Skip to main content
x
የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነትና ደኅንነት ፖሊሲ ማሻሻል ለምንና እንዴት?
በተለያዩ አገሮች ኢትዮጵያን በመወከል በአምባሳደርነትና በቆንስላ ጄኔራልነት የሚያገለግሉ ዲፕሎማቶች ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገው ነበር

የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነትና ደኅንነት ፖሊሲ ማሻሻል ለምንና እንዴት?

ሁለት አሠርት ዓመታት ለመሙላት ጥቂት ጊዜ የቀረውንና በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለማሻሻል እየተሠራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ከገባ 17 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይኼንን ፖሊሲና ስትራቴጂ በፊታውራሪነት ያረቀቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ በዋናነት ወደ ውስጥ የሚመለከተውን ይህ ፖሊሲ ከውጭ ጠላትና የደኅንነት ሥጋት በላይ በጠላትነት የሚፈርጀው ድህነትን ነው፡፡

በ1995 ዓ.ም. ወጥቶ እስካሁን በተግባር ላይ ያለው ይኼ ፖሊሲ በመግቢያው ላይ ስለተመሳሳይ ዓይነት ፖሊሲዎች አስፈላጊነትና ግብ ሲያስረዳ፣ ‹‹የደኅንነት ፖሊሲ በመሠረቱ አገራዊ ህልውናን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ የደኅንነት መጀመርያም መጨረሻም አገራዊ ህልውና ማረጋገጥ ነው፡፡ ሌሎች አገራዊ የደኅንነት ጉዳዮች የሚነሱት ህልውና ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ከብሔራዊ ጥቅም አኳያም መነሻውና መድረሻው አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ነገር ሁሉ የሚመጣው አገራዊ ህልውና ከተረጋገጠ በኋላ ነው፤›› በማለት ያትታል፡፡

በዚህም መነሻነት በዚያን ወቅት ይበጃሉ የተባሉ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የተገመገሙበት ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ መነሻዎች ናቸው ተብለው የተለዩ ሦስት ጉዳዮችን ይተነትናል፡፡ የመጀመሪያው ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንደ ፖሊሲ መነሻ፣ ሁለተኛው አገራዊ ክብር እንደ ፖሊሲ መነሻና ሦስተኛው ግሎባላይዜሽን እንደ ፖሊሲ መነሻ ናቸው፡፡

ሰነዱ ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እንደ ፖሊሲ መነሻ በትንታኔ ሲያቀርብ፣ ‹‹በአገራችን ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ከድህነት፣ ከድንቁርናና ከኋላ ቀርነት ተላቆ የተመቻቸ ኑሮ እንዲኖር ለማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ የአገራችን ሕዝብ እጅግ መሠረታዊ የሆነው ጥቅም ድህነትን፣ በሽታንና ድንቁርናን ማስወገድ ነው፤›› በማለት አውስቶ፣ ‹‹ፈጣን ዕድገት አረጋግጠን ሕዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ካልቻልን በስተቀር፣ በአገራችን ከፍተኛ ብጥብጥና መበታተን እንደሚመጣ በፍፁም አያጠራጥርም፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹ዴሞክራሲን በአገራችን ዕውን የማድረግ ጉዳይ ልማትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ዕልቂትና ብተናን የማስቀረት፣ ብሔራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ጉዳይም ጭምር ነው፤›› በማለት መነሻው ምን ያህል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ‹‹የአገራዊ ጥቅማችን አልፋና ኦሜጋ ልማትና ዴሞክራሲ ናቸው፡፡ የውጭ ጉዳይና አገራዊ የደኅንነት ፖሊሲዎቻችን መነሻና መድረሻም ልማትና ዴሞክራሲ ሊሆኑ ይገባል፤›› ይላል፡፡

