Skip to main content
x
የመሸታ ወጎች

የመሸታ ወጎች

በጠዋቱ ደጋግሞ ወደ አፉ የላከው መለኪያ ሥራውን ጀምሯል፡፡ ያለበትን የሚያውቅ አይመስልም፡፡ በሩ ባደፈ መጋረጃ የተጋረደበት ደጃፍ ላይ ጋደም እንደማለት ብሎ ተቀምጧል፡፡ ረፍዱ ላይ የወጣው ከረር ያለ ፀሐይ ልብ ልቡን ይለዋል፡፡ ሰካራሙ ግን እንኳንስ ቦታ ቀይሮ ጥላ ሥር መቀመጥ እስከሆዱ የተከፈተውን የሸሚዞቹን ቁልፎች እንኳ አስተካክሎ መቆለፍ አልቻለም፡፡

የዛለ ሰውነቱንም ማዘዝ የሚችል አይመስልም፡፡ የሚንቀሳቀሱት ድፍርስ አይኖቹ ናቸው፡፡ ግድግዳውን ተደግፎ በጠባቡ መተላለፊያ ላይ እግሮቹን አንጥፎ ቁጭ እንዳለ ፀሐይ ይመታዋል፡፡ ቃል አይተነፍስም አላፊ አግዳሚውን በግርታ ይመለከታል፡፡ አቧራ እያቦነኑበት በጎኑ የሚያልፉ ተሽከርካሪዎች እንኳ ምቾት አልነሱትም፡፡

የተደገፈው የጭቃ ቤት የጉሊት መደብ በሚያህል ቦታ ላይ  ቦታ ላይ የተገነባች እጅግ ደሳሳ ጎጆ ነች፡፡ መግቢያው ላይ ከተጋረደው አዋራ የጠጣ መጋረጃ ጀርባ መሸተኞች በአግዳሚ ወንበሮች ላይ ተደርድረው ሞቅ ያለ ጭዋታ ይዘዋል፡፡ ከፊት ለፊታቸው ቁጭ ቁጭ በተደረጉት አዳፋ ጠረጴዛዎች ላይ አመድ የተጠቀጠቀባቸውና እንደ ሲጋራ መተርኮሻ የሚጠቀሟቸው ትንንሽ የመርቲ ቲማቲም ቆርቆሮዎች ተደርድረዋል፡፡

በአግዳሚ ወንበሮች የታጨቀችውን ጠባቧን ክፍል የሞሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ በጨዋታቸው መካከል አለፍ አለፍ እያሉ በመለኪያ የተሞላላቸውን አረቄ ይጨልጣሉ፡፡ መለኪያቸውን ደጋግማ የምትሞላላቸው አሳላፊ መኝታ ተደርጎ በማዳበሪያና በጣውላ የተዋቀረ ቆጥ ከወለሉ ብዙም ሳይርቅ አለ፡፡ መኝታዋን እያዩ ይተርቧትና ያስቋታል፡፡ ከወደቆጡ በኩል ሞቅ ያለ ሙዚቃ ተለቋል፡፡ ከሙዚቃው ጋር አብሮ የሚጫወተው በሕይወቱ ፍፁም ደስተኛ የሚመስለው ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) ነው፡፡ ዳንሱን ያወቀበት ባይመስልም ሥልቱን ባልጠበቀ ሁኔታ ባለበት ሆኖ እጆቹን ወንጨፍ ወንጨፍ ያደርጋል፡፡ አብሮ ለመዝፈንም ይሞክርና ግጥሙን ጠፍቶበት ይተወዋል፡፡ ሞቅ ብሎታል፡፡ ምናልባትም በክፍሉ ካሉት ውስጥ ቀድሞ መጠጣት የጀመረው እሱ ሊሆን ይችላል፡፡

የመሸታ ወጎች

 

እንደ አብዛኞቹ ሰካራሞች አይረብሽም፣ አያለቅስምም ሞቅታው ደስተኛ የሚያደርገው ፍልቅልቅ ፍጡር ነው፡፡ የሚኖረው በየመንደሩ ዞሮ የውኃ ኮዳዎችን ለቃቅሞ በመሸጥ በሚያገኘው ጥቂት ገንዘብ ነው፡፡ የገረጣ ቆዳው፣ በላዩ የነተበ ሸሚዙ ኑሮ እንዳልተመቸው ይመሰክራሉ፡፡ እውነታውን የሚያስረሳውና ደስተኛ የሚያደርገው ደጋግሞ ወደ አፉ የሚልከው መለኪያ ነው፡፡ ሞቅ ይለው ሲጀምር ፈገግታው ይደምቃል፡፡ በራስ መተማመኑም የሚጨምረውም ያኔ ነው፡፡

