ አልቻለችም፡፡ ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ብዙ ገንዘብ ባክኗል፡፡ ያውም የሌለን ገንዘብ ባክኗል፡፡ ብዙ ተንኮል ተሠርቷል፡፡ ሕዝቡ በመበረታታትና በመቀራረብ ፋንታ ተራርቋል፡፡ ተንኮል ብቻ ተማረ፡፡ ምድሩ የሚያበቅል አይመስልም፡፡ የሚሰፋ አይመስልም፡፡ የሚተርፍ ነገር ቢኖርም ለኢትዮጵያ ግምጃ ቤት አይገባም፡፡ እና እኔ የነበረው መንግሥት (አሁንም አሉ) ሁሉንም ነገር እነሱ ብቻ የሠሩት ጥፋት ነው አልልም፡፡ ትምህርት ቤት፣ መንገድና  አውሮፕላን ማረፊያዎች ተሠርተዋል፡፡ ይህንን አልነሳቸውም፡፡ አልሠሩም አልልም፡፡ ግን ቆጥረን ልንጨርሰው የማንችለው መጥፎ ነገር ተሠርቷል፡፡ ሕዝብ ደግሞ ተንኮል ተማረ፡፡ መጠላላት አሳየ፡፡ ለምሳሌ ድሮ አማራና ኦሮሞ ይፎካከራል፡፡ በጦርነት ሳይሆን እዲሁ ይጣላ ይሆን እንጂ ሌላ ነገር የለም፡፡ የአሁኑ ንቅናቄ ያመጣው ነገር አማራና ኦሮሞ ባህር ዳር ተገናኝተው ጉዳያቸውን ሁሉ ፍትል አድርገው ተነጋግረው አንጣላም፣ ምንም ቢሆን አንድ ላይ ነው የምንቆመው አሉ፡፡ ደስ ይላል፡፡ የኦሮሞና የአማራ ጋብቻ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ እንዴት አድርገህ አማራና ኦሮሞን እንደምትለየው እኔ አይገባኝም፡፡ ድሮ ይገባኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ድሮ እንዴት ይገባዎት ነበር?

አቶ ቡልቻ፡- አጠገቤ ብቻ ያለውን ብቻ ነው የማየው፡፡ በልጅነቴ ጎረቤቴም አጠገቤ የማነጋግረውና የማጫወተው ሁሉ ኦሮሚኛ የሚናገር ነበር፡፡ ያኔ ምንም አላውቅም ነበር፡፡ አሁን ወለጋ አይደለም ሸዋ በሙሉ ተጋብቷል፡፡ ይህንን ነው የማውቀው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ለኔ ብሩህ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ሆኖ ይታየኛል፡፡ ይህ መልካም ነገር ብዙ ነገሮች ይቀይራል፡፡ ልክ እንደ አሜሪካ ገበሬ የእኛም ገበሬ መኪና ገዝቶ ሲነዳ ይታየኛል፡፡ አንጎላ ባላገሩ መኪና አለው፡፡  ለምሳሌ እዚህ አገር ገንዘብ ያለው አንዳንድ ሰው ልጁን ሲድር የውጭ አገር ነው የሚመስለው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ግን ልጁን ለመዳር የሚበቃ ገንዘብ የለውም፡፡ ካደረገም መላ ጎረቤቱን ጠርቶ ምግብ ቅጠል ላይ አድርጎ ነው የሚበላው፣ ባላገሩ ምንም የለውም፡፡ በጣም ደሃ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንኳን የተደባለቀ ነው፡፡ ድሮ ያለ ጫማ የሚሄዱ ነበሩ፡፡ አሁን እኔ ደስ ከሚለኝ አንዱ ከተማ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጫማ ያደርጋሉ፡፡ እዚህ ከተማ ማለቴ ነው፡፡ ባላገሩ ግን በእግሩ ነው፡፡ ስለዚህ መሻሻል እየመጣ ስለሆነ ይሻሻላል ተስፋ አለኝ፡፡ አሁን በኦሮሞ ውስጥ ቄሮ የሚባሉ አሉ፡፡ እነሱ ደስ ይሉኛል፡፡ ምንም ጥፋት አልሠሩም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብታይ መቶ ከሚሆኑ ሰዎች 60 እና 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት ነው፡፡ እኔ አሁን 88 ዓመቴ ነው፡፡ ብዙ ነገር አይቻለሁ፡፡ አሁንም ጉልበት አለኝ፡፡ ፓርላማ ለመግባት እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለ ምኞት እንዳለዎ ሰምቻለሁ፡፡ ግን በዚህ ዕድሜ ፓርላማ ለመግባት የፈለጉት ለምንድነው?