በሁለተኛ መነሻነት የሚያነሳው የአገራዊ ክብርን በተመለከተ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ለውጭ ገዥዎች ሳይንበረከኩ ነፃነታቸውን አስከብረው መቆየታቸው፣ ብቸኛና በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀች አገር ስለሆነች ይህ አኩሪ መሆኑን በመተንተን የሚጀምረው ይህ ክፍል፣ በታሪክ የተገኙ ድንቅ የፈጠራ ውጤቶች እንደሚያኮሩም ያወሳል፡፡ የዚህ ኩራት ምንጭም ምንም ሳይሆን የቀደመው ትውልድ ተጨባጭ የሥራ ውጤት እንደሆነም ይገልጻል፡፡

ይሁንና ምንም እንኳን እነዚህ እሴቶች አሁን ያለው ትውልድ ሊኮራባቸውና  ሊንከባከባቸው የሚገቡ ቢሆንም፣ ‹‹ሊያሳፍሩትና ሊያሸማቅቁት የሚገቡ የአገራዊ ውርደት ገጽታዎች አሉ፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

ይህም ውርደት የሚመነጨው አገሪቱ በዋናነት ተመፅዋችና ተስፈኛ በመሆኗ ሲሆን፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ ራሳችንን መመገብ አቅቶን በየዓመቱ ምግብ ልመና እንደ ሕዝብ ወደ አደባባይ እየወጣን ነው፡፡ ከልመና በላይ የአንድን ሕዝብ ክብር የሚገፍና አንድን ሕዝብ ለከፋ ውርደት የሚዳርግ ነገር የለም፤›› ሲል ስሜት ይኮረኩራል፡፡

በዚህም ምክንያት የሚያኮራ ታሪክ ተሸክማ ያለች አገር በተጨባጭ የአገሮች ጭራ ሆና መሠለፏን በማስመር፣ የዚህ ውርደት ዋነኛ ምንጭ ድህነትና ኋላ ቀርነት ነው በማለት ወደ ቀደመው መነሻ ያንደረድረዋል፡፡

ስለዚህም ‹‹አገራዊ ክብራችንን ማስጠበቅ እንደ ፖሊሲ መነሻ መቅረብ ካለበት፣ ለዚሁ ሲባል ጭምር ከምንም ነገር በላይ በልማትና በዴሞክራሲ ላይ በመረባረብ አገራዊ ክብራችንን ማስጠበቅ በሚል መልክ ብቻ ነው ልንወስደው የምንችለው፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

በመቀጠልም ግሎባላይዜሽንን እንደ መነሻነት ሲተነትን፣ ‹‹በአገራችን ልማትና ዴሞክራሲን ከሌላው ዓለም ተነጥለን፣ በተራሮቻችን ዙሪያ መሽገን፣ በሮቻችንን ዘግተን ከቶ ልናረጋግጥ አንችልም፣›› ሲል የቀደሙት መነሻዎች ምን ያህል በዓለም አቀፍ ኃይሎች ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ እንደሚችሉና ያለ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ግንዛቤ ሊሳኩ እንደማይችሉ ያስገነዝባል፡፡

በዚህ መነሻም፣ ‹‹የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲያችን መነሻና መድረሻ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ ሲባል፣ ይኼንኑ በግሎባላይዜሽን ማዕቀፍ ውስጥ ማስፈጸም ማለት በመሆኑ ግሎባላይዜሽንም አንዱ የፖሊሲ መነሻ መሆኑን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የአገራዊ ውርደታችን ምንጭ የሚደርቀው ሁሉንም ነገር ለልማትና ለዴሞክራሲ ተገዥ በማድረግ በመረባረብ በመሆኑ፣ አገራዊ ክብራችንን የመጠበቅ ጉዳይ ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ከማድረግ ዓላማ ጋር አንድና ያው እንደሆነ ማስቀደም ይቻላል፤›› ሲል ከቀደሙት ሁለት መነሻዎች ጋር በማቆራኘት ይዘጋል፡፡

