Skip to main content
x
‹‹የእግር ኳሱ ሥርዓትና አካሄድ ለብልጣ ብልጦችና ለሕገወጥ ደላሎች መበልፀጊያ የተመቸ ሆኗል››

‹‹የእግር ኳሱ ሥርዓትና አካሄድ ለብልጣ ብልጦችና ለሕገወጥ ደላሎች መበልፀጊያ የተመቸ ሆኗል››

አቶ አስናቀ ደምሴ፣ የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሠልጣኞች ማኅበር የሕግ አገልግሎት ኃላፊ

ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በብዙ መልኩ ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ጎኑ ጎልቶ የሚነገርበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣ በወርኃዊ የአገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ በከፍተኛ  ደረጃ ውጤቷ ማሽቆልቆሉ ይጠቀሳል፡፡ በሌላ በኩል አግልግሎቱን ያጠናቀቀው የፌዴሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ በቅርቡ በሚደረገው የፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ የምረጡኝ” ዘመቻ ላይ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ እንደ ብዙዎቹ እምነት እግር ኳሱን ለማስተዳደር የሚመጡ አካላት በመልካም ፈቃደኝነት ካልሆነ የማይከፈላቸው መሆኑ እየታወቀ በየአራት ዓመቱ ለመመረጥ የሚደረገው ፍትጊያና እሰጣ ገባ ግልጽ አይደለም፡፡ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ መልኩ ወቀሳና ትችት የሚበዛበት መሆኑን የሚናገሩት እነዚሁ ወገኖች፣ ሆኖም ግን ለመመረጥ የሚደረገው ግብግብና ለዚያ የሚመደበው በጀት ከፍተኛ መሆኑ እንዴት ነው ነገሩ? የሚያስብል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ወስዶ ሲያስተዳድር የቆየው የአቶ ጁነዲን ባሻ ካቢኔ ቀደም ሲል ከነበረው አመራር አንፃር በብዙ ነገሩ ‹‹እጅግ ያነሰ›› መሆኑም ይነገራል፡፡ ይሁንና አመራሩ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ ከክልል ውክልና ያገኙ በርካታ ናቸው እየተባለም ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የእግር ኳሱ ውጤት የሚያንገበግባቸው ሙያተኞች በበኩላቸው ስፖርቱ በሌለበት የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ የሚደረገው ሩጫ አንድ ቦታ ላይ ሊገታ እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡ ከነዚህ ሙያተነኞች መካከል የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሠልጣኞች ማኅበር የሕግ አገልግሎት ባለሙያ አቶ አስናቀ ደምሴ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ያገኙት አቶ አስናቀ፣ በእግር ኳስ ተጨዋችነት ከዞን ጀምሮ በተለያዩ ዲቪዚዮኖች፣ በክለብ ደረጃ ደግሞ ለኪራይ ቤት ለአሥር ዓመታት ከዚያም ክለቡን በማሠልጠንም ለአሥር ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ባለሙያው በአሁኑ ወቅት ለዓመታት ከሠሩበትና ከሚወዱት የእግር ኳስ ሙያ ውጪ በተማሩት የሕግ ሙያ ላይ እየሠሩ ቢገኙም፣ እግር ኳሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት ደረጃ ያሳስባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ በሙያው ያሳለፉ እግር ኳሰኞችን ብቃቱ የላቸውም በሚሉ የብልጣ ብልጦች አካሄድ ስሜታቸው መነካቱን ጭምር ይናገራሉ፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የሙያ አጋሮቻቸው እንደ ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደ ባለሙያ ከሩቅ ሆኖ መርዶ አርጂ ከመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን ይናገራሉ፡፡ በተለይም በቅርቡ በሚደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ላይ የማኅበሩ አባላት የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ የእግር ኳሱ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓመታት በዝምታና በእርስ በርስ መነቋቆር ለሙያው ለይስሙላ ካልሆነ ባይተዋር ሆነው የቆዩት አሠልጣኞች በአሁኑ ወቅት በሙያ ማኅበር ተደራጅተው ለሙያው በሙያው ቋንቋ መናገር ጀምረዋል፡፡ እርሶ እንደ ሕግ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ባለሙያ መነሻው ምንድነው?