‹‹እኔ ሰካራም ነኝ፤›› አለ ሁለት እጆቹን እያወናጨፈ ፍፁም ደስተኛ በሆነ መንፈስ፡፡ ምናልባት በስካሩ የሚኮራ ብቸኛው ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚሠራ እየሳቀ ዝርግፍ አድርጎ ይናገር ገባ፡፡ ፕላሲትክ ቃርሞ በመሸጥ የሚያገኘው ለአረቄው ከተረፈው በቂው እንደሆነ ተናግሮ በመለኪያው የቀረችውን ጭላጭ ወደ አፉ ላከና ልቡ ወደ ሙዚቃው ተሳበ፡፡

የሚወደው የአገር ባህል ሙዚቃ ሲመጣ እጁን እንደ ጥይት ሙዚቃ ወደሚመጣበት አቅጣጫ አነጣጥሮ ‹‹ይኸውና መጣ የኔ ዘፈን፤›› ብሎ አብሮ ያስነካው ገባ፡፡ በየመሀሉ ግን እኔ ሰካራም ነኝ ይላል በድርጊቱ በመኩራራት፡፡ እንደ ሙሉቀን ያሉ ቋሚ ደንበኞች ያሏት 24 በተለምዶ ‹‹አንበሳ ሰፈር›› በመባል በሚታወቀው መንደር ውስጥ የምትገኘው አረቄ ቤት በር የሚከፈተው ንጋት 12 ሰዓት ተኩል ከመሆኑ በፊት ነው፡፡ ደንበኞቿ ያደረ ስካራቸውን ለማብረድ ጎራ ይላሉ፡፡ ‹‹እሾህን በሾህ የሚባል ነገር አለ፡፡ መጠጥ ያሰክረናል የሚበርድልንም በመጠጥ ነው፤›› አለ አንደኛው አረቄ አፍቃሪ፡፡

ቤቱን የሞሉት ጠጪዎች በተለያየ የሙያ መስክ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ፀጉር አስተካካይ፣ የእንጨት ባለሙያ፣ ደላላ፣ ግንበኛ ናቸው፡፡ ‹‹እኛ ጠጪዎች ነን እንጂ ሰካራሞች አይደለንም፤›› የሚለው ፀጉር አስተካካዩ ነው፡፡ ሰካራም የሚላቸው ሌሊቱን ሲጠጡ የሚያድሩትንና ያደረባቸውን ስካር ለማስታገስ በር የሚያስከፍቱትን ነው፡፡ በዚህ መስፈርት መሠረት ረፋዱ ላይ ቤቱን የሞሉት ጠጪዎች መለስተኛ ሰካራሞች ወይም መጠጠ አፍቃሪ የሚባሉት ናቸው፡፡ የሚጠጡትም ተባራሪ ሥራ ተገኝቶ እስኪደወልላቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መግቢያው ላይ ደካክሞት እንደተቀመጠው ሰካራም ሞቅታቸው ወደ ድካም እንዳይቀየርባቸውም የሚጠጡት እንዳገኙ ሳይሆን በዘዴ እያባባሉ ነው፡፡ የፈለገ ነገር ቢመጣ በቦዶ ሆዳቸው አረቄ አይጨልጡም፡፡ እርግጥ ነው ቁርሳቸውን ሳይበሉ ነው ከቤት የሚወጡት፡፡ ቁርስ የሚበሉት አብሮ በመጠጣት የተላመዱ ጓደኛሞች አረቄ ቤቷ ውስጥ ተቃጥረው ነው፡፡

