Skip to main content
x

እሳት ጎርሰን ቤንዚን ጠጥተን ይቻላል ወይ?

ሰላም! ሰላም! ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የተቀደደ ሰማንያ መስፋት ጀምሯል እያለ አገር ያማኛል አሉ። ‹ቀዶ ቀዶ ከጨረሰ በኋላ አገር ሁሉ የሚያማህ ምን አምጣ ብሎ ነው?› አትሉኝም። እኔ ምን አውቃለሁ? ‹‹እውቀት ቢኖረኝ ኖሮ ደላላ እሆን ነበር?›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አግኝተህ ነው? እንኳን ገበያው አገር የሚመራው ባላዋቂ ዕውቀት አይደል እንዴ?›› ብሎ አሽሟጠጠኝ። ለካ ያለማወቅም ዕውቀት አለ? ወይ ጊዜና ሰው? እናላችሁ ሰሞኑን በጠዋት በረህ ድረስ ተብዬ ተደወለልኝ። ብር እየሞተብን ብር ብለህ ድረስ ማለት እኮ ይገርማል። ስደርስ ሁለት ባልና ሚስት እሳት ሆነው ይጠብቁኛል። ሰላምታ የለ ምን የለ። ‹‹ገምታት!›› አሉኝ። ‹‹ምኗን?›› ብዬ ግራ ቀኝ ስቃብዝ አንዲት አሮጌ ዳትሰን መኪና ጠቆሙኝ። እሷን ነው?›› አልኩ። ሚስቲቱ ታዲያ፣ ‹‹እኔን ልትገምተኝ ነው ታዲያ? ብላ አይኗ ከቮልስ መብራት በለጠ። ‹‹አንድ መቶ ሺሕ ታወጣለች…›› ከማለቴ ‹‹ይኼ ሌባ ሊበላኝ…›› እያለች ታስነካው ጀመር።

ሌባ ብሎ ስያሜ እንደ መኖሪያ መታወቂያ ለማንም በሚታደልበት በዚህ ጊዜ ተሰደብኩ ብሎ ቡራ ከረዩ አያዋጣም ብዬ ዝም። እሺ ብዬ ስሰማት ለካ ባልና ሚስት ሰማንያ ቀደው፣ ባል መኪናዋን ሸጦ ግማሹን ሊሰጣት ተስማምተው ኖሯል። እና የእኔ ግምት ከባልየው በሰላሳ ሺሕ ይበልጣል። ነገሩ ሲገባኝ ድለላውን ትቼ ስለፀባቸው ቀስ ብዬ ሚስቲቱን ስጠይቃት። ‹‹ሌላ ወዶ ነዋ…›› ብላ በሐሳብ ተብከነከነች። ከዚያማ ምኑ ይነገራል፡፡ ‹‹ካስተዋላችሁት ሰማንያውን ድጋሚ መጻፍ አይከብድም። ብር ጠፊ ነው…›› ምናምን ብዬ ስለፈልፍ፣ ‹‹አሁን አንተ ደላላ ነህ? ብር ምን ይሰራል ትለኛለህ? ዶላር ይንሳህ…›› ብላ ረገመችኝ። በዚህ ጊዜ ሰው ይኼን አለ ተብሎ ሌላ መመንዘር፣ እንኳን ለነገር ለውጭ ምንዛሪም ስላላዋጣ ዝም አልኳ። ዶላር ይንሳህ አባባሏ ግን መስጦኛል። 

ግን እኔ ምለው፣ ምንድነው እንዲህ ቫይረስ በቫይረስ የሆነው ወሬው ሁሉ? ፍቺውንና ወረቀት መቅደዱን ተውት ለጊዜው። ጉንፋንንና ሰሞኑን ባልታወቀ ምክንያት ከሥራ የሚለቁት ባለሥልጣናት ጉዳይ  ባናነሳው ይሻላል። በተለይ ጉንፋንን በተመለከተ መንግሥታችን የዜጎቹ በሽታ የመከላከል አቅም ማነስ መሆኑን አውቆ የፍራፍሬ መሸጫ ዋጋ ላይ ተመን ካላወጣ ዋጋም የለን እያልኩ ነው። “የሥጋ እንጂ መቼ የፍራፍሬው አስቸገረን?” ሲለኝ ነበር የባሻዬ ልጅ። ጁስ መዝናኛችን ቁርጥና ክትፎ ወስፋት መቆለፊያችን መሆኑን አይቶ ነዋ። ይመስለኛል ለአመጋገብና ለአለባበስ ባህል እንክብካቤና ዕድገት መብት ልኳንዳ ቤት ውሎ ስቴኪኒ ሰክቶ የሚዞረውን የልብ ልብ ሳይሰጠው አልቀረም። ታዲያ አንድ ቀልደኛ ወዳጄ ምን ይላል መሰላችሁ? “የመሰብሰብ መብት የተፈቀደው ልኳንዳ ቤት ብቻ ነው እንዴ?” አይገርማችሁም? ሊያይዘኝ እኮ ነው።

እኔም ተራዬን “የመበተን ግዴታ ሲተገበር ያየኸው ሌላ የት ነው?” እለዋለኋ። ማምሻም ዕድሜ ነዋ። አይደል እንዴ? እንዲያው (ይህችን ግን ብሎ ሥልታዊና ስትራቴጄያዊ በሆነ አረማመድ ቀኝ ኋላ መመለስ ስወዳት) እያደር የምሰማው የቫይረስ ብዛት አሳስቦኛል። በአዕምሮም፣ በሥጋም፣ በመንፈስም ላይ ሆኗላ የሚራባው ቫይረሱ። ይኼን የአፍሪካ መሪዎች በመዲናችን ተሰባስበው ዝናው በገዛ ሚዲያዎቻችን በልጧቸው ቁጭ ያለውን ዚካ የሚሉትን ቫይረስ አይደለም የማወራችሁ። ኡጋንዳ ይሁን አንጎላ ዜጎች ቆዳቸውን የሚያነጣ ቅባት ሲለቀለቁ እየዋሉ የቆዳ ችግር በራሳቸው ላይ ፈለሰፉ ሲባል የሰማሁትን ነው። ካላመናችሁ ሲኤንኤን የሚባለውን ጣቢያ ጠይቁት። ዘንድሮ መቼም ጣቢያ በመቀያየር የወሬ አምሮታችን ይረካ እንደሆነ እንጂ ታራሚና ተመካሪ መሆን አቅቶናል። እና ፈረንጅ ለመሆን ምንትስ የሚባል ቅባት አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎችን ጉድና መዘዙን ከፊል በአስተርጓሚ፣ ከፊል በነሲብ ተረድቼ ‹ይኼ ደግሞ ምን የሚባለው ቫይረስ ይሆን?› ስል ሰነበትኩ። ይኼኔ እኮ እንግሊዝኛ በማስተርጎሜ ‹ምኑ ፋራ ነው› ብሎ የሚንቀኝ አይጠፋም!

መቼም መናናቅ እንደ ወንዛችን እንደ ቀዬያችን ድሩ የሚጀምረው ከመተዋወቅ ነው ይባላል። ምን ይባላል ነው እንጂ። ሰማንያ መቃደድ ድረስ እንዲህ እንደ ዋዛ ይደረሳል እንዴ? “የምን ፈራ ተባ?” አሉ ባሻዬ ሀቅ ይዘው ሰው ሲሞግቱ። እንዳለመታደል ሆኖ ቀሪው ዓለም ተዋውቆም ሳይተዋወቅም ሲከባበር እኛ ሳንተዋወቅ ተገለማምጠን፣ ስንተዋወቅ ‹ክፍ እርክስ› ስንባባል የዕድሜ ጀንበር ታዘቀዝቃለች። በነገራችን ላይ ቀላል ልማድ ትመስላለች። ችግሯ ታዲያ ወዳጆቼ፣ ይኼው ለምታዩት አለመግባባትና አለመደማመጥ ሁነኛ መሠረት እሷ መሆኗ ነው። ፖለቲከኛው ሲፖተልክ አይደመጥ፣ ጋዜጠኛው ሲተነትን አይደመጥ፣ መምህሩን ተማሪው አይሰማው፣ ተማሪውን መምህሩ ዞሮ አያየው፣ ሴቶች አይደመጡ፣ ወንዶች አይደመጡ  . . . ምኑ ቅጡ! ቅጥ አጥተናል። ለምን? ተዋወቅንና ተናናቅና!

‹‹እህ መቼ ነው ‹እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው› ብሎ የአገሬ ሶቅራጦስ የሚነሳው?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ አዋየኝ ስለው፣ “የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ከተዘጋ አልቆየም እንዴ?” ብሎ እሱ እኔን መጠየቅ። “እኔ ምን አውቃለሁ?” ስለው፣ “ለነገሩ በሶቅራጥስ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ አልነበረም፤” አለኝ ጥልቅ ሐሳብ ውስጥ እየዋኘ። ነገሩ ገብቶኛል። ‘ዛሬ በምግብና በዩኒቨርስቲ ራሳችንን በበቂ ሁኔታ በቻልንበት ዘመን እንዴት ይኼን የሚያስገነዝብ የኅብረተሰብ ሳይንስ ምሁር ይጠፋል?’ ለማለት እንደሆነ ገብቶኛል። ነገሩማ ብዙዎቻችንን ቶሎ ይገባናል እኮ? ትምህርት የማይገባን የበዛው ነገር ቦታውን ይዞበት ይሆን ታዲያ? እውነቴን እኮ ነው። ሁሌ በብዛትና በጥራት እየተጨቃጨቅን በነገር ተዋውቀን በነገር እንደተናናቅን ልንቀር እኮ ነው። እስኪ አንዳንዴ ያልተጠየቀም እንጠይቅ ጎበዝ። ነው ወይስ ጥያቄም መኮረጅ ማርክ ያሰጣል ዘንድሮ? ወይ ነዶ!

መቼም ያለምክንያት ሰው ይብላኝ እንደማይል ታውቃላችሁ። በእነ አምታታው በከተማ በጠራራ ፀሐይ ገንዘቡን ተበልቶ ወላ ሽማግሌ ወላ ሕግ ያላስመለሱለት ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው። ይኼን ስላቸው ለባሻዬ፣ “እህል እንጂ ገንዘብ ይበላል እንዴ?” ብለው ለአገሩ እንግዳ ሆኑብኝ። ይኼኔ ልጃቸው ደለብ ያለ መጽሐፍ እያነበበ ፈንጠር ብሎ ተቀምጦ ነበር። ምን ቢል ጥሩ ነው? “በእህሉ ፈንታ ገንዘቡ ያለ ዋጋ በየቦታው ተዝረክርኮ ሲገኝ ታዲያ ሰው ምን ይብላ?” አይል መሰላችሁ? ባላየ ባልሰማ ባልነበረ ቡና ሳላከትም ወጥቼ ላጥ ስልላችሁ፣ ማኪያቶ 30 ብር እየሸጠ የዋይፋይ ‘ኔትወርኩን’ መሰብሰብ ያቃተው ገጽታ ገንቢ ፎቅ ሥር ቆሜያለሁ። እንጃ ለምን እንደቆምኩ። ምናልባት ከእኔ ከሰውዬው ልጅ እሱ (የብሎኬቱ ልጅ) ከገንቢ ገጽታው ያጋባብኝ ይሆናል ብዬ ይሆናላ። የሚሉንን ቀርቶ የምንለውን አጥርተን ማወቅ ያቃተን ጊዜ ላይ መሆናችንን ረሳችሁት? መቼ ይሆን ግን መርሳት ራሱን የሚረሳው ጎበዝ? እንደ ዘበት የተረሳሳነው በዛን አቦ!

በሉ እንሰነባበት። ደንበኛዬ የድለላዬን ኮሚሽን በጊዜው አስገብቶልኝ ኖሮ ከዚያች ላይ የተወሰነች ቆንጥሬ ወደተመለደችዋ የእኔና የባሻዬ ልጅ መቃጠሪ ግሮሰሪ ተጣደፍኩ። አንድ ታክሲ ልይዝ አንድ አስፋልት መንገድ መሻገር እንደ ቀረኝ ቅድም ያነሳሁላችሁን ያምታታንና የተምታታንበትን ነገር አስተዋልኩ። ልሻገር ዜብራዬን ይዤ ቆሜያለሁ። እግረኛ እንዲሻገር አሽከርካሪ እንዲቆም መብራቶቹ አዘዋል። በአካባቢው ትራፊክ ፖሊስ የለም ተብሎ ይሁን የተሽከርካሪው ብዛት አነስተኛ ነው ተብሎ (ሰበብ ካለ በሕግ ላይ የበላይ መሆን አለ የተባለ ይመስል) አሽከርካሪው ሁሉ እየጣሰ እየነዳ አላሳልፈን አለ። ሥርዓት ይዞ የነበረው መስመር ተዘጋጋ። አንድ መኪና ብቻ መብራት እስኪለቀቅ ይጠብቃል። ሌላው ወደዚያ አሽከርካሪ እየተገላመጠ፣ “ወገኛ! አንተን ብሎ ሕግ አክባሪ! አቦ አታካብድ ንዳው!” እያለው ያልፋል። ተገርሜ፣ ተገርሜ ጉድ ስል ሰፈሬ ደርሼ ወደ ግሮሰሪዋ ገባሁ። የባሻዬ ልጅ አግሎ ጠበቀኝ። መፍዘዜን አይቶ አንድ አንድ ‘ሻት’ አዘዘ። በዚህ ላይ ‘ሻት’ ተጨምሮበት ብዬ “ይቅርብኝ!” አልኩ።

“ምን ሆነሃል?” ሲለኝ ያየሁትን ተራ ጉዳይ የመሰለ ታላቅ የኅብረተሰብ ህሊና አመላካች ክስተት አጫወትኩት። “ምን ታደርገዋለህ?” ብሎ ትከሻውን ሰበቀ። “መጀመርያ ‘መንገድ የለ!’ ‘መሄጃ የለ’ ስንል ኖርን። መንገዱ ሲሠራ ‘መብራት የለው!’ ‘ሕግ የለው!’ ‘ቀለም የለው’ ብለን ተቸን። ሁሉም ሲኖረው ግን እኛ ጠፋን። ቆይ ግን በምን አፋችን ነው እንዲህ በትንሹ እየተገማመትና እየተዛዘብን ስናበቃ ‘ቢዝነስ በቼይን ሆኗል፣’ ‘ቅጥር በዘመድ ነው፣’ ‘ሥልጣን በወገን ነው፣’ ‘ፍትሕ በገንዘብ ነው’ ብለን የምንተቸው? በመንገድ አካሄድና ሥርዓት ያልታመንን ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር መሻሻል፣ ታማኝ የምንሆነው በምን መሥፈርት ነው?” ስለው፣ “ተወኝ እባክህ እኛ እኮ ከተምታታብን ቆየ፤” ብሎ አረሳሳኝ። የሚያምታታንም ተምታቶበት የተምታታነውም እያምታታን ግን ወዴት ነው እየሄድን ያለነው? በ‘አርገው መታ… መታ… መታ…’ ብቻ የሚለቀን ይመስላችኋል? አንዳንዴማ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ብግን የሚያደርግ ነገር ሲገጥም ውስጣችን ይነድ የለ? ትዕግሥት የሚባል ነገር ባይኖር ኖሮ እሳት ጎርሶ ቤንዚን ጠጥቶ እንዴት ይኮን ነበር? እስኪ አስቡበት። ሄድኩ እኔ። መልካም ሰንበት!