Skip to main content
x
ዶጋሊ እና የኢትዮጵያ ነፀብራቅ

ዶጋሊ እና የኢትዮጵያ ነፀብራቅ

‹‹ከሮማውያን ቅርሶች መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የትኛው ነው?›› ተብለህ ብትጠየቅ፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ሮም ውስጥ ፍርስራሹ የሚታየው ኮሎሲየም ነው፤›› በማለት ትመልሳለህ? ረዥም ዘመን ያስቆጠሩትን አሊያም ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደሩትን የሮማውያን ግንባታዎች ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ፣ የሮማውያንን መንገዶች መዘንጋት አይኖርብንም?›› የሚለው ጥያቄያዊ ሐተታ የሠፈረው ከአንድ የባሕር ማዶ የጉዞ ድርሳን ላይ ነው፡፡

ይኼንን ድርሳን እያነበብኩ ነበር በጣሊያን መዲና በሮም ታላቅ ቦታ የሚሰጠው የመጀመርያው አውራ ጎዳና ቪያ ፐብሊካ (የፐብሊካን አውራ ጎዳና) በእነሱ በጋ (ሰመር)፣ በእኛ ክረምት ነሐሴ 2010 ዓ.ም. የተመላለስኩት፡፡ የኦሊምፒክ ፋና ወጊው አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ እየሮጠ የሸነፈበት ቪያ አፒያም አልቀረችብኝም፡፡ በዚያ አጋጣሚ ነበር ተርሚኒ በሚባለው ባቡር ጣቢያ በሚገኝበት አካባቢ ስደርስ ከአንድ ታሪካዊ ሐውልት ጋር የተፋጠጥኩት፡፡ ከባቡር ጣቢያ መናኸሪያው ፊት ለፊት የሚገኘው ሰፊ አደባባይ ‹‹ፒያዛ ዴ ቺኴንቶ›› (የአምስት መቶዎቹ አደባባይ) ይባላል፡፡ በዶጋሊ ጦርነት ለተደመሰሱት 500 የጣሊያን ወታደሮች መታሰቢያ የተሰጠ አደባባይ ነው፡፡

 ከአደባባዩ አቅራቢያ ለወታደሮቹ የቆመ ሐውልት ይታያል፡፡ ሐውልቱን ተጠጋሁት፣ ከአንድ መቶ ሠላሳ ዓመታት በፊት በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን ኢትዮጵያ በግዛቷ ከምፅዋ ወደብ አቅራቢያ በምትገኘው ዶጋሊ (በአካባቢው አጠራር ተድዓሊ ይባላል) ከጣሊያን ጋር ያደረገችው ጦርነት በጠቅላይ አዝማቹ ራስ አሉላ አማካይነት የተቀዳጀችው ድልና ለመጀመርያ ጊዜ የነጭ ሠራዊት በጥቁር ድል የተመታበት፣ 500 ወታደሮች የተደመሰሱበት ታሪክ ታወሰኝ፡፡ በሐውልቱ እምብርት ላይ በጣሊያንኛ ‹‹AGLI EROL DI DOGALI›› ተጽፎበታል፡፡ ለዶጋሊ ጀግኖች እንደማለት ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? አልኩኝ፡፡ በዶጋሊ ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩት፣ ድሉን የጨበጡት፣ ራስ አሉላና ሠራዊታቸውም አይደሉ እንዴ ብዬ ማሰላሰሉን ያዝኩ፡፡   

ጣሊያኖቹ ወታደሮቻቸው ሽንፈትን ቢጨልጡም ማክበራቸውን ግን አልተዉም፡፡ ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም. በያኔዋ የኢትዮጵያ፣ በአሁኗ የኤርትራ ምድር በዶጋሊ የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት መቋጨቱን ተከትሎ ለጀግኖቹ መታሰቢያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በምፅዋ ከተማ ከቆመው (ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ያፈረሰው)፣ እንዲሁም በደርግ ዘመን የዶጋሊ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ጦርነቱ በተካሄደበት ሥፍራ ‹‹የቀይ ኮከብ›› ሐውልት አቁመው ነበር፡፡ የኤርትራ ነፃነትን ተከትሎ ሁሉም መታሰቢያዎች ከሥፍራቸው ተነቅለዋል፡፡

የዶጋሊን ጨምሮ በ19ኛው ምዕት ዓመት በአፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመን በጉንደትና በጉራዕ ከባዕዳን ወራሪዎች ጋር በተደረጉት ጦርነቶች የኢትዮጵያ ድሎችና የዘመኑን ባለቀይ ቢጫና አረንጓዴ ሰንደቅ ዓላማ የሚዘክር መታሰቢያ ዕውን የሚሆነው መቼ ይሆን?

