Skip to main content
x
እስራኤልና ኢራን በምድረ ሶሪያ
አሜሪካ ወታደሮቿን ከሶሪያ አስወጣለሁ ማለቷ አይኤስ እንዲያንሰራራ ዕድል ይፈጥራል ተበሏል

እስራኤልና ኢራን በምድረ ሶሪያ

አሜሪካና ሩሲያ ጎራ ለይተው የእጅ አዙር ጦርነታቸውን የሚያካሂዱባት ሶሪያ ከትናንት በስቲያ (ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም.)  የእስራኤልን ሚሳይሎች ስታስተናግድ አድራለች፡፡

እስራኤል ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጣለች ሲል የዘገበው አልጀዚራ፣ በሶሪያ በኩልም በርካቶች ሚሳይሎች በአየር ኃይል ተመትተው መምከናቸውን አሳውቋል ብሏል፡፡

በሶሪያ የኢራን ወታደሮች ይገኙበታል የተባለውን አካባቢ የእስራኤል ሚሳይሎች ሌሊቱን ሲዘንቡ ማደራቸውን ተከትሎም ‹‹በሶሪያ ግዛት የሚገኘውን የኢራን ጓድ ዒላማ አድርገን የአየር ድብደባ አካሂደናል፡፡ የሶሪያ መከላከያ በእስራኤል ወታደሮች ወይም ግዛት ጥቃት የመፈጸም ሙከራ እንዳያደርግም አስጠንቅቀናል፤›› ሲሉ የእስራኤል መከላከያ መግለጫ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡

በሶሪያ የሚገኙት የኢራን ወታደሮችም ኢራን ከአገር ውጭ ያላትን ወታደራዊ ኃይል የሚወክሉ ናቸው፡፡ ኢራን እንደ ሩሲያ ሁሉ የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ የጀርባ አጥንት ስትሆን፣ ወታደሮቿም ከሰባት ዓመት በላይ የጦርነት አውድማ በሆነችው ሶሪያ ይገኛሉ፡፡

የአልጀዚራው ሃሪ ፋውቤት ከደቡባዊ እስራኤል ከምትገኘው ኢላት እንደዘገበው፣ እስራኤል ወታደራዊ ዕርምጃ በሶሪያ ምድር ላይ መውሰዷን ማረጋገጧ የተለመደ አካሄድ አይደለም፡፡

በሶሪያም ዋና ከተማ ደማስቆ ከትናንት በስቲያ ሌሊቱን ከባባድ ፍንዳታዎች ይሰሙ እንደነበር የዓይን እማኞች የገለጹ ሲሆን፣ የሶሪያው ዜና ጣቢያ ሳና በበኩሉ የአየር ጥቃት እንደነበርና በርካቶቹም ሚሳይሎች ተመትተው እንደተጣሉ አሳውቋል፡፡

እስራኤልና ኢራን በምድረ ሶሪያ
ከወር በፊት ደማስቆ በሚሳይል ተደብድባ ነበር

 

በሶሪያ ደቡባዊ ክፍል በርካታ ሚሳይሎች ተመትተው መክሸፋቸውን የአገሪቱ ሚዲያ ብቻም ሳይሆን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም አሳውቋል፡፡ ‹‹እስራኤል ድንበር ተሻግራ የፈጸመችውን የሚሳያል ጥቃት ግቡን ሳይመታ መቆጣጠር ችለናል፤›› ሲል የሶሪያ መከላከያ ማሳወቁንም ሳና ዘግቧል፡፡

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴርም በትዊተር ገጹ ‹‹የሶሪያ መከላከያ ሰባት የእስራኤል ሮኬቶች በደማስቆ አየር ማረፊያ አቅራቢያ አክሽፏል፤›› ማለቱን አልጀዚራ አስፍሯል፡፡

በጥቃቱ በሰውም ሆነ በአየር ማረፊያ ላይ ጉዳት እንዳልደረሰም ተነግሯል፡፡ እስራኤል ጥቃቷን ከፈጸመች በኋላ የእስራኤል መከላከያ የአገሪቱ የብረት ምሽግ (አይረን ዶም) መከላከያ ሥርዓት ከሰሜናዊ የጎላን ተራራ ከሶሪያ ድንበር በኩል ሮኬት ተተኩሶ ማክሸፉን አስታውቋል፡፡ ሰሜናዊ ጎላን ለሊባኖስ ድንበር የቀረበ መሆኑንና ሮኬቱ በትክክል ከየት ቦታ እንደተወነጨፈ ግን ከእስራኤል ወገን አልተነገረም፡፡

ኢራን ለሶሪያ ጠንካራ ወታደራዊ ድጋፍ ታደርጋለች የሚሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ፣ ባለፈው ሳምንት መከላከያቸውን ሲያወድሱ ተደምጠው ነበር፡፡

ኢራንና ሂዝቦላህ ለሶሪያ የሚያደርጉትን ድጋፍ ለመቀልበስ ባለፉት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን መሰንዘራቸውን ለካቢኔያቸው ያሳወቁት ናታንያሁ፣ ከዚህ ቀደም በድንበር አካባቢ ኢራንን ዒላማ አድርገው ስለሚወስዱ ወታደራዊ ዕርምጃዎች ብዙም ተናግረው አያውቁም ነበር፡፡

