Skip to main content
x
አቅም ለሌላቸው ከተሞች የጤና አገልግሎት ለማስፋፋት የቆመው

አቅም ለሌላቸው ከተሞች የጤና አገልግሎት ለማስፋፋት የቆመው

የሺጥላ ኃይሉ (ዶ/ር) የአምሪፍ ሔልዝ አፍሪካ ምክትል ካንትሪ ዳይሬክተርና የፕሮግራም ኃላፊ ናቸው፡፡ የተወለዱት፣ የመጀመርያና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን በጎንደር በሕክምና ሳይንስ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ወደ አሜሪካ አቅንተው እዛ በሚገኘው አትላስ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ በሔልዝ ሰርቪስ ማኔጅመንት ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የደም ባንክ ምክትል ዳይሬክተር፣ በዚሁ ባንክ የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአምሪፍ ሔልዝ አፍሪካ ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምሪፍ የትና መቼ እንደተቋቋመ፣ ማን እንዳቋቋመውና አምሪፍ ቃሉ ምን እንደሆነ ቢገልጹልን?

ዶ/ር የሺጥላ፡- ‹‹አምሪፍ›› የእንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃል ሲሆን፣ በዝርዝር ሲታይም ‹‹አፍሪካ ሜዲካል ሪሰርች ፋውንዴሽን›› ማለት ነው፡፡ የተመሠረተውም ‹‹ላስቲንግ ሔልዝ ቼንጅ ኢን አፍሪካ›› የሚል ራዕይ አንግቦ በ1949 ዓ.ም. ናይሮቢ አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ያቋቋሙት እንግሊዛዊ፣ አውስትራሊያዊና ኖርዲካዊ የሆኑ ሦስት የፕላስቲክ ሰርጂን ሐኪሞች ናቸው፡፡ የአገልግሎት ትኩረቱም በምሥራቅ አፍሪካ (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ) ውስጥ ኋላቀር ወይም መገናኛን ጨምሮ ምንም ዓይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎትና የሕክምና ተደራሽ በሌሉባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ በዚህም አገልግሎት በወባ፣ በቲቢ፣ በእሳት ቃጠሎ ለተጎዱ ሰዎች የሕይወት አድንና የፕላስቲክ ሰርጀሪ ሥራ አከናውነዋል፡፡ በአነስተኛ አውሮፕላን ከፍ ብሎ በተጠቀሱት አገሮች እየተዘዋወሩ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ይህን መሰል አገልግሎት ከሰጡት ሐኪሞች መካከል ሁለቱ በእንግሊዝ ንግሥት የ‹‹ሰር›› ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል፡፡ መሥራቾቹ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ያቋቋሙት ድርጅት ግን 62 ዓመት እንደሞላውና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰባት አገሮች ካንትሪ ቢሮዎች አሉት፡፡ ከዚህም ሌላ በ35 የአፍሪካ አገሮች የተለያዩ የአውትሪችና የሥልጠና ፕሮግራሞች፣ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- አምሪፍ ሔልዝ አፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼ ተቋቋመ? በየትኞቹ አካባቢዎች ነው በይበልጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው?

ዶ/ር የሺጥላ፡- አምሪፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመው በ1994 ዓ.ም. ሲሆን አብዛኞቹ ፕሮግራሞቻችን ያሉት በታዳጊ ክልሎች ማለትም በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ነው፡፡ በተጨማሪም ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ በመሀል ከተሞችና በአብዛኛው አቅም በሌላቸው ከተሞች (ሳለምስ ኤርያ) ውስጥም እንሠራለን፡፡ በከተሞች ካተኮርንባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ቀጨኔ፣ ጉለሌ፣ አዲስ ከተማ መሀል በውኃና ሳኒቴሽን የጤና የኤችአይቪ ኤድስ ላይ ትኩረት ያደረገ የሕክምና ሥራዎች እንሠራለን፡፡ ይህ ዓይነትም ሥራ የሚሠራው የጤና አገልግሎት ለማግኘት ግንዛቤም ሆነ የገንዘብ አቅምም የሌላቸውን ማኅበረሰቦች በመርዳት ነው፡፡ ለዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ሐዋሳ በተካሄደው የጤና ሚኒስቴር ዓመታዊ ግምገማ ላይ የኢኪዩቲ አምባሳደር በማለት አንድ ትልቅ ፓናል እንድንመራ ተደርጓል፡፡ በተረፈ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመቋቋሙ በፊት በ1960ዎቹ ዓመታት በአውሮፕላን እየተመላለሱ መቐለ፣ ጎንደርና ወሎ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ አምሪፍ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስፔን፣ በጣሊያን፣ በኖርዲክ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና ጀርመን ቢሮዎች አሉት፡፡ የቢሮዎቹ ዋና ተግባር ፈንድ ሞቢላይዝ ማድረግ ሲሆን እያንዳንዱም ቢሮ እስከ 20 የሚጠጉ ፕሮግራም ዴቨሎፕመንት ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች አሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የሰው ኃይልን ከማብቃት ጋር የተያያዘው ፕሮግራማችሁን ቢያብራሩልን?

