Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከግምገማው እንደወጡ ለደላላ ወዳጃቸው ደወሉ

ክቡር ሚኒስትሩ ከግምገማው እንደወጡ ለደላላ ወዳጃቸው ደወሉ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ሥራ እየሄዱ ነው]

 • ምን ገጠመህ ዛሬ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • መኪናው ፀጥ ብሏል፤ ሬዲዮ መስማት ተውክ እንዴ?
 • ከሬዲዮ ጋርማ ተሰነባበትን፡፡
 • ምን ተፈጠረ ደግሞ?
 • ከሬዲዮ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቴሌቪዥኑም ጋ ተቆራረጥን፡፡
 • እኮ ምን ሆንክ?
 • ክቡር ሚኒስትር በኢትዮጵያ ሚዲያዎች አፈርኩኝ፡፡
 • ምን አልከኝ?
 • በሚዲያዎቹ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡
 • ዛሬ ገና ነው የገባህ?
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • እስቲ ንገረኝ ሚዲያ መቼ ነው ለአገሪቷ ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጎ የሚያውቀው?
 • የምን ዕድገት ነው የሚያወሩት?
 • ስማ የዓረብ ስፕሪንግ ያቀጣጠሉት ሚዲያዎች መሆኑን ረሳኸው?
 • ምንድን ነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሚዲያ የጥፋት ኃይል እንጂ ልማት አያመጣም፡፡
 • እዚህ ላይማ አይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ሚዲያማ ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
 • አሁን ሚዲያ መስማት ትቻለሁ እያልከኝ ነው አይደል እንዴ?
 • እኔ መስማት ያቆምኩት ሥርዓቱ የፈጠራቸውን የሚዲያ ተቋማት ነው፡፡
 • ግራ እያጋባኸኝ ነው ሰውዬ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት፡፡
 • የምን ጥያቄ ነው?
 • እስቲ እሑድ ዕለት ምን ነበር?
 • የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ነዋ፡፡
 • አገሪቷ ውስጥ ነው ያልኩዎት?
 • የእግር ኳስ ጨዋታ ነበር እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሁላችንንም አስጨንቆን ያለፈ ጉዳይ ነበር እኮ?
 • አትሌቶቻችን ውድድር ነበራቸው እንዴ?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር? ኢሬቻ አልነበር እንዴ?
 • ስማ ልማታዊ መንግሥታችን ካደረገው ጥንቃቄ የተነሳ በጣም በሰላማዊ ሁኔታ ነው እኮ ያለፈው፡፡
 • ለነገሩ ልማታዊ ሚዲያዎቹም በሰላም ተጠናቀቀ ብለው ነው ያለፉት፡፡
 • እውነታቸውን ነዋ ታዲያ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔማ የግል ሚዲያዎችን ስከታተል ነበር፡፡
 • ምን አሉ ታዲያ?
 • ምንም እንኳን በዓሉ በሰላም ቢጠናቀቅም፣ ታዳሚዎቹ መንግሥትን በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመው ነበር፡፡
 • ሚዲያዎቹ ለምን አፍራሽ አልሆኑም እያልከኝ ነው?
 • እውነቱን ለምን አይዘግቡም ነው ያልኩት፡፡
 • የምን እውነት ነው?
 • አሁን ከኢሬቻ በላይ የሚያሳስብ ነገር ነበር?
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ማለቴ ኢሬቻ እየተከበረ የካታሎንያውያን መገንጠልና በወደፊቱ የባርሴሎና ክለብ ላይ የሚያመጣውን ዕጣ ፈንታ መዘገብ ነበረበት?
 • የአንተ ችግር እኮ ይኼ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለግሎባላይዜሽን ምንም አታውቅም ማለት ነው?
 • የምን ግሎባላይዜሽን ነው?
 • ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት ጊዜ ስለካታሎናውያን መገንጠል መወራቱ ምን ችግር አለው?
 • የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች አሉ?
 • ምን አልክ አንተ?
 • ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ በብሔር ፖለቲካ እየታመሰች ስለዓለም አንድ መንደርነት ሲያወሩ ትንሽ አያፍሩም?
 • እስቲ ያልተጠየቅከውን አታውራ፡፡
 • ለነገሩ መንግሥትንም በጣም አድንቄዋለሁ፡፡
 • ለምን?
 • ያ ሁሉ የተቃውሞ ናዳ ሲወርድበት ዝም ማለቱ ነዋ፡፡
 • ይኼ ምን ያስደንቃል?
 • እኔማ ሕዝቡ ላይ የዱላ ናዳ ይወርድበታል ብዬ ነበር፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላም ትፈቅዳላችሁ ማለት ነው?
 • ምን?
 • ሰላማዊ ሠልፍ!

 

[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ይደውሉላቸዋል]

 • ለምንድን ነው ስልኬን የማታነሳው?
 • ምን ሆነሽ ነው ደጋግመሽ ስልክ የምትደውይልኝ? ሥራ አላሠራ አልሽኝ እኮ?
 • ችግር ተፈጥሮ ነው፡፡
 • ልጆቹ ሰላም አይደሉም እንዴ?
 • ሰላም ናቸው፡፡
 • ቤትስ ሰላም አይደለም?
 • ኧረ ሰላም ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ተፈጥሮ ነው እንዲህ ደጋግመሽ የደወልሽው?
 • አፋጣኝ ጉዳይ ገጥሞኝ ነዋ፡፡
 • የምን አፋጣኝ ጉዳይ?
 • ተያዘ እኮ ነው የምልህ?
 • ምን ትቀልጃለሽ?
 • አሁን ስለነገሩኝ ነው ደጋግሜ የደወልኩልህ፡፡
 • መቼ ተያዘ?
 • ዛሬ ጠዋት፡፡
 • ሜሴጅ አትልኪልኝም ነበር እንዴ?
 • ስማ መያዙን ስሰማ በጣም ስለደነገጥኩ፣ ሜሴጅ ምናምን አልመጣልኝም ነበር፡፡
 • አሁን ምንድን ነው የሚውጠን?
 • ቶሎ ብለህ የሆነ ነገር አድርግ፡፡
 • ምን አደርጋለሁ ብለሽ ነው? ያው እጄን መስጠት ነው፡፡
 • እኔ እኮ በአንዴ ምንድነው የሚያልፈሰፍስህ?
 • ለመሆኑ የት ነው የተያዘው?
 • ኬላ ላይ ነዋ፡፡
 • ከአገር ሊወጣ ሲል?
 • ሰውዬ ምንድን ነው የምትቀባጥረው?
 • ተያዘ አልሽኝ አይደል እንዴ?
 • ታዲያ ከአሁን በፊትስ ስንቴ ተይዞ የለም እንዴ?
 • ምኑ? ደላላው?
 • የምን ደላላ ነው?
 • ማን ነው የተያዘው ታዲያ?
 • በኮንትሮባንድ የሚገባው ሞባይል ነው እንጂ፡፡
 • ኡፍፍፍ… እንዲያው ቆሌ የሚገፍ ነገር ቆሌሽን ይግፈፈው፡፡
 • ምን ሆነህ ነው?
 • እኔ እኮ ተያዘ ስትይኝ፣ ደላላው መስሎኝ እኔንም ይጠቁመኛል ብዬ ነው፡፡
 • ሞባይሉ ነው እባክህ የተያዘው፡፡
 • አሁን ለዚህ ነው ይኼን ሁሉ ስልክ የምትደውይው?
 • ሰውዬ ሞኝ ነህ እንዴ?
 • እንዴት?
 • ቴሌ ከውጭ የሚገባ ስልክ እንዲቀረጥ ማለቱን አልሰማህም እንዴ?
 • ታዲያ ምን ይጠበስ?
 • ከአንድ ሻንጣ የሚገርም ትርፍ ነዋ የምናገኘው፡፡
 • እኔ አሁን ራሴን ማረጋጋት እፈልጋለሁ፡፡
 • እኔ መረጋጋት አልቻልኩማ?
 • ራስሽን ማረጋጋት ነዋ፡፡
 • የምረጋጋው ሲለቀቅ ነው፡፡
 • ምኑ?
 • ስልኩ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ግምገማ ተቀምጠዋል]

 • እንኳን ደህና መጡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡
 • ምነው አረፈዱ ክቡር ሚኒስትር?
 • መንገድ ተዘግቶብኝ ነው፡፡
 • ለመሆኑ በየትኛው መኪና ነው የመጡት ክቡር ሚኒስትር?
 • በቪ8ቱ ነዋ፡፡
 • መንግሥት አንድ መመርያ አውጥቶ ነበር፡፡
 • የምን መመርያ?
 • እንዲያውም መመርያው እርስዎን በቀጥታ ይመለከታል፡፡
 • የትኛው መመርያ ነው?
 • ቪ8 መኪና ለፊልድ ሥራ ብቻ ይዋል ተብሏል አይደል?
 • እሱንማ ሰምቻለሁ፡፡
 • ታዲያ ከተማ ውስጥ ለምንድነው በቪ8 የሚሄዱት?
 • በእግሬ አልሄድ እንግዲህ፡፡
 • ቀልድ አይደለም እኮ የያዝነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አሁን ይህቺ መመርያ ቁም ነገር መሆኗ ነው?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁልጊዜ መንግሥት መመርያ ያወጣል ተተግብሮ ግን አያውቅም፡፡
 • አገር ውስጥ የሉም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከአገር ለመውጣትም እናንተኑ ማስፈቀድ እንዳለብኝ ተነግሮኛል?
 • ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ እንዳለን ረሱት?
 • እሱማ እኔም ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ ገብቻለሁ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • በቃ እየተደረገ ያለው ዘመቻ አስፈርቶኛል፡፡
 • ምን አስፈራዎት?
 • በቃ ከዛሬ ነገ ያስገቡኛል እያልኩኝ እፈራለሁ፡፡
 • የሚፈሩ ከሆነ ታዲያ የመንግሥት መመርያን ለምን አያስፈጽሙም?
 • እ…
 • ወይስ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም ብለው ነው?
 • አልገባኝም? ምን እያላችሁኝ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በሙስና ዘመቻው እያንዳንዱ ባለሥልጣን በመንግሥት ማይክሮስኮፕ ሥር እንደሆነ አያውቁም?
 • እ…
 • እያንዳንዱ ሹመኛ ምን እንደሚነዳ? ምን እንዳለው? ምን እንደሚያደርግ እናውቃለን፡፡
 • እ…
 • ክቡር ሚኒስትር ከተዘፈቁበት ሙስና ሊወጡ አልቻሉም፡፡
 • ጓዶች ወድጄ እኮ አይደለም?
 • ምን ማለት ነው?
 • ሙስና ደሜ ውስጥ ነው፡፡
 • ምን አሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ እኮ ከእናንተ በላይ የሚረዳኝ የለም ብዬ ነው የማስበው፡፡
 • ለምንድነው የምንረዳዎት?
 • ያው ስለሱስ ከሱሰኛ በላይ ማን ሊረዳው ይችላል ብዬ ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እናንተም ሙሰኞች ናችሁ እያሉን ነው?
 • መቼም ከሙስና የፀዳችሁ ናችሁ ብዬ አላምንም፡፡
 • የሚናገሩትን ነገር ያውቃሉ?
 • አሁን ጓዶች ሂስና ግለሂስ እንዳወርድ ይፈቀድልኝ?
 • እርስዎ እንዲያውም መውረድ ነው ያለብዎት፡፡
 • የት?
 • ወህኒ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከግምገማው እንደወጡ ለደላላ ወዳጃቸው ደወሉ]

 • ሄሎ ወዳጄ፡፡
 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
 • ምን ደኅንነት አለ ከአሁን በኋላ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሊያከተምልኝ ነው መሰለኝ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ከግምገማ ወጥቼ ነው የማዋራህ፡፡
 • ጠንከር ያለ ግምገማ ነበር?
 • በጣም ጠንካራ ግምገማ ነበር፡፡
 • ታዲያ ችግር አለ?
 • ከችግርም በላይ ነው እንጂ፡፡
 • ይኼን ያህል ክቡር ሚኒስትር?
 • አዝማሚያው ደስ አላለኝም፡፡
 • እ…
 • በማይክሮስኮፕ እየታየሁ እንደሆነ ነው የተነገረኝ፡፡
 • እኛም አይቀርልንም በሉኛ?
 • እንግዲህ ማየት ነው፡፡
 • ለማንኛውም ሁልጊዜ የምንጠቀመው ስትራቴጂ እስከ ደም ጠብታ የሚለውን መሆኑን ያውቃሉ?
 • ምን እያልክ ነው?
 • እንደነገሩኝ ከቦታዎ ሊነሱ ይችላሉ፡፡
 • እሱማ እግዚአብሔር ከወደደኝ ነው፡፡
 • ከዚያ ውጪ ምን ይደረጋሉ?
 • ወደ ቂሊንጦም ልላክ እችላለሁ፡፡
 • ስለዚህ ለሁሉም መዘጋጀት አለብን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይደረግ እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ከቦታዎ ከመነሳትዎ በፊት ጥሩ ስትራቴጂ መቀየስ አለብን፡፡
 • የምን ስትራቴጂ?
 • እርስዎን ማቋቋም አለብን፡፡፡
 • ለነገሩ ከመንግሥት የተማርኩት ጥሩ የማቋቋሚያ ሥልት አለኝ፡፡
 • ምን ዓይነት ሥልት ክቡር ሚኒስትር?
 • ከባለሀብቶች ገቢ ማሰባሰብ ነዋ፡፡
 • ቴሌቶን ልናዘጋጅ?
 • ገንዘቡን የምናሰባስበው በቴሌቶን አይደለም፡፡
 • ታዲያ በምንድነው?
 • በኤስኤምኤስ!