ደማስቆ ከወር በፊትም የሚሳይል ጥቃትን አስተናግዳ ነበር፡፡ የኢራንና ሂዝቦላህ ወታደራዊ መንደር በሚባሉ አካባቢዎች ላይ የሚሳይል ጥቃቱ ሲፈጸም የእስራኤል ወዳጅ አሜሪካ የቀዝቃዛው ጦርነት ተፋላሚ ሩሲያ ለኢራንና ሂዝቦላህ ከለላ ሆናም ነበር፡፡

በወቅቱ ለአንድ ሰዓት በተደረገው ከባድ ድብደባ 15 የኢራንና የሂዝቦላህ ወታደራዊ ሥፍራዎች ተመትተዋል፡፡ ጥቃቱ መፈጸሙን የሩሲያው ዜና ወኪል አር አይኤ የሶሪያ የደኅንነት አካላትን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር፡፡ እስራኤል ጥቃቱን ስለመፈጸሟም ተነግሯል፡፡ በወቅቱም የሶሪያ አየር ኃይል የእስራኤልን የጦር ጄት መጥቶ መጣሉንና አራት ሚሳይሎችን ማክሸፉንም አሳውቆ ነበር፡፡

እስራኤል በወቅቱ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባ የነበረ ቢሆንም፣ በዚያን ጊዜ ግን በምዕራብ ሶሪያ የሂዝቦላህና የኢራን ጦር ሠፈር በሆነውና የመሣሪያ መጋዘን በሚገኝበት አል ኪስዋ ድብደባ ተፈጽሞ ነበር፡፡ በደቡብ ደማስቆ ‹‹ግላስ ሃውስ›› እየተባለ በሚጠራው የኢራን ማዕከላዊ ኮማንድ ፖስትም የድብደባው ሰለባ ነበር፡፡ ሥፍራው የሚሳይል ዌር ሀውስ ይሆናል የሚል ጥርጣሬም ነበር፡፡

እስራኤል በሶሪያ ውስጥ ለሚፈጸም የአየር ጥቃት እምብዛም ኃላፊነት ወስዳ ባታውቅም አሁን ላይ ግን ጥቃት መፈጸሟን አምናለች፡፡ ቢቢሲ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ ይህ የዘመቻው መጀመርያ ነው፡፡

እስራኤልና ኢራን ለምን ጠላታሞች ሆኑ?

እስራኤል በሶሪያ የሚገኙ የኢራን ወታደራዊ ሠፈሮችን ዒላማ አድርጋ መምታቷ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ለዓመታት የከረመ አለመግባባት ያባብሰዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1979 የኢራን አብዮት ከተካሄደና የሃይማኖት መሪዎች ወደ ሥልጣኑ ከመጡ ወዲህ ለእስራኤል ቦታ አልሰጡም፡፡ እስራኤላውያን የሙስሊም ሥፍራ በሆነው ሠፍረዋል ብለውም ያምናሉ፡፡ ሕገወጥ ሠፋሪ በማለትም ለእስራኤል በዚያ መኖር ዕውቅና አልሰጡም፡፡ ይህም በእስራኤልና ኢራን መካከል ቁርሾ ፈጥሯል፡፡

እስራኤል ለኢራን፣ ኢራንም ለእስራኤል ተኝተው የሚያድሩ አገሮችም አይደሉም፡፡ የኢራን የኑክሌር ማብለያ እስራኤልን እንቅልፍ ከነሳ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢራን በተደጋጋሚ በአሜሪካ ግፊት ለሚጣልባት ማዕቀብ እስራኤል የጀርባ አጥንት ናት፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ. በ2011 በሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የጎረቤቷን ሶሪያ ጦርነት በዓይነ ቁራኛ ትከታተላለች፡፡ ሆኖም በሶሪያና በሶሪያ አማፅያን መካከል ባለው ጦርነት ጣልቃ ስትገባ አትስተዋልም፡፡ ሆኖም ኢራን ለሶሪያ መንግሥት የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ እስራኤልን አላስደሰተም፡፡ ኢራን ለእስራኤል ሥጋት ለሆኑት ሊባኖሳውያን በሚስጥር መሣሪያ ታሻግራለች የሚል ሥጋትም አለ፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትርም ኢራን በሶሪያ በምታሠልፈው ጦር ምክንያት እስራኤል ለችግር እንድትጋለጥ ዕድል አንፈጥርም ሲሉም በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡ ይህም ቢሆን ግን እስራኤልና ኢራን በቀጥታ ጦርነት ገብተው አያውቁም፡፡ ሆኖም ኢራን በምትደግፋቸው ሂዝቦላህና የፍልስጤም ሚሊሻ ሃማስ በኩል በእስራኤል ጋር የእጅ አዙር ጦርነት ታካሂዳለች፡፡ ኢራን ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳይሎች ያላት ሲሆን፣ ለእስራኤል ድንበር አካባቢዎች ጠንካራ ወዳጆች አሏት፡፡  

በእስራኤል በኩል ጠንካራ ወታደራዊ ክፍል ያለ ሲሆን፣ የኑክሌር መሣሪያም ባለቤት ናት፡፡ በአሜሪካም ትደገፋለች፡፡