አቶ ቡልቻ፡- እሞክራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የፓርላማ አባል ለመሆን የሚያበቃ ጉልበት አለኝ ብለው ያስባሉ?

አቶ ቡልቻ፡- በጉልበቴና በሥጋዬ በጣም እችላለሁ፡፡ በጉልበቴ ጠንካራ ነኝ፡፡ ምንም የጎደለኝ ነገር የለም፡፡ መኪና አለኝ እንጂ አሁንም በቅሎ ላይ ተቀምጬ መሄድ እችላለሁ፡፡ አሁን ፓርላማ ለመግባት ሐሳቡ ቢኖረኝም ይህንን ሐሳቤን ልቀይር እችላለሁ፡፡ ግን ብችል ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሐሳቡ አለኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህን ያህል ፓርላማ ለመግባት የፈለጉበት የተለየ ነገር አለ?

አቶ ቡልቻ፡- ፓርላማ ውስጥ የምናገረው ብዙ ነገር አለ፡፡ እንዳልኩህ ኢትዮጵያ ወደ ላይ ከፍ ብላ ሀብታም መሆን ስትችል ለምን እንዲህ ሆነች ብዬ ይቆጨኛል፡፡ ከሶማሊያ እንኳን ታንሳለች፡፡ ፈረንጆች እዚያ ሄደዋል፡፡ ጣሊያኖች ሄደው ብዙ ገንዘብ አፍስሰዋል፡፡ እኛ ጋ በፍርኃት ነው የሚመጡት፡፡ እዚህ መጥተው ትንሽ ትንሽ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ ለምን ከፍ ያደርጉም? ገንዘብ አላቸው፡፡ ከፍ ለማድረግ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ አንተም ራስህን ብትጠይቅህ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እንዳሉ ልትናገር ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አሁኑ አለመረጋጋት ሲጠፋ ያሳስባል፡፡ ግርግር እየሰሙ ኢንቨስት ለማድረግ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡

አቶ ቡልቻ፡- አዎ! ለምሳሌ በአማራና በትግራይ ክልል አካባቢ የምትሰማው ነገር አለ፡፡ ኦሮሚያም ትሰማለህ፡፡ ነገር ግን ይኼ ችግር ቢወገድ ደስ ይለኛል፡፡ ከሁሉ የበለጠ የሚያሳዝነኝ ኦሮሞ ኦሮሞን ሲገድል ነው፡፡ ዓይተን አናውቅም፡፡ አሁን ነው የምናየው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የኢትዮጵያን ጉዳይ ያውቃሉ፡፡ እንደ አንድ አባት አሁን እዚህም እዚያም የሚነሳውን ግጭት እንዴት መፍታት ይቻላል ይላሉ? መንግሥት ምን ማድረግ ይኖርበታል? ሌላውስ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- መንግሥት ብዙ ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ ማድረግ የሚችለው ሰላም እንዲሰፍን ነው፡፡ ሰላም ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሰው ሰውን እንዳይገድል፣ ከሌላ ቦታ የመጣን ሰው እንዳይገድልና እንዳያስፈራራ ለማድረግ የፀጥታ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ጥሮ ግሮ ፀጥታና ሰላም ማስፈን ይኖርበታል፡፡ ይህ እንደሚሆን ደግሞ አምናለሁ፡፡ ትልልቆች ደግሞ ሰው እንዳይጣላ፣ አንዱ ከአንዱ ሲጣላ ማስቆም አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከረገበ እገዛ የሚያደርጉ ሁሉ ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኦነግ ስም የሚጠሩ ወይም በኦነግ ሥር ነበሩ የሚባሉ ሁለትና ሦስት ቡድኖች ገብተዋል፡፡ ይህ ምን ያመለክታል?