ዶ/ር የሺጥላ፡- የሰው ኃይልን ከማብቃት ጋር የተያያዘ ሥራ እናከናውናለን፡፡ ለጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ሥልጠና መስጠትና አዋላጅ ነርሶችን ለሦስት ዓመት ያህል አሠልጥኖ በማስመረቅ በየአካባቢያቸው ተመልሰው ወላዶችን እንዲያገለግሉ እያደረግን ነው፡፡ መንግሥት ካሠለጠናቸው 40,000 የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች መካከል የተወሰኑትን ያሠለጠነው አምሪፍ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለደብረ ብርሃን፣ ለአርባ ምንጭ፣ ለነገሌ፣ ለጅግጅጋና ለጋምቤላ ጤና ሳይንስ ኮሌጆች የፋይናንስ እገዛ፣ የትምህርት መገልገያዎችን በማሟላት በተለይም የትምህርቱን ጥራት ለመጠበቅ እንዲቻል ለመምህራኑ የሌደርሺፕ ማኔጅመንትና ገቨርነንስ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ የካሪኩለም ክለሳ በሚደረግበትም ጊዜ ተገቢውን እገዛና ድጋፍ አበርክተናል፡፡ በጤና ተደራሽነት ላይ ከምንሠራቸው ፕሮግራሞች መካከል ማኅበራዊ ንቅናቄ (ሶሻል ሞብላይዜሽን) በመፍጠር የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲዳብር የማድረግ ሥራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ግንዛቤ ማጎልበት ያስፈለገበት ምክንያት ኅብረተሰቡ በየአቅራቢያው በሚገኙ የጤና ተቋማት እንዲገለገሉባቸው ወይም እንዲጠቀሙባቸው ለማድረግ እንዲያስችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አምሪፍ የጤና ሥርዓቱን ከማስፋፋት አኳያ ምን እንደሠራ ቢገልጹልን?

ዶ/ር የሺጥላ፡- አንዱና ትልቁ የምንሠራው ሥራ የመንግሥት አቅጣጫ የሆነውን የእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት ለእናቶች፣ ለጨቅላና ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የተለያዩ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያም እንሠራለን፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን በብዙ የጤና ተቋማት ውስጥ ‹‹ዩዝ ፍሬንድሊ ሰርቪስ›› የሚል ማዕከል አቋቁመናል፡፡ በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን ሙሉ ለሙሉ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጋሞጎፋ፣ ሰገን፣ ወላይታ ዞኖች በድምሩ እስከ 70 ማዕከል ለማቋቋም በቅተናል፡፡ ከዚህም ሌላ በወላይታ በጂንካና ቱርሚ አካባቢዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ጅማና ለቀምት፣ በአማራ ክልል ባህርዳር ዙሪያ፣ ደብረ ብርሃን ቀወት፣ ሸዋሮቢት የቤተሰብ ዕቅድና የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት ከምንሰጥባቸው አካባቢዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሌላው የአምሪፍ ትልቁ ሥራው የውኃ ሃይጅንና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ነው፡፡ ይህም ፕሮግራም በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በደቡብ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ውስጥ እየተከናወነ ነው፡፡ እስከ 100 ሜትር ጥልቀት በመቆፈር ውኃ እናወጣለን፡፡ መስመርም በመዘርጋት በየአካባቢው ኅብረተሰብ የንጹሕ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጤና ሥርዓቱን ማጠናከር በሚለው ፕሮግራማችሁ ውስጥ አቅም የሌላቸውን ወገኖች ለማቀፍ ወይም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የታሰበ ነገር አለ?

ዶ/ር የሺጥላ፡- አቅም የሌላቸው ወገኖች እንዲጠቀሙ ለማድረግ የጤና መድን ሽፋንን የማጠናከር ሥራ ነው የምንሠራው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ ፈንድ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ያሉት ማኅበረሰቦች የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን ላይ በመሳተፍ የጤና መድን ሽፋን አባል እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናችንን መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምታከናውኑት አጠቃላይ የሕክምና አገልግሎት ከየትኞቹ ለጋሽ አገሮች ወይም ድርጅቶች ጋር ነው አብራችሁ የምትሠሩት?

