Skip to main content
x
በዚምባቡዌ ተቃውሞ ያስከተለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ
ዚምባቤያውያን በሃራሬ ተቃውሞዋቸውን ገልጸዋል

በዚምባቡዌ ተቃውሞ ያስከተለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ

ዚምባቤያውያን የቤንዚንና ናፍጣ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ በዚምባቡዌ ዋና ከተማ ሃራሬና በቡላዋዮ ለተቃውሞ ወጥተዋል፡፡

መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ካሳወቀ በኋላ ለተቃውሞ የወጡት ዚምባቤያውያን በየመንገዱ ጎማ ሲያቃጥሉና ድንጋይ ሲወረውሩ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተስተውለዋል፡፡

ለተቃውሞ የወጡት መንገድ በመዝጋት ተቃውሞዋቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ መንገዶችንና የአውቶቡስ መሄጃዎችን በተቃጠለ ጎማ ዘግተዋልም ተብሏል፡፡

በተለይ በሁለቱ ከተማዎች ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ እየተፈጸመ ያለውን ዘረፋ ለማስቆም የአገሪቱ መከላከያና ፖሊሶችም ተሰማርተዋል፡፡

በርካታ ሱቆችና ሱፐርማርኬቶች ከትናንት በስቲያ (ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም.) ተዘግተው የዋሉ መሆናቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ማድረጉን ለመቃወም የወጡ ዜጎች ከፀጥታ አካላት ጋር በፈጠሩት ግጭት ቁጥራቸው ያልተገለጸ መሞታቸውም ተነግሯል፡፡ በሁለቱ ከተሞች ለተቃውሞ ከወጡት ዜጎች በመቶዎች የሚቆጠሩትም ታስረዋል፡፡

የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማንጋጋዋ የነዳጅ ዋጋ የጨመረው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ፍላጎት ለማርገብና የነዳጅ ሕገወጥ ንግድን ለማስቆም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዚምባቡዌ መንግሥት የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማንሰራራት እየሠራ ቢሆንም፣ የደመወዝ ጭማሪ አለመደረጉና የዋጋ ግሽበቱም ማየሉ ዚምባቤያውያን እንዲከፉ አድርጓል፡፡

በዚምባቡዌ ተቃውሞ ያስከተለው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ

 

ዚምባቤያውያን ለምን ከፋቸው?

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ መሪነት ጊዜ ዓለም አቀፍ ረጂዎች ሆኑ የገንዘብ ተቋማት ዚምባቡዌ ላይ ጫና በመፍጠር ኢኮኖሚውን አሽመድምደዋል፡፡ ይህም የዚምባቤያውያንን ኑሮ አመሳቅሏል፡፡ ኢኮኖሚ በተጎሳቆለበት ዘመን ከሮበርት ሙጋቤ ሥልጣን የተረከቡት ኤመርሰን ማንጋጋዋ፣ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ጅምር ሥራ ላይ ናቸው፡፡

በመሆኑም የኑሮ ሁኔታ ገና አልተስተካከለም፡፡ የቢቢሲው ኢምፓክት ፕሮግራም  ተሳታፊው ጋዜጠኛና የሕግ ባለሙያ ብሬን ሃንግዊ የዚምባቤያውያንን ብስጭት ከነዳጅ ጭማሪው ጋር አያይዞ እንዲህ ገልጾታል፡፡