የሆኖ ሆኖ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. የዶጋሊ ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀበት 132ኛ ዓመትን ያሰብንበት ነበር፡፡ ስለዕለቱ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበርን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት የተሰማ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የዕለቱን ታሪካዊ ዳራ እዚህ ላይ ማንሳት ወደድን፡፡

የተድዓሊ - ዶጋሊ ድል 132ኛ ዓመት

ጣሊያን አንድነትና ውህደቷን እ.ኤ.አ. በ1861 ከመሠረተች በኋላ የቅኝ ግዛትን ለማስፋትና ኃያል አገር ለመሆን የቀይ ባሕርን ዳርቻና ምፅዋን ከያዘች በኋላ ወደ ሰሐጢ ከተማ ዘለቀች፡፡ መቀመጫቸውን አስመራ የሆነው የምድሪ ባሕሪ ገዥ ራስ አሉላ በምዕራብ ኢትዮጵያ የደርቡሾች እንቅስቃሴን ለመግታት በከሰላው (ገለባት) ጦርነት እያሉ ጣሊያኖች የዊዓንና የዙላን ሠፈሮች መያዛቸውን፣ በሰሐጢም መመሸጋቸውን እንደሰሙ ወደ አስመራ በመመለስ ለጄኔራል ካርሎ ዢኒም ደብዳቤ ጻፉለት፡፡ የታሪክ ጸሐፊው አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ‹‹አፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚባለው መጽሐፋቸው ደብዳቤውንና የጦርነት ውሉውን ዘግበውታል፡፡ ራስ አሉላ ጄኔራሉን ያስጠነቀቁበት ደብዳቤ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹እንግዲህ ወዳጅ ከሆንን ጦር ሠራዊትዎን ከዊዓ ያስነሱ፣ ነጋዴውም በአድገዴ (ሐባብ) በኩል መሆኑ ቀርቶ ለመሸጥም ለመግዛትም ከጊንዳዕ በኩል ይመላለስ፣ ዊዓ ያለው ጦርዎ እስከ ጥር 13 ቀን ድረስ ይልቀቅ፡፡ ዙላ ያለው ወታደርዎ ከአንድ ወር በኋላ ይውጡ፡፡ ወዳጅነት ከፈለጉ ይህ መፈጸም አለበት፡፡ ያለዚያ ግን ወዳጅነት መቅረቱን ይወቁት፤›› በማለት ጥር 5 ቀን 1879 ዓ.ም. ለጻፉት ደብዳቤ ቀና ምላሽ አላገኙም፡፡

 ‹‹ስለዚህ ኮሎኒል ክሪስቶፎሪስ ትዕዛዙ ከሰዓት በላይ እንደ ደረሰው ሌሊቱ ጭምር ሲዘጋጅ አድሮ ሲነጋ 540 የነጭ፣ ሃምሳ የአገር ተወላጅ ወታደር ሁሉም በደንብ የታጠቁ አሥር የሚሆኑ መድፎች ከምንኩሎ ተነስተው ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት ተኩል ዶጋሊ አጠገብ ሲደርሱ፣ ራስ አሉላ ወታደሮቻቸውን ግራና ቀኝ ሥፍራ ሥፍራ አስይዘው ይጠባበቁ ነበር፡፡ ጣሊያኖቹ ግን፣ ሁል ጊዜ የኢትዮጵያን ጦር በመናቅ መንገድ ለመንገድ ሲመጡ፣ ‹‹ራስ አሉላ እነርሱን በጥሩ አይተው ወደ ጊንዳ እንደሚሸሹ የጦር መኮንኖቹ አምነው ይኸንኑ በጉዞ ላይ ይጨዋወቱ ነበር›› ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የራስ አሉላን አመጣጥና የጦራቸውን ብዛት የሰሙ አንዳንድ በጣልያኖቹ ውስጥ የተቀጠሩ ፓሽ ባዙቆች ከጉዞ ላይ ሰረቅ እያሉ ወደ ጫካ በመግባት የጠፉ ቢኖሩም፣ በቅርብ የመጣውም መቀደም ብሎ የነበረውም የነጭ ወታደር ወደ ፊት ሲገሰግስ ሳለ ሳያስበው ከራስ አሉላ ጦር የእሩምታ ተኩስ ላይ ወደቀ፡፡