በዚህም ባህሪው ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወደ ውስጥ ተመልካች እንደሆነ፣ ውጫዊ ጉዳዮችን ከውስጣዊው ሒደት ጋር ባቆራኘ መነሻ ላይ እንደ ተመሠረተ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህም ፖሊሲው ድህነትን፣ ድንቁርናንና ኋላ ቀርነትን እንጂ ጠላት አለብኝ ብሎ የሚፈርጀው ውጫዊ ጠላትን አይደለም፡፡ እናም የዚህ ፖሊሲና ስትራቴጂ ዓላማ፣ ‹‹ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል የተመቻቸ የውጭና የደኅንነት ሁኔታ መፍጠር ይሆናል፡፡ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት መነሻም መዳረሻም ልማትና ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ ይሆናል፤›› ሲል ያስረግጣል፡፡ ለዚህም ዋናው ትኩረት በአገር ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎች መሆናቸውን ያትታል፡፡

የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲው የሚነሱበት ጥያቄዎች

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ትኩረቱን ድህነት ላይ ቢያደርግም፣ በዋናነት ሉዓላዊነት ላይ የተንጠለጠለ ይዘት ስላለው ድንበር ላይ እንጂ ግለሰባዊ ነፃነትና ለሕዝቦች ቀጥተኛ ትኩረት የሰጠ አይደለም ሲሉ የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡

ከእነዚህ ተቺዎች መካከል የሕግ ባለሙያውና የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዓለማየሁ ፈንታው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖለሲና ስትራቴጂ መንግሥት ተኮር ከሆነው አካሄድ ሙሉ በሙሉ በመቀየር፣ ሕዝብ ተኮር አካሄድን መከተልና ለዚህም ተግባራዊነት ሙሉ ዕውቅና መስጠት አለበት፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

ምንም እንኳን የአመለካከት ለውጦች የተስተዋሉ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ማዕከላዊ ጥቅም እያለ ቆይቷል ሲሉ አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የዲስኩር ለውጡ የተግባር ለውጥን አላስከተለም፡፡ የሰዎች ደኅንነት የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲውና ስትራቴጂው ማዕከል መሆን ይገባዋል፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ በኋላ የአገሮች የደኅንነት ፖሊሲዎች ትኩረት እያደረጉ የመጡት፣ ከአገራዊ ደኅንነት ይልቅ የሰዎች ደኅንነታ ላይ ነው የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹በአዲሱ ትርጉሙ ደኅንነት የአገሮች ደኅንነት ብቻ ሳይሆን ከግለሰቦች ደኅንነት ጋር ይዛመዳል፤›› ይላሉ፡፡ ይህ በቀላሉ ሲቀመጥም፣ የድንበር ደኅንነት ሳይሆን የሰዎች ደኅንነት ነው ባይ ናቸው፡፡

ይህም የፖሊሲውና ስትራቴጂው ማዕከላዊ አጀንዳ እንዳልሆነ ለማሳየት መንግሥት የውስጥ ችግሮችን ለመፍታት በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች እንደሚስተዋልም ያትታሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከፖሊሲው በተቃራኒ አገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፍላጎቷን በጦርነት ለማስፈጸም እንደምትጥር ማሳያ የሆነው በሶማሊያ ጦር ማሰማራቷ እንደሆነ የሚያወሱት ተንታኙ፣ ይህ በየትኛውም የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህ ሲመዘን ተቀባይነት የሌለው ነው ይላሉ፡፡ ጦርነት ሰላምን ያመጣል በሚል እሳቤ የመጨረሻ አማራጭ መሆን ሲገባው፣ ሰላምን ግን በሶማሊያ ሊያመጣ አልቻለም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በፖሊሲው በክፍል አንድ የመከላከያ በጀትን በሚመለከት ያስቀመጠውን ገደብም የጣሰ እንደነበር በማውሳት፣ ይህ አንዱ የፖሊሲው ድክመት እንደሆነ እኚሁ ተንታኝ በሌላ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ባነሱበት ጽሑፋቸው ያስረዳሉ፡፡ ፖሊሲው ምንም እንኳን የመከላከያ በጀት ዓለም አቀፍ ልምድን ባገናዘበ መንገድ ከአገራዊ ጠቅላላ ምርት (ጂኤንፒ) ሁለት በመቶ መብለጥ የለበትም በማለት አስቀምጦ ይህ እንኳን ለአገሪቱ የበጀት ጫና ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ መስመር ቢያሰምርም፣ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶችን ዋቢ በማድረግ በተደጋጋሚ ይህ የመከላከያ ወጪ በጀት ከተሰመረው የሁለት በመቶ ህዳግ መብለጡን ያስታውሳሉ፡፡