አቶ አስናቀ፡- ዋናውና ትልቁ ነገር ከመቼውም ጊዜ በባሰ ሁኔታ የአገሪቱ የእግር ኳስ ውጤት አሳዛኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ችግሩ ነገ ሊለወጥ ይችላል በሚል ተስፋ የሚጣልበትም አይደለም፡፡ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት በመሄድ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት እንደ አንድ የስፖርት ቤተሰብ፣ እንደ ባለድርሻ አካልና ባለቤት ለዚህ ጉዳይ የድርሻችንን ለማበርከት ተነስተናል፡፡ ስፖርቱ ተጎዳ ማለት እኛም አብረን እንጎዳለን፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰባችን ስሜትም አብሮ እየተጎዳ ነው፡፡ ባለው አካሄድ ባለሙያውም ሆነ የስፖርት ቤተሰቡ ይህ ነው የሚሉት እግር ኳስ እየታየ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ችግር ምንድነው?

አቶ አስናቀ፡- አንዱና ዋናው ችግር አስተዳደራዊ ነው፡፡ ሌላው ስፖርቱ እንዴት ይለወጣል? የሚለውን ብቻ ሳይሆን ክፍተቱንም ለመመልከት የአሠራር ሥርዓት የለም፡፡ ስፖርቱን በሚመለከት እንዲህና እንዲያ ብሎ ለመነጋገር የተዘረጋ ሥርዓት የለም፡፡ ቀደም ሲል የነበረውም ሆነ አሁን ያለው የፌዴሬሽኑ አመራር በውድድር ዓመቱ የሚደረጉ መርሐ ግብሮችን ከማከናወን በስተቀር ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ለእግር ኳሱ መሠረት ተብለው በሚነገሩ መሠረተ ልማቶች ላይ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚሠራው የልማት ሥራ የለም፡፡ ስለዚህ ነገም ተስፋው እየጨለመ ስለሚሄድ እዚህ ጋ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሁን ጂቡቲንና ሶማሊያን ስናሸንፍ መገናኛ ብዙኃኑ ሳይቀር መጨፈር የሚያስኬደን አይመስለኝም፡፡ አገሪቱ የነበራትን ታሪክና ዝና በቅጡ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለዚያ ደግሞ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ እኛም ወደ ትግሉ የገባነው ይህንኑ መነሻ አድርገንና ችግሩም ተስተካክሎ እግር ኳሱ ወደ ሚፈለገው ደረጃ መሄድ እንዲችል ካልሆነ ሌላ የተለየ ጥቅም ፍለጋ አይደልም፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በዚህ ደረጃ ለመጓዝ ምን ያህል አቅም አለው? ምክንያቱም ብዙዎቹ አሠልጣኞች ኳሱን ተጫውተው ከማለፍ ያለፈ በአካዴሚው ሊጠቀስ የሚችል ዕውቀትና አቅም የላቸውም የሚሉ ስላሉ ነው፡፡