አቶ ቡልቻ፡- እሱን እኮ ነው የነገርኩህ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ችግሩን ያረግባል፡፡ እንዲህ ሲመጡ ጠመንጃ የሚያነሳው መሄጃ የለውም፡፡ ለዚህ ነው ይቆማል ያልኩት፡፡ መሄጃ የለም፡፡ እነሱ የጀመሩት ግጭት ይቆማል፡፡ ጠመንጃ እንኳን ያልቃል፡፡ እነሱ አሁን የጀመሩት ግጭት ይቆማል፡፡ እርግጥ ችግር አለ፡፡ አንዱ ለጊዜው መሣሪያ ስላለው እውጥሃሁ ውጣ የሚል ከሆነ ችግር ነው፡፡ ይህ ጥሩ አይደለም፡፡ ይህም ቢሆን ግን ማዕከላዊው መንግሥት ጥሩ ከሆነ የትም መሄድ አይቻልም፡፡ ጠመንጃ አለኝ የሚለውም ከምንም አይቆጠርም፡፡ አሁን ጥሩ ዕድል አለን፡፡ የዛሬ ዓመት ብትጠይቀኝ ይህንን አልልም ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ዕድል ደግሞ ሊያመልጥ ይችላል፡፡ በጊዜው ልትጠቀምበት ካልቻልክ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል፡፡ ይህ መልካም ዕድል ከእጃችን እንዲወጣ አንፍቀድ፡፡ እንበርታ ነው የምለው፡፡ ወጣት፣ ሽማግሌውና ሁሉም አገሬን ማለት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ አገሬን እናድናት ብለን ከተነሳን ሁሉም ችግሮቻችን ይወገዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህች አገር ተለውጣ ለማየት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- ሁላችንም በአንድ አቅጣጫ ከሠራን ጠንካራ እንሆናለን፡፡ መቀመጥ ጥሩ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኮንስትራክሽን ላይ የሚሠሩ ብዙ ሰዎች በቅልጥፍና ከመሥራት አካፋ ተደግፈው ይቆማሉ፡፡ እዲህ ያለው ነገር ትንሽ መስሎ ይታየናል፡፡ ግን በጣም ይጎዳናል፡፡ ወሬ ማውራት ይጎዳል፡፡ በሥራ ጊዜ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ ሰዎች ጋር እንዲሁ ቁጭ ብለን ስንጫወት ሠራተኞቻችሁ ጎበዞች አይደሉም ይላሉ፡፡ ሕንፃ ሲገነባ ሠራተኞቻችሁ አይሮጡም፡፡ አሜሪካ ብትሄድ በሥራ ቦታ ላይ ሠራተኛ ቆሞ አይታይም፡፡ ስለዚህ እዚህ አገር አንድ ቦታ ላይ የምታየው ነገር በሚሊዮን ስታስበው ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ ቢሮ አካባቢም ተመሳሳይ ነው፡፡ እኔም አውቃለሁ፣ አያለሁ፡፡ ሰዎች ቡናና ቴሌፎን ላይ ጊዜ ያጠፋሉ፡፡ ስለዚህ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ መትጋት አለበት፡፡ ለአጭር ጊዜ ነው የምንኖረው፡፡ አገር ከሌሎች ወደ ኋላ ስትቀር ደስ አይልም፡፡ ባንበጣበጥም ወደ ኋላ መቅረት ደስ አይልም፡፡ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ሠራተኛው አይሠራም ይቆማል ይላሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- በቂ የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ አንድ ምክንያት አይሆንም?

አቶ ቡልቻ፡- ሥራም የለም፡፡ ግን በአጠቃላይ ያሉት በደንብ እየሠሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ በጣም የሥራ እጥረት አለ፡፡ ምናልባት ባለፈው መንግሥት ትንሽ ቅር የሚለኝና የምፈርድባቸው ሰው ሥራ እንዳይፈታ አልሠሩም፡፡ ሥራ አጥነት በአንድ ጀንበር የሚጠፋ ይመስላቸዋል፡፡ ያለው ካልሠራ እንዴት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ይሥራ፡፡ የሥራ ዕድል ይከፈት፡፡