ከዚህ በዘለለም አገራዊ ደኅነቱን ለማስጠበቅ ድህነት፣ ድንቁርናና ኋላ ቀርነት እንዳሉ በመጥቀስ ዴሞክራሲን ማስፋት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ በፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ ቢቀመጥም፣ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ በወረቀትና በተግባር ሊጣጣም እንዳልቻለ ይገልጻሉ፡፡ እዚህም ላይ በአገሪቱ በስፋት የሚስተዋለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ልብ ይሏል በማለት ያነፃፅራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርሆዎች

የውጭ ግንኙነት ስድስት መርሆዎች እንዳሉት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 86 የተደነገገ ሲሆን፣ ፖሊሲው ሲወጣም እነዚህን መርሆዎች ያገናዘበ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ የሕገ መንግሥት መርሆዎች የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅም የሚያስጠብቅና የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማራመድ፣ የመንግሥታትን ሉዓላዊነትና እኩልነት ማክበር፣ በሌሎች አገሮች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባት፣ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩና የሕዝቦቿን ጥቅም የማይፃረሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችን ማክበር፣ ከጎረቤት አገሮችና ከሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ኅብረትና የሕዝቦች ወንድማማችነትን ማጎልበትና በአገሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡

የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለምን ማሻሻል ያስፈልጋል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገሮች ኢትዮጵያን በመወከል በአምባሳደርነትና በቆንስላ ጄኔራልነት ከሚያገለግሉ ዲፕሎማቶች ጋር ባለፈው ሳምንት በነበራቸው ውይይት፣ ኢትዮጵያ ወጥ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እየሠራች እንዳልሆነና ተሿሚዎችም የሚጠበቅባቸውን ያህል ተግባራት እየፈጸሙ እንዳልሆነ ተናግረው ነበር፡፡ ስለዚህም ካሁን በኋላ በአገሮቹ የሚሾሙ አምባሳደሮች የዜጎችን ደኅንነትና መብት ቅድሚያ ሰጥተው የሚሠሩ መሆን እንዳለባቸው አስምረዋል፡፡ በያሉበት አገርም የዜጎች መብት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ የሚያገለግል እንደራሴ ያስፈልጋልም ሲሉ አሳስበው ነበር፡፡

በዚህ መነሻነትም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ማሻሻል እንደሚገባ በመገንዘብ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ዴኤታ ደረጃ የሚመራ ቡድን ተቋቁሞ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂን የማሻሻል ሒደት ተጀምሯል፡፡ ምንም እንኳን ይኼንን ፖሊሲ ለማሻሻል ካሁን ቀደም በሐሳብ ደረጃ የተነገረ ቢሆንም፣ ቡድን ተቋቁሞ ሥራው የተጀመረው በቅርብ ነው፡፡ በተለይ ይኼንን ፖሊሲ ለማሻሻል ፍላጎት እንዳለ ሲገለጽ የነበረው፣ ኤርትራን በሚመለከት ኢትዮጵያ ያላትን ፖሊሲ መቀየር እንደምትፈልግ ሲታወቅ ነበር፡፡