‹‹ኮሎኔል ክሪስቶፎሪስ ወታደሩ በቶሎ የመከላከያ ሥፍራ እየፈለገ በመያዝ እንዲመክት ለየሹማምንቱ ትዕዛዝ ወዲያው ሰጥቶ ወታደር ከወታደር እየተታኮሰ ውጊያው በተጋጋለበት ሰዓት ዕርዳታ እንዲደርስለት ወደ ካርሎ ዤኒ በጥድፊያ መላክተኛ ላከ፡፡ ዳሩ ግን፣ ተኩሱ በሚጋጋልበት ሰዓት ኢትዮጵያውያኑ እያደር ዙሪያውን እንደ ቀለበት ከበው ጠላቶቻቸውን መውጫ መግቢያ አሳጧቸው፡፡ ጣልያኖቹም በያለበት መከበባቸውን ሲያውቁት ጠንክረው ይዋጉ ጀመር፡፡ ነገር ግን፣ ከያዙት የጦር መሣሪያ ግማሹ በተለይ መድፉና መትረየሱ ከግብፆች በውርስ ይሁን በግዥ ያገኙት አሮጌ መሣሪያ ስለነበረ በመካከሉ አልሠራ እያለ አስቸገረ፡፡ ጥይቱም አለቀባቸው፡፡ ወደ ዤኒ የተላከው መልዕክተኛ ጣልያኖቹ አደገኛ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አስረድቶ በአራትና በአምስት ሰዓት መካከል ደርሶ ዕርዳታው ተዘጋጅቶ ከመላኩ በፊት ራስ አሉላና ወታደሮቻቸው ከወዲህ የድል አድራጊነት ሥራቸውን አከናውነው ጨረሱ፡፡ ውጊያውም ያለቀው በመጨረሻ ላይ በጨበጣ ጦርነት ነበር፡፡

‹‹በውጊያው ላይ ዋናው አዝማች ኮሎኔል ቶማስ ደ ክሪስቶፎሪስ ከ22 የጦር መኮንኖቹ ጋር በጦሩ ሜዳ ላይ እየተዋጋ ወደቀ፡፡ ከመሞቱም በፊት ሻምላውን በቀኝ እጁ ይዞ፣ ‹‹ጣሊያን ህያው ትሁን ጣልያን ህያው ትሁን፣ ወደ ፊት ቅደም፣ በለው፤›› እያለ በመጮኸ የጀግንነት ሙያ ለማሳየት ሞክሮ እንደነበር በቁስለኞቹ አንደበት የተነገረው፣ በኋለኛው ጊዜ በወገኖቹ በጣልያኖቹ ዘንድ የመደነቅ ታሪክ አግኝቷል፡፡ ያልተናገረውንም በመጨማመር ቆስሎ ከመውደቁና ሕይወቱ ከመጥፋቱ በፊት በሕይወት ላሉት 12 ወታደሮች በውጊያ ወድቀው ለተረፈረፉት ወታደሮች ‹‹የብረት ሰላምታ ስጡ›› የሚል ቃል ወርውሯል እየተባለ በየጊዜው ሲጻፍና ሲታመን የቆየውን የዛሬው ተመራማሪ ጸሐፊ አንጀሎ ደልቦካ የፈጠራ ወሬ አድርጎታል፡፡

‹‹በውጊያው ላይ ራሱ ኮሎኔል ክርስቶፎሪስ ከ22 የጦር መኮንኖች ጋር ሲወድቅ 418 ወታደሮች ሞተዋል፡፡ ‹‹ከነዚህም ውስጥ ቆስለው ወደ ምፅዋ እንደርሳለን ብለው በሌሊት ጉዞ እያቃሰቱ በመንገድ የሞቱ ምፅዋ ደርሰው ነፍሳቸውን ያተረፉም ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹም ምፅዋ ሆስፒታል እንደተገኙ ለየዘመዶቻቸው በጻፉት ላይ፣ ሹማምንቶቻችን ያለምንም ጥናትና ድርጅት ከጦርነት ላይ አጋፍጠውን ‘ጣልያን ህያው ትሁን ወደ ፊት ግፋ’ ብለው በመጨረሻ እኛን ጥለውን እነሱ ሸሹ የሚል ሮሮ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ከተረፉት የጦር መኮንኖች መካከል ካፒቱን ሚሸሊኒ የሚባለው የመድፈኛ የጦር መኮንን እንደ ቆሰለ ሳይሞት የሞተ በመምሰል ከሬሳ ጋር ድምፁን አጥፍቶ ውሎ ሲጨልምና ፀጥ ሲል ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በሌሊት የችግር ጉዞ ተጉዞ ምጥዋ ከገባ በኋላ፣ እንደ ቀሩት ቁስለኞች በራስ ሙዱር ሆስፒታል ታክሞ ከዳነ በኋላ ወደ አገሩ በሕይወት ለመመለስ ችሏል፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደገለጹት በኢትዮጵያ፣ የጦርነት ዝክረ ነገር በመዝገብ ይዞ ለትውልድ ማቆየት እምብዛም ስላልተለመደ፣ በዶጋሊ ጦርነት ከኢትዮጵያ ወገን የሞቱትንም፣ የቆሰሉትንም የሹማምንቱንም፣ የወታደሩንም ቁጥር በትክክል አይታወቅም፡፡ ደልቦካ  በመጽሐፉ ከራስ አሉላ ወገን የሞተውም የቆሰለውም እስከ አንድ ሺሕ መድረሱን ያመለክታል፡፡