አቶ አስናቀ፡- ይኼ በእግር ኳሱ ሲጠቀሙ የኖሩ ብልጣ ብልጦች ወደፊትም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ካልሆነ እውነታው ሌላ ነው፡፡ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር አቶ ጁነዲንን ጨምሮ የተወዳደሩት ሁሉም በግላቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ክልሎች መርጠዋቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የእግር ኳስ አሠልጣኞች ማኅበር ቢያንስ በማኅበር ተደራጅተናል፡፡ ለምንድነው አቅም የላቸውም የሚባለው? ያለ አቅም ነው እንዴ ማኅበር ያደራጀነው? መመዘኛውስ ምንድነው? ለዚህ ነው እውነታው ሌላ ነው የምለው፡፡ የአገሪቱን እግር ኳስ እዚህ ያደረሱት እነማን ናቸው? ይህ እውነታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አሠልጣኞች አቅም አላቸው? የላቸውም? ወደ ሚለው እሰጣ ገባ ከመግባታችን በፊት መጀመርያ መመዘኛ ሊቀመጥላቸው ይገባል፡፡ በሌለ ነገር የሙያተኞቻችንን ስም በማጥፋት የምናተርፈው ቢኖር ውድቀትና ውርደት ነው፡፡ መከባበር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ለሙያው ትክክለኛው ማነው የሚለውን ለማወቅ ደግሞ ትክክለኛ መመዘኛ መስፈርት ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ሙያተኞች ይህን ስንል የአቅማችን ቦታ ይሰጠን ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አሠልጣኞች በእግር ኳሱ ጉዳይ በትክክል ይመለከተናል ብለን እናስባለን፡፡ እውነታውም ይኼው ነው፡፡ ኅብረተሰባችን ስለ እግር ኳስ ስናወራ ካልሆነ በሌላ ስለማያውቀን የምናውቀውን እንድናሳውቀው ደግሞ ተሳትፎ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ አሠልጣኞች አቅም የላቸውም ለሚሉን መልሳችን ቢያንስ እኛ አሥርም እንሁን ሃያ በአቅማችን ተደራጅተናል፤ በዚህ ብቻም ሳንወሰን አቅም አንዳለን ለማሳየት አስፈላጊውን ሁሉ ትግል ለማድረግ ዝግጁ ሆነናል፡፡