ላለፉት 17 ዓመታት በአገሪቱ በተግባር ላይ የቆየው የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ መሻሻል አለበት የሚሉ ባለሙያዎችና ዲፕሎማቶች፣ በርካታ መከራከሪያ ነጥቦችን ያነሳሉ፡፡ የመጀመርያው በዓለም እየታየ ያለው የኃይል አሠላለፍ ለውጥ ሲሆን፣ በአሜሪካ የበላይነት የሚመራው ዓለም አቀፍ አስተዳደር አሁን ተገዳዳሪዎች እየመጡበት መሆኑ፣ ከአንድ ወገን የዓለም አስተዳደር (ዩኒ ፖላር) ወደ ባለ ብዙ ወገን የዓለም አስተዳደር (መልቲ ፖላር) የዓለም አስተዳደር ምዕራፍ እየተገባና አዳዲስ ኃያላን እየተፈጠሩ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ ይኼንንም ሲያስረዱ የጽንፈኝነት ፖለቲካን መግነንና የቻይናን እየጠነከረች መምጣት እንደ ምሳሌ ያነሳሉ፡፡

በውጭ ጉዳይ ዘርፍ ጎላ ብለው ከሚታዩና ከፍተኛ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች አንዱ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በቅርቡ ለጥናት፣ ለምክርና ለትብብር ማዕከል በጻፉት ጽሑፍ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፍኖተ ካርታ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ የውጭ ግንኙነትን ለማካሄድ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነበር፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሠረተ ነገር ግን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተግባር የምታሳየው ማንነት ያላት አገር መሆኗንም ለዓለም ያስመሰከረችበት ነበር ይላሉ፡፡

ነገር ግን አሁን በምሥራቅ አፍሪካ እያደገ በመጣው የተለያዩ አገሮች ፍላጎትና በዓለም አቀፍ የኃይል አሠላለፍ ምክንያት፣ እስካሁን ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ፖሊሲ መሻሻሉ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አሁን ያለው ፖሊሲ በ1995 ዓ.ም. ሲወጣ አሁን እየታዩ ያሉ ዓለም አቀፍ ክስተቶች እምብዛም ያልታዩ በመሆናቸው፣ ፖሊሲው የተንጠለጠለባቸው መሠረታዊ መርሆዎች በዚህ ወቅት ስለማይሠሩ ፖሊሲውን ማሻሻል አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

በምሥራቅ አፍሪካና በጎረቤት አገሮች፣ እንዲሁም በቀይ ባህር አካባቢ እየታዩ ያሉ ለውጦችን አገሪቱ በንቃት መከታተል እንዳለባት የሚያስገነዝቡት አምባሳደር ተቀዳ፣ ኢትዮጵያ አገሮች በዙሪያዋ ባሉ አገሮች ፍላጎት ሲያሳዩ ቢያንስ የማወቅ መብት እንዳላትና ሊነገራት እንደሚገባ፣ ብሎም ለምን ጉዳይ እንደመጡ ሊጤንና ከብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት አኳያ መታየት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

አሁን እየታየ ባለው የቀይ ባህር አካባቢ ሽሚያ ከቀይ ባህር ወዲህ ብቻ ሳይሆን፣ ከማዶም ምን እየሆነ እንዳለ መከታተልና ማወቅ አስፈላጊ ነው ሲሉም ይመክራሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከኤርትራ ጋር የተደረገው ዕርቅ ብዙ ነገሮችን ሊለውጥ የሚችል እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ይኼንን ሲሉም ኢትዮጵያና ኤርትራ ካሁን ቀደም በመርህና በሕግ ላይ ያልተመሠረተ ግንኙነት በመመሥረታቸው የገቡበት ጦርነት እንዳይደገም ለማድረግ ሁሉንም በሕግ ማዕቀፍ ማሰር እንደሚገባ በማሳሰብ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ትልቅ የፖሊሲ ግብዓት እንደሚሆን ይናገራሉ፡፡