ስለዚህ ጄኔራል ካርሎ ዤኒ የራስ አሉላን ከነጦራቸው ወደ አሥመራ መመለሳቸውን ከሰላዮቹ ካረጋገጠ በኋላ ድንጋጤው በርዶ ወደ ዶጋሊ ሰው ልኮ የሞቱትን የወገኖቹን ሬሳ በሰላምና በፀጥታ ያስለቅም ጀመር፡፡ ፌሪኒ ኦታቪዬ የሚባለው የሐምሳ አለቃ ወደ ጣሊያን አገር ለወንድሙ ለሉዊጂ ከምጥዋ የጻፈውን ደብዳቤ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት የሚባለው መጽሐፍ እንዲህ አስፍሮታል፡፡   

‹‹ውድ ወንድሜ ከጦርነቱ ወዲህ በሦስተኛው ቀን ባለቆቼ ትዕዛዝ ጦርነቱ ወደ ተደረገበት ቦታ የጀግናውን ያገራችንን ተወላጅ የሌተና ኮሎኔል ቶማሶ ደክሪስቶፎሪስንና ከእርሱ ጋር የወደቁትን ሬሳ ለማምጣት ሄድን… እንዴት ያለ አስቀያሚ ትርዒት አለው፡፡ ሦስት ጉብታዎች ራቁታቸውን በሆኑና ገና በሚደሙ ሬሳዎች ተሸፍነዋል፡፡ የእነዚህም ሰውነታቸው ከብዙ ቦታ ተቆራርጧል፡፡ አንዳንዶቹም የተሰለቡ አሉ፡፡ ጅብና አሞራ ምንም ያህል አልጎዳቸውም፡፡ ውሎ በማደር ሬሳዎቹ ጠቋቁረዋል… ከጥቂት ፍለጋ በኋላ የኮሎኔል ክሪስቶፎሪስን ሬሳ አገኘንና በድንኳን ጨርቅ ጠቅልለን በግመል አጉዘን ወደ ምንኩሎ ስንደርስ የክብር አቀባበል ተደርጎለት፣ በካቶሊኮቹ መቃብር ተቀበረ…፡፡››  

በዶጋሊው ጦርነት የራስ አሉላ የጉብዝና ወሬ በመላው ኢትዮጵያ ተሠራጭቷል፡፡ በጣሊያኖቹም በኩል …. የዐፄ ዮሐንስ መኰንን የበለጡ የታወቁና በየመጽሐፉ የሚወሱ ናቸው፡፡ ከዶጋሊ ጦርነት ወዲህ በየጊዜው እንደዚህ እየተባለ ተገጥሞላቸዋል፡፡