ሪፖርተር፡- አስተዳደራዊ ዕውቀትና ቴክኒካል ዕውቀት ለየቅል ናቸው የሚሉ አሉ፤

አቶ አስናቀ፡- እኔ ምሳሌ አድርጌ ብወስድ አስናቀ ይችላል አይችልም ብሎ ለማለት መመዘኛው ምንድነው? መጀመርያ መመዘኛ ሊወጣልኝ ይገባል፡፡ እከሌ የተባለው አሠልጣኝ ያለው ችሎታ እንዲህ ብሎ ለማለት የተቀመጠ መስፈርት ሊኖር ይገባል፡፡ በሌለ ነገር ጊዜ ከማባከን ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለ እግር ኳስ ለማውራት ከመስፈርቶቹ አንዱና ዋናው የሙያው ቋንቋ፤ ዕውቀትና ክህሎት ናቸው፡፡ ለዚህ የሚቀርበው ማን ነው ይታወቃል፤ በዚህ ረገድ የተሟላ ሰብዕና ያለን እኛና እኛ ነን ብለን እናምናለን፤ የለም እናንተ አይደላችሁም የሚሉን ካሉ ደግሞ እስከዛሬ ከሙያው ውጪ የሆኑ መርተውት ውጤቱ ታየ፤ አሁን ደግሞ ለሙያው ባለቤቶች ሰጥቶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አስተዳደራዊ ክህሎት ስለሚባለው የአሠልጣኞች ማኅበር እንደ ሙያ ማኅበር በዘርፉ ተሳትፎ ሊኖረን ይገባል ስንል ሁሉም ነገር ተጠቃሎ ይሰጠን እያልን አይደለም፡፡ በእኛ እምነት ለስፖርቱ ቁርጠኝነቱና ጊዜው ያላቸው ባለሀብቶች፣ ከቴክኒክና ከሙያው ጋር በአንድም ሆነ በሌላ ቁርኝቱ ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን እንዳለፉት ዓመታት ከእኛ በላይ ለአሳር በሚሉ ብልጣ ብልጦች መቀጠል ግን አይቻልም፡፡ እንደ ባለድርሻ እኛም ይመለከተናል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ በተረፈ ለእግር ኳሱ ሊያግዙ የሚችሉ በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው ዕውቀቱ ያላቸው ምሁራን እንደሚያስፈልጉ እናምናለን፡፡ ጥያቄያችን እንደ ባለሙያ ያገባናል ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ እኛ ብቻ ነን ልክ፣ እኛ ብቻ ነን ይህ ቦታ ማግኘት ያለብን የምንልበት ምክንያት አይኖርም፤ በድርሻችን አብረን እንሥራ ነው የምንለው፡፡ እንዲህ ማለት ወንጀል አይደለም፤ እንዲያውም ልንበረታታ ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ በኃላፊነት ሊጠየቅ የሚገባው መዋቅር ሊኖረው ይገባል፡፡ የፌዴሬሽኑ እያንዳንዱ ዲፓርትመንት ሥልጣንና ተግባሩ በውል ታውቆ ተጠያቂነትና ግልጽነት ሊኖር ይገባል፤ ከዚህ አንፃር ያለው ነገር ብዙም አስደሳች አይደለም፤ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን በግምት መመራት የለበትም፤ ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት ያስፈልገዋል፡፡ በሌላው አገር ብሔራዊ ቡድን አይደለም ክለብ ማናጀር አለው፤ አሌክስ ፈርጉሰን፣ አርሴን ቬንገርና የመሳሰሉት አሠልጣኞች ሳይሆኑ ማናጀሮች ናቸው፡፡ ከነዚህ ባለሙያተኞች አጠገብ ዶክተር፣ የሥነ ምግብ፣ የሥነ ልቦናና የመሳሰሉት አይኖሩም፣ አያስፈልጉም ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ወይም እነ አከሌ በዚህ ረገድ አታሟሉም የሚባል ነገር ካለ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት መስፈርት ማውጣት ያስፈልጋል፤ በጭፍን የምንሄድበት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ እንዳንሳሳት እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በእግር ኳሱ አልፈው ከመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪም በላይ አግኝተው በከፍተኛ ደረጃ የኃላፊነት ሥራ ላይ ያሉ ሙያተኞች እንዳሉ ማመን ይኖርብናል፡፡ በዚህ ረገድ ወደ ራሴ ስመጣ ይህን ተቋም በተገቢው መንገድ የመምራት አቅም እንዳለኝ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቼም በተመሳሳይ አቅሙና ብቃቱ እንዳላቸው ማረጋገጫ መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ በብልጣ ብልጦች አካሄድ የሚደነብር የለም፡፡ ፍርዱን የሚሰጠው ኅብረተሰባችን ስለሆነ ማለቴ ነው፡፡ ሌላው እስከዛሬ እንደዚህ ዓይነት ነገር ተሰምቶ አያውቅም፤ አሁን እኛም የሙያው ባለቤቶች ነን ያገባናል ብለን ስንነሳ ይኼ ሁሉ ነገር ለምን ሊነሳ እንደቻለ በራሱ ግልጽ አይደልም፡፡ እዚያ ጋ ምንድነው ያለው ነገር? ለምንድነው ትርምስ ሊፈጠር የቻለው? ሥጋቱስ ከየት የመጣ ነው? የተባለው ስፖርቱን በሙያችን እናገልግል ነው? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይመለከተኛል የሚል የመንግሥት አካል ጉዳዩን ክትትል ሊያደርግበት ይገባል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ይህን ያህል ሥጋት የምንሆን ከሆነ በግሌ ይህ ማኅበር በቀጣይ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሚፈለገው ምንድነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አስናቀ፡- በግሌ ሙያተኛው በዚህ ተደናግጦ እንዲሸሽ ለማድረግ ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ማኅበር ቆርጠን ገብተንበታል፤ ዘንድሮ ላይሳካልን ይችል ይሆናል በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ እንደሚሳካልን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሌላው በኅብረተሰባችን እንዲታወቅ የምንፈልገው ባለው ነገር የግል ጥቅማቸውን ሲያስጠብቁ በኖሩ ብልጣ ብልጦች አማካይነት እግር ኳሱ መበደል የሌለበት መሆኑን ነው፡፡ ስፖርት ስሜቱና ዝንባሌው ያላቸውን አገልጋዮች ይፈልጋል፡፡ አሠልጣኞቻችን ባመጧቸው ቡድኖች እየኖሩ አቅም የላቸውም ብሎ ማለት ሌላ አደባባይ ወጥቶ እንዲታወቅ ያለመፈለግ ጉዳይ ካልሆነ ሌላ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ለሁሉም ነገር መመዘኛ ሊኖረን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡-  በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው ስፖርት ሳይንስ ያጠኑ በእግር ኳስ ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእግር ኳሱ አልፈው የበቁ ሙያተኞች መካከል ትልቅ አለመግባባት አለ፡፡ እነዚህን ሁለት አመለካከቶች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

