Skip to main content
x
የኢራናውያኑ አብዮት ሲታወስ
ኢራናውያን በየዓመቱ ፌብሩዋሪ 11 የኢራን አብዮት ድል የመታበትን ቀን ያከብራሉ

የኢራናውያኑ አብዮት ሲታወስ

እ.ኤ.አ. 1979 ለኢራናውያን ልዩ ዓመት እንደነበር ይነገራል፡፡ የኢራናውያን አብዮት የተቀጣጠለበትና ድል የተቀዳጀበት ይኸው ዓመት፣ ኢራን አሁን ላላት ጥንካሬ  መሠረት የተጣለበትም ወቅት ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከትናንት በስቲያ 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ኢራናውያን 40ኛ ዓመት የአብዮት በዓላቸውን በመላ አገሪቱ በመውጣት ያከበሩ ሲሆን፣ ዕለቱም ዝናባማ እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የእስልምና አስተምርሆን በመከተል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥንካሬን መፍጠር ዓላማ አድርጎ ከ40 ዓመት በፊት የተቀጣጠለው አብዮት መሳካትም ዛሬ ላይ አገሪቱ ከእስራኤል በተለይም ከአሜሪካ የሚገጥማትን ፈተና ለመጋፈጥ ጥንካሬን ፈጥሮለታል፡፡ በተለይም አገሪቱ የኑክሌር ማብላያ ግንባታዋን እንድታጠናክር፣ ለአሜሪካና ለአጋሮቿ አልንበረከክም የሚል አቋም እንድታራምድም ወቅቱ በሕዝቡ መሀል የፈጠረው የአንድነት መንፈስ ቀላል አልነበረም፡፡

40ኛው ዓመት የአብዮት ቀን ሲከበር የተንፀባረቀውም፣ ኢራናውያኑ ያላቸውን አንድነት እንደሚያጠናክሩና የእስልምና አስተምርሆን በመከተል ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን አጠናክረው አሜሪካ የጣለችባቸውን ገደብ ለማዳከም እንደሚተጉ ነው፡፡

በቴህራን አዛዲ (የነፃነት) አደባባይ ለተሰባሰቡ ኢራናውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ፣ አሜሪካ ኢራንን ከሌሎች አገሮች ለማግለል የምታደርገውን ጥረት አጣጥለውታል፡፡ የኢራንን እስላማዊ ሪፐብሊክም እንደማያዳክመው ተናግረዋል፡፡

‹‹በኢራን በሙሉ ሕዝቡ ወጥቶ አብዮቱን ማክበሩ ጠላቶች መጥፎ ዓላማቸውን ለማሳካት እንደማይችሉ ማሳያ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ሩሃኒ፣ አገሪቷ ከውጭ ኃይሎች ከሚቃጣባት ማስፈራሪያ ራሷን ለመጠበቅ የኑክሌር ፕሮግራሟን ታስቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረትም የማንንም ፈቃድ እንደማትጠይቅና ፕሮግራሟንም እንምትገፋበት አክለዋል፡፡

briefs
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ

በየዓመቱ ፌብሩዋሪ 11 ቀን የሚከበረውን የኢራን አብዮት፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የሚያከብረው ሲሆን፣ ይህም አብዮቱ በሕዝቡ ድጋፍ እንዳለው ማሳያ ሆኗል፡፡ ለ14 ዓመታት ያህል በቱርክ፣ በኢራቅና በፈረንሣይ በስደት የቆዩት የኢራን የበላይ ጠባቂ አያቶላህ ኮሚኒ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 1 ቀን 1979 ወደ ኢራን የተመለሱበትን ቀን ለማወደስም የሚከበር ነው፡፡

ከትናንት በስቲያ በተከበረው የኢራን አብዮት በዓል የቀጣናው ተቀናቃኞች ኢራንና እስራኤል የቃላት ጦርነትም ተወራውረውበታል፡፡ አገሮቹ አንዱ አንዱን እንደሚያጠፋ የተዛዛቱበትም ነበር፡፡ የኢራኑ እስልምና ሪቮሊውሽነሪ ጋርድ ኮርፕስ ኮማንደር፣ አሜሪካ ኢራንን አጠቃለሁ ካለች በምላሹ የእስራኤልን ቴልአቪቭና ሃፋይ ከተሞች እንደሚያወድሙ አሳውቀዋል፡፡