ዶ/ር የሺጥላ፡- ከዩኤስአይዲ፣ ከአይዲፊዲ፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከካናዳ፣ ከኔዘርላንድስና ከስፔን መንግሥታት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ በተለይ ትላልቅ ፋርማሲዩቲካል ኩባንያዎች፣ ከፓርክ ፋውንዴሽን፣ ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው በእናቶች የጡትና የማሕፀን በር ጫፍ ካንሰር ላይ ከሚሠራው ቢኤምኤስ ፋውንዴሽንና ከሌሎች ፋውንዴሽን ጋር አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የክሊኒካልና የሰርጂካል አውትሪች ፕሮግራም እንዳላችሁ ይታወቃል? ፕሮግራሙን ለማስፈጸም እንዴት እየተንቀሳቀሳችሁ ነው?

ዶ/ር የሺጥላ፡- የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ የደረሰባቸውን ሕፃናት፣ በፊስቱላ የሚሰቃዩ እናቶችን፣ በእሳት ቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውንና በተመሳሳይ መልኩ የአካል ዲፎርሚዲ ያለባቸውን ሰዎች ከአዲስ አበባ ከሚገኙ ሆስፒታሎች የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች በተለያዩ ቦታዎች ባሉት የጤና ተቋማት እያንቀሳቀስን አገልግሎት እንዲሰጡ እናደርጋለን፡፡ ይህ ዓይነቱ አውትሪች ፕሮግራም ያስፈለገበት ምክንያት በየቦታው የሚገኙ ተቋማቱ የተጠቀሰውን የሕክምና አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎቹ አገልግሎቱን በሚሰጡበት ጊዜ በተቋማቱ ላሉት ሐኪሞች ሥልጠናም ይሰጣሉ፡፡ ለባለሙያዎቹ የአየር ቲኬትና አባል በመሸፈን ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ከገጠር መጥቶ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ከተደረገለት በኋላ መመለሻ ገንዘብ ለሌለው ታካሚ የትራንስፖርት ወጪውንም እንሸፍናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የከብት አርቢው ኅብረተሰብ የአውት ሪች ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆን ምን የታሰበለት ነገር አለ?

ዶ/ር የሺጥላ፡- ለከብት አርቢው ኅብረተሰብ ሆስፒታል ቢቋቋምለት እንደልቡ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር የአውት ሪች ፕሮግራም ለከብት አርቢው ኅብረተሰብ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ግንዛቤ በመነሳት በአፋር፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተለይ ለከብት አርቢው ኅብረተሰብ አገልግሎት የሚውል ከዩኤስአይዲ በተገኘ የ30 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ተቀርጿል፡፡ በዚህም ፕሮጀክት አርብቶ አደሮቹ ከብቶቻቸውን ይዘው የሚንቀሳቀሱባቸውን ቦታዎች (ሞቢሊቲ ፓተርኒቲ) ጂፒኤስን በመጠቀም አሠርተናል፡፡ በዚህም ከየሆስፒታሉ ስፔሻሊስቶችን በማሰባሰብ አርብቶ አደሮቹ ባሉበት እየሄዱ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ በቅርቡ ይከናወናል፡፡

ሪፖርተር፡- አምሪፍ በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለምን ያህል ሰዎች የጤና አገልግሎት ሰጥቷል? ወደፊትስ ምን አቅዷል?

ዶ/ር የሺጥላ፡- ባለፈው ዓመት ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለጤና ተደራሽ አድርገናል፡፡ ከዚህም ሌላ ወደ ሦስት ሚሊዮን ለሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በሥራ ላይ የሚሰጡ አጫጭር ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ከ450 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እንተገብራለን፡፡ ከፕሮጀክቶቹም መካከል አንደኛው በትራኮማ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አገሪቱ ትራኮማን አጠፋለሁ ብላ ቃል ገብታለች፡፡ በዚህም መሠረት በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ መድኃኒቱን በማሠራጨትና በሽታው ለደረሰባቸው ሰዎች ሰርጀሪ ለመሥራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ስምምነት አድርገናል፡፡ በዚህ ሦስት ወራት ውስጥ አፋር ላይ የመድኃኒት ርጭት ሥራ እየተከናወነና ሰው መድኃኒቱን እየወሰደ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