‹‹ቅዳሜ ከሰዓት 10 ሰዓት ሲሆን ነዳጅ ለመቅዳት ተሠለፍኩ፡፡ በርካታ መኪኖች መስመራቸውን ይዘው ተሠልፈዋል፡፡ መኪኖቹ ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል ነበር የተሠለፉት፡፡ የሚሰጠው አገልግሎት በጣም ቀርፋፋ በመሆኑ በአካባቢው የተሠለፍን አብዛኞቻችን ጓደኛ በመሆን አሰልቺውን ጊዜ ለመርሳት ሞክረናል፡፡ ነዳጅ ማደያው ለመድረስ 100 ሜትር ያህል ሲቀረኝ ለእኩለ ሌሊት አንድ ሰዓት ብቻ ነበር የቀረው፡፡ ከፊቴ አንድ አምስት መኪናዎች ነበሩ፡፡ በድንገት ነዳጅ የሚቀዱት ሠራተኞች ፓምፑን ዘጉ፣ ዕቃቸውን መሸከፍ ጀመሩ፡፡ ወዲያውም ከነዳጅ ማደያው ወጡ፡፡ ይህ ምን ያህል ርጉምጉምታ፣ ተስፋ መቁረጥ ብስጭትና ብሶት ሊፈጥር እንደሚችል ማንም በምናቡ ሊያየው ይችላል፡፡››

ጋዜጠኛ ሃንግዊ እንደሚለው፣ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ የጨመረው፣ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለማረጋጋት ነው፡፡ ቤንዚን በሊትር ከነበረበት የ1.24 ዶላር ወደ 3.31 ዶላር፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር ከ1.36 ዶላር ወደ 3.11 ዶላር አሻቅቧል፡፡

ይህንንም ዚምባቤያውያን በመቃወም በከተማዋ ሃራሬና በደቡባዌ ክፍል በምትገኘው ቡላዋዮ ከተማ ለተቃውሞ ወጥተዋል፡፡

እንደ ሃንግዊ፣ ድንገተኛው የዋጋ ጭማሪ ዚምባቤያውያን በየቀኑ ለኑሯቸው የሚያደርጉትን ግብግብ የሚያከፋ፣ በገቢ ልክ መኖርንም የሚያመሳቅል ነው፡፡

በዚምባቡዌ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ማን ያጋግለዋል?

በነዳጅ መጨመር ሳቢያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሰዎች መሞታቸውን የገለጹት  የደኅንነት ሚኒስትሩ አውን ንኩብ፣ ምን ያህል እንደ ሞቱ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ሚስተር ንኩብ እንደሚሉት፣ ተቃውሞውን እያጋጋሉ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የፖለቲካ መብት ተሟጋቾችም የድርጊቱ ተባባሪዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫም፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት የሚታደግ ይሆናል ብለዋል፡፡

ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው መንግሥትን ለማንኮታኮትና አገሪቱን ምስቅልቅል ውስጥ በመጣል ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሠሩ አካላት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ ሠራተኞች ማኅበር ምን አለ?

ግንባር ቀደም የሆነው የዚምባቡዌ ኮንግረስ ትሬድ ዩኒየን መንግሥትን ወቅሷል፡፡

አሶሽየትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ የሠራተኛ ማኅበሩ መንግሥትን ‹‹ለድሆች ምንም የማያስብ›› ሲል ገልጾታል፡፡ ‹‹መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ያለው አይመስልም›› ያለው ማኅበሩ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን እንዲለቁ ጠይቋል፡፡

በርካታ ተቃዋሚዎችም ባለፈው እሑድ ወደ ሩሲያና መካከለኛው እስያ አገሮች ለሥራ ጉብኝት ያቀኑትን ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋ ጉዟቸውን እንዲሰርዙና ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በማንጋጋዋ ውድቀት አለመደሰታችንን ማንጋጋዋ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፤›› ሲሉ መደመጣቸውንም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል በማለት የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ሩሲያ፣ ካዛኪስታን፣ ቤላሩስና አዘርባጃንን ለመጎብኘት ያቀኑትና በስዊዘርላንድ ዳቮስ የሚካሄደውን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ተሳትፈው ለመመለስ ያቀዱት ፕሬዚዳንት ማንጋጋዋ፣ ሥልጣኑን የተረከቡት በኅዳር 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሳቸውን መምጣት አብዛኞቹ ዚምባቤያውያን ቢደገፉትም፣ የኢኮኖሚው አለመረጋጋት ግን ነቀፌታን አስከትሎባቸዋል፡፡

በአገሪቱ ዋና ተቃዋሚ ሙቭመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ፣ ‹‹አገሪቷ ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህም ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያድግ ይችላል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