‹‹አሜሪካ በእኛ ላይ ጥቃት ከፈጸመች ቴሌአቪቭንና ሃፋይን እናጠፋለን፤›› ላሉት ጄኔራል ያዶላህ ጃቫኒ ፈጣን ምላሽ የሰጡት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ፤ ‹‹ኢራን እስራኤልን ከነካች ለኢራናውያን ይህ የመጨረሻው የአብዮት ክብረ በዓል ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከኢራን የሚሰነዘርን ዛቻ ጆሮ ዳባ ልበስ ባልለውም በዛቻው አልደናበርም፤›› ያሉት ናታንያሁ፣ ኢራን በእስራኤል ከተሞች ላይ ጥፋት ከፈጸመች የኢራን አብዮት መቼም አይከበርም ብለዋል፡፡

በመቶ ሺዎች በአንዳንድ ከተሞች እስከ ሚሊዮን የሚደርሱ ኢራናውያን አብዮቱን ለማክበር ሲወጡ ‹‹ለአሜሪካ ሞት፣ ለእስራኤል ሞት›› እያሉ ይፎክሩ እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

አገሮች ከኢራን ጋር የገቡትን የኑክሌር ውል ያፈረሱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከ40 ዓመታት በፊት የተካሄደውን የኢራን አብዮት ለአገሪቱ ውድቀት ነበር ብለውታል፡፡

‹‹40 ዓመታት ሙስና፣ 40 ዓመታት ረገጣ፣ 40 ዓመታት ሽብር፣ 40 የውድቀት ዓመታት፤›› ብለው በእንግሊዝኛና በፋርስ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውም ተዘግቧል፡፡ 

ትራምፕ ይህን ይበሉ እንጂ የኢራን አብዮት ለኢራናውያኑ ከአምባገነን መንግሥት የተላቀቁበት፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡበትና ራስን በራስ ለማስተዳደር መሠረት የጣሉበት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ሩሃኒ ተናግረዋል፡፡

briefs
ፕሬዚዳንት ሃሰን ሩሃኒ

ኢራን በአሜሪካና በእስራኤል የሚቀነባበርን ሸፍጥ ለመቆጣጠር መቻሏንም በማውሳት፣ አገሪቷ የራሷን መንግሥታዊ ሥርዓት መዘርጋቷን ገልጸዋል፡፡

ከኢራን አብዮት በኋላ ቁልፍ ቦታ የተሰጠው የኢራን ኑክሌር ማብላያ ጣቢያ ግንባታ፣ አሁንም ድረስ ኢራንን ከሌሎች አገሮች የሚያወዛግባት አጀንዳ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ኢራናውያን በተደጋጋሚ ሲቃወሙ ይሰማል፡፡

በውጭ ጉዳይ የተወጠረችው ኢራን አሜሪካ ከኑክሌር ስምምነቱ ራሷን ማግለሏን ስትቃወም የነበረ ሲሆን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጀርመን ደግሞ የኑክሌር ስምምነቱ እንዳይፈርስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ሆኖም 40ኛው የኢራን አብዮት ሲከበር እንደ አሜሪካ ሁሉ በአውሮፓውያኑም ላይ እምነት ማሳደር እንደማይገባ የኢራን የበላይ ጠባቂ አያቶላህ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ደግሞ አሜሪካ በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶው የጠራችውና ‹‹የወደፊቱ የመካለኛው ምሥራቅ ሰላምና ደኅንነት›› ጉባዔ ይካሄዳል፡፡ በጉባዔው የእስራኤሉ ናታንሁ፣ የኢራን ባላንጣ ሳዑዲ ዓረቢያና አጋሮቿ ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

 (ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)