Skip to main content
x
አሥር የትምህርት ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያካትተው የስኩልኔት ዝርጋታ ሊጀመር ነው

አሥር የትምህርት ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያካትተው የስኩልኔት ዝርጋታ ሊጀመር ነው

  • 300 ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችም ተካተዋል
  • ዝርጋታው 26.4 ሚሊዮን ዶላር ይፈጃል

አሥር የትምህርት ኮሌጅ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎችንና 300 ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶችን የስኩልኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚያደርገው የመረጃ መረብ ዝርጋታ ሊጀመር ነው፡፡

የትምህርት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር ገበየሁ ወርቅነህ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሁሉም ክልሎች ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች የተመረጡ 300ዎቹን እንዲሁም የትምህርት ኮሌጅ ያላቸውን አሥር ዩኒቨርሲቲዎች የስኩልኔት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ 26.4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይሆናል፡፡

ኮምፒውተሮችና የተለያዩ ቁሳቁሶች ተገዝተው አብላጫው ቁሳቁስ አገር ውስጥ የገባ ሲሆን፣ የቅድመ ሙከራ በሚደረግባቸው በኦሮሚያ ክልል ሆለታ ዓለም ገና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአዲስ አበባ አሳይ ትምህርት ቤት በቅርቡ የኔትወርክ ዝርጋታው ይጀመራል ብለዋል፡፡

የእነዚህ እንደተጠናቀቀ በቀሪዎቹ ተቋማት ዝርጋታው የሚቀጥል ሲሆን፣ እስከ ግንቦት 2010 ዓ.ም. የስኩልኔት ዝርጋታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የኔትወርክ ዝርጋታው ከሥር ከሥር የሚያልቅላቸው ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎቸ ወዲያው ወደ መጠቀሙ የሚገቡ ሲሆን፣ ከ2011 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ ግን ሁሉም በፕሮጀክቱ የተያዙት ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም የስኩልኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ችግር የነበረው ቴክኖሎጂውን የሚያውቅ ባለሙያም ሆነ መምህር ባለመኖሩ ቀላል የቴክኒክ ብልሽት ሲያጋጥም እንኳን ማስተካከል አለመቻሉ ሲሆን፣ ይህንን መሠረታዊ ችግር ለማቃለል ሲባል አሥር የትምህርት ኮሌጅ ባላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ቴክኖሎጂውን በማስገባት፤ መምህራን ሠልጥነው እንዲወጡ ለማስቻል መታለሙንም ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት ነባር 65 ትምህርት ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ በኩል ከዚህ ቀደም የስኩልኔት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የተደረጉ ሲሆን፣ አዲስ የተገነቡት 11 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በአሁኑ ፕሮጀክት ተካተዋል፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙት ሦስት ሺሕ ያህል የመንግሥት የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከግማሽ በላይ ያህሉ የስኩልኔት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ 120 ትምህርት ቤቶች ደግሞ የኮምፒውተር ቤተ ሙከራ ተቋቁሞላቸዋል፡፡

የስኩልኔት ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤቶችን እርስ በርሳቸው በማስተሳሰር ከመዕከል የሚሠራጩ የትምህርት መርጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማስቻልና የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ እንደ አንድ አማራጭ የሚያገለግል በመሆኑ፣ በአገሪቱ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን በሙሉ ቀስ በቀስ የስኩልኔት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ገበየሁ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