መብቱን ዮሐንስ ላሉላ ቢሰጠው

እንደ ቀትር እሳት ቱርክን ገላመጠው

ጣልያንም ወደቀ እያንቀጠቀጠው

አጭዶና ከምሮ እንደ ገብስ አሰጣው

      አባ ነጋ አሉላ ካሥመራ ቢነሣ

      እንዳንበሳ ሆኖ እሳት እያገሣ

      የችግር ምሥጋና ባይወሳ

      ቢቸግረው ጣልያን አለ ፎርሳ ፎርሳ

ጣልያን በሀገርህ አልሰማህም ወሬ

የበዝብዝ አሽከሮች እነሞት አይፈሬ

ዘለው ጉብ ይላሉ እንደ ጐፈር አውሬ

      አባ ነጋ አሉላ የደጋ ላይ ኮሶ

      በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተቀምሶ

ጣልያን ሰሐጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ

በብረት ምጣዱ በሰሐጢ አደጋ

አንገርግቦ ቆላው አሉላ አባ ነጋ

      ተው ተመከር ጣልያን ይሻላል ምክር

      ሰሐጢ ላይ ሆነህ መሬት ብትቆፍር

      ኋላ ይሆንልሃል ላንተው መቃብር

      ይቺ አገር ኢትዮጵያ የበዝብዝ አገር

      ምንም አትቃጣ እንዳራስ ነብር፡፡

ራስ አሉላ አባ ነጋ ሲገለጹ

በተምቤን (ትግራይ) በ1819 ዓ.ም. የተወለዱት ራስ አሉላ እንግዳ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጄኔራል ሆነው በጉንደት፣ በጉራዕ፣ ኩፊት፣ ገለባት፣ ዶጋሊና ዓድዋ ዐውደ ውጊያዎች ተካፍለዋል፡፡

ዶ/ር አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ፣ ‹‹ዘለዓለም የማይረሳው ከጥንት እስከ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ›› በሚለው ድርሳናቸው ከዳሰሷቸው ጀግኖች አንዱ ራስ አሉላ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በ1950ዎቹ በጣሊያን ሲጀመር ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ጥናት ያቀረቡት አባ ገብረ ኢየሱስ ስለራስ አሉላ ገጽታ ከልጅነት ትውስታቸው ጋር አያይዘው ተርከዋል፡፡

በአፈ ታሪክ እንደሚባለው ራስ አሉላ በቤተ መንግሥት ውስጥ አገልጋይ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን በያይነቱ ሽልማት ባጌጡ መሰቦች ግብር ወደ እንግዳ ቤት ሲጓዝ አዩና ‹‹ለማን ነው›› ብለው ሲጠይቁ ከተሸካሚዎች አንድዋ እየቀለደች ‹‹ላንተ ነው›› አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም መልሰው ‹‹እግዚአብሔር ያለው እንደሆነስ ማን ያውቃል ቢሆንም ይቆይ እንጂ፤ ይቀር መሰለሽን›› አሉዋት ይባላል፡፡ ተረቱ ለማናቸውም ኢትዮጵያዊ ሰው ወደ ግል ሙያ የሚያነቃቃ ነውና፤ ሁልጊዜ ይደጋገማል፡፡

በውነቱም እግዚአብሔር በሰጣቸው ዕድል ከኢትዮጵያውያን ጀግኖች አንደኛ ሆኑ፡፡ የአፍሪካ አቀማመጥን ለሚመለከት ሰው፣ በስተምሥራቅ አንድ ያውራሪስ አፍንጫ የመሰለውን የመሬት ቅርፅ ይገጥመዋል፡፡ እሱ ያፍሪቃ ቀንድ ይባላል፡፡ በሐድራሙት አገር ፊት ለፊት በሚገኘው ባሕር ላይ ባለው መሬት በቀንዱ ጫፍ በአሉላ የተሰየመ ከተማ አለ፡፡ በመጀመሪያ ጊዜያችን የጂዮግራፊ ትምህርትን ስናጠና የከተማዋ ስምና የራስ አሉላ ስም አውቀው ጠይቀው ያዛመዱዋቸው ሆኖ ይታየን ነበረ፡፡ ምክንያቱም የራስ አሉላ ዓላማ የኢትዮጵያ ድንበር በባሕረ ኤርትራ በሞላው ተዘርግቶ እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የሚገኘው በባሕርና በየብስ ያለው ስፋት መሆኑን ለዓለም ማስታወቅ ስለነበረ ነው፡፡ በስተሰሜንና በምሥራቅ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መሬት ራስ አሉላ እንደ አንድ የብረት ግንብ ተገምተው ይከላከሉለት ነበር፡፡

በሕፃንነቴ የሰማሁትን ነገር በማስታወስ ላይ ነኝ ይላሉ አባ ገብረ ኢየሱስ፡፡ ሦስት የውጭ አገር ሰዎች ወደ አንድ የኢትዮጵያ ግዛት ሲሄዱ በሐማሴን በኩል ማለፍ ነበረባቸውና ከራስ አሉላ ፈቃድ ማግኘት ሲፈልጉ በራስ አሉላ ፊት ቀርበው እርስ በርሳቸው ‹‹ራስ አሉላ እንደ አንድ ትልቅ ጋራ ይመስሉን ነበር እንጂ እንዲሁ ትንሽ ናቸውን›› ሲባባሉ ሰሙዋቸውና፤ ‹‹ከምድር በላይ ያለኝ ቁመቴ እንደዚህ ቢሆን ቅሉ ከግሬ በታች በምድሬ ውስጥ ያለኝ ሥር ጥልቅነቱ እኒህን ጋራዎች የሚያክል መሆኑን አወቅ በልና ንገራቸው›› ሲሉ ካስተርጓሚ ጋር የተነጋገሩትን ነው፡፡

