Skip to main content
x
የዓለም አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ አፀደቀ

የዓለም አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ አፀደቀ

  • ሁለተኛው የዓለም አንጓዴ ልማት ሳምንት ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀምሯል

ከአምስት ዓመታት በፊት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በጥቂት የሐሳብ አመንጪዎች አማካይነት የተመሠረተው የዓለም አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የሚውል የ50 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ብድር ማፅደቁን አስታወቀ፡፡

በ12 አገሮች ስምምት የተመሠረተው ይህ ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት (ግሎባል ግሪን ግሮውዝ ኢንስቲትዩት) በኢትዮጵያ የሚተገበረውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማስፈጸሚያዎችን መነሻ በማድረግ በተለይ ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የመስኖ ሥራዎችን ለማከናወን ሊውል እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ፍራንክ ሪስበርማን ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) እንዲሁም ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ይማም ጋር በመሆን ሰኞ፣ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኒስቴሩ ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን ሴዑል፣ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ያደረገው ይህ ተቋም ለኢትዮጵያ እንዲሰጠው በወሰነው የብድርና የዕርዳታ ገንዘብ ወደፊት በተለያዩ ፕሮጀክቶች መስክም እየጨመረ እንደሚሔድ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመሠረተው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ማዕከል ከዓለም የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ያፀደቀው የገንዘብ መጠን 45 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የአምስት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ ለታሰበው የመስኖ ሥራ ፕሮጀክት እንደሚያወጣ ተጠቅሷል፡፡ በመሆኑም በመስኖ ሥራና በተያያዥ ፕሮጀክቶች ከ330 ሺሕ ያላነሱ ሰዎች በቀጥታ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአፍሪካ ሲዘጋጅ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም አረንጓዴ ልማት ሳምንት ጉባዔን ኢትዮጵያ፣ ከዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት ማስተናገድ ትጀምራለች፡፡ ጉባዔው ከ500 በላይ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ ከሚኒስትሮች ጀምሮ ከፍተኛ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች፣ ሕግ አውጪዎችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በመታደም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የቀረጿቸው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴዎች በተምሳሌነት የሚቀርቡባቸው 15 የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎችን የዓለም ታዳጊ አገሮችን በመወከል እየመራች ብትገኝም፣ እንደ አሜሪካ ያሉ በዓለም ከፍተኛ የከባቢ አየር በካይ አገሮች በፓሪስ የተደረሰበትን የሙቀት አማቂና የበካይ ጋዞች ልቀትን የመቀነስ ስምምነት ማፍረሷ ትልቅ ሥጋት አሳድሯል፡፡

ሚኒስትሩ ገመዶ ዳሌም ሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ፍራንክ ሪስበርማን የአሜሪካ ከስምምነቱ መውጣት እንደ ቻይና፣ ህንድና ካናዳ ያሉ አገሮች እያሳዩት ባለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየተካካሰ ቢሆንም፣ አሜሪካ ውሳኔዋን በማጤን ዳግመኛ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመራው ዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ስምምነት በማክበር ትመለሳለች ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትር ገመዶ አሜሪካን የማግባባት ዘመቻዎች እየተካሔዱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተር ሪስበርማን፣ በበኩላቸው በቀድሞው የአሜሪካ መንግሥት የተደረሰውን ስምምነት፣ ፕሬዚዳንት ዶላንልድ ትራምፕ ውቅድ በማድረግ እንደ ከሰል ድንጋይ ያሉ የተዘጉ በካይ ኢንዱስትሪዎችን በመክፈት ለአሜሪካውያን የሥራ ዕድሎችን እመልሳለሁ ማለታቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሪስበርማን በፀሐይ ኃይል የሚሠሩና ሌሎችም ለአየር ንብረት ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች የድንጋይ ከሰል ምርትን ተቀባይነት እያሳጡት በመሆናቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅሰቀሳ ወቅት ቃል እንደገቡት የከሰል ድንጋይ አምራች ኢንዱትሪዎችን ወደ ሥራ ለመመለስ ሳይቻላቸው እንደቀሩ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