Skip to main content
x

የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች የተቃውሞ አድማ እያደረጉ ነው

ካምፕ የገባው የኦነግ ጦር ተመርዟል መባሉን በመቃወም በኦሮሚያ ክልል የወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ ሰኞ ሚያዚያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ የተቃውሞ አድማ እያደረጉ ነው።

በአድማው ምክንያት ከወሊሶ ወደ አዲስ አበባ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ወሊሶ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዳይገቡና እንዳይወጡ ወጣቶች መንገድ የዘጉ ሲሆን፣ በከተማዋ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችም በአድማው ምክንያት አገልግሎት አቋርጠዋል። የመንግሥት ተቋማትና ትምህርት ቤቶችም ዝግ ናቸው፡፡

ከመንግሥት ጋር በተደረገ ስምምነት ትጥቅ ፈትተው ወደ ጦላይ ካምፕ እንዲገቡ የተደረጉ የኦነግ ጦር አባላት ውስጥ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑት በምግብ ተመርዘዋል መባሉ፣ በከተማዋ ለተቀሰቀሰው የተቃውሞ አድማ ምክንያት መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማዋ ወጣቶች ገልጸዋል።

ማለዳ ላይ ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች የኦሮሚያ ክልልን በሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ላይ ያነጣጠሩ ወቀሳዎችን ሲሰነዝሩ ተሰምተዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የክልሉን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በኦነግ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም 200 የሚሆኑ የኦነግ ጦር አባላት የበሉት ምግብ የተበከለ በመሆኑ ለበሽታ መጋለጣቸውን አመላክቷል፡፡

ግንባሩ በመግለጫው ያጋጠመው ችግር በአስቸኳይ ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ አክሏል፡፡