ይሁንና የአገሪቱ የውስጣዊ ሰላምና የደኅንነት ጉዳይ ይህን ያህል አሳሳቢ በሆነበት ጊዜ ስለውጭ ግንኙነትና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ የሚደረግ ውይይት እምብዛም አስቸኳይ አይሆንም ይላሉ፡፡ ሆኖም ከአሁን ቀደም የነበረው ፖሊሲ ምንም እንኳን የአፈጻጸም ክፍተቶች የተስተዋሉበት ቢሆንም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገማች የሆነ ፖሊሲ የምታራምድ፣ ተደማጭና ተቀባይነት ያላት አድርጓታል በማለትም ያሳስባሉ፡፡

‹‹የራሳችን ተሞክሮ እንዳሳየን፣ በደንብ የተቀናጀ ፖሊሲና ስትራቴጂ አለ ማለት በሰነዱ የተቀመጠውን በማስፈጸም ረገድ ውጤታማ ይኮናል ማለት አይደለም፡፡ በተግባር ትክክል እንሆናለን የሚል ዋስትናም የለም፤›› ሲሉም አበክረው ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዲጂታል ዓለም መጎልበት፣ መረጃ በቀላሉ ማግኘትና መተንነት መቻልም አንዱ የፖሊሲ ግብዓት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአምባሳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ጠቅሰዋል፡፡ ግሎባላይዜሽንን እንደ አዲስ ትርጉም በሰጠው በዚህ የኢንተርኔትና የኢንፎርሜሽን ዘመን የሚኖር ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እነዚህን ዕድገቶችና ለውጦች ከግንዛቤ ያስገባ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ሐሳባቸውን በጽሑፍ ያሰፈሩት የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፃድቃን ወልደ ትንሳዔ (ሌተና ጄኔራል)፣ የውጭ ግንኙነትና የአገር ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከፍተኛ መግባባት ሊደረግባት የሚገባና ሁሉም ሊገዛው የሚገባ ሰነድ መሆን እንዳለበት ያሰምራሉ፡፡

‹‹የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በእኔ አመለካከት ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ በክብደቱና በአገር ህልውና፣ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ለማስተዳደር እጅግ መሠረታዊ የሆነ ነው፡፡ በትክክል ከተሠራ ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ፣ ይኼ ካልሆነ ደግሞ አገርን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ፖሊሲ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የአገር ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ በአገር አቀፍ ደረጃ መሠረታዊ መግባባት ሊደረስበት የሚገባ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን የተወሰኑና በአንድ ወቅት በሥልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ፍላጎት መግለጫ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ የአንድ ፓርቲ የፖሊሲ ምርጫ ብቻ መሆንም የለበትም፣›› በማለት አሳስበው፣ ‹‹ይኼ ሲደረግ ደግሞ ያለፈውን ፖሊሲ መገምገም ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ የሚወጣው ፖሊሲ ተፈላጊው ውጤት እንዲኖረው መሥራት ተገቢ ይመስለኛል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

አምባሳደር ተቀዳ በጽሑፋቸው ማጠቃለያ ላይ፣ ‹‹ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለኢትዮጵያ ግልጽ የሆነና በግልጽነት ላይ የተመሠረተ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲ የሚያስፈልግበት ጊዜ አሁን ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹በዓለም ኃያላን መካከል እየተፈጠረ ያለውን ውጥረት ለማርገብ ባንችል እንኳ፣ በአገራችን ውስጥ በምናከናውነው ሥራ ቢያንስ ለመባባሳቸው ተጨማሪ ነዳጅ አለመሆን እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

ፖሊሲው መከለስ አለበትም ሲባል በተለይ በቀጣናው እየተፈጠሩ ያሉ ፖለቲካዊ ኩነቶችን፣ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ከዓረብ አገሮች ያላትንና የሚኖራትን ግንኙነት እንደገና መከለስን፣ እንዲሁም ቀጣናው ኃያላን አገሮች ስለሚሻኮቱበት ወደ ብጥብጥ እንዳያመራ ነገሮችን የሚያጤንና የሚያካትት የፖሊሲ ሰነድ ሊኖር እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