ራስ አሉላ በከሰላም በምፅዋም፣ በምዕራብም በምሥራቅ፣ የኢትዮጵያ ድንበር በጀግንነት ጠብቀዋል፡፡ በከሰላ ወገን በኩፊት ላይ ድርቦሾቹን ድል ነስተዋል፡፡

‹‹ኧረ ጉዱ በዛ ጉዱ በዛ፣

በዠልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ›› ብሎ አንድ ኢትዮጵያዊ ዘመረ፡፡ የዘመረበትን ጠላት ለመውጋት ደግሞ ወደ ሰሐጢ አመሩ፡፡ የምፅዋና የዙላ ወደቦችና የዊዐ የሰሐጢ መንደሮች በጣልያን እጅ መያዛቸውን በማስማት አዘኑ፡፡ በጦርም ሊቃወሟቸው እንዳስፈለገ ተረዱና ጥር ወር 1879 ዓ.ም. ራስ አሉላ ወደ ጦር ግንባር አመሩ፡፡

ሰሐጢ የነበረውን የጣሊያን ጦር ጭፍራን ከበውት ሳለ ለእርዳታው ከምፅዋ ይጓዝ የነበረውን የአምስት መቶ ወታደሮች ጭፍራ ተዳዕሊ (ዶጋሊ) በተባለው ኮረብታ ላይ ከበው ጨረሱት፡፡ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደሚሉት ጦርነቱ የ15 ደቂቃዎች ብቻ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ወታደር በጋለ ጀግንነቱ ሲገጥም ጠላቱን እንዴት በመሰለ አኳኋን እንደሚሻማው አስረዱት፡፡ ይህን በመሰለ ድል አድራጊነት ራስ አሉላ የፈለጉትን አገኙ፣ ጄኔራል ጄይ ይባል የነበረው የጣሊያን ጦር ሠራዊት አዛዥ ሰሐጢና ዊዐን ለቀቀ፡፡ በምፅዋ ወደብ በኩል መሣሪያዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ ተላለፉ፡፡ ራስ አሉላ፣ በምዕራብም በከሰላ፣ በምሥራቅም በምፅዋ ወገን የኢትዮጵያን ጥንታውያን ድንበሮች አስከበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ጀግንነት ተወዳዳሪ እንደሌለውም ለዓለም አስረዱ፡፡

የ19ኛው ምዕት ዓመት ኢትዮጵያዊ ጀግና በአንዳንዶች ዘንድ ‹‹አፍሪካዊ ጄኔራል›› የሚባሉት ራስ አሉላ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የካቲት 8 ቀን 1889 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሙሾ አውራጇ እንዲህ አንጎራጎረች፡፡

‹‹ከም መንዳላይ ተመን ተወርዋሪ

ከም ኣንበጣ አብ ግድም ሰፋሪ

ከም ኣንበሳ ብቅልጽም ሰባሪ

ሰብኣይኪ ከሰላ ውሽማ ባህሪ

ኣባ ነጋውንዶ ኣግኒኻ ቀታሊ

ለከ ሞትስ ዘይቋሪ ዜጽንሖ ፈጣሪ››

አባ ገብረ ኢየሱስ ወደ አማርኛ እንዲህ መለሱት፡፡

እንደ መንደላይ እባብ የበረሃ እባብ እየተወረወረ

እንደአንበጣ በጋራ ላይ ይሰፍር የነበረ

እንደአንበሳ በቅልጥሙ ጠላትን እየሰባበረ

ከሰላ ላይ ውሎ በምፅዋ እያደረ

የኢትዮጵያ ድንበሮች በሁሉ ያስከበረ

አባ ነጋ ደግሞ ሙቶ ቀረ፡፡  ራስ አሉላ ከታላቅ መኳንንቶች የተወለዱ አይደሉም፡፡ በግብራቸው ሙያ ራሳቸውን ለታሪክ የወለዱ ናቸው ይሏቸዋል፡፡