Skip to main content
x
በአገር አቀፍ የውኃ ተቋማት ቆጠራ አራት ሺሕ ሰዎች ይሳተፋሉ
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)

በአገር አቀፍ የውኃ ተቋማት ቆጠራ አራት ሺሕ ሰዎች ይሳተፋሉ

በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት አገር አቀፍ የውኃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ኃይጂን አጠባበቅ ተቋማት ቆጠራ ሊካሄድ ነው፡፡

ቆጠራው በዋናነት በገጠርና በከተማ የውኃ ተቋማት መሠረተ ልማቶችን ከውኃ መገኛ ቦታ እስከ ማከፋፈያ ቦኖና የቤት ለቤት መስመሮችን በማካተት የሚከናወን ሲሆን፣ በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሥርጭት፣ እንዲሁም የውኃ ተቋማትን ጥራት ለማወቅ ይረዳል ተብሏል፡፡

በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ እንደሚደረግ ለጋዜጠኞች የገለጹት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ  (ዶ/ር)፣ ቆጠራው በሚደረጉባቸው ቀናት ኅብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡፡

ሚኒስትሩ ቆጠራው ሲደረግ በቆጠራው የሚሳተፉ አራት ሺሕ የሚሆኑ የቆጠራ ባለሙያዎችና 500 አስተባባሪዎች የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው፣ በክልሎች በተለይም በወረዳና በቀበሌ ኮሚሽኑ የፀጥታ አካላት ጋር ውይይቶች ተደርጓል ብለዋል፡፡

‹‹በቆጣሪዎች ላይ ምንም ዓይነት ችግር ይፈጠራል ብለን አንገምትም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ባሻገር ሊመጡ የሚችሉ ተፅዕኖዎች ካሉ በወረዳዎችና በቀበሌዎች የፀጥታና የአስተዳደር መዋቅሩ ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፤›› ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ለዚህም ነው ሚዲያ ላይ ቀርበን መግለጫ መስጠት ያስፈለገው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ቆጠራውን አስመልክቶም በአሁኑ ጊዜ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች የተለዩ በመሆናቸው ችግሩ ሲፈታ ቆጠራው ይደረጋል ተብሏል፡፡ 

ይህን መሰል ቆጠራ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግ ሁለተኛው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም 2003/04 ዓ.ም. ተመሳሳይ ቆጠራ ተደርጎ ነበር፡፡

መጀመርያ ተደርጎ በነበረው ቆጠራና በሌሎች መረጃዎች መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ 600 ሺሕ የሚሆኑ የመጠጥ ውኃና የንፅህና ተቋማት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የንፁህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በገጠር 74 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ በከተማ ደግሞ 62 በመቶ ነው፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ እንደተመለከተው፣ ከዚህ ቀደም የውኃ ሽፋንን ጨምሮ በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የሚሰበሰቡ መረጃዎች ወጥነት ያለው ሥርዓት ስላልተዘረጋላቸው አስተዳደራዊ በሆኑ መረጃዎች በመመርኮዝ የሚሠሉ በመሆናቸው ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግቡ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከነበረው ቆጠራ በተለየ ሁኔታ ሁለተኛው አገር አቀፍ ቆጠራ በቴክኖሎጂ ይታገዛል ተብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ቆጠራውን ለማከናወንና መረጃዎችን ለማሰባሰብ 4,075 የሚሆኑ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

በ2.1 ሚሊዮን ዶላር የተገዙት እነዚህ ታብሌቶች ከዚህ ቀደም የነበረውን በወረቀት የታገዘ የመረጃ አሰባሰብ ያስቀይራሉ ተብሏል፡፡ ይህ ቆጠራ ወጪው በዕርዳታ ለጋሽ ተቋማት እንደሚሸፈን ታውቋል፡፡ ከጠቅላላው ወጪው ውስጥ 60.2 ሚሊዮን ብር ለታብሌት ኮምፒዩተር መግዣ፣ 111 ሚሊዮን ብር ደግሞ ሶፍትዌር መግዣን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎች ሲውል፣ ቀሪው ደግሞ ለቆጠራ ሥራው ወጪ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