Skip to main content
x
የፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ከምርጫ ራሳቸውን ማግለል
ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡቶፍሊካ

የፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ከምርጫ ራሳቸውን ማግለል

የአልጄሪያው ፕሬዚዳንት አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ ለሚያዝያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ተወስኖ የነበረውን የአገሪቱን ምርጫ በማራዘማቸውና ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እንደማይፈልጉ በማሳወቃቸው ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ ድጋፍን ለመግለጽ በአልጄሪያ ጎዳናዎች ተምሟል፡፡

የ82 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ማለታቸው አልጄሪያውያንን ለተቃውሞ እንዲወጡ አድርጎ ነበር፡፡ አልጄሪያን ለ20 ዓመታት የመሩትና እ.ኤ.አ. በ2013 የጤና ዕክል ከገጠማቸው ወዲህ በመገናኛ ብዙኃን ብዙም የማይታዩት ፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ፣ ለሳምንታት የዘለቀውን ተቃውሞ ተከትሎ ለምርጫ እንደማይወዳደሩ ቢያሳውቁም፣ ምርጫው ተራዝሟል ከማለት በዘለለ መቼ እንደሚካሄድ አልተናገሩም፡፡

ቢቢሲ በሚስተር ቡቶፍሊካ ስም የወጣውን መረጃ ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር በቅርቡ ይከናወናል፡፡ ሆኖም ፕሬዚዳንቱ ከተላለፈው ምርጫ በፊት ሥልጣን ይልቀቁ አይልቀቁ አልታወቀም፡፡

ኤኤፍ ፒ እንደዘገበው፣ የአልጄሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦያህ የሥራ ስንብት መልቀቂያ በማስገባታቸው በምትካቸው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኑረደን ቢዶ ተሹመዋል፡፡ አዲስ መንግሥት የመመሥረት ኃላፊነትም ተሰጥቷቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ምን ተናገሩ?

‹‹ለአምስተኛ ጊዜ አልወዳደርም፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በእኔ በኩል የሚነሳ ጥያቄም የለም፡፡ በጤናዬና በዕድሜ ምክንያት ለሕዝቤ የማደርገው የመጨረሻ ሥራ ቢኖር አዲሲቷን አልጄሪያ ሪፐብሊክ ለመመሥረት የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፤›› ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ከሳምንታት በፊት፣ ዳግም ለፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ የሥራ ጊዜ ሳይጨርሱ ቀድመው ከሥልጣን እንደሚወርዱ አሳውቀው የነበረው ቡቶፍሊካ፣ ይህ ንግግራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አልጄሪያውያንን ጎዳና ከመውጣት አላገደም ነበር፡፡ ተማሪዎችና መምህራንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሠልፍ ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ሱቆች ተዘግተው፣ የባቡር አገልግሎትም ተቋርጦ ከርሟል፡፡

ቡቶፍሊካ ከምርጫ ራሳቸውን ለማግለል ምን አስገደዳቸው?

አልጄሪያውያን ለተቃውሞ ወጥተውም፣ ባቡር አገልግሎት ተቋርጦም ሆነ ሱቆች በተቃውሞው ተዘግተው ምላሽ ያልሰጡት ቡቶፍሊካ፣ ሰኞን ግን ዝም ማለት አልቻሉም፡፡ ከአንድ ሺሕ በላይ ዳኞች ቡቶፍሊካ የሚሳተፉበትን ምርጫ እንደማይቆጣጠሩ ማሳወቃቸው ቡቶፍሊካ ከምርጫው ራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል ጌድ ጎለህ ‹‹መከላከያውና ሕዝቡ አንድ ዓይነት የወደፊት ራዕይ አለው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ ያነሱትም መከላከያ ሠራዊቱ ለተቃውሞ በመጡት ላይ ርህራሄ ማሳየቱን ነው፡፡

ጫና እንደሚጠፈርባቸው የሚናገሩት ከፍተኛ የሃይማኖት አባቶች ቡድን መሪ ኢማም ጀማል ጐውል ‹‹በሥራችን ጣልቃ አትግቡ›› ሲሉ አሳውቀዋል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ሚስተር ቡቶፍሊካን ተቃውመው ለሳምንታት ያህል ተቃውሞ ለወጡ አልጄሪያውያን ግማሽ ድል ነው፡፡ ምክንያቱም ቡቶፍሊካ የምርጫ ቀኑን ማራዘማቸውን ተናገሩ እንጂ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ አላሳወቁም፡፡ አዲሱ የምርጫ ቀን አለመታወቁ ዳግሞ የለውጥ ሒደቱን ጊዜ ክፍት አድርጎታል፡፡

ይህ ደግሞ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ጥያቄን አስነስቷል፡፡ ቡቶፍሊካ ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ የምርጫ ጊዜን በማራዘም በሥልጣን መቆየት አይገባቸውም የሚል መነጋገሪያንም አጭሯል፡፡ በሌላ በኩል የምርጫ ጊዜው መራዘም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ ጊዜ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ዕጩዎች በአግባቡ ቅስቀሳ እንዲያደርጉና ሚስተር ቡቶፍሊካ ከሥልጣን እንዲወርዱ ሕዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ለመመለስም ጊዜ ማግኘቱ መልካም ነው፡፡

ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ ግን ፕሬዚዳንቱ መቼ እንደሚለቁ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት የምርጫው ሕጋዊ መሆን ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ እያመለከተ ነው፡፡ የጊዜው ባለሥልጣናት፣ ዳኞችና የምርጫ ቦርድ አመራሮች ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋልም ተብሏል፡፡

የቡቶፍሊካ ጤና መቃወስ በምርጫው ላለመሳተፋቸው ምክንያት ነው?

ፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደሩ ያስታወቁት ለሁለት ሳምንታት ያህል በስዊዝ ሆስፒታል ሲከታተሉ የነበረውን ሕክምና ጨርሰው አገራቸው በገቡ ማግስት ነው፡፡ የጤናቸው ጉዳይ ሥጋት ላይ የጣላቸው አልጄሪያውያንም ቡቶፍሊካ ቢሮዋቸው ውስጥ ቢሞቱ በአገሪቱ አደገኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ይከሰታል የሚል ነው፡፡

ቡቶፍሊካ የመጨረሻ ንግግር ለሕዝባቸው ያደረጉት እ.ኤ.አ. በ2014 ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ነው፡፡

አልጄሪያን ቅኝ የገዛችው ፈረንሳይ ምልከታ

በርካታ አልጄሪያውያን አገራቸው ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከሆነች ወዲህ በሙስና ውስጥ እንደተዘፈቀች ያምናሉ፡፡ ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳልሆኑም ይነገራል፡፡ በመሆኑም ፕሬዚዳንት ቡቶፍሊካ ከሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በኋላ በምርጫ እንደማይሳተፉ ያሳወቁ ሲሆን፣ ፈረንሳይም የቡቶፍሊካን ውሳኔ መልካም ብላለች፡፡ የፈረንሳዩ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን የቪስ ለድሬን፣ ፈረንሳይ አልጄሪያን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግራት አካሄድ ይኖራል ብላ እንደምታምን ተናግረዋል፡፡