አጎቴ ነው ለምትለው ሰው ተቀጥራ የምትሠራው አሳላፊ ግን ከአረቄ በስተቀር ምግብ አትሸጥም፡፡ ይሁንና ደንበኞቿ ከመጠጣታቸው በፊት ቁርስ ስለሚፈልጉ አብራቸው ቶሎ የሚደርስ ነገር ታዘጋጃለች፡፡ ቁርሳቸው ሁለት ዓይነት ነው፡፡ የፆምና የፍስክ፡፡ በፆም ወቅት ቲማቲም በሽንኩርት ጠብሰው ይበላሉ፡፡ በፍስኩ ደግሞ ትሪ ሙሉ ጥብስ ጥርግ ያደርጋሉ፡፡ በአካባቢው ከሚገኙ ሥጋ ቤቶች ቅንጥብጣቢ የሚሉትን ቁርጥራጭ ሥጋ በርካሽ ይገዛሉ፡፡ ለስድስት ሆነው የሚበሉትን ቅንጥብጣቢ የሚገዙት 30 ብር በማይሞላ ገንዘብ ነው፡፡ ከቁርስ በኋላ ‹‹ደብል›› በሚሏት ሁለት መለኪያ በምትይዘው ብርጭቆ የሚሞላላቸውን ፅዋ ያነሳሉ፡፡

ከመጠጥ ቤቱ የሚወጡት ሥራ የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡ የሚወዱት የሐባሻ አረቄ ከስንዴ፣ በቆሎ እንደሚሠራ የምትናገረው አሳላፊዋ የተለያዩ የአረቄ ዓይነቶች እንዳሉ ትገልጻለች፡፡ የሐበሻ፣ ነጭና ቀይ የኮሶ፣ የነጭ ሽንኩርት የእንስላል አረቄ በስፋት ከሚታወቁት መካከል ናቸው፡፡ የአረቄው ዓይነት እንደየ አካባቢውም ይለያያል፡፡ እሷ በጀሪካን እየገዛች የምትቸረችረውን የሐበሻ አረቄ የምታስመጣው ከጎጃም ነው፡፡ በአንድ ትንፋሽ የሚጨልጡት መለኪያ አረቄ በሦስት ብር፣ ሁለት መለኪያ ደግሞ በአምስት ብር ይሸጣል፡፡ አንዴ ከተቀመጡ ምን ያህል እንደሚመጡ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ዋጋውም ኪስ የማይጎዳ ዓይነት ስለሆነ ሲደጋግሙም ብዙ ላይታወቃቸው ይችላሉ፡፡

ሞቅታቸው ወደ ስካር እንዳይሻገር ግን ምግባቸውን በአግባቡ ይመገባሉ፡፡ ውኃም ደጋግመው ይጠጣሉ፡፡ ከዚያ ለሥራ እስኪጠሩ ድረስ ወሬ እየተቀባበሉ ይጫወታሉ፡፡ ይተራረባሉ፡፡ ጨዋታ የሚችል ንጉሥ ነው፡፡ ከሁሉም የተሻለ ጨዋታ አዋቂ የሚሉት ሰው መጋረጃውን ገልጦ ሲገባ ‹‹ጃሚ›› ብለው አቆላምጠው እየጠሩት ወደ ውስጥ እንዲገባ ጋበዙት፡፡ ጃሚ እንዳሉት ተጫዋች አይመስልም ፊቱን እስከ ግንባሩ በደፋው ኮፍያ ሽፍኗል፡፡ ኮስተር እንዳለ የሚንቀጠቀጡ እጆቹን ለሰላምታ ዘርግቶ ከአንዱ ጥግ ተቀመጥ፡፡ የጓደኞቹ ፈገግታ ግን አልጠፋም ‹‹ቆይ ትንሽ›› ይረጋጋና ታዩታላችሁ አሉ፡፡

አሳላፊዋ ፈጥና በመለኪያው አረቄ ሞልታ ከፊቱ አኖረችለት፡፡ ጃሚ አንድ ሁለት ካለ በኋላ እጆቹ መንቀጥቀጣቸውን አቁመው ተረጋጉ፡፡ ኮፍያውን ወደ ኋላ ገፋ አድርጎ በጉጉት የሚጠብቁትን ጓደኞቹን በጨዋታ ያዛቸው፡፡ በተናገረ ቁጥር ደጋግመው ይስቁለታል፡፡ ከውስጣቸው የተሻለ እንደሆነ አድርገው ስለሚያስቡት ከቀልደኛነቱ ባለፈ ያከብሩታል፡፡ ‹‹ኒሳን ሚኒባስ አለችው፤›› አለ አንደኛው በጓደኛው በመኩራራት ዓይነት፡፡ የነርቭ ችግር እንዳለበት ካልጠጣ የሚንቀጠቀጠው ጃሚ ሹፌር ኖሯል፡፡

በጠባቧ መሸታ ቤት የሚሰባሰቡት ጓደኞቹ ታማኝ የሐባሻ አረቄ ደንበኞች ናቸው፡፡ ሌላ መጠጥ አይቀላቅሉም፡፡ ‹‹ለጤናችን ጥሩ አይደለም አረቄ እኮ ንፁህ ነው ክፋት የለውም፤›› ይላሉ፡፡ በአካባቢው ጠጅ ቤቶች ቢኖሩም ለጠጅ ፍቅር የላቸውም፡፡ ጠጥተው ታመው የሚያውቁም ጠጅ ባለበት አይደርሱም፡፡ ‹‹አፈር መልስ›› ከሚባለው በአካባቢው ከሚገኘው ጠጅ ቤት በቁማቸው ገብተው በእንብርክካቸው የሚወጡትን እያዩ ደፍረው እንደማይጠጡም ይናገራሉ፡፡ እንደ ሲሚንቶ ያሉ ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ ስላሉም ደፍሮ መጠጣት የማይታሰብ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም ነው በሐበሻ አረቄ የቆረቡት፡፡

ሁለተኛ ቤታቸው በሆነችው አረቄ ቤት ቡና አስፈልተው ይጠጣሉ፡፡ በሩ እስኪዘጋ ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ ላይወጡ ይችላሉ፡፡ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራት እዚያው እያሠሩ መብላት ነው፡፡ ደንበኝነታቸውን የሚያውቁ ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን ቅንጥብጣቢ ይልኩላቸዋል፡፡ ዋናው ቀደም ብሎ ማዘዝ ላይ ነው፡፡ ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ ለምሳ የተላከው ቅንጥብጣቢ በቢጫ ፌስታል እንደታሰረ መለኪያዎቹ የተደረደሩበት ጠረጴዛ ላይ ሰፈረ፡፡ ጠቀም ያለ ምሳ ጎርሰው ሁለተኛውን ዙር የመጠጥ ፕሮግራም ለመጀመር ተነሱ፡፡ ወደ ስካር ያደላ ሞቅታቸውን ጋብ ማድረግ ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ሕመምንም ማስቀረት እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በጀሪካን በጠርሙስ ታሽጎ አዲስ አበባ የሚገባው አረቄ ከማጀት አደባባይ የወጣ ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ ጠጅም ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ባህር ማዶም እየተላከ ይገኛሉ፡፡ ጠላም የሁለቱን ያህል ባይሆንም አገሬው በስፋት የሚያዘወትረው ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡ ጠላ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በበዓላትና በልዩ ልዩ ድግሶች ላይ የሚዘወተር፣ በአንዳንዱ አካባቢዎች ደግሞ የመጠጥ ውኃ ምትክ ሆኖ የሚጠጣ ተወዳጅ መጠጥ ነው፡፡ ጠላ የአውደ ዓመት ትዝታ፣ የነፍሰ ጡሮች አምሮት ከመሆን ባለፈ አዘጋጅተው ለገበያ ለሚያቀርቡ መተዳደሪያ ነው፡፡

ሾላ ገበያ ውስጥ የሚገኘው የወ/ሮ ሰብለ ኮራ ጠላ ቤት መግቢያው ላይ ጣሳ አልተሰቀለም፡፡ የምታዘጋጀውን ምርጥ ጠላ በዝና የሰሙ አምሮታቸውን ለማስታገስ የሚገቡበት፣ ቋሚ ደንበኞቿ ደግሞ ውሏቸውን ያደረጉበት መደናቀፊያ ነች፡፡ እንደ መፍረስ ያለው ጭቃ ቤት ለወይዘሮዋ እንደ መኖሪያም እንደ ንግድ ቤትም ነው፡፡ ወይዘሮ ሰብለ የጠላ ንግድ መተዳደሪያ ብቻ ሳይሆን ያደገችበት፣ ከልጅነት እስከ እውቀት የምታውቀው ሙያ ነው፡፡

ወላጅ እናቷ በአካባቢው የታወቀ ምርጥ ጠላ ጠማቂ ነበሩ፡፡ ቤታቸው በጠላቸው ፍቅር የተለከፉ መሸተኞች የሚሰባሰቡበት ነው፡፡ እሳቸው ከሞቱም በኋላ መሰባሰቢያ መሆኑ አልቀረም፡፡ እንዲያውም ለሠርግና ለልዩ ልዩ ድግሶች አቅርቡልን የሚሉ እየመጡላቸው ነው፡፡ ወ/ሮ ሰብለ ከእናቷ የወረሰችውን ሙያ መተዳደሪያዋ ካደረገች ሰባት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ጠላ መጥመቅ ከሥራ በላይ የአኗኗር ዘይቤዋ ነውና ጠላዋ ምንም አይወጣለትም፡፡

 ጠላ ለመጥመቅ ዝግጅት የሚጀምረው ከጌሾና ብቅል ነው፡፡ ተቀርጥፎ የሚደርቀው ጌሾ እንጨቱ ከቅጠሉ ተለይቶ ይወቀጣል፡፡ በወይራ፣ በጥንጁትና በሀባሎ ቅጠል ታጥኖ በተዘጋጀ እንስራ ውስጥ ጌሾውን መጠንሰስ ይጀመራል፡፡ ጌሾው በተጠነሰሰ በአምስተኛው ቀን ከገብስ፣ ከበቆሎ፣ ከዘንጋዳ፣ ከማሽላ፣ ከጥቁር ጤፍ ድብልቅ የተዘጋጀ የጠላ ቂጣ ከብቅል ጋር ተቀይጦ ከጥንስሱ ጋር ይደባለቃል፡፡ ይህ ከሆነ ከሦስት ቀናት በኋላ ደግም ከተለያየ እህል የተዘጋጀ የአሻሮ እህል ይሰናዳል፡፡

የአሻሮውን እህል በሁለት ዓይነት መንገዶች አዘጋጅቶ ከጥንስሱ መቀላቀል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው መንገድ እህሉን ለቀናት ዘፍዝፎ በማጠንፈፍ በፀሐይ አድርቆ መቁላት ከዚያም ነው፡፡ የደረቆት ጠላ ከተፈጨ በኋላ ቀጥታ ዱቄቱን ከጥንስሱ ጋር የሚቀየጥበት ደረቆት የሚባለው የደረቆት ጠላ ሥራውም አንፃራዊ ቅለት ያለው በጣዕሙም የሚመረጠው ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ አሻሮ የሚባለው ሲሆን፣ እህሉ ሳይዘፈዘፍ በደረቁ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶ ዱቄቱን እንኩሮ ካደረጉ በኋላ ከጥንስሱ ጋር የሚቀየጥበት ነው፡፡

 ፊሊተርና ሙሌት የሚባሉት ጠላዎች ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ቢሆንም ፊሊተር ድፍድፍ ላይ ውኃ እየጨመሩና በወንፊት እያጣሩ የሚዘጋጀ ነው፡፡ ሙሌት ግን እንዲሁ በጠላው ድፍድፍ ላይ ውኃ ተሞልቶ በወንፊት ሳይጣራ የሚቀርብ ጉሽ ጠላ ነው፡፡ ፊሊተር ጠላ ለማዘጋጀት እስከ 15 ቀናት ሲፈጅ፣ ሙሌት ደግሞ እስከ 12 ቀናት ይወስዳል፡፡ ወ/ሮ ሰብለ በአንድ የጠላ ጠመቃ ሒደት ከ80 እስከ 90 ኪሎ እህል ያስፈልጋታል፡፡ በአንዴም ከ500 እስከ 600 ሊትር ጠላ የምታዘጋጅ ሲሆን፣ በሊትር 15፣  በጣሳ ደግሞ 10 ብር ትቸረችራለት፡፡ ከወጪዋ የበለጠ ትርፍ እንደምታገኝ የምትናገረው ወይዘሮ ሰብለ በቀን እስከ 1,000 ብር ሸጣ ትውላለች፡፡

ለሠርግና ለአርባ ድግስ እስከ 300 ሊትር ጠላ የሚጠይቋት ደንበኞቿ ገቢዋን ከፍ ያደርጉላታል፡፡ ጠላው ተሸጦ የሚቀረው ቅራሪ ውኃ ጠማኝ ለሚል የሚሰጥ ደንበኛ መሳቢያ ዘዴ ይሆናል፡፡ በጎን ደግሞ አረቄም ትሸጣለች፡፡

‹‹የሐበሻ አረቄ የኔ ወዳጅ ነች ከአገሬ የነቀለችኝ እሷ ነች፤›› አሉ አረቄ ፉት ሳይሉ መዋል የማይችሉት አቶ ሽፈራው ታከለ፡፡ አቶ ሽፈራው ምርጥ አረቄ አጣጥመው ደረጃ ማውጣት የሚችሉ ‹‹ሱሰኛ›› ናቸው፡፡ አረቄ የጀመሩት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ በአስተማሪያቸው አማካይነት እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ የሚሉት አቶ ሽፈራው፣ ትምህርታቸውን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጠው አረቄ ቤት መለኪያ ሲያንቋርሩ መዋልን ሥራዬ እንዳሉ ያስታውሳሉ፡፡

 መሸተኛ መሆናቸውን ማንም ያውቀዋል፡፡ የጉልበት ሠራተኛ ሲሆኑ፣ በቀን የሚሠሩት እስካልሰከሩ ድረስ ለጥቂት ሰዓት ብቻ ነው፡፡ ውሏቸው ጠላ ቤት አረቄ ሲያሳድዱ ነው፡፡ ለረዥም ዓመት የጠጡበት የወ/ሮ ሰብለ ጠላ ቤት ሁለተኛ ቤታቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ የቤተሰብ ያህል ቅርርብ ያላቸው፣ ወ/ሮ ሰብለ ሳይኖሩ ቤቱን የሚጠብቁ፣ ደንበኛን የሚያስተናገዱ ታማኝ ሰው ለመሆን በቅተዋል፡፡

የሸክም ሥራ ሠርተው በቀን እስከ 50 ብር ቢያገኙ አብዛኛው ለአረቄ መግዣ ይውላል፡፡ መለኪያውን ወደ አፋቸው በወሰዱ ቁጥር ሞቅ እያላቸው ጨዋታቸውም በዚያው መጠን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ የሐበሻ አረቄ ያተረፈላቸውን ጦስ ሲዘረዝሩ ሳቅ ይቀድማቸዋል፡፡ ሕይወታቸው እንደተበላሸ ቢሰማቸውም በሐባሻ አረቄ አያዝኑም ‹‹ወዳጄ ነች›› ይላሉ፡፡ በሕይወታቸው ከሁሉ ነገር በላይ የሚቆጫቸው ነገር ኑሯቸው ሳይሆን የሚተዳደሩበት የጉልበት ሥራ ስያሜ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ወዛደር›› መባልን አይፈልጉም፡፡ እንዲሁ ስሙን ይጠሉታል፡፡ ‹‹ወዛደር ከምንባል ላባደር ብንባል ይሻለኛል፡፡ ለምን ስማችን አይቀየርም›› ብለው ሲማረሩ ይችን ጨዋታቸውን የሚያውቁ ጓደኞቻቸው ሳቃቸው አመለጣቸው፡፡

አቶ ሽፈራው የሥራቸው ስያሜ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሞቅ ሲላቸው ነው፡፡ በመለኪያ የሚቀዳላቸውን አረቄ ደጋግመው እየሳቡ እንዴት ወዛደር መባል እንደሌለባቸው በስሜት ይተነትኑ ጀመር፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ሞቅታቸው ወደ ስካር ተለውጦ ባሉበት ሆነው መሬቱን በእግራቸው እየመቱ ‹‹የመንዙን ተወላጅ ሽፈራው ታከለን ማን አባቱ ነክቶ፤›› እያሉ መፎከር ጀመሩ፡፡

እንደ እሳቸው ያሉ ጠጪዎች ቢሰክሩም የከፋ ነገር ስለማያደርሱ ወ/ሮ ሰብለ ፈገግ እንዳሉ ነው የሚያዩዋቸው፡፡ ሞቅታ ውስጥ ገብቶ አልከፍልም የሚል ፀብ የሚፈልግም ቢሆን በፀባይ ይሸኛል እንጂ አገፈታትሮ የሚያወጣው የለም፡፡