አቶ አስናቀ፡- መጀመርያ የእግር ኳስ መሠረቱ ምንድነው ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ በሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው የተማሩ ልጆች እንዳሉ አውቃለሁ፤ ጥሩም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ሳይኮሎጂስት፣ ፊዚዮሎጅስት፣ ፉትቦል ስፔሻላይዜሽንና በሌሎችም ዲፓርትመንቶች ተምረው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ሕግ ስማር አሠልጣኝ ለመሆን አይደለም፤ የራሴ ግብ ስላለኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልንጋባባ ይገባል፤ ምክንያቱም በስፖርቱ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተምረው የሚወጡ ምሁራን በተማሩበት የሙያ ዘርፍ አስተምረው ጥሩ ጥሩ ዜጋ ከማፍራትም ባሻገር ስፖርቱን በምርምር ማገዝ የሚችሉ በርካታ መምህራን እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የለም የተማርነው ፉትቦል ስፔሻላይዜሽን ነው የሚሉ ከሆነ ደግሞ መሬት ላይ ካለው ከእግር ኳሱ ባህሪ ጋር ማለትም ስፖርቱ ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ በተግባር ምን ምን እንደሚያስፈልገውና እነዚያን አልፈው ከመጡ መጠቀም የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ተጫውቶ ያለፈና ከዚያም አሠልጣኝ ሆኖ ያለፈ ከሆነ ዕውቀቱን የበለጠ ይጨምርለታል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው አሠልጣኙ ሁሉንም ነገር ስለማያሟላ ፊዚዮሎጂስት፣ ሳይኮሎጂስት፣ ፊዚዮትራፒስትና የመሳሰሉት ድጋፍ ሰጪ አካላት የሚመደቡለት፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን እነዚህ ሁሉ ሰዎች አሠልጣኝ ለመሆን ካልሆነ ሌላ ነገር አይመኙም፤ ሁሉም ሲያወሩ የምትሰማው ስለአሠልጣኙ የሥልጠና ዘይቤ ካልሆነ ሌላ ነገር በአንደበታቸው ሲነገር አይደመጥም፡፡ አንድ ፊዚዮሎጂስት ማውራት የሚጠበቅበት የተጨዋቹን ሰብዕና፣ የተጨዋቹን ቁመናና ጡንቻ እንዲሁም የልብ ዓመታቱን ነው፡፡ ሚዲያውም እኛም እያስተናገድን ያለው ይህንን የተጣረሰ የአሠራር ሥርዓት ነው፤ እንዴት ይሆናል? ስለዚህ ለእግር ኳሱ የምናስብ ከሆነ ልንግባባ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኝ ብለን የምናስቀምጠው ሰው ሳይኮሎጂስትና ፊዚዮሎጂስት ላይሆን ስለሚችል መጠቀም ያለብንን ያህል ለመጠቀም በሚገባ መለየትና ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ በአገራችን የተደበላለቀ አሠራር በመኖሩ ምክንያት ልንግባባ አልቻልንም፡፡ ለመግባባት ደግሞ የግድ ትክክለኛውን አሠራር መከተል ያስፈልጋል፡፡ ያለፈው ቁስል ለእግር ኳሱ አይጠቅምም፡፡ በየጊዜው የውድቀት ታሪክን መናዘዝም አይጠቅመንም፤ የሚጠቅመን ሁላችንም በዕውቀታችን፣ በአቅማችንና በችሎታችን መሥራት ስንችል ብቻ ነው፡፡ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ የአንድ ሰው ዕውቀትና ጽናት የሚለካው ድሮ በነበረበት መሆን የለበትም፡፡ የሚገርመው እግር ኳሱ እየተጎዳ ያለው፣ ብልጣ ብልጦች አንተን ለእኔ ‹‹እሱ እኮ ሌባ›› ነው፤ እኔን ደግሞ ለአንተ ያንኑ እያሉ በሚኖሩ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የበለፀጉ አካላት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እግር ኳስ በሌለበት ስለ እግር ኳስ አንዳች ነገር የሌለው ለእግር ኳሱ ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት ያደረጉ ሙያተኞች የሚወረፉበት አግባብ ነው ያለው፡፡     

ሪፖርተር፡- በእርስዎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቁመና እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አስናቀ፡- በመጀመርያ ደረጃ የተቋሙ አደረጃጀትና የሚመራውን አካል መመልከት የግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም አደረጃጀት ትክክለኛ አመራር ከሌለ ብቻውን ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በአገሪቱ የወጣቶች አካዴሚ ተከፍቷል፤ ነገር ግን ይህ አካዴሚ ከተቋቋመለት ግብ አኳያ ውጤታማነቱ ምን ያህል ነው? የሚለው ካልሆነ በስተቀር ትርጉም እንደሌለው ሁሉ የፌዴሬሽኑም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከዚህ ተነስተን ስንመለከተው አሁን እግር ኳሱ ያለበት ደረጃ ራሱ እግር ኳሱ የሚመራበት አግባብ ትክክል እንዳልሆነ ልትረዳ ትችላለህ፡፡ ለዚህ ደግሞ ውጤቱ ምስክር ነው፡፡ ከፕሪሚየር ሊግ፣ ከከፍተኛ ሊግና ከብሔራዊ ሊግ ውጪ ከዚያ በታች የሚገኙት ሊጎች በምን ዓይነት ቁመና ላይ እንዳሉ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የአንድ አገር እግር ኳስ መሠረቱ የት ነው? አይታወቅም፡፡ እነዚህ ነገሮች ባሉበት ነው እግር ኳሳችን አለቀለት እያልን የምንጮኸው፡፡ ለምንድነው ውጤት ውጤት የምንለው? መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ እግር ኳሱ እየተመራበት ያለው አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ ከመሠረቱ ጀምሮ እንደገና ለማደራጀት ጥሩ አደረጃጀትና አቅም ያለው አመራር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት አሁን ያለው አመራር እንዴት ነው? ለሚል አካል ማብራሪያ አያስፈልግም፡፡ አካዴሚያችን መጋቢነቱ ለማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እግር ኳሳችን በአጠቃላይ የጠራ አመራር፣ የጠራ ሥርዓት፣ አቅምና ክህሎት እንዲሁም ቅንነት ጭምር ያስፈልገዋል፡፡ አገር አቀፍ የሆነ ስትራቴጂክ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ የሚናገር ሰው ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ያለው እውነታ የሚናገር ስው በማንኛውም መመዘኛ ቦታ አይኖረውም፤ እስከመቼ ግልጽ አይደለም፡፡ ለማደግ የምንፈልግ ከሆነ ግን ይህን መጥፎ ኔትዎርክ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በፌዴሬሽኑ ቋሚ ኮሚቴ የሚባል አለ፤ እያንዳንዱ ኮሚቴ እንዴትና በእነማን እንደሚመራ ግልጽ መስፈርት አይቀመጥም፡፡ ነገር ግን በሙያው ዕድሜያቸውን ያሳለፉ ሰዎች ለዚህ አልታደሉም፡፡ ቀደም ሲል በብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ በአሁኑ ወቅት የሉበትም፤ እንዴት ነው እነዚህ ሰዎች በሌሉበት ስለእግር ኳስ መነጋገር የሚቻለው? መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የአሠልጣኞች ማኅበር ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚካሄደው የኢትዮጵያ እግር     ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለው ይደመጣል፡፡ ትክክል ነው?

አቶ አስናቀ፡- ትክክል ነው፡፡ ከሙያ ማኅበራችን ለሁለት አባሎቻችን ክልሎች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ያቀረብናቸው አሉ፡፡ እነዚህ ያቀረብናቸው ሕግና ሕጉን በተከተለ መልኩ መስፈርቱን እስካሟሉ ድረስ ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ማኅበሩ አቅርቧል፡፡ እነዚህ  ዕጩዎቻችን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌና አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ናቸው፡፡ እንደ ማኅበር ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትኩረት እንዲሰጧቸው እንፈልጋለን